Friday, September 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹እኛ የምንሸጠው ምግብ የምንበላውን ነው››

ወ/ሮ ምሥራች አበራ፣ የታፑ የበሰሉ ምግቦች ማዘጋጃ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ

የበሰሉ ምግቦችን አዘጋጅቶ የሚሸጠው ታፑ በ2009 ዓ.ም. ዓመታዊ ሽያጩ 18.5 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ከተቋቋመ አሥር ዓመቱን የደፈነው ታፑ ሥራውን የጀመረው በጦር ኃይሎች አካባቢ ሳንቡሳ በመሸጥ ነበር፡፡ አቅሙ ከፍ ሲል አንባሻና ድፎ ዳቦ ማታ በማዘጋጀት ለሱፐር ማርኬቶችና ሱቆች ማከፋፈል ጀመረ፡፡ ከዚያም የሐበሻ ባህላዊ ምግቦችን ወደ ማዘጋጀት ገባ፡፡ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ ሙሉ በሙሉ  ባህላዊ ምግቦችን አዘጋጅቶ በአዲስ አበባ ውስጥ በከፈታቸው አምስት ሱቆች ዶሮ ወጥን ጨምሮ ሌሎች ምግቦችን እያቀረበ ይገኛል፡፡ በአንድ ሰው የተጀመረውን ሥራ ዛሬ የሚሠሩ የቀጠራቸው ከ110 በላይ የሚሆኑ ሠራተኞቹ ናቸው፡፡ በክልል ዋና ዋና ከተሞችም የቴክአዌይ ማዕከሎችን ለመክፈት እንቅስቃሴ የጀመረው ታፑ ምርቱን ወደ ቻይናና ዱባይ በመላክ ጥሩ ውጤት ማግኘት መቻሉን ይናገራል፡፡ ይህንን በማስፋት በቅርቡ የሚከፈቱት ኢንዱስትሪ ፓርኮች በአንዱ በመግባት 50 በመቶውን ወደ ውጭ ለመላክ ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡  የባህላዊ ምግቦች አዘገጃጀትና የገበያ ሁኔታን በተመለከተ የድርጅቱን መሥራችና ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ የምስራች አበራን ታምራት ጌታቸው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ታፑ የበሰሉ ምግቦች ማዘጋጀት እንዴት ጀመረ?

ወ/ሮ የምስራች፡- የመጀመርያ ሥራዬ ጋዜጠኛ ሲሆን በአማራ ክልል መገናኛ ብዙኃን  በሪፖርተርነት እሠራ ነበር፡፡ የተወለድኩትና ያደግኩትም የክልሉ የመገናኛ ብዙኃን ዋና መሥሪያ ቤት ባለበት ባህር ዳር ከተማ ነው፡፡ ከዚያም ወደ አዲስ አበባ በመዘዋወር ለአንድ ዓመት በአዲስ አበባ ለክልሉ ዋና ዘጋቢ በመሆን ስሠራ ቆየሁ፡፡ ነገሩን ሳየው ምንም ስለማያዋጣ የራሴን ሥራ መጀመር እንዳለብኝ በመወሰን ከባለቤቴ አቶ ማርቆስ ተክለግዛው ጋር በመመካከር ሥራዬን በገዛ ፈቃዴ በመልቀቅ በ2000 ዓ.ም. ጦር ኃይሎች አካባቢ በትንሽ ሱቅ በአደባባዩ ላይ ለሚተላለፈው ሰው ሳምቡሳ በምስር፣ በሥጋ እያዘጋጁ መሸጥ ጀመርኩ፡፡ ሥራው እያደገ በመምጣቱ ከእህቶቼና ወንድሞቼ ጋር በመሆን አንባሻና ድፎ ዳቦ በመጨመር በየአትክልት ቤቱና በየሱፐር ማርኬቱ ማታ እየጋገርን ጠዋት ማከፋፈል ያዝን፡፡ ለአምስት ዓመት በጋራ ከሠራን በኋላ በ2006 ዓ.ም. ሙሉ በሙሉ ራሴን ችዬ በመውጣት ኢትዮጵያዊ ባህላዊ ምግቦችን በማዘጋጀት፣ በማቀናበርና አሽጎ ለገበያ የማቅረብ ጀመርሁ፡፡  

ሪፖርተር፡- አሁን ታፑ ምን ምን ዓይነት ምግቦችን እየሠራ ለገበያ ያቀርባል? የቴክአዌይ አገልግሎቱንስ እንዴት ጀመረ?

ወ/ሮ የምስራች፡- የተለያዩ ወጦች፣ እንጀራ፣ ድፎ ዳቦ፣ አንባሻና ኩኪስ አዘጋጅቶ በማቅረብ ሥራ ላይ የተሰማራን ሲሆን፣ በተፈለገው ትዕዛዝ ደግሞ የሚሠሩ የሐበሻና የፈረንጅ ምግቦችን አብስለን እናቀርባለን፡፡ ሳንቡሳውን ስጀምር እኛ አካባቢ ይውሉ ለነበሩ ሠራተኞች  እንጀራ በሽሮ ወጥ እየቋጠሩ ለምሣ እንዲወስዱ የማድረግ ሐሳብ ነበረኝ፡፡ እሱን ሐሳብ ነው ዛሬ እየተገበርኩ ያለሁት፡፡ 

ሪፖርተር፡- በአዲስ አበባ በየትኞቹ አካባቢዎች የቴክአዌይ አገልግሎቱን ትሰጣላችሁ? ከአዲስ አበባ ውጭ በየትኞች የአገሪቱ ክፍል ለማቅረብ አስባችኋል?

ወ/ሮ የምስራች፡- የእኛን አገር ባህላዊ ምግቦች በማንኪያ በቀላሉ እንዲበሉ እያደረግን  የምናዘጋጀው፡፡ በአዲስ አበባ መገናኛ ባለው ሱቃችን አገልግሎቱን የጀመርን ሲሆን፣ በቅርቡ ደግሞ በከተማዋ በተለያየ ቦታ ባሉን በፊት ድፎ ዳቦና አንባሻ መሸጫና ማከፋፈያ የነበሩን ሱቆች ላይ እንጀምራለን፡፡ በክልል ደግሞ በዋና ዋና ከተሞች ለማቅረብ አስበናል፡፡ ሐሳባችን ግን በወረዳዎች ደረጃ ለማድረስ ነው፡፡ በዚህ ሥራ ሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግም አስበናል፡፡ ድርጅቱም ምግብ አብስሎ ለመሸጥ እያንዳንዱ ቦታ መድረስ ስለማይችል እነሱ ማብሰሉን እንዲሠሩ እኛ ደግሞ የቁጥጥር ሥራ ብቻ ለመሥራት አስበናል፡፡  ምክንያቱም እንደ ታፑ  በባህር ዳር፣ በመቐለና አዲስ አበባ እንዲሁም ታች ወረዳ ላይ የሚሸጠው ምግብ በአንድ ዓይነት ደረጃ አንድ ዓይነት ጣዕም እንዲኖረው እንፈልጋለን፡፡ ታፑ ሥራ ሲጀምር የነበረ ድፎ ዳቦ ጣዕም ነው ዛሬም ያለው አሥር ዓመት መቆየት የቻልነውም አብስለን የምንሸጠው ምግብ በማይዋዥቅ ጣዕም በመሆኑ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ባህላዊ ምግቦችን በሚመለከት አስገዳጅ ደንብም ሕግም የለም፡፡ ታፑ ላለፉት አሥር ዓመታት በምን መሥፈርት ነው ሲሠራ የቆየው?

ወ/ሮ የምስራች፡- እኛ መጀመርያ ምግቡን ለገበያ ብለን አይደለም የምናዘጋጀው ለእያንዳንዱ ምግቦቻችን በጊዜ ሒደት ለየትኛው ምግብ ምን እንደሚያስፈልገው አውቀናል፡፡ ለምሳሌ ለዶሮ የሚገባውን የበርበሬ፣ የቅቤ እንዲሁም ሌሎች መቀመሚያዎቻችን መጠን አውቀናል፡፡ ድፎ ዳቦ ለምሳሌ በሁለት ሰዓት ውስጥ ማድረስ ይቻላል፡፡ እኛ ግን ትክክለኛውን ሒደቱን ጠብቀን በስድስት ሰዓት ውስጥ  ነው የምናደርሰው፤ ሌላ ደግሞ ከደንበኞቻችን የምንሰበስበው አስተያየትን በመጠቀም የራሳችንን ቋሚ የሆነ ጣዕም አዘጋጅተን ላለፉት አሥር ዓመታት ስንሠራ የቆየነው፡፡ እንደውም ከራሳችን አልፈን የዶሮ ወጥ አሠራርን በሚመለከት ድርሻ እንዲኖረውና ሕግ ሆኖ እንዲወጣ ከመንግሥት ጋር እየሠራን እንገኛለን፡፡ ለባህላዊ ምግቦቻችን ሕጎች ባለመኖራቸው እኛ ራሱ እየተጎዳን ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- በታፑ ያለው የምግብ ማምረቻ ድርጅት የንፅህናው ነገር ምን ይመስላል?

ወ/ሮ የምስራች፡- ንፅህናን በሚመለከት በድርጅቱ ራሱን የቻለ ተቋም አለው፡፡ ምርቶች የሚገዙት ከማኅበራት ነው፤ የሚፈጨውና የሚቀመመው በሌላ ሰው ነው፡፡ ወደ ፋብሪካ ምርቱ ከገባ በኋላ ደግሞ ራሱን የቻለ የጤና፣ የሥነ ምግብ ባለሙያ ከውጭ የተቀጠሩ አሉ፤ በነሱ ከታዩ በኋላ ነው ታይተው ለምግብነት የሚዘጋጁት፡፡ የሠራተኞቻችን አለባበስ፣ አሠራራቸውን  በሚመለከት የራሳችን ተቆጣጣሪዎች ይከታተላሉ፡፡ ከዚህም ሌላ በየክፍሎቹ የተተከሉ ካሜራዎች 24 ሰዓት ቀረፃ ስለሚያደርጉ ድርጅቱ ከተቀመጠው መሥፈርት በታች ወይም በላይ ቢሠራ እንኳ ስህተቱ የት? ማንና መቼ? በማን እንደተፈጸመ ማግኘት ስለሚቻል ቁጥጥሩ ጥብቅ ነው፡፡ ከዚህም አልፈን የምግቡን ጤናማነት በሚመለከት ደግሞ በየዓመቱ ፓስተር ኢንስቲትዩት እያስመረመርን ነው የምንቀጥለው፡፡ ይዘቱን በሚመለከት ደግሞ በቅርቡ በብሌስ የምግብ ላቦራቶሪ አስመርምረን ጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳለን ተገልጾልናል፡፡ ይህን እንግዲህ አሁን ተከራይተን በምንሠራበት በተጣበበ ቦታ ነው ንፅህናውን የጠበቀ  ምግብ ማቅረብ የቻልነው፡፡ ሙሉ ለሙሉ ግን ጥራቱን በራሳችን ለመቆጣጠርና ለመሥራት እንዲያስችለን በቅርቡ ለመንግሥት ያቀረብነው የሥራ ዕቅድ ተቀባይነት ካገኘ የራሳችንን ጥሬ ዕቃ በከፊል ከማቅረብ ጀምሮ ከፍተኛ የምግብ ፍተሻ ላቦራቶሪ በማቋቋም የንፅህናውን ጉዳይ በራሳችን ድርጅት በአንድ መስመር ስለሚያልፍ ችግሩን መቶ በመቶ መቅረፍ ያስችለናል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ታፑ ምርቱን ወደ ውጭ ለመላክ ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ ገልጸዋል፡፡ ወዴት ነው የሚልከው? ሌላው ብዙ ጊዜ የሐበሻ ምግቦች በአፍላቶክሊን የመጠቃት ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ ይህንስ ችግር ታፑ እንዴት አድርጎ ነው የሚልከው?

ወ/ሮ የምስራች፡- የአፋላቶክሲን (ሻጋታ) ችግር በአገሪቱ ያለው ለምግብ አገልግሎት የሚውሉ ግብዓቶች የአመራረትና የአገበያየት ችግር ነው፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ 700 ኩንታል በርበሬ በማኅበራት ገዝተን 400 ኩንታሉ በእኛ ድርጅት የትም ሳይሄድ ውድቅ ሆኗል፡፡ ችግሩ አገር አቀፍ ነው፡፡ ታፑ በራሱ ችግሩን ለመቅረፍ ከፊል ጥሬ ምርቱን ከታች ከገበሬው  እየሰበሰበ ነው የሚሠራው፡፡ ከበርካታ ማኅበራትም ጋር ጥብቅ የሆነ የጥሬ ዕቃ ምርት አመራረትና አሰባሰብ ላይ ለመሥራት እየሞከረ ይገኛል፡፡ እኛ ጋ ደግሞ፣ ለምግብነት ስናዘጋጅ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ችግሩን በተቻለን መጠን እንቀንሳለን፡፡ ለምሳሌ የሙከራ ምርታችንን ወደ ዱባይና ቻይና ልከን ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት አግኝቶ ገብቷል፡፡ በቀጣይ ወደ አውሮፓና አሜሪካ ለመላክ ተዘጋጅተናል፡፡ ሌላው አሁን በነዚህ አገሮች የሚገኙ ምርቶቻችን ተጠቃሚዎች ኢትዮጵያውያን ብቻ ናቸው የሌሎች አገር ዜጎችም የኛን ባህላዊ ምግቦችን እንዲለምዱት እናደርጋለን፡፡  

ሪፖርተር፡- በአዲስ አበባ ምግብ ከሌሎች አገር ከተሞች ውድ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ችግሩን ምን ይመስልዎታል? ታፑስ ይህን ተመልክቶ የሚሠራው ሥራ አለ?

ወ/ሮ የምስራች፡- ከእርሻ ወደ ጉርሻ የሚባል አባባል አለ፡፡ በቂ ጥሬ ምርት የሚመረት ከሆነ በቂ ጉርሻ ይኖራል ማለት ነው፡፡ በከተማዋ ደግሞ ለምግብ ቤቶች የሚከራዩ ቤቶች ውድ ናቸው፡፡ ስንቶቻችን ነን የምንበላውንና የምንጠጣውን ለገበያ የምናቀርበው? ከዓለም በምግብ ወንጀል ከሚሠራባቸው ጥቂት አገሮች ኢትዮጵያ አንዷ ነች፡፡ በስም ብቻ አንድ ዓይነት የሆነን ምግብ መቶ በመቶ ዋጋ ልዩነት ጎረቤትህ ታገኛለህ፡፡ ይህንን የገበያውን ሁኔታ ተቆጣጥሮ መፍትሔ የሚሰጥ አካል አለመኖርም ላለው የዋጋ ውድነት አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ታፑ ይህን ችግር ለማስተካከል ዋጋውን ቋሚ አድርጓል፡፡ በዚህም ትርፉን በመቀነስ ጥሩ ምግብ በማቅረብ ምሳሌ በመሆን ዋጋውንም ለማረጋጋት እየሠራ ነው ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- ከተለመዱት የባህላዊ ምግቦች ውጭ ሌሎች ባህላዊ ምግቦችን ከማስተዋወቅ አንፃር ታፑ ምን እየሠራ ነው?

ወ/ሮ የምስራች፡- በቀጣይም ከየክልሎቹ የተወጣጡ ምግብ አብሳዮች ወደ ማዕከላችን በማምጣት የራሳቸውን ባህላዊ ምግብ ሠርተው ለገበያ እንዲያቀርቡ በማድረግ ተጨማሪ ባህላዊ ምግቦችን ለገበያ ለማስተዋወቅ ተዘጋጅተናል፡፡ ሌላው በየክልሉ የምንከፍታቸው ማዕከሎች እርስ በርሳቸው የባህል ምግቦቻቸውን አሠራር የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ይሆናል፡፡ በመሆኑም አንድ ኢትዮጵያዊ የራሱን ባህላዊ ምግብ ባሉን ማዕከላችን ቢሄድ ማግኘት ስለሚችል በዚያውም የሌላውን የመቅመስ ዕድል ያገኛል፡፡  

ሪፖርተር፡- በምርምር ማዕከሉ ምን ሠርቶ ያገኘው ነገር አለ?

ወ/ሮ የምስራች፡- ታፑ ሲጀምርም በጥናትና በምርምር ነው የሚጓዘው፣ የሚያበስለው፤ ለምግብ የቆይታ ጊዜ ምን እንጨምርበት፣ እንቀንስበት የሚለውን በየጊዜው ጥናት ያደርጋል፡፡ ሥራውን ለማዘመን ዓለም ላይ ምን አዲስ ነገር መጥቷል እያለ ይዳስሳል፡፡  ባህላዊ ምግባችንም ደረጃ እንዲወጣላቸው ከመንግሥት ጋር የሚሠራው እንዳለ ሆኖ ማለት ነው፡፡ ሌላው ከግኝቶቹ አንዱ የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግብ በዓለም ላይ ተበትኖ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደማይዳረስ ነው ያየነው፡፡ በኢንተርኔት መረብ ላይ ሽያጭ የማካሄድ ሐሳብም አለን፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ግን በቀጥታ የወጡን፣ የድፎ ዳቦውንና የምስር ወጡን ከነሙሉ ጣዕሙ ናፍቆ ማግኘት እንደሚፈልግ አይተናል፡፡ ስለዚህም ምግቡ ሲዘጋጅ ኦንላይን የሚያሳይ ቪዲዮ አብሮ በመልቀቅ የሚፈልግ ከየትኛውም የዓለም ጥግ ሆኖ ማዘዝና መብላት እንዲችል በአማዞን ይህንን ሽያጭ የምንጀምርበት ሁኔታ እየፈጠርን እንገኛለን፡፡ 

ሪፖርተር፡- ታፑ ባለፉት አሥር ዓመታት ባህላዊ ምግብ አብስሎ በመሸጥ ሲሠራ ቆይቷል፤ በዚህ ቆይታው የኅብረተሰቡ የአመጋገብ ሁኔታ ተቀይሯል ብሎ ያስባል?

ወ/ሮ የምስራች፡- ይህ እንደ አገር ጥናት የሚፈልግ ቢሆንም፣ እኛ እንዳየነው ግን አሁንም የተቀየረ ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ እኛም ይህንን ለመቀየር የተመጣጠነና ቅለት ያለው ምግብ ለማዘጋጀት እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ታፑ ሥራውን ለመሥራት ፈተና የሆኑበት ጉዳዮች ምንድናቸው?

ወ/ሮ የምስራች፡- ታፑ በመጀመርያ ከፍተኛ የቦታ ጥበት አለበት፡፡ በየኪራይ ቤቱ ተጣቦ ነው ያለው፡፡ ሌላው እንደ አገርም ቢሆን የግብዓት አቅርቦት፣ የባህላዊ ምግቦች አሠራር ገዥ ሕግ አለመኖር፣ በየጊዜው የሚቆራረጠው መብራት፣ የተማረ የሰው ኃይል ችግር አለበት፡፡ ይህን ሴክተር ለብቻው የሚቆጣጠር አካል የሚመረምር ላቦራቶሪ አለመኖር ከብዙ በትንሹ ሲሆን፣ በዚህ ሴክተር ምንም እንደሌለ የሚያሳየው የንግድ ፈቃዳችን እንኳ ያገኘነው ‹‹ልዩ ልዩ›› በሚል ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች