Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርኢትዮጵያዊነት ኃይል ሲሆን

ኢትዮጵያዊነት ኃይል ሲሆን

ቀን:

በወልደ ሚካኤል ጉዲሶ

በየቀኑ ጠዋት ጠዋት ወደ ቢሮዬ ስገባ የተለያዩ ምንጮችን በማነፍነፍ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ዜናዎችንና ትንታኔዎችን አነባለሁ፡፡ ጋዜጣ ማንበብ፣ ሬዲዮ ማዳመጥ፣ ቴሌቪዥን መከታተል፣ ኢንተርኔት መጎርጎር፣ . . . ወዘተ፡፡ ከሁሉም ነገር በፊት ግን የመስመር ችግር ካላጋጠመኝ በስተቀር በኢንተርኔት ላይ ያሉትን መረጃዎች ቢያንስ በርዕሰ ጉዳይ ደረጃ አነባለሁ፣ ወይም ያነቡኛል፡፡ መረጃ ኃይልም ደኅንነትም ነው ይባል የለ! እርስዎም ከመረጃ አይራቁ፡፡ አገራዊ ጉዳዮችን በሠለጠነ መንገድ ለመደገፍም ሆነ ለመቃወም አቅምም ዕድልም ያገኛሉና፡፡ የተባለውን ብቻ ሳይሆን ያዩትንና የሰሙትን ደምረው የራስዎን ዳኝነት መስጠት በሚያስችልዎት ውሳኔ ላይ ይደርሳሉ፡፡ የመረጃ ድህነት ከሀብት ድህነት የላቀ ጉዳት አለው፡፡

      መረጃ የሌለው ሕዝብ (ዕውቀትም ማለት ይቻላል) ከልማትም፣ ከዕድገትም የራቀና እንደ በቀቀን ያሉትን ብቻ ለማስተጋባት የተዘጋጀ መሣሪያ ይሆናል፡፡ በማያውቀው ሁኔታ የጥፋት መልዕክተኛ የመሆን ዕድሉም ሰፊ ነው፡፡ እኛ ኢትየጵያውያን ደግሞ የራሳችንንም ሆነ ራሳችንን የማናጠፋ፣ ሌላውን ወይም የሌላውን ያላግባብ የማናጠፋ ሕዝቦች መሆናችንን እኛ ብቻ ሳንሆን ሌላውም ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ከጥንት ጀምሮ ‹‹መሪዎቻችን›› ያሉትን ብቻ የመቀበል እንጂ፣ አስፈላጊ ሲሆን እነርሱንም የመገሰጽ ወይም የመጠራጠር ባህል በአብዛኛው የለንም፡፡ ካለም የዚህን ያህል የምናውቀው ነገር ብዙ አይመስለኝም፡፡ ለዚህ አንዱ ምክንያት መሪዎችን በሠሯቸው ትልልቅ ሥራዎች ልክ ማድነቅና ማክበር ሲገባን፣ ነገር ግን ከፈጣሪ በላይ እንድናመልክ የሚያስገድዱን አመለካከቶች ስለነበሩ ነው፡፡ አሁንም እነዚህ አመለካከቶች በየጓዳው መጥፋቱን እጠራጠራለሁ፡፡ ከተሳሳትኩ በእዚሁ መንገድ ቢያርሙኝ ለእኔ ብቻ ሳይሆን፣ ይኼንኑ ጽሑፍ ለሚያነቡ ሰዎች ሁሉ ባለውለታ ይሆናሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

      መንግሥታት ወይም የመንግሥታት መሪዎች በዙፋናቸው እስከሚቀመጡና ቤተ መንግሥት እስከሚገቡ ድረስ ብዙ ነገሮችን ቃል ይገባሉ፡፡ (አንዳንድ ተቺዎች ደግሞ ይዋሻሉም ይላሉ)፡፡ ይኼንኑ ሥልጣን ከያዙ በኋላ (ሁሉንም ማለቴ አይደለም) ቀደም ሲል ለሕዝቡ የገቡትን ቃል እየረሱ ብቻ ሳይሆን፣ ችላ እያሉ መምጣት ይጀምራሉ፡፡ ለዚህ ችላ ማለት ደግሞ ተጠያቂዎቹ መሪዎች ብቻ አይደሉም፡፡ መሪውን መከታና ጋሻ አድርገው፣ ደንብና ሕግን አዛብተው የሚተረጉሙ አንዳንድ አማካሪዎችም ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ብዙውን ጊዜ ራሳችንን በእነዚያ መሪዎች ወንበር አካባቢ ባናስቀምጥም፣ በያለንበት የምንሰማቸውና የምናያቸው ክስተቶች ይኖራሉ፡፡ ከእነዚህም አንዱና ዋንኛው መሪውን ‹‹ያለ ድርጊቱ›› ጥፋተኛ አድርጎ በመሣል ሌላውንም ሕዝብ በማያውቀው ሁኔታ ይኼንኑ ክፋት እንዲከተል ዘመቻ ማድረግ፡፡ መልካም ሥራ ያልሠራውን ወይም እንዲሠራ ድጋፍ ያላደረጉትን ያህል ‹‹ቆራጡ መሪያችን፣ ባለዕራዩ መሪያችን፣ አብዮታዊ መሪያችን፣ ጀግናው መሪያችን፣. . . ወዘተ እያሉ ከፍ ከፍ ያደርጋሉ፡፡ አንዳንድ መሪዎች ይኼንን ሽንገላ ከልባቸው መቀበላቸውን እጠራጠራለሁ፡፡

      አንዳንዱ ደግሞ ይኼንን ሙገሳ የሕይወት ዘመኑ ከመቃረቡ በፊት ዕውን ሆኖ ማየት የሚፈልግም ይመስላል ይላሉ፡፡ አንዳንዶች የቀድሞው ወታደራዊ መንግሥት መሪ የነበሩት ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም፣ በተለይም በኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) መመሥረቻ ጉባዔ ላይ ይመስለኛል (ከአብዮታዊ መሪያችን ጋር ወደፊት፣ ከቆራጡ መሪያችን ጋር ወደፊት፣ . . . ወዘተ) የሚሉ መፈክሮች እንደ ሰማይ መና ሲዘንቡላቸው በኃፍረት ይሁን ወይም በኩራት መሆኑ በማይታወቅ ሁኔታ ሲሽኮረመሙ ዓይቻቸዋለሁ፡፡ ከሁለቱ የትኛውን እመስላለሁ ብለው ራሳቸውን ያስቀመጡበትን ደረጃ ራሳቸው ይወቁ!! እነዚህን መፈክሮች እኛ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳንሆን፣ የቀድሞ የዛምቢያው ፕሬዚዳንት ኬኔት ካውንዳን የመሳሰሉ የአፍሪካ መሪዎችም ውስጣቸው እየሳቀ ወይም እያሾፉብን በሚመስል ሁኔታ መድረኩን በጭብጨባ ቀውጢ ያደርጉ እንደነበረ ትዝ ይላል፡፡

      ኬኔት ካውንዳ እንዲያውም ነጭ ጨርቅ በእጃቸው እያውለበለቡ፣ እኔ እንደምላችሁ እናንተም እንዲሁ ድገሙ እያሉ እንደ ማስገደድ ይቃጣቸው እንደ ነበረ የብዙዎች መነጋገሪያ አጀንዳም ሆኖ ነበር፡፡ ስለዚህ የመሪዎችን መረጃ ወደ ሕዝቡ የሚያሠራጩ አካላት ባለ ሁለት ሥለት ቢላዋ ወይም እንደ ቀቀን (የተባለውን ብቻ የሚያስተጋቡ) መሆን የለባቸውም፡፡ በሕዝብ ቋንቋና ባህል መሠረት መረጃዎቹን በአግባቡ አስታርቀው፣ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል እውነተኛ ድልድይ የሚሠሩ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡

      የመረጃን ኃያልነትና ደኅንነት ለሦስተኛ ክፍል ጽሑፌ መንደርደሪያ አድርጌ የተጠቀምኩት ያለምክንያት አይደለም፡፡ ከላይ የገለጽኳቸውን የመረጃ ምንጮች በተለይም ኢንተርኔትን በምከታተልባቸው የመጨረሻዎቹ ዓመታት፣ አንዳንድ ሚዲያዎች ስለኢትዮጵያችን የሚያሠፍሯቸው ዘገባዎችና ትንታኔዎች በእውነተኛ በጭብጥ ላይ የተመሠረቱ ናቸው ማለት ያስችላል፡፡ ጠንካራ የነበርነውና የሆንነውን ኢትዮጵያውን ሕዝቦች የበለጠ ጠንካራ የሚያደርጉን ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፡፡ የጋዜጠኝነት መርህ መነሻውና መድረሻውም ጥሬ ሀቁን ሳይበረዝና ሳይከለስ ለመረጃ ፈላጊ ኅብረተሰብ ማስተላለፍ ነውና፡፡

      በጥንካሬያችን መሀል ያጋጠሙንን ጉድለቶች መሸፈን የሚያስችል ብርታት የሚሰጡም ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ሚዲያዎቹ እንደ አገራቸው የውስጥ ፖለቲካ ነፀብራቅና እንደ የኤዲቶሪያል ፖሊሲያቸው ስለኢትዮጵያችን የሚያሠራጩት መረጃ አንዳንዴ ‹‹የጥፋት መልዕክት›› ያዘሉ ቢመስሉንም፣ የአንዳንዶቹ ትንታኔ ደግሞ አገራችን ዳግም ወደኋላ ወደማትመለስበት የልማት መስመር በአንፃራዊነት መግባቷን የሚያበስሩ ናቸው፡፡ በእነዚህም መነሻ በርቱ የሚሉም ይመስላሉ፡፡ በርቱ የሚሉን የሚመስለኝ የመበርታታችንን ጥንካሬ ስለተረዱ ነው፡፡ ቀደም ሲል በአፍሪካ ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ ላይ ካሉ አገሮች መካከል እየተባለች ትጠራ የነበረችው ኢትዮጵያ፣ አሁን አሁን ደግሞ በዓለም ፈጣን ዕድገት ማስመዝገብ ሒደት ላይ ካሉ አገሮች መካከል እየተባለች ስትጠራ የምንሰማው ሁላችንም በድህነታችን ያፈርነውን ያህል (ምንም እንኳ ድህነቱን ባንሻገርም)፣ ለውጥና መሻሻል እያሳየን ስለመጣንበት ሹም ቢሆንም ተስፋም ሆነ ኩራት ቢጤ ከፊት ለፊቱ የማይታየው ዜጋ ይኖራል ብዬ አልጠብቅም፡፡ ለማንኛውም ግን ወደ ኩራት የሚያደርሰን ባይሆንም ባለን ካልኮራን የሌለንን ከየት ልናመጣ ነው!?

በእነዚህ ዓለም አቀፍ ግዙፍ ሚዲያዎች ዘገባዎችም ሆኑ ትንታኔዎች የሚጻፉት ስለአገራችን ብቻ ሳይሆን፣ ስለሌሎች አገሮች ልዩ ልዩ ርዕሰ ጉዳዮችም ነው፡፡ ይሁን እንጂ ስለአገራችን የሚጽፏቸው ጭብጦች በተለይም የኢትዮጵያችንን ዕድገትና ፍጥነት የሚያወዳድሩት ቻይናን ከመሳሰሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሁለተኛነት ከሚገኙና ግዙፍ ኢኮኖሚ ከገነቡ አገሮች ጋር መሆኑ ነው፡፡ ከርዕሶቹም መካከል ‹‹ኢትዮጵያ ቀጣይዋ ቻይና ትሆን ይሆን?›› የሚል ዓብይ ርዕስ ይገኝበታል፡፡ ይህ መልካም ትንበያ ትክክል ሊሆን እንደሚችል የሚያረጋግጥ አንድ ትዝታ ላጋራዎት ነውና በአክብሮት ይከታተሉኝ፡፡

      በ1966 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አብዮት ሲፈነዳና ወታደራዊ መንግሥት ሥልጣኑን ሲረከብ በሆሳዕና ከተማ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ነበርኩ፡፡ ወታደራዊ መንግሥቱ መንበረ ሥልጣኑን በቁጥጥር ሥር ማድረጉን ካረጋገጠ በኋላ፣ በተንቀሳቃሽ ወታደራዊ መኮንኖች ቡድን አማካይነት ከወሰዳቸው ዕርምጃዎች አንዱ ወደ ተለያዩ የአገራችን ከተሞች በመዘዋወር በሰፋፊ ስክሪኖች ሜዳ ላይ ፊልሞችን ለሕዝብ ማሳየት ነበር፡፡ ዛሬም ቢሆን ከአዕምሮዬ በማይጠፋው ትዝታ የማስታውሰው ነገር ቢኖር፣ በጣም ሸንቀጥ ባሉ አለባበሶችና አንገት ላይ ግራና ቀኝ ተደርድረው በሚያብረቀርቁ ማዕረግ ገላጭ ዓርማዎች አሸብርቀው ይታዩ የነበሩ መኮንኖች ያሳዩ የነበረው ፊልም የቻይና ነበረ፡፡ ቻይና ስል ካራቴ እንዳይመስላችሁ!! በወቅቱ በፊልሙ ላይ ይታይ የነበረው ቁም ነገር ፊታቸው በጣም የተጎሳቆሉና ችግር የገረፋቸው የሚመስሉ በብዙ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ቻይናውያን ዋሻ ወይም የውስጥ ለውስጥ መሸጋገሪያ ቦይ ለመሥራት፣ አንድ ትልቅ ተራራ እንደ ግሬደር እንዴት ይንዱት እንደ ነበረ ነው፡፡ እንደ ንብ ከበው አቧራ፣ ጭቃና ዝናብ እየተፈራረቀባቸው አስቸጋሪው መልክዓ ምድር ሳይበግራቸው የዛሬዋን ቻይና ለቀጣዩ ቻይናዊ ማሻገር ችለዋል፡፡ ቻይናውያኑ የማይናድ ይመስል የነበረውን ግዙፍ ተራራ ንደው፣ እንዴት አስቸጋሪውን የሕይወት ውጣ ውረድ አልፈው ዛሬ በዓለም ሁለተኛው ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤቶች መሆናቸው አስገራሚና ጥንካሬያቸውን ገላጭ ነው፡፡

      ቻይናውያን ዛሬ ያንን የችግርና የቸነፈር ዘመን አልፈው ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን፣ ዓለምን በአስገራሚ ሁኔታ እየለወጡ የመጡ ሕዝቦች ስለመሆናቸው ልባቸውን ሞልተው ይናገራሉ፣ እኛም በተግባር እያየን ነው፡፡ ይኼንን ችግር ይጋፈጡ በነበረበት ጊዜ ረሃብ፣ ጥማት፣ ጉስቁልናና ሌሎች ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች አላጋጠሟቸውም ማለት አይደለም፡፡ ተራራ ሲንዱ፣ ዛፍ ሲገነድሱ፣ ድንጋይ ሲፈነቅሉ፣ ጋራና ሸንተረር ሲወጡና ሲወርዱ የበርካታ ዜጎችን ሕይወት መስዋዕትነት አስከፍሏቸዋል፡፡ እንደ ጦር ሜዳ ወታደር ላባቸውን አንጠባጥበዋል፣ ደማቸውን አፍስሰዋል፣ አጥንታቸውን ከስክሰዋል፡፡

      እኛ በዘመናችን የህዳሴ ግድብን ስንገነባ ተራሮችን ለመናድ በዘመናዊ ማሽኖች  የተጠቀምነውን ያህል፣ እነርሱ ደግሞ በሕዝቦቻቸው ጉልበት እየተጠቀሙ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ተቋቁመው ዛሬ ለዓለም ሕዝቦች ኃያልነታቸውን አስመስክረዋል፡፡ ይኼንን መስዋዕትነት የከፈሉ የቻይና ዜጎች ይህ መስዋዕትነት ለምንና ለማን እንደሆነ በወቅቱ በተሟላ ሁኔታ ግንዛቤ ላይኖራቸው ይችል ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ በሕይወት ያሉም ሆኑ ያለፉ የዚያን ጊዜ የልማት አርበኞች የቻይና ዜጎች ባለውለታዎች ናቸው፡፡ የቻይናውን አባት እንደሆነ ከሚነገርለት ከኮሙዩኒስቱ ማኦ ዜቱንግ እስከ የአሁኑ መሪ ዢ ጂንፒንግ ድረስ ያሉ የቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲና መንግሥት አመራሮች፣ ከሕዝቡ ጋር እጅና ጓንት ሆነው በመዝለቃቸው ልማቱም አብሯቸው ዘልቋል፡፡ አንዳንዴም ይኼንኑ ልማታዊ ጉዞ በከባድ ሙስና ሊያደናቅፉ የሚሞክሩ አካላትን በአደባባይ እስከ መረሸን ይደርሱ እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ሲሆን፣ ቻይና አሁንም በሙስና ዙሪያ ያላት አቋም ጠንካራ ስለመሆኑ በርካቶች ይመሰክራሉ፡፡

      የስኬታቸው ሚስጥርም ለእኛ ለኢትዮጵያውያንና ለሌሎች በማደግ ላይ ላሉ አገሮች መልካም ተሞክሮ ሆኖላቸዋል፡፡ የእዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ይኼንን ፊልም የተመለከተው ከአርባ ዓመታት በፊት ሲሆን፣ እኛም እንደ አገር ከአርባ ዓመታት በኋላ ሳይሆን ቻይና ከአርባዎቹ ዓመታት ወዲህ ያስመዘገበችውን ውጤትና ስኬት ከሃያ ዓመታት በኋላ ማስመዝገብ እንደምንችል ሳስብ ደስተኛ ያደርገኛል፡፡ አንዲት የምጣኔ ሀብት ሳይንቲስት በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ትምህርት ላይ እያለሁ ስለሕይወት ታሪኳ ስታጫውተን፣ አንደኛውና ሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች ያስከተሉባቸውን ረሃብና ዕልቂት መቋቋም ሲያቅታቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው ‹‹ቆዳ›› እኝክ አድርገው መብላታቸውን እማኝነት ሰጥታለች፡፡ እኛንና አገራችንን ለእዚህ ዓይነት ችግር ያበቃንና ወደ ፊትም ሊያበቃን የሚችል መነሻ ባይኖርም፣ ሰላማችንን በባህላዊና በዘመናዊ የአስተዳደር ዘይቤ እያስጠበቅን ኢትዮጵያዊነትን ከፍ አድርገን ማሳየት የማንችልበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡ ጀምረነዋልም፡፡

       ይኼንን ካላደረግን ግን በቅርብ ርቀት የምናገኛቸው የአፍሪካና የመካከለኛ ምሥራቅ አገሮች ወቅታዊ ሁኔታ ያስተማረንና የሚያስተምረን ብዙ ነገር እንዳለ ማወቅ ይገባናል፡፡ አርቆ ማየትንና ነቅቶ መጠበቅን ዘወትር የኢትዮጵያዊነት መለያ ባህርይ አድርገን ማስቀጠል አለብን፡፡ እንኳን የራሳችንን ሰላምና ደኅንነት የሌሎችንም ወዳጅ አገሮች ሁለንተናዊ ጥቅም የማስከበር አኩሪ ታሪክ አለን አይደል? ሰላማችንን እያስጠበቅን፣ በሁሉም ቦታና ጊዜ መቻቻልን፣ መዋደድንና መከባበርን ተግባራዊ እያደረግን በጋራ መራመድ ከቻልን ከላይ የተገለጹት መገናኛ ብዙኃን እንዳሉት ሁሉ በጥረታችን የአፍሪካ ቻይና የማንሆንበት ምክንያት ከቶ አይኖርም፡፡ ወደ ቀድሞው የምሥራቅ አፍሪካ የዳቦ ቅርጫትነት መሸጋገርን የሚገታን ኃይል አይገኝም፡፡ ልናስመዘግብ ያሰብነው ‹‹ታሪካዊ ሚና›› በተቻለ መጠን ልማታችን ሳይደናቀፍ፣ ንብረታችን ሳይወድምና የዜጎቻችን ሕይወት ሳያልፍ ቢሆን ተመራጭ ያደርገዋል፡፡ ይህ ከሆነ ድህነትን ታሪክ በማድረግ ቀድሞ ወደ ነበርንበት የሥልጣኔ ማማ ተመልሰን እንወጣለን፡፡ አይመስላችሁም? ለዚህም እስቲ ሐሳብ እንለዋወጥ፣ ሐሳባችንን እናጋራ፣ በአገራችን ወቅታዊ ጉዳዮች ሁላችንም ያለንን ዕውቀት ሳንቆጥብና ሳንሳሳ አስተዋጽኦ እናድርግ፡፡ አገራችን የጋራ እንጂ የጥቂቶች አይደለችምና፡፡ የሁላችንም ስለሆነች ሁላችንም ለሰላሟና ለልማቷ ልንረባረብ ይገባል፡፡

      በአንድ ወቅት ከጎንደር እስከ ድሬዳዋ አድርጌ በነበረው ጉዞ ከአንድ የውጭ አገር ዜጋ ጋር መረጃዎችን የመለዋወጥ ዕድል አጋጥሞኝ ነበር፡፡ የየት አገር ዜጋ እንደሆነ ከመጠየቅ ጀምሮ መረጃ መለዋወጥ ጀመርንና ስለአገራችን ማወቅ የሚፈልጋቸውን ነገሮች በጥንቃቄ ነገርኩት፡፡ በተራው የእሱን አገር ታሪክ እንዲያጫውተኝ ጋበዝኩት፡፡ ለእሱ ምንም ላይመስለው የሚችለውንና ለእኔ በግሌ አስደንጋጭ የሆነ ምላሽ ሰጠኝ፡፡ ይኼውም ‹‹እኛ እኮ ታሪክ የለንም›› አለኝ፡፡ እንዴት ስለው፣ ‹‹በቃ ይኼው ነው መልሴ ምንም የማሻሽለው ነገር የለም›› ብሎ ቁጭ፡፡ የእኛን ታሪክ ለማወቅ የፈለገውን ያህል የራሱን ለመግለጽ ለምን አልፈለገም የሚል ጥያቄ ፈጠረብኝ፡፡ ለአውስትራሊያዊው የእኛን እውነተኛ ታሪክ ስገልጽለት ከሦስት ሺሕ ዓመታት በላይ ታሪክ ያለን ሕዝቦች መሆናችንን ገልጬለት ስለነበረ ከዚያ ጋር መወዳደር ያልፈለገ ወይም ስለአገሩ መናገር ትርጉም የማይሰጠው ወጣት ይሆናል ብዬም ራሴን አረጋጋሁ፡፡ ከዚያም ከእርሱ መልስ የማላገኝበት ጥያቄ መሆኑን ስለተረዳሁ ገፍቼ መሄዴን ትቼ በኢትዮጵያዊ ጨዋነት በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች እየተጨዋወትን ድሬዳዋ ገባንና በሰላም ተለያየን፡፡ ወጣቱ የዛሬውንም ሆነ የቀድሞውን ታሪክ በአግባቡ ማወቅ አለበት የምንለውም ለዚህ ነው፡፡

      ከሦስት ሺሕ ዓመታት ጀምሮ የነበረው ኢትዮጵያዊነት ኃይል ነው ያልኩት ለዚህ ነው፡፡ አሁንም ኢትዮጵያዊነት ኃይል ነው፡፡ ወጣቱ የአገሩን ታሪክ ማወቅ አለበት ሲባል ማን የጻፈውን ታሪክ የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ እኔ አንድ ኢትዮጵያዊ ከእዚህ ቀደም የተጻፉትንም ሆነ ወደፊት የሚጻፉትን ታሪኮች በታሪክነታቸው፣ ብሎም ጸሐፊዎቹን የማደንቅና የማከብራቸው ግለሰብ ነኝ፡፡ እዚህ ላይ መታየት ያለበት የተጻፉ ጭብጦች የሚያገዝፉት ‹‹ታሪክ ሠሪውን ሕዝብ ወይስ መሪዎችን ብቻ?›› የሚለው ነው፡፡ ይህ ጥያቄ ሁሌም መልስ ማግኘት ይፈልጋል፡፡   በዘመኑ ኖረውም ሆነ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ያገኙትን መረጃ መነሻ አድርገው የጻፉ፣ በተለይም የአገር ውስጥ ምሁራንን አሁንም ደግሜ ላደንቃቸው እፈልጋለሁ፡፡ ምክንያቱም ባገኙት አጋጣሚ ልክ መጓዝ ችለዋል ነው፡፡ ከውጭ አገር አነፍንፈው አገራችንን የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን ያመጡ እንደ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ያሉ ቁርጠኛ ባለውለታዎችንም እዚህ ላይ ማስታወሱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

      በበርካታ አገሮች የወደፊቱን አገር ተረካቢ ትውልድ የሚያስተምሩና የሚቀርፁ መጻሕፍት በቡድን ይጻፋሉ፡፡ ደራሲዎችም የመንግሥትን፣ የግልን ባለሀብቶችንና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የገንዘብ ድጋፍ ያገኛሉ፡፡ ይኼንን ማድረግ ታሪኩን ለሚጽፉ ሰዎች ብቻ ሳይሆን ድጋፍ ለሚያደርጉ አካላትም እንደ አገራዊ ክብር ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ይህ ባህል በአገራችን የለም፡፡ በአብዛኛው እንዲሁ አልተጀመረም ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ያለመሆኑ ታሪኩ እውነተኛ ታሪክ ተኮር ሳይሆን ገበያ ተኮር ወይም ልብ ወለድ ይሆንና ቀጣዩን ትውልድ በእውነተኛ ታሪክነታቸው ሳይሆን፣ ትውልድን እርስ በርስ ቢያንስ ተገቢ ያልሆነ የአመለካከት ግጭቶች እንዲፈጠሩ ያደርጋሉ፡፡ ለሚጽፉ ሰዎች ድጋፍ የማድረግ ባህል ቢለመድ በርካቶች እንዲህ ዓይነት ሥራዎችን ቢያንስ ከአዕምሮ ተጠያቂነት ነፃ በሚያደርጋቸው ሁኔታ ለማሠራት ያበረታታቸዋል፡፡ ይህ መሆኑ በአንድ በኩል መረጃ ለማሰባሰብ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የማሳተሚያ ገንዘብ ለማግኘት አዕምሮአቸው ሳይጨናነቅ ተረጋግተው እንዲሠሩም ያስችሏቸዋል፡፡ ግለሰቦች አቅም ኖሯቸው በግል ጥረታቸው የሚሠሩትን ታሪክ ለማጣጣል ባይሆንም፣ ታሪክ ነክ የሆኑ ነገሮችን በጋራ መሥራት አገራዊ ተዓማኒነትን ያሳድገዋል፡፡ ይኼንን ማድረግ ካልቻልን እውነተኛ መረጃ የሌለን ሕዝቦች እንሆናለን፡፡

      ከአክራሪ ብሔርተኝነት ይልቅ ኅብረ ብሔራዊነትን ኢትዮጵያዊነትን አጉልተው የሚያሳዩ ጽሑፎች እየተበራከቱ መምጣት አለባቸው፡፡ ሁላችንም እንደ አቅማችን ይኼንኑ እንድናደርግ የበለጠ ሰፊ ምኅዳር ተከፍቶልናል፡፡ የአገራችንን ጥቅምና ደኅንነት በሚያስከብር ሁኔታ በጎረቤቶቻችን ሰላም እንዲሰፍን፣ ያላግባብ መበልፀግ እንዲጠፋ (ማጥፋት የሚቻል ቢሆን)፣ ብልሹ መልካም አስተዳደር እንዲቀረፍ፣ ዘላቂ አንድነት በመካከላችን እንዲያብብ በርካታ ሥራዎች ስለመጀመራቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በየመድረኩ ልባችንን በአድናቆት በሚያንጠለጥልና ተስፋ በሚያፈነጥቅ ሁኔታ በጋራ እንሥራ እያሉን ነውና ከጎናቸው እንቁም፡፡ እንደ ሙያችንና አቅማችን እናግዛቸው፡፡

      ምጣኔ ሀብታችን እንዳይንገራገጭና ከገባበት ተግዳሮቶች ፈጥኖ እንዲወጣ ብሎም የዕድገት ፍጥነታችን እመርታ እንዲኖረው ቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ አየር መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይልና የባህር ትራንስፖርት፣ . . . የመሳሰሉ ቁልፍ ኢኮኖሚያዊ ተቋሞቻችንን አቅም ላላቸው የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ክፍት ማድረጋቸውም፣ መንግሥት ምን ያህል ለፈጣን ለውጥ ዝግጁና ቁርጠኛ መሆኑን እያስመሰከረ ስለመምጣቱ ተጨማሪ ማረጋገጫ ሆኗል፡፡ በእርግጥም በውጭ ግንኙነት ረገድ የቀድሞ ወንድምና እህት ዛሬ ደግሞ የቅርብ ጎረቤት የሆንን የኤርትራና የኢትዮጵያ ሕዝቦች በመካከላችን መቀራረብና መተማመን እንዲኖር፣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የአልጀርሱን ስምምነት ዕውን ለማድረግ መንግሥታችን ቆርጦ መነሳቱ ለሁለቱ ወገኖች ትልቅ የምሥራች ነው፡፡ እርስ በርስ በጠላትነት መተያየቱ ቀርቶ በጋራ እንድንለማና በጋራ እንድንኖር ያስችለናል፡፡

      ስለኤርትራ ከተነሳ አይቀር ሁለቱም ወገኖች እውነተኛ ሰላምና መከባበር መሥርተው ቢኖሩ በተለይ አሁን ኤርትራ ከገባችበት የምጣኔ ሀብት ድቀትና ከዓለም መንግሥታት መገለል መውጣት ያስችላታል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ሰላምም ሆነ ጦርነት በመካከላቸው የሌላቸው ሁለቱም አገሮች ከአሥርት ዓመታት በፊት ተከስቶ በነበረው ጦርነት ከሁለቱም ወገኖች ከ80 ሺሕ በላይ ዜጎች ለሕልፈተ ሞት ተዳርገዋል፡፡ በቅርብ ጊዜ ሲኤንኤን እንደዘገበው በኤርትራ ዴሞክራሲ መጥፋት ከአገሪቱ ጠቅላላ ሕዝብ ሦስት ከመቶ ያህሎቹ ለስደት ተዳርገዋል፡፡ ስምምነቱ ወደ መሬት መውረዱ የዜጎች ሥጋት እንዲያበቃና ሁለቱም አገሮች በጠላትነት መፈራረጃቸው እንዲቆም የበኩሉን አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ ስምምነቱ እንዲመጣም ሁላችንም መልካም እንመኝ፡፡ እንዲያው ከተመኘን አይቀር የኤርትራን መንግሥትና ሕዝብ ሆድ አራርቶ በስምምነቱ ላይ የአሰብን ወደብ ቢመርቁልን እንዴት እናመሠግናቸው ይሆን!? (እንዲያው አንባቢን ፈገግ ለማድረግ ያህል እንጂ የምር መስሏችሁ ሰውየው በጦርነት ሊያስገባ ነው እንዳትሉኝ አደራችሁን)፡፡ አሁንም ደግሜ ልባቸውንና ሆዳቸውን ያራራ እላለሁ፡፡ መልካሙን መመኘት እኮ ለሁለቱም ወገኖች የህሊና ፈውስ ነው፡፡

      አፋርን ተሻግሮ አሰብ ከተማ እስከሚደረስ ድረስ ያለው ተፈጥሯዊ የመሬት አቀማመጥ ሰው የሚኖርበት አካባቢ ይደረሳል ተብሎ የሚታሰብ ባይሆንም ሲደረስ ግን ወደቡ፣ ነዳጅ ማጣሪያው፣ ጨው ማምረቻው፣ አውሮፕላን ማረፊያው፣ ቀይ ባህሩ አሁንም በተስፋ ብርሃን ወገግ ብለው ይታዩኛል፡፡ በተግባር አውቃቸዋለሁና ነው፡፡ አቦ!! ባይመለስልንም ደግሞ ‹‹እኛም አውቀናል፣ ጉድጓድ ምሰናል›› ነውና መልካሙን እንመኝላቸው፡፡ ለእኛ ሰላሙ ይሻለናል፡፡ በሰላማችንና በብርቱ ጥረታችን የአሰብ ወደብ ከነበረበት ጊዜ የበለጠ ለምተናል፡፡ ወደፊትም የበለጠ እንለማለን፡፡ የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥትነትን ሚናም ከወትሮው የበለጠ መወጣት ጀምረናልና፡፡

      በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተለያዩ መድረኮች ይፋዊ ንግግሮችና እስካሁን በተወሰዱ ዕርምጃዎች ኢትዮጵያዊነት ኃይል መሆኑን ማሳያዎች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ የዘር ጥላቻ እንዳይኖርና ወንድማማችነት እንዲጎለብት የወደፊቷን  ኢትዮጵያ ማስቀጠል የሚችሉ ትኩስ ኃይሎች ወደ መንግሥታዊ አስተዳደር እንዲገቡ መደረጉ፣ በተለያዩ ኃላፊነቶችና ቦታዎች አስተዋፅኦ ላደረጉ ግለሰቦች ዕውቅና መሰጠቱ፣ ከሁሉም በላይ ከጥላቻና የእርስ በርስ መበቃቀል ራሳችንን እንድናርቅ እየተገለጹ ያሉ አስተሳሰቦችና አቀራረቦች በጣም የሚያቀራርቡን ናቸው፡፡ የቀደምት አባቶቹን አደራ እየተረከበ ያለው ወጣትም ይህንኑ አደራ ሊወጣ የሚችለው፣ ትምክህትንና ጠባብነትን አንግቦ መሆን እንዳልጠቀመን ወደኋላ መለስ ብሎ ማየት ይጠይቃል፡፡

      ወጣቱ የዘመኑ ጎጠኝነትና ዘረኝነት ሊቅ ሳይሆን የዘመኑ ቴክኖሎጂና ረቂቅ ጥበብ ባለሙያ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ከሆነ ኢትዮጵያዊነት በእርግጥም ኃይል፣ በእርግጥም አንድነት ሆኖ ይዘልቃል፡፡ ይህ ካልሆነ በየጊዜውና በየወንዙ የምንማማል ሕዝቦች እንሆንና ጠንካራ፣ የተከበረችና የተወደደች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ የማናስረክብ እንሆናለን፡፡ ወቅቱንና ቦታውን ያልተጠቀምን ዜጎችና የታሪክ ተወቃሽም እንሆናለን፡፡ በየትኛውም መሥፈርት የአገራችን ሰላም እንዲደፈርስ፣ በየትኛውም መንገድ በሕዝቦቻችን መከባበርና መረዳዳት እንዳይጠፋ፣ በየትኛውም መሥፈርት የሚመጣው ለውጥ ከሰውና ከሀብት መውደም ውጪ እንዲሆን ሌት ከቀን መሥራት አለብን፡፡ ይኼንን ማድረግ ሲገባን፣ ማድረግ እየቻልን፣ ሳናደርግ ጊዜያችንን ካጠፋን ችግሩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ይመለከተናል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ኃይል እንዲሆን ሁላችንም የየድርሻችንን ሚና እንጫወት፡፡ ሁላችንም መደጋገፍን እንጂ አንዱ በሌላ ላይ ያላግባብ እጅ መቀሰር ይቅርብን፡፡ ለዛሬው በዚሁ ላብቃ፡፡ ሰላም ለእኛም ለአገራችንም ይሁን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...