በዘለዓለም እሸቴ (ዶ/ር)
በቅድሚያ የፍቅር ሐዋርያና የኢትዮጵያ ማንዴላ ለሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በሕይወታቸው ላይ የተቃጣውን እኩይ ሴራ ስንመለከት፣ ከደጋፊነት አልፈን በፍጥነት ወደ ረዳትነት መሸጋገር አገራዊ ግዴታ እንደሆነ መገንዘብ ይገባናል። ለማመንታት ጊዜ የለም። በቃ። በዚህ የመደመር መርሐ ግብር ውስጥ መከናወን ያለባቸው አራት ዓበይት ጉዳዮች አሉ።
ጥናት
የኢትዮጵያን አስተዳደር በተመለከተ ያስከተለውን ግጭትና የሕዝብ መፈናቀል መዘዝ ይጠና ያሉትን ዶ/ር ዓብይን፣ በዚህ ጥናት ላይ መሳተፍና የመፍትሔው አካል መሆን። ባለፈው 44 ዓመታት የሞከርናቸውን የለውጥ መንገዶች በሙሉ መፈተሽና ወደ ብርሃን ማምጣት።
ትምህርት
መከላከያ፣ ፍርድ ቤት፣ ሚዲያና ምርጫ ቦርድ የመሳሰሉት ከፖለቲካ ወገንተኝነት ገለልተኛ ሆነው ለዴሞክራሲ ዘብ እንዲቆሙ ዶ/ር ዓብይ የጀመሩትን የማስተማር ሒደት ላይ ተባባሪ በመሆን፣ የጨለማውን ጊዜ አካሄድ በዕውቀት ብርሃን መግለጽ። ጊዜው የፍቅር፣ ይቅርታና መደመር ነውና ይህንን አዲስ ርዕዮተ ዓለም በሁላችንም ዘንድ እንዲሰርፅ መማርና ማስተማር።
ለውጥ
መከላከያ፣ ፍርድ ቤት፣ ሚዲያና ምርጫ ቦርድ የመሳሰሉት መዋቅራዊና ሕጋዊ ለውጦች ላይ በሚደረገው ሒደት በተሳታፊነት ራስን በማቅረብ፣ ለውጡ ከውስጥ ወደ ውጭ እንዲዘልቅና ለተዓማኒ ምርጫ መሠረት እንዲጥል ማድረግ። ሕዝብም በነፍስ ወከፍ ልውጠትን በማካሄድ ለአዲሱ የኢትዮጵያ የብርሃን ዘመን መዘጋጀት።
ፀሎት
በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ተዓምራዊ ጉዞ የኢትዮጵያ አምላክ እጅ ያለበት ስለሆነ፣ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ እኩይ እንዳያኮላሽብን በየቤተ እምነታችን ሆነን ወደ ፈጣሪ መጮህን ማብዛት። ይህም የፀሎት አጀንዳ በገሃድ ስናደርግ እርስ በርሳችን በፍቅር ሰንሰለት እያያያዘን ወደ አንድነት ያመጣናል።
ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲ በሚያስኬድ ሽግግር ላይ ትገኛለች። ለዚህ የሽግግር ሒደት የሽግግር መንግሥት ማቋቋም ለዛሬ መፍትሔ አይደለም። ነገር ግን የሚያስፈልገው በሕዝብ ዘንድ ተዓማኒ የሆኑትና የሽግግር ድልድይ ከሆኑት ከዶ/ር ዓብይ ጋር መደመር ነው። ይህንን አስተሳሰብ ለመፈተሽ እንዲረዳን ከዚህ የሚከተሉትን ስምንት ነጥቦች አነሳለሁ።
በአብሮነት መላ መፍጠር
መፍትሔን እንደ ስጦታ ከመጠየቅ በአብሮነት መላ መፍጠር ይሁንልን። ከእኚህ የኢትዮጵያ ልጅ ዶ/ር ዓብይ ጋር ተያይዘን በመሥራት፣ ከእሳቸው የሽግግር ድልድይ ጋር መደመር ይሻለናል። አጋርነትን መግለጽ ማለት በሩቅ ሆኖ “ጥሩ ጅማሬ ነው” ብሎ መደገፍ ብቻ ሳይሆን፣ ቀረብ ብሎ ዴሞክራሲ እንዲወለድና ለእውነተኛ ምርጫ ተዓማኒነት የሚያስፈልጉትን ነገሮች ሁሉ በአብሮነት ማሳለጥ ነው።
የዶ/ር ዓብይ አህመድ ሰብዕና
ዶ/ር ዓብይ በተለየ መንገድ የኢትዮጵያዊነትን ገጽታ እያንፀባረቁ ይገኛሉ። አንድም በፓርላማ ሆነው ሲናገሩ አንበሳ ናቸው ያሰኛል። ደግሞ የዕርቅን ዘንባባ ይዘው፣ ለውስጥም ለውጭም የፍቅር ጥሪ ሲያቀርቡ እርግብ ናቸው ያሰኛል። ከዚህ እልፍ ስንል ደግሞ ተበጣጥሰንና አጥር አበጅተን ስንባላ፣ ከኢትዮጵያ አልፈው የምሥራቅ አፍሪካ ድንበር አልታያቸው ብሎ አንድ አፍሪካን ሲያልሙ፣ ምድር ላይ ጥሬ ከሚለቅመው ዶሮ ይልቅ ከፍ ብሎ የሚበረው ንስር ናቸው ብለን እንደመድማለን።
የኢትዮጵያዊነትን ምንነት በሰብዕናቸው የሚያንፀባርቁትን እኚህን የኢትዮጵያ ልጅ፣ ጥሪያቸውን ተቀብለንና በወንበራቸው ዙሪያ ተቀምጠን እውነተኛ ዴሞክራሲ ለማዋለድ ለእርሳቸው የአዋላጅነት ዕድል ለመስጠት፣ የሚታመኑ ናቸውና። ምክንያቱም በአመራራቸው ምክንያት ሕዝብ በአደባባይ ፍቅሩን ሰጣቸው። እሳቸውም የሕዝብን ድምፅ በመስማት ከምንም በላይ ለሕዝብ ታማኝነታቸውን በየዕለቱ ሲገልጡ ይታያሉ።
ኢትዮጵያ የተዓምር አገር
ለመሆኑ የኢትዮጵያ ጉዞ በዚህ አጭር ጊዜ ያየነው ከተለመደው ወጣ ያለ ነው። ተዓምር ሆኖብን በእውነት የኢትዮጵያ አምላክ አለ አልተባለምን? ታዲያ በተዓምር የተጀመረው ይኼ ሒደት በተዓምራዊነቱ እንዲቀጥል እምነት ልናጣ አይገባም። በሁሉም ጎራ የተሠለፉትን የኢትዮጵያ ድንቅዬ ልጆቿን አሳትፋ፣ ዓለም ከዚህ በፊት ያላየውን አዲስ መንገድ ኢትዮጵያ ማሳየት ትችላለች። ሌሎች አገሮች የኢትዮጵያ መንገድ ብለው የሚጠሩት አካሄድ ለመጀመርያ ጊዜ ለመቀየስ እንነሳ።
የትግሉ ባለአደራና ጠባቂ ሕዝብ ነው
እናውቅልሃለን ብለን ሕዝቡን ከራሳችን ጎን ማሠለፍ ከእንግዲህ አይቻልም። የሚያዋጣው ራሳችንን ከሕዝብ ጎን ማሠለፍ ነው። የኢትዮጵያ የለውጥ ጉዞ ባለቤት ሕዝብ ነው። ባለአደራውም ሕዝብ ነው። ከእንግዲህ ሕዝብ ራሱ ንጉሥ ሆኖ በምርጫ ካርድ አገልጋይ የሚሆነውን መንግሥት እስኪመርጥ ድረስ አያርፍምና ሁላችንም የሕዝብን ድምፅ እያደመጥን ከዶ/ር ዓብይ አመራር ጋር በአብሮነት መጓዝ ጥሩ ነው።
የራስን የቤት ሥራ መወጣት
ድሮ ድሮ ምርጫ ስለሌለ ሁሉም ተቃዋሚ መሆን ነበረበት። ግማሹ በሰላማዊ ትግል፣ ሌላው በትጥቅ ትግል ግዴታ ስለሆነ ተሠለፈ። ተወያይቶ ሐሳብን ያማከለ ኅብረት በማድረግ ለመቀናጀት ፋታ አልነበረውም። ዛሬ ግን ሁኔታው እየተቀየረ ነው። ጊዜው የተበታተነው ተፎካካሪ በአስተሳሰብ ዙሪያ ኃይሉን በማቀናጀት ፈርጠም ያለ ተፎካካሪ በመሆን መቅረብ የሚጠበቅበት ወቅት ነው። ጊዜው የትግል ሥልት የሚያስቀይር ነው። የተፎካካሪው ውበት እንዲወጣና እንዲያስደምመን፣ የራስን የቤት ሥራ መወጣት ይጠይቃል። ታዲያ ይህንን የራስን የቤት ሥራ ለመሥራት ጥድፊያ ላይ እንሁን።
ልዩ ብቸኛ አጋጣሚ
ሁልጊዜ ከዜሮ መጀመር ለአሁኑ ወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ መልስ አይደለም። ያለውን ሥርዓት ድምጥማጡን አጥፍቶ አዲስ ሽግግር መንግሥት እናቋቁም ብለን ከምንታገል፣ በሕዝብ የፀደቀውን የዶ/ር ዓብይ አህመድ ድልድይ የመሆን ልዩ ብቸኛ አጋጣሚ በመጠቀም፣ ወደ እውነተኛ ምርጫ መሄድ ላይ ማተኮር ይሻላል። ይህን የተጀመረው የለውጥ መንገድ እንዳይሰምር በመንግሥትና በኢሕአዴግ ውስጥ ሆነው እንቅፋት የሚሆኑትን ወንድሞቻችንን አይጠቅማችሁም ብለን ልንሞግታቸው ያስፈልጋል።
ሕዝብ የወለደው አመራር
ብዙ ጊዜ የሽግግር መንግሥት ከአምባገነን መሪ ለመላቀቅ፣ ወይም መንግሥት በአመፅ ምክንያት መግዛት ሲሳነውና ሲፍረከረክ፣ ከዜሮ ለመጀመር ሲገደድ የሚደረግ ክስተት ነው። አሁን ያለው አመራር ግን በሕዝብ ምርጫ የመጣ ባይሆንም በሕዝብ ትግል የተወለደ ነው። በእነ አቶ ለማ፣ በአቶ ገዱ፣ በአቶ ደመቀና በሌሎችም የለውጥ አራማጆች ታጋይነትና በኢትዮጵያ ወጣቶች ደምና እንግልት የመጣ ነው። ስለዚህ ይህንን አክብሮ ከዚህ ሕዝባዊ ከሆነ አመራር ጋር መደመርና ሌሎችም እንዲደመሩ ተግቶ መሥራት መልካም ነው።
አዲስ ጊዜና አዲስ አመለካከት
ሁሉም የሽግግር መንግሥት እውነተኛ ዴሞክራሲ እንዳመጣ ታሪክ አይነግረንም። ትናንት በጨለማው ዘመን የሽግግር መንግሥት ስንል ከርመን፣ ዛሬ ጊዜው ተቀይሮ ብርሃን ሲወጣም፣ ይህ የድሮ ሐሳባችን ጊዜውን ይመጥነው እንደሆነ ሳንለካው፣ ትናንት የጻፍነውን ወረቀት ዛሬም ያንኑ ብቻ ማንበብ እውቀት አይሆንም። ከሩቅ በመሆንና የማያባራ ትዕዛዝ ለዶ/ር ዓብይ ከመስጠት፣ ጠጋ ብለን በጋራ የምንስማማበት የዴሞክራሲ ውልደት ፍላጎት ላይ ተመሥርተን ወደ ውይይት ማምራት ይሻላል።
የኢትዮጵያ ልጆች ከሩቅ ከቅርብ ለዶ/ር ዓብይ ተልዕኮ መሳካት ሲረባረቡ ማየት፣ ይህ ሕዝብ ታሪክ ሊሠራ ቆርጦ መነሳቱን ያሳያል። አብሮ መብላት ብቻ ሳይሆን፣ አብሮ መሥራትም የተካነ እንደሆነ ሊያስረግጥ ተነስቷል። እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አሰበ፡፡ ይባርካታልም።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡