ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለመደገፍ ሰላማዊ ሠልፍ በወጣው ሕዝብ ላይ የተፈጸመው የቦምብ ጥቃት ማክሸፍ ያልተቻለው፣ በተፈጠረ ክፍተት መሆኑን ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ፡፡
በቅርቡ የተሾሙት የፌዴራል ፖሊስ ጄኔራል ዳይሬክተር አቶ ዘይኑ ጀማል በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ ቅዳሜ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ በተዘጋጀው ሠልፍ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የተዘጋጀው መድረክ፣ ከሕዝቡ በተወሰነ ርቀት ላይ መሆን ሲገባው መቀራረቡ እንደ አንድ ክፍተት ተወስዷል፡፡
የቦምብ ጥቃቱ ከመድረኩ ብዙም ሳይርቅ መፈጸሙም የክፍተቱ ውጤት መሆኑን አክለዋል፡፡ ሌላው አስገራሚውና በፌዴራል ፖሊስ ታሪክም ታይቶ የማይታወቀው፣ ቦምብን ያህል የጦር መሣሪያ ብዙ ሕዝብ በተሳተፈበት መድረክ ላይ መገኘቱ መሆኑን አቶ ዘይኑ አስረድተዋል፡፡
የድርጊቱን ፈጻሚ፣ ዒላማ፣ በድርጊቱ ውስጥ የፖሊስ ተሳትፎ መኖር አለመኖሩን ለመለየትና የመላው የአገሪቱን ሕዝቦች ጥያቄ ለመመለስ፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና ከፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የተወጣጡ በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ምርመራ መጀመራቸውን አሳውቀዋል፡፡ የአሜሪካ ፌዴራል የምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ባለሙያዎች መጥተው የምርመራ ሥራ መጀመራቸውንም ገልጸዋል፡፡
በምርምራው ሒደት ውስጥ ተጎጂዎች፣ የዓይን እማኞችና ተጠርጣሪዎች የመረጃ ምንጭ ስለሚሆኑ በድጋፍ ሠልፉ ላይ የደረሰው የቦምብ ጥቃት ሆን ተብሎ በፖሊስ ቸልተኝነት የተፈጠረ መሆን አለመሆኑን ለመለየት እንደሚቻልም አቶ ዘይኑ አስረድተዋል፡፡ በደረሰው የቦምብ ጥቃት የሁለት ሰዎች ሕይወት የጠፋ ሲሆን፣ ከ100 በላይ የሚቆጠሩ ጉዳት ሲደርስባቸው 40 ያህሉ ደግሞ ከፍተኛ ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑ ታውቋል፡፡