Wednesday, October 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  አየር መንገድ በሞተር ችግር የቆሙ አራት አውሮፕላኖችን አስጠግኖ እያስነሳ እንደሆነ አስታወቀ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ዋና ሥራ አስፈጻሚው የመልቀቂያ ደብዳቤ አላስገባሁም አሉ

  የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሮልስ ሮይስ ሞተሮች የተገጣጠሙላቸው አራት ቦይንግ ቢ787-8 አውሮፕላኖች ካለፈው ሚያዝያ ወር ጀምሮ ቆመው የነበሩ ቢሆንም፣ ከሞተር አምራቹ ኩባንያ ጋር በመነጋገር ሞተሮቹ እየተጠገኑ አውሮፕላኖቹ ወደ ሥራ በመመለስ ላይ መሆናቸውን አስታወቀ፡፡ አየር መንገዱ ለቆሙት አውሮፕላኖች ካሳ እየተከፈለው መሆኑን ገልጿል፡፡

        የእንግሊዝ የአውሮፕላን ሞተር አምራች ሮልስ ሮይስ ኩባንያ ለድሪምላይነር አውሮፕላኖች ያመረተው ሮልስ ሮይስ ትሬንት 1000 የተባለው ሞተር በገጠመው የቴክኒክ እክል፣ ይህ ሞተር የተገጠመላቸው አውሮፕላኖች በመላው ዓለም እንዲቆሙ ተደርጓል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቡድን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፣ ማንኛውም አዲስ አውሮፕላን ሲፈበረክ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ይዞ የሚመጣ በመሆኑ ቴክኖሎጂው እስኪዳብር የሚያጋጥሙ አንዳንድ የቴክኒክ ችግሮች ይፈጠራሉ፡፡ ‹‹ይህ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ የተለመደ ነው፡፡ አዲስ አውሮፕላን ገና እንደተወለደ ሕፃን ነው፤›› ብለዋል፡፡

        ቢ787 ድሪምላይነር አውሮፕላን ምጡቅ ቴክኖጂዎች የተገጠሙለት ዘመናዊ አውሮፕላን መሆኑን የገለጹት አቶ ተወልደ፣ አዲስ አውሮፕላን እንደመሆኑ ቀደም ብለው እንደተሠሩት ቢ777 እና ሌሎች አውሮፕላኖች ቴክኖሎጂዎቹ እስኪዳብሩ አንዳንድ ችግሮች እንደገጠሙት አስረድተዋል፡፡ ለድሪምላይነር አውሮፕላን የሚሆኑ ሁለት የሞተር ዓይነቶች ተመርተዋል፡፡ አንደኛው የአሜሪካ ጄኔራል ኤሌክትሮኒክ (ጂኢ) ያመረተው ሲሆን፣ ሁለተኛው ሮልስ ሮይስ ያመረተው ትሬንት 1000 ሞተር ነው፡፡ ሁለቱ ቀዳሚ የአውሮፕላን ሞተር አምራች ኩባንያዎች እኩል (50-50) የገበያ ድርሻ አላቸው፡፡ ሁለቱም ሞተሮች የገጠማቸው የቴክኒክ እክል ቢኖርም፣ ጂኢ የመጠባበቂያ ተለዋጭ ሞተር በማዘጋጀቱ ያለምንም ውጣ ውረድ ችግሩን ሊወጣ እንደቻለ አቶ ተወልደ ተናግረዋል፡፡ ሮልስ ሮይስ እንደ ጄኔራል ኤሌክትሪክ በቂ የሆነ ተለዋጭ ሞተሮችን ባለመዘጋጀቱ ችግሩ ሊፈጠር እንደቻለ አስረድተዋል፡፡ በሮልስ ሮይስ ትሬንት 1000 ሞተር የብሌድ መሰንጠቅ በመታየቱ፣ በዓለም ላይ ያሉ ይህ ሞተር የተገጠመላቸው 50 ያህል አውሮፕላኖች ቆመዋል፡፡

  አውሮፕላኖች በአሜሪካ፣ በደቡብ አሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በእስያና በመካከለኛው ምሥራቅ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድም ከሚያዝያ ወር ጀምሮ አራት 787-8 አውሮፕላኖች በዚሁ ምክንያት ቆመውበት ነበር፡፡ ሮልስ ሮይስ በእንግሊዝና በሲንጋፖር ሁለት የጥገና ማዕከላት ያሉት በመሆኑ እንከን የተገኘባቸው ሞተሮች ተፈተው ወደ ጥገና ማዕከላቱ እየተላኩ፣ ስንጥቅ የተገኘባቸው ብሌዶች እየተለወጡ ይመለሳሉ፡፡ ሞተሩ ወደ ጥገና ማዕከሉ ተልኮ ተጠግኖ እስኪመጣ አንድ ወር እንደሚፈጅ ታውቋል፡፡

  ‹‹ችግሩ ሁለት ነው፡፡ አንደኛው ሮልስ ሮይስ ተለዋጭ ሞተሮች አለማዘጋጀቱ ነው፡፡ ሁለተኛው ሁለት የጥገና ማዕከላት ስላሉት ብሌዶቹ ተለውጠው እስኪመጡ ጊዜ መውሰዱ ነው፤›› ያሉት አቶ ተወልደ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሁለቱ አውሮፕላኖች አራት ሞተሮች እንግሊዝ ተልከው ማስተካከያ ተደርጎላቸው ከመጡ በኋላ በአውሮፕላኖቹ ላይ ተገጥመው ሥራ መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ተገቢው ሙከራ ከተደረገላቸው በኋላ ሁለቱ አውሮፕላኖች ያለምንም ችግር መብረር ጀምረዋል፤›› ያሉት አቶ ተወልደ፣ የቀሪዎቹ ሁለት አውሮፕላች አራት ሞተሮች ለተመሳሳይ ጥገና ወደ እንግሊዝ መላካቸውን ገልጸው፣ የመጀመርያው ሰኔ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ሁለተኛው ሐምሌ 12 ቀን 2010 ዓ.ም. እንደሚመለሱ ተናግረዋል፡፡ ‹‹አሁን መሬት ላይ ያሉን ሁለት አውሮፕላኖች ብቻ ናቸው፡፡ እነሱም ሞተራቸው እንደመጣ ተገቢው ሙከራ ተደርጎ ወደ ሥራ ይመለሳሉ፤›› ብለዋል፡፡

  የኢትዮጵያ አየር መንገድ በግዥ ወቅት ከሮልስ ሮይስ ኩባንያ ጋር ሲዋዋል በሞተሮቹ ላይ እንከን ቢገኝ ኩባንያው ተለዋጭ ሞተሮች ካላቀረበ፣ ለአየር መንገዱ ካሳ እንደሚከፈል በውል ውስጥ እንዲገባ ማድረጉን አቶ ተወልደ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይህን በማድረጋችን ሮልስ ሮይስ ተገቢውን ካሳ እየከፈለን ነው፡፡ እንደውም ገቢ እያገኘን ነው፤›› ብለዋል፡፡

  ሮልስ ሮይስ በየወሩ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ እስከ ሁለት ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የማካካሻ ክፍያ እየፈጸመ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እንደ ኤርባስ ኤ350 እና ቦይንግ 787-900 ያሉ ዘመናዊና አዲስ አውሮፕላኖች በመግባት ላይ በመሆናቸው በአየር መንገዱ የበረራ ክንዋኔዎች ላይ የጎላ ተፅዕኖ እንዳልደረሰ ተናግረዋል፡፡

  የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦይንግ ኩባንያ ቀደም ሲል የገዛቸው ድሪምላይነር አውሮፕላኖችን ሸጧቸው መልሶ በመከራየቱ፣ አየር መንገዱን እንደጎዳው በማኅበራዊ ድረ ገጽ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት አቶ ተወልደ፣ ቦይንግ ኩባንያ በመጀመርያ ያመረታቸው 12 ቦይንግ 787-8 አውሮፕላኖች ክብደት እንደነበራቸው ገልጸዋል፡፡ የክብደታቸው መጠን ቦይንግ የሽያጭ ቅስቀሳ ሲያደርግ ከገለጸው መጠን ከፍ ያለ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

  ‹‹ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ተደራድረን ስድስቱን አውሮፕላኖች በጥሩ ዋጋ ገዝተናቸዋል፡፡ ከመግዛታችን በፊት እኛ ለፈለግነው የ10 ሰዓት የአውሮፓ በረራዎች ችግር እንደማይኖራቸው አረጋግጠናል፡፡ አማካሪ ቀጥረን አውሮፕላኖቹን አስጠንተናል፡፡ የእኛም የአውሮፕላን ኢንጂነሮች የቴክኒክ ምርመራ አድርገው ችግር እንደማይኖራቸው አረጋግጠውልናል፤›› ያሉት አቶ ተወልደ፣ ከአውሮፕላን አከራዮች ጋር ድርድር ተደርጎ አውሮፕላኖቹ ለአከራይ ኩባንያ እንደተሸጡ ገልጸዋል፡፡

  የአንድ ድሪምላይነር አውሮፕላን ዋጋ 120 ሚሊዮን ዶላር ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እነዚህን ስድስት አውሮፕላኖች እያንዳንዳቸውን በ80 ሚሊዮን ዶላር እንደገዛቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ አውሮፕላኖቹን መልሶ እያንዳንዳቸውን በ90 ሚሊዮን ዶላር በመሸጡ 60 ሚሊዮን ዶላር ትርፍ ማግኘቱን፣ ይኼም በሒሳብ መዝገቡ በግልጽ የሰፈረ እውነታ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ አየር መንገዱ አውሮፕላኖቹን መልሶ ተከራይቶ እየሠራባቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

  ‹‹በጥሬ ገንዘብ 60 ሚሊዮን ዶላር ትርፍ ወደ ባንክ ሒሳባችን ገብቷል፡፡ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ሸጦ መልሶ መከራየት (Sale Lease Back) የተለመደ አሠራር ነው፡፡ አውሮፕላን ገዝተህ ገንዘብ ሳትከፍል አትርፈህ ትሸጥና ትከራየዋለህ፡፡ ገንዘቡን ሌላ ቅድሚያ ለምትሰጠው ፕሮጀክት ታውለዋለህ፡፡ ይህ በኢንዱስትሪ ውስጥ ላሉ ባለሙያዎች ግልጽ ነው፡፡ ከኢንዱስትሪ ውጪ ላሉ ሰዎች በማኅበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ የሐሰት ዘገባዎች ብዥታ ሊፈጥሩ ይችላሉ፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጠራ የሒሳብ መዝገብ አያያዝ የሚጠቀም በመሆኑ፣ ዓለም አቀፍ ባንኮች ለማበደር እንደሚጫረቱ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የብድር ጥያቄ ስናቀርብ ከ20 በላይ ዓለም አቀፍ ታዋቂ ባንኮች ብድር ለማቅረብ ይሻማሉ፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው ግልጽ የሆነ አሠራር ስለምንከተል ነው፡፡ የኢትዮጵያም አየር መንገድ መንግሥታዊ ተቋም በመሆኑ በሚመለከተው አካል የሒሳብ መዝገቡ ተመርምሮ የገለጽኳቸው የአውሮፕላኖች ግዥና ሽያጭ በማንኛውም ጊዜ ሊታይ የሚችል ነው፤›› ብለዋል፡፡

  በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሥራ መልቀቂያ ለኩባንያው ዳይሬክተሮች ቦርድ እንዳቀረቡ የቀረበው ዘገባ ሐሰት እንደሆነ አስተባብለዋል፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ እንዳቀረቡ የሚገልጽ ዘገባ በማኅበራዊ ሚዲያ የተሠራጨ ቢሆንም፣ ይህን አስመልክቶ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ የሥራ መልቀቂያ ጥያቄ አለማቅረባቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ‹‹መደበኛ ሥራዬን በማከናወን ላይ እገኛለሁ፡፡ እናንተም ያገኛችሁኝ ቢሮዬ ውስጥ ነው፡፡ የሥራ ጫና እየጨመረ መጥቷል፡፡ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ብሔራዊ ኩራት የሆነው ብሔራዊ አየር መንገዳችንን ፈጣን ዕድገት ለማስቀጠል እኔና ባልደረቦቼ ከመቼውም በበለጠ ጠንክረን በመሥራት ላይ እንገኛለን፤›› ብለዋል፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች