Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ትልቁ ዳኛ የራስ ህሊና!

አንድ ጎልማሳ ስልክ እየተነጋገረ ነው፣ ‹‹የኢቲቪ ግብር መክፈያ ጣቢያ የት ነው የሚገኘው? ያለብኝን ሁሉ ውዝፍ ግብር ከእነ ወለዱ መክፈል እፈልጋለሁ . . . ›› እያለ ያወራል፡፡ ቀጥሎም፣ ‹‹ለነገሩ ኢቲቪ በዚህ ግልጽነቱ ከቀጠለ ጃም መደረጉ አይቀርም . . . ›› እያለ መሳቅ ጀመረ፡፡ ወያላው ደግሞ ደረቱን እየደቃ፣ ‹‹አባቴን ገድለውብኝ ነበር . . . አባቴን . . . ›› እያለ ዕንባ እየተናነቀው ያብራራል፡፡ ሌላው ጥግ ላይ የተቀመጠው ደግሞ እንደ መራቀቅ እያለ፣ ‹‹ኖ ሞር ግንቦት ሃያ! ሰኔ 16 ኢዝ አወር ደይ . . . ›› አለ፡፡ ከፊል አማርኛውን ያወርደዋል፡፡ ሌላው ደግሞ፣ ‹‹ቦምቡ የፈነዳበት ቦታ ነበርኩኝ . . . ለጥቂት ነው የሳተኝ . . .›› በማለት ያብራራል፡፡ ወቸው ጉድ! ሁኔታውን ለተመለከተው ዛሬም ሰኔ 16 ነው እንዴ ያሰኛል፡፡ ሕዝቡ ውስጥ ያለው ስሜት ገና ትኩስ ከመሆኑ የተነሳ ወሬው ሁሉ ‹ዓብይ አህመድ! ፍቅር ያሸንፋል! ሰኔ 16! መደመር! የቀን ጅቦች!› የመሳሰሉ ነበሩ፡፡ የጉዟችን መዳረሻ ስቴዲዮም ሲሆን፣ መነሻችን ደግሞ ቦሌ ነው፡፡

ሾፌሩ፣ ‹‹መቼም በእኔ ዕድሜ እንደዚህ ሕዝቡ ልሙትልህ ያለው መሪ አይቼም አላውቅም፤›› በማለት ለጀመረው ወሬ ወያላው ሲመልስ፣ ‹‹መቼ ሌላውን የምታይበት ዕድል አጋጠመህና ነው? ከኖርካቸው ሰላሳ ዓመታት ውስጥ ሃያ ሰባቱን ማን እንደጨፈረብህ ዘንግተኸዋል መሰለኝ?›› በማለት መለሰለት፡፡ የሚገርመው አብዛኛዎቹ የታክሲ ውስጥ ጥቅሶች ተቀያይረዋል፡፡ በፊት ‹የቤትሽን አመል እዚያው! መብታችሁ ታክሲ ውስጥ ትዝ አይበላችሁ› የሚሉትና የመሳሰሉት ተለውጠው፣ አሁን በዓብይ ዙሪያ በሚያጠነጥኑ፣ በፍቅር ዙሪያ በሚያተኩሩ፣ በመደመር ዙሪያ በሚያተኩሩ ጥቅሶች ታክሲው ተጨናንቋል፡፡

አንዲት ሴት፣ ‹‹ሕዝቡን ላስተዋለው ከባዕድ አገዛዝ የተላቀቀ ነው የሚመስለው፤›› በማለት ላነሳችው ሐሳብ ከጎኗ የተቀመጠው ሰው ሲመልስ፣ ‹‹እሱ በስንት ትርፉ? መንገድ ገንብቶልሽ፣ መሠረተ ልማትን ሰጥቶሽ እኮ ነው፡፡ ከዚያ የባሰ ነገር ውስጥ እኮ ነው የከረምነው . . . ›› በማለት ሲያብራራ፣ ወያላው ድንገት ጣልቃ ገብቶ፣ ‹‹የሰው እንትን ላይ ውኃ ከማንጠልል የከፋ ነገር ማንም መጤ አድርጎ አያውቅም፤›› ሲል ሾፌሩ ተቀብሎ፣ ‹‹አታውሩ፣ አትሽኑ ብለውን ነበር እኮ?›› በማለት ለመቀለድ ሞከረ፡፡

አንድ ሰው ሁሉንም ወሬ በአንክሮ ሲከታተል ቆይቶ፣ ‹‹እንዲያው ይኼ ሰውዬ እንደመር ባለ? ይቅርታን በሰበከ?›› እያለ በሐዘን ስሜት ሲያለቃቅስ ወያላው ሒሳብ እየሰበሰበ ማንጎራጎር ጀምሮ ነበር፡፡ ዘፈኑን የምናውቀው ይመስላል፡፡ ግን የሆነ ነገሩን እንደቀየረው ተገንዝበናል፡፡ ‹‹የመጀመርያዬ ነው ባለሥልጣን ስወድ . . .፣ የመጀመርያዬ ነው ባለሥልጣን ስመርጥ . . . ፣ የመጀመርያዬ ነው  . . . ›› እያለ ደጋግሞ ጆሮዋችን ላይ አቃጨለብን፡፡ ወያላው ደጋግሞ ከማንጎራጎሩ የተነሳ ሁሉም ሰው አፍ ላይ ‹የመጀመርያዬ ነው› የምትለዋ ዓረፍተ ነገር እየመጣች ይመስላል፡፡ ይኼን ጊዜ ሾፌሩ፣ ‹‹እርስዎስ ከዚህ በፊት በባለሥልጣን ፍቅር ወድቀው ያውቃሉ? ካልሆነ ከወያላው ጋር ብንደመርሳ?›› ሲል ሰማነው፡፡

መቼም ስለጅብ ባህርይ ከመጀመርያው ጀምሮ ሲያብራራ የነበረውን ሰውዬ ሳናነሳው አላልፍም፡፡ እንዲያውም ወሬውን ላጤነው ከጅቦች ጋር ብዙ ዓመት የቆየ ነው የሚመስለው፡፡ ሌላው ደግሞ ከጠቅላዩ ውጪ ምንም ሌላ ወሬ የሌለው ይመስላል፡፡ ‹‹ይኼንን ሁሉ የፍቅር ዶፍ እንዴት ይሆን የቻልከው?›› እያለ ይመራመራል፡፡ ሌላው ተቀበለውና፣ ‹‹መሸክም የሚያቅተው ጥላቻ ነው እንጂ፣ ፍቅርን ለመሸከም ሰፊ ጫንቃ አያስፈልግህም፤›› በማለት መለሰለት፡፡ ይኼን ጊዜ ጥልቅ ብሎ የገባው ስለጅቦች ሲያወራ የነበረው ሰው፣ ‹‹ታዲያ ጅቦቹ በምን ጫንቃቸው ነው የመቶ ሚሊዮን ሕዝብ ጥላቻ ተሸክመው የኖሩት?›› የሚል ጥያቄ አንስቶ የመለሰለት ሰው አልነበረም፡፡ ሁሉም ሰው ‹አሁን ጥላችን የምናስተናግድበት አይደለም› ያለ ይመስላል፡፡

አንድ መጨረሻ ላይ የተቀመጠው ሰው ብቻውን ከፌስቡክ ላይ ያነበባቸውን ቀልዶች ‹ሼር› እያደረገልን ነው፡፡ በተለይ አንዲት ሴት አለች ያለውን ሲነግረን ፈገግ አልን፡፡ አንድ ባለሥልጣን ሥልጣናቸውን ለቀቁ ሲባል ሰምታ፣ ‹‹የሸጎጠውን ይዞ እንኳንም ጠፋልን፤›› በማለት አስፈገገችን፡፡ በዚህም አላበቃም፡፡ ‹‹ዓብይ ደም ሰጠ ሲባል ሰምተው አያሌ የከተማችን ቆነጃጅት የደም ማነስ አለብን እያሉ ጥቁር አንበሳ አካባቢ መታየታቸውን ያስተዋለው ጎረምሳ፣ የሰው ደም ከመጠጡት ውሰዱ አላቸው›› በማለት ሲሳለቅ ሳንፈልግ አሳቀን፡፡ ሌላው ተቀብሎት፣ ‹‹ከደም መጣጭ ወደ ደም ለጋሽ ሥርዓት እንኳን በደህና መጡ፤›› እያለ ተሳለቀ፡፡ የመጀመርያው ሰው፣ ‹‹አሁን ደግሞ የደም ባንኩ ላይ ቦምብ እንዳይወረወሩ ፍራ፤›› በማለት ብቻውን ሳቀ፡፡

ሌላው ደግሞ፣ ‹‹ኤፍቢአይ መምጣቱ ግን አግባብ ነው? በሌለን ዶላር? ለእነሱ በዶላር መክፈል ይቻላል?›› እያለ ዶላር እንቆጥብ ሲል ወያላው ተቀብሎ፣ ‹‹እንዲያውም ካነሳኸው አይቀር የአዲስ አበባ ኮረዳዎች ቶሎ ቶሎ እየፈነዱ ያሉበትንም ሁኔታ አጣርቶ ቢሄድልን፤›› እያለ ቀለደ፡፡ ይኼን ጊዜ መጀመርያ አስተያየቷን አቀብላ የነበረችው ልጅ፣ ‹‹ክፍተት አሳይተዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች ቁጥር ሰላሳ ደረሰ እኮ? ይኼ ቁጥር እየጨመረ ሄዶ እነ ጉደኞቹን ያካተተ መሆኑ የታወቀ ዕለት ወየው! ወየው!›› ስትል ሌላው ተቀብሏት፣ ‹‹እኔ ግን አዲስ ሐሳብ አለኝ?›› ሲል ምን ይሆን በሚል ስሜት ትኩረት ሲሰጠው፣ ‹‹ባንዲራችን ላይ ያለው ኮከብ ተነስቶ በምትኩ የመደመር ምልክት እንዲገባበት ነው ፍላጎቴ፤›› በማለት አስተያየቱን ሰጠ፡፡ እንግዲህ የሰው ፍላጎት የተለያየ ስለሆነ ምን ማለት ይቻላል? ዴሞክራሲ ነዋ!

ይኼ ጊዜ ወያላው፣ ‹‹ኧረ የእግር ኳስ ተጫዋቾቻችንን እግር ቢፈቱልን? ስንት ዘመን ከታሰረ እኮ፤›› እያለ በእግር ኳስ ቡድኖቻችን ላይ ማሾፍ ጀመረ፡፡ ሾፌሩ ደግሞ፣ ‹‹አሁንማ ዕድሜ ለዓብይ ማን ፖለቲከኛ፣ ማን ቀልደኛ ያልሆነ አለ?›› በማለት ሐሳቡን ደመረ፡፡ አሁን አሁን የዓብይ መብላት፣ መጠጣት፣ መዋልና ማደር እያስጨነቃቸው ያሉ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ተነስተዋል፡፡ ጥግ ላይ ተቀምጦ ከፌስ ቡክ የቃረማቸውን ነገሮች ሲያደርሰን የነበረው ወጣት አንድ ግጥም ይዞልን ከተፍ አለ፡፡

‹‹አትንኩት ዓብይን

ዓብይን አትንኩ

እርሱን ከምትነኩ

እንኩ ነፍሴን እንኩ

አለ የኢትዮጵያ ሕዝብ . . . ›› በማለት የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዓብይ ሟች ነው፡፡ የሚል ሐሳብ ያዘለ ግጥም የመሰለ ነገር አመጣ፡፡ ወያላው በማስከተል፣ ‹‹ዕድሜ ለዓብያችን ገጣሚያን፣ ደራሲያንና ኢትዮጵያዊያን አድርጎናልና፤›› ዘንድሮ ምን የማይባል አለ?

አንድ ጎልማሳ ደግሞ፣ ‹‹ስለዓብይ ከሆነ ስድ ንባቡም ግጥም ይሆናል፡፡ የማያስቀው ያስቃል . . . ›› አለና ምን ይላል ብለን ስንጠብቅ፣ ‹‹የዓብይን ደም የወሰደችው ነርስ የአክስቴ ልጅ ናት . . . ›› ብሎ ትኩረት ሰበሰበ፡፡ ስለዓብይ ተወርቶ ማን ጆሮ ሊነሳ? ሰውዬው ቀጠለ፣ ‹‹እርሷ እንደተናገረችው ከሆነ ደሙ ቀይ ብቻ አይደለም! አረንጓዴም፣ ቢጫም አለው፤›› በማለት ሳቀ፡፡ እኛም አብረን ሳቅን፡፡ ጊዜው የመደመር አይደል?

ይህንን ሁሉ ሲያዳምጡ የነበሩ አዛውንት መስቀል አደባባይ መብራት ይዞን እንደቆምን፣ ‹‹እዚህ ሥፍራ የተሰው ወገኖቻችንን እግዚአብሔር ነፍሳቸውን በገነት ያኑርልን፡፡ ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን  ይስጥልን፣ የተጎዱትን ደግሞ በምሕረቱ ይጎብኛቸው . . . ›› ብለው ፀሎት አደረሱ፡፡ እኛም የአዛውንቱን አስተዋይ ምክር የራሳችንን አድርገን ሁላችንም የህሊና ፀሎት አደረስን፡፡ ታክሲያችን ስታዲዮም ደርሶ ወደ ጉዳያችን ስናዘግም ሁሉም ተሳፋሪዎች ከህሊናቸው ጋር እየተነጋገሩ የሚራመዱ ይመስሉ ነበር፡፡ የሰው ልጅ ትልቁ ዳኛ የገዛ ራሱ ህሊና ነው ይባል የለ? መልካም ጉዞ

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት