Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኤርትራ ልዑካን ቡድን በብሔራዊ ቤተ መንግሥት

የኤርትራ ልዑካን ቡድን በብሔራዊ ቤተ መንግሥት

ቀን:

ማክሰኞ ሰኔ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ምሽት በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ለኤርትራ መንግሥት ልዑካን ቡድን አቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹ወደፊት ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ሕዝብ የሚሻለው መንገድ ይህ ነው ተብላችሁ ለመደመር ስለመጣችሁ አመሠግናለሁ፤›› ካሉ በኋላ የኤርትራ ልዑካንን እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል፡፡

በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ያለው የልዩነት አጥር ፈርሶ አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ እንዲከፍቱ የሃይማኖት አባቶች፣ አርቲስቶች፣ እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦች ፖለቲካውን ማገዝ እንደሚኖርባቸው በመጠቆም፣ ‹‹ኤርትራውያን የክረምት ወቅት ሳያልቅ አገራቸሁን ጎብኙ›› በማለት ጋብዘዋል፡፡ ‹‹አርቲስቶች የመጪው አዲስ ዓመት ዝግጅት በአዲስ አበባና በአስመራ የሚደረግ ስለሚሆን፣ ከወዲሁ ዝግጅታችሁን ጀምሩ፤›› ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

‹‹ስትጣሉ እንኳን በልክ ይሁን መታረቅ አለና፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹የዛሬው ዕለት ጥቁሩ መጋረጃ መቀደዱን ያሳያል፡፡ ካሁን በኋላም የተጀመረው የሰላምና የፍቅር መንገድ እንዴት ተጠናክሮ እንደሚሄድ እንሠራለን፤›› በማለት በሁለቱ አገሮች መካከል አዲስ ምዕራፍ መከፈቱን አብስረዋል፡፡

በተመሳሳይ የኤርትራን የልዑካን ቡድን እየመሩ አዲስ አበባ የሚገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኦስማን ሳልህ በበኩላቸው፣ ‹‹በሁለቱ አገሮች መሪዎች በተደረገው ጥረት አማካይነት ዛሬ የሰላም በር ተከፍቷል፤›› በማለት፣ እርሳቸውም በሁለቱ አገሮች መካከል አዲስ ምዕራፍ መከፈቱን በትግርኛ ባደረጉት ንግግር ይፋ አድርገዋል፡፡

‹‹እኛ ሁለት ሕዝቦች ሳንሆን አንድ ሕዝብ ነን፡፡ በአንድ ላይም ለመኖር እንፈልጋለን፡፡ ድንበር የሚጋርደን ሊሆን አይገባም፤›› ሲሉም የአብሮነት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ባለፉት 27 ዓመታት ሊደረግ የሚገባው አልተደረገም ብለው፣ ‹‹አሁን ግን አንድ ላይ ወደፊት በመጓዝ የባከነውን ጊዜ የምንተካበት ሁኔታ መፍጠር ይኖርብናል፤›› በማለት፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ሊኖር ስለሚገባው የወደፊት ግንኙነት ጠቁመዋል፡፡

‹‹ከ20 ዓመታት በኋላ የተገናኘን አይመስልም፤›› በማለት ስለተደረገው አቀባበል አስተያየት በመስጠት የጀመሩት የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የፖለቲካ አማካሪና የቀኝ እጅ የሚባሉት አቶ የማነ ገብረ አብ በበኩላቸው፣ ‹‹አንድ የሚያሳዝን የታሪክ ምዕራፍ ዘግተን ወደ አዲስ ምዕራፍ ገብተናል፤›› ሲሉ በአማርኛ ተናግረዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳልህ የተመራው ከፍተኛ የልዑካን ቡድን፣ ማክሰኞ ሰኔ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. አዲስ አበባ ሲደርስ አቀባበል አድርገውለታል፡፡

የአልጀርሱን ስምምነት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ በመቀበል የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ እንዲሸጋገር የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. የወሰነውን ውሳኔ ተከትሎ፣ የኤርትራ መንግሥት አንድ የልዑክ ቡድን ወደ አዲስ አበባ እንደሚልክ ሰኔ 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ባስታወቀው መሠረት የመጣ የልዑካን ቡድን ነው፡፡

ከፍተኛ የጥበቃ ቁጥጥር በተደረገበት የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትሩ ተከስተ አብርሃም (ዶ/ር)፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ፣ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የቦርድ ሊቀመንበር አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር) ተገኝተው ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የሃይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ አትሌቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና አርቲስቶች ከረፋዱ ጀምሮ የልዑክ ቡድኑን ለመቀበል በተዘጋጀው ሥነ ሥርዓት ላይ ለመታደም ከረፋዱ ጀምሮ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተዋል፡፡ የልዑካን ቡድኑን ይዞ የመጣው አውሮፕላን ከቀኑ 7፡50 ሰዓት ላይ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ደርሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...