Tuesday, February 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርሽብርና አሸባሪነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀቲት

ሽብርና አሸባሪነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀቲት

ቀን:

በመርሐ ጽድቅ መኮንን ዓባይነህ

በሥልጠናም ሆነ በልምምድ ረገድ የሕግ ሙያተኛ ነኝ፡፡ ከዚሁ በመነጨ ምክንያት ታዲያ በአየር ላይም ቢሆን የአገሪቱ ሕገ መንግሥት እንዲከበርና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የበኩሌን ጥረት ማድረግ ምርጫዬ ብቻ ሳይሆን ግዴታዬ ሆኖ ቆይቷል፡፡

የዜጎችን መሠረታዊ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች የሚመለከቱትና በደማቁ የተጻፉት የሕገ መንግሥቱ ወርቃማ ድንጋጌዎች በመሬት ላይ ከሚታየው ተቃራኒ እውነታ ጋር አልፈዋል፡፡ አለመጣጣማቸው ፈጽሞ ተስፋ አላስቆረጠኝም፡፡ በእርግጥ ለሙያው ቅርብ ሆኖ ሲያበቁ በመሬት ላይ ገቢራዊ የማይደረግን የሕግ ሥርዓት ለረዥም ጊዜ ያላግባብ እያንቆለጳጰሱ መቀጠል የቱን ያህል እንደሚያታክትና የራስን ህሊና ሳይቀር እንደሚፈታተን ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ ሆኖም ችግሩ እስካልተቀለበሰ ድረስ ዜጎች ሁሉ በየፊናቸው የሚያካሂዱትን ትግል ማቋረጥ እንደሌለባቸው በፅኑ አምናለሁ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እነሆ ይኼንኑ ጥረት አጠናክሮ ለመቀጠል አሁን አሁን በአገር ውስጥ አደፋፋሪ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ መምጣታቸውን በአንክሮ መቀበል፣ ከዚህ በፊት ታይቶ ባልታወቀ የራስ መተማመን በመወሰድ ላይ ያሉትን ተከታታይና አነቃቂ የለውጥ ዕርምጃዎች በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መደገፉ ተገቢና አስፈላጊ መስሎ ይሰማኛል፡፡ አበው ‹‹ጋን በጠጠር ይደገፋል›› እንዲሉ፡፡

በእኔ በኩል አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ከፍተኛው የአገሪቱ ሕግ አስፈጻሚነትና አስተዳደራዊ ሥልጣን ከመጡበት ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. አንስቶ እየሆነ ያለው ነገር ሁሉ የህልም እንጂ የእውነት መስሎ አይሰማኝም፡፡ በተለይ ሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ለኢሕዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት የመንግሥት ሥራ አፈጻጸም ሪፖርትና ከምክር ቤቱ እንደራሴዎች ለተሰነዘሩላቸው አያሌ ጥያቄዎች የሰጡት ማብራሪያ፣ ተስፋዬ ይበልጥ እንዲያንሰራራና እንዲለመልም ሳያደርገው አልቀረም፡፡ ከቀደሙት ሌሎች አጋጣሚዎች በበለጠ ሁኔታ በዚያ መድረክ ሰውዬው ከግምቴ ውጪ ብልህ፣ ቀጥተኛ፣ ግልጽና ደፋር መሪ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፡፡

በዕለቱ ከተከበሩ የሕዝብ እንደራሴዎች በቀረቡላቸው ጉዳዮች ላይ ባላቸው ጥልቅ ዕውቀት፣ ነገሮችን በተነተኑበት ችሎታና በራሳቸው ተማምነው በወሰዷቸው የማያወላውሉ አቋሞች በጣም ተገርሜያለሁ፡፡ አቀራረባቸው ቀላልና እንግድነት የማይታይበት ነው፡፡ እያንዳንዱን ጥያቄ በተመለከተ በምክር ቤቱ ያደርጉት የነበረው ገለጻም በዝርዝር ዕውቀት ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ የሚደርሱባቸው ድምዳሜዎችም በበቂና አሳማኝ ምክንያቶች የተደገፉ ናቸው፡፡

ከአንደበተ ርዕቱነታቸው ባሻገር የቋንቋ አጠቃቀማቸው ሳይቀር ደረጃውን የጠበቀ፣ የቅርብም ሆነ የሩቅ አድማጭ ተመልካቾቻቸውን ዓይንና ጀሮ ለጊዜው የመያዝ ብቻ ሳይሆን እስከመጨረሻው ተቆጣጥሮ የማቆየት አቅም ያለው ነው፡፡

ሪፖርቱ ለፓርላማው በንባብ ከተሰማ በኋላ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅድሚያ የቀረበላቸው ጥያቄ የፀረ ሽብር አዋጁን አተገባበር የሚመለከት እንደነበር ሁላችንም እናስታውሳለን፡፡ መንግሥት በሽብር፣ በከባድ ሙስናና በነፍስ ግድያ ወንጀሎች ተጠርጥረው የተያዙትን፣ የተከሰሱትንና የተፈረደባቸውን ወንጀለኞች ሳይቀር በምሕረትና በይቅርታ ስም በተከታታይ እየለቀቀ ያለበትን አድራጎት ተገቢነት ክፉኛ የተቃወሙት አንዷ የሕዝብ እንደራሴ፣ በሥራ ላይ ያለው የፀረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 ዓ.ም. እየተጣሰ ነውና በእሳቸው አስተያየት ሕጉ በወረቀት ላይ እንዳለ ቢታወቅም፣ በግብር የተሻረበትን ምክንያት እንዲያስረዷቸው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠይቀዋቸው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በአቀራረቡ ሲታይ ፍፁም ተገዳዳሪ ለሚመስለው ለዚያ የሴት እንደራሴዋ ቅሬታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተባ አንደበታቸው የሰጡት ምላሽ አስደማሚ ነበር ለማለት እደፍራለሁ፡፡

ቀድሞ ነገር በወንጀል ተከሰው የተፈረደባቸው ሰዎች ማረሚያ ቤት ከገቡ በኋላ የሕግ ታራሚዎች እንጂ ወንጀለኞች አይባሉም እስከማለት መጠበባቸው ሳያንስ፣ ከሁሉ በላይ ሽብር ምንድን ነው? አሸባሪስ ማን ነው? ሲሉ ያልተጠበቀና ስሜት የሚያነሳሳ ጥያቄ በመሰንዘር ወደማብራሪያቸው የተንደረደሩት አዲሱ መራሔ መንግሥት የሕዝብ እንደራሴዋ የጠቀሱት አዋጅ የተመሠረተበትን ፍልስፍና ሳይቀር በመተንተኑ ረገድ የዋዛ አልነበሩም፡፡

እንደ እሳቸው እምነት ከሆነ ሽብር ሕገ መንግሥቱ ከሚፈቅደው አሠራር ውጪ በሥልጣን ላይ ያለን አንድ መንግሥት ለማቆየት ሲባል የፖሊስ፣ የደኅንነትና የመከላከያ አባላት ጭምር በንፁኃን ሰዎች ላይ የሚፈጽሙትን ድብደባ፣ ግርፋትና ጨለማ ቤት የመዝጋት ተግባራት ያካትታል፡፡ አሸባሪ የሚባለው ደግሞ በዚህ ዓይነቱ አሰቃቂና ጭካኔ የተመላበት አድራጎት የተሳተፈ ማንኛውም ሰው ስለሆነ፣ እገሌ ከእገሌ ሳይባል እጃቸው ያለበት ወገኖች ሁሉ መንግሥት በመሆናቸው ብቻ ከሕግ ተጠያቂነት የሚድኑበት አንዳች ምክንያት አይኖርም በማለት ለሕዝብ እንደራሴዎቹ እቅጩን ሲነግሯቸው ታዝበናል፡፡

ይህንን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሀቲት ጥያቄው ከተነሳበት አዋጅ ቁጥር 652/2001 ዓ.ም አንዳንድ ድንጋጌዎች ጋር ማገናዘቡ፣ የአንደበታቸውን ገዥነት ብቻ ሳይሆን የዕይታቸውን ስፋት ለመረዳት ያግዛል ብዬ አምናለሁ፡፡

አዋጁ ‹‹ሽብር›› የሚለውን ቃል በተዘዋዋሪ እንጂ በቀጥታ ሲተረጉመው አናይም፡፡ እንዲያውም ወደ ጽንሰ ሐሳቡ ፈራ ተባ እያለ የሚጠጋው ከመንስዔው ወይም ከይዘቱ ይልቅ በውጤቱ ላይ በማተኮር ይመስላል፡፡ ከዚያ ይልቅ በሽብርተኝነት የሚፈጸሙ ድርጊቶችን ነው በአንቀጽ 3 ሥር የሚዘረዝረው፡፡ ስሙን ሲጠየቅ የአባቱን ስም በመናገር እንደሚጀምር ሰው ማለት ነው፡፡

አዋጁ በአንቀጽ 3 ሥር ‹‹የሽብርተኝነት ድርጊት›› ነው ሲል አጥብቆ የሚኮንነው ‹‹አንድን የተወሰነ ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊ ወይም ርዕዮተ ዓለማዊ ዓላማ ለማራመድ አስቦ ማንኛውም ግለሰብ ወይም በቡድን የተደራጀ የትኛውም ኃይል በመንግሥት ላይ አንዳች ዓይነት ተፅዕኖ ለማሳደር፣ ኅብረተሰቡን ወይም የኅብረተሰቡን ክፍል ለማስፈራራት ወይም የአገሪቱን ሕገ መንግሥታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ማኅበራዊ ተቋማት ለማናጋት ወይም ለማፍረስ የሚፈጽመውን ማናቸውንም የወንጀል ተግባር፤›› ነው፡፡

በዚህ ኃይለ ቃል መነሻነት ከፍ ብሎ የተጠቀሰውን ዓላማ ለማራመድ ታስቦ በማንኛውም ሰው ወይም ቡድን የተፈጸመ ወይም የሚፈጸም ‹‹የነፍስ ግድያ ወይም ከፍተኛ አካላዊ ጉዳት፣ የአንድን ኅብረተሰብ ወይም የዚህኑ ክፍል ደኅንነት ወይም ጤና ለከፍተኛ አደጋ ማጋለጥ፣ ዕገታ ወይም ጠለፋ፣ በግል ንብረትም ሆነ በተፈጥሮ ሀብት፣ በአካባቢ፣ በታሪካዊ ወይም በባህላዊ ቅርሶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረስ፣ ማናቸውንም የሕዝብ አገልግሎት ለከፍተኛ አደጋ ማጋለጥ፣ መያዝ፣ በቁጥጥር ሥር ማዋል፣ ማቋረጥ ወይም ማበላሸት ወይም ከእነዚሁ ድርጊቶች መካከል አንዱን ወይም ሌላውን ለመፈጸም መዛት፤” በአሸባሪነት ወንጀል የሚያስጠይቅና “ከ15 ዓመታት እስከ ዕድሜ ልክ በሚደርስ ጽኑ እስራት ወይም በሞት የሚያስቀጣ፤” ከባድ ጥፋት እንደሆነ በዝርዝር መደንጉን እንመለከታለን፡፡

እንግዲህ የአገሪቱ የፀረ ሽብር አዋጅ ሽብርተኝነትን የሚተረጉመው በዚህ ዓይነት መንገድ መሆኑ ከታወቀ፣ የሕዝቡን ደኅንነትና የመንግሥቱን ፀጥታ በመጠበቅ ስም ከመደበኛው የወንጀል መከላከልና ምርመራ አካሄድ ባፈነገጠ አሠራር፣ ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያለው የፖለቲካ ድርጅት የሚመራበትን አብዮታዊ ዴሞክራሲ ከሰላማዊ ጥቃት ለመከላከል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳብራሩት ከመስመር የወጣ የሰብዓዊ መብት ረገጣ የሚፈጽሙ የፖሊስ፣ የፀጥታና የመከላከያ አባላት ቢኖሩ በትርጓሜው የመሸፈናቸው ዕድል ከፍተኛ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር በዘፈቀደ የሚፈጽሙት ኢሕገ መንግሥታዊ የሰቆቃ ድርጊት በአዋጅ ቁጥር 652/2001 ዓ.ም. አንቀጽ 3 መሠረት የሽብርተኝነትን ወንጀል ስለሚያቋቁም፣ የመንግሥት አካላት በመሆናቸው ብቻ በአሸባሪነት ተይዘው ላለመጠየቃቸው አንዳችም ዋስትና የለም፡፡

የትኛውም መንግሥት መቼውንም ጊዜ ቢሆን በራሱ ላይ የሚቃጣውን ጥቃት እንጂ፣ ራሱ በዜጎቹ ላይ የሚፈጽመውን ኢሕገ መንግሥታዊ ድርጊት በሽብርተኝነት ይፈርጃል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን አቋም የተለየ የሚያደርገው ታዲያ ራሳቸው እንደመሰከሩት በዚህ አገርና ደግ ሕዝብ ላይ ሲፈጸም ለቆየው ገደብ የለሽ ጥፋትና ውድመት፣ መንግሥታቸው ጭምር ኃላፊነት እንደሚወስድ በአደባባይ ለመናገር ሐሞት ማግኘታቸው ብቻ ነው፡፡

ያም ሆኖ ታዲያ ይህ አስተያየታቸው በቅንነት መታየትና በአርቆ አስተዋይነት መወሰድ ይኖርበታል፡፡ በወንጀል ፍርድ ቤት እንደተሰጠ የተከሳሽነት ቃል ተቆጥሮ ለምክር ቤቱ ከቀረበበት ዓውድ ውጪ ያላግባብ እየተለጠጠ መተቸት አይኖርበትም፡፡

በሁሉም አገሮች ዘንድ እኩል ተቀባይነት ያለው ትርጓሜ አይገኝለት እንጂ፣ ሽብርተኝነት በመሠረቱ ድንበር ዘለል የሆነ ዓለም አቀፍ ወንጀል ነው፡፡ አሁን በደረስንበት የዕድገት ደረጃ የሽብር መቆጣጠሪያ ሕግ የሌለው አገር የለም፡፡ ኢትዮጵያችንም ይህ ሕግ ያለጥርጥር ያስፈልጋታል፡፡

ይልቁንም አገራችን በመስኩ የተደረጉ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውሎችን የፈረመች በመሆኗ፣ እነዚህን ውሎች በብሔራዊ ደረጃ ገቢራዊ ለማድረግ ዝርዝር የማስፈጸሚያ ሕግጋትን ማውጣት መብቷ ብቻ ሳይሆን ግዴታዋም ጭምር ነው፡፡ ከእነዚህ ውሎች መካከል እ.ኤ.አ. በ1999 በቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የዛሬው የአፍሪካ ኅብረት) መሪዎች አልጀርስ ላይ የፀደቀውን አኅጉር አቀፍ የሽብር መከላከያና መቆጣጠሪያ ስምምነት ብቻ ለአብነት ያህል መጥቀሱ ይበቃል፡፡

ከዚህ ባፈነገጠና ወደ ጽንፍ በተገፋ አቋም አንዳንድ ወገኖች እንደሚያቀነቅኑት፣ አዋጁ ከናካቴው እንዲሰረዝ ሳይሆን እንዲሻሻል ነው የሚያስፈልገው፡፡ የተንሻፈፈው ፖለቲካችን ከእውነተኛው የደኅንነት ፍላጎታችን ጋር ተጣጥሞና ተቃንቶ መራመድ አለበት፡፡

መሬቱ ይቅለላቸውና አልፎ አልፎ ምፀት በተላበሰው አነጋገራቸው የምናስታውሳቸው ሟቹ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ፣ ‹‹በሥልጣኔ ከገፉት አገሮች የሕግ መድበል ከእነ ኮማው የገለበጥነው ነው፤›› በማለት ያረገርጉለት የነበረው የአገሪቱ ፀረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 ዓ.ም. በቴክኒክም ሆነ በይዘት ረገድ ሰፊ ጉድለቶች የሚታዩበት እንደሆነ፣ የመስኩ ባለሙያዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች አንስተናል፡፡ እነሆ ጊዜው ደርሶና ሰሚ ተገኝቶ መከለስ የሚገባው ስለመሆኑ ውሳኔ ላይ ከተደረሰ፣ ትርጓሜውን የያዘውን አንቀጽ 3 ጨምሮ በተለይ የአዋጁ አንቀጽ 5 (ለሽብርተኝነት ድጋፍና ከለላ ስለመስጠት)፣ አንቀጽ 6 (ሽብርተኝነትን ስለማበረታታት) እና አንቀጽ 7 (በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ ስለመሳተፍ) ድንጋጌዎች ከመጠን በላይ አሻሚና ያላግባብ ተስፋፍተው የሚሠራባቸው በመሆናቸው ሕገ መንግሥቱ ለዜጎች የሰጠውን የተሟላ የመሠረታዊ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች ጥበቃ በማይሸራርፍ ሁኔታ ተለቅመው መሻሻል ይኖርባቸዋል፡፡

በመጨረሻም የፀረ ሽብር ሕግ ዓይነተኛ ዓላማ የሕዝብን ደኅንነት ከተደራጀ ጥቃት መከላከልና የመንግሥትን ፀጥታ ማረጋገጥ ነው፡፡ በዚህ ፀባዩ ከመደበኛው የወንጀል ሕግ የተለየ ዓላማ የለውም፡፡ ሆኖም በመሬት ላይ ተፈጻሚ ሲደረግ በሕግ አስከባሪ አካላት በኩል ብርቱ የጥንቃቄ ዕርምጃ ካልተወሰደና በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ካልተሠራበት፣ ከሌላው የወንጀል ሕግ በበለጠ ሁኔታ ለሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች ረገጣ የቀረበ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የካቲት አብዮት – ጥያቄዎችሽ ዛሬም እየወዘወዙን ነው!

በበቀለ ሹሜ አጭር መግቢያ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከ1960ዎች ወጣቶች ርዝራዦች አንዱ...

የሰሞኑ የ“መኖሪያ ቤቶች” የጨረታ ሽያጭ ምን ዓይነት ሕጋዊ መሠረት አለው?   

በዳዊት ዮሐንስ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ አየር ላይ ከሚንሸረሸሩ ዜናዎች...

ሁለቱ ወጎች፡ ከሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! እስከ በዓሉ ቤርሙዳ

በተክለ ጻድቅ በላቸው ሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! ከሁለት ሦስት ዓመት...

ለትግራይ ክልል ድርቅ ተፈናቃዮች አፋጣኝና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲደረግ ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዩች ቋሚ...