Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንገድ የቀሩ ዕቅዶች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ላለፉት ስምንት ዓመታት የመጀመርያውና ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች በአገሪቱ እየተተገበሩ ይገኛሉ፡፡ የመጀመርያው ዕቅድ ይፋ በተደረገ ሰሞን መንግሥት ከመነሻው ትችት ሲሰነዘርበት፣ አፋጣኝ ምላሹ በሰነድ ተደጉሰው የቀረቡት ሰፋፊ ዕቅዶች ‹‹የተለጠጡ ናቸው፡፡ ቢሆኑም ግን ሊተገበሩ የሚችሉ ናቸው፤›› በማለት ሲከራከር ቆይቷል፡፡

የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ድንገት ዱብ ማለት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ለመንግሥት የወቀሳውም የሙገሳም ምንጭ ሆነው አሁን ድረስ ግን ዘልቀዋል፡፡ በውጭ ታዛቢዎች ዘንድ በአፍሪካ የራሳቸው የተወጠነ የኢኮኖሚ ዕቅድ ያላቸው ጥቂት አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ ጎልታ እንድትጠቀስ ከሚያደርጓት ምክንያቶች ውስጥ፣ ይኼው በፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም መስመሯ የተቃኙ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎቿን የቀመረችበት የዕቅድ ሰነድ አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል፡፡

በሌላ በኩል ግን አገሪቱ እንዲህ ያለውን የተለጠጠ ዕቅድ ለመተግበር የተነሳችው ተገቢው የካፒታል አቅም ወይም ገንዘብ ሳይኖራት በውጭ ብድር፣ ዕርዳታና ከውጭ የሚመጡ ፕሮጀክቶች በራሳቸው ይዘው ይመጣሉ ከሚል መነሻ ስለመሆኑ ሰፊ ትችት ሲያስነሱ የሚታዩ እውነታዎች ናቸው፡፡ የአንድ ሰሞን መፈክር የነበረው የኢኮኖሚው ዕቅድ አሁን ላይ ስሙንም እያነሳ የሚናገርና መግለጫ የሚሰጥ የመንግሥት ኃላፊ እስኪጠፋ ድረስ ዕቅዱ የተረሳ ይመስላል፡፡

ከጅምሩም ሙሉ ለሙሉ ባናሳካውም እንሞክረው በማለት የጀመረው መንግሥት፣ ከስምንት ዓመታት በኋላ አብዛኞቹ የተጀመሩ ትልልቅ ዕቅዶች መንገድ መቅረታቸውን በሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርም የታቀዱት ዕቅዶች፣ የተጣሉት የመሠረት ድንጋዮች እንኳን ተገንብተው ተቆጥረውም እንደማያልቁ ሲገልጹ የተደመጡት፣ መንግሥት ያሰባቸው ዕቅዶች አለመሳካታቸው ብቻም ሳይሆን፣ አገሪቱን ለከፍተኛ የውጭ ብድር ዕዳ ዳርገው፣ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሊያስከትሉ የሚችሉበት ደረጃ መድረሳቸውን የሚያሳዩ ስለመሆናቸው የታየበት እውነታ ተፈጥሯል፡፡ በዚህ ሳቢያም አይነኬ የነበሩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ወደ ግል እንዲዛወሩ እስከመወሰን ተደርሷል፡፡

በቅርቡ ብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ለመንግሥት ያቀረበው የሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን የሁለት ዓመት ከመንፈቅ አተገባበር የቃኘው ሪፖርት የአብዛኞቹን ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ሁኔታ ያሳየ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ሪፖርቱ በ2005 ዓ.ም. ከቀረበው የአፈጻጸም ሪፖርት ጋር ተመሳሳይነት ቢኖረውም፣ የዘንድሮው አፈጻጸም ከዚያን ጊዜው በብዙ መልኩ ከዕቅድ የራቁ ወይም መንገድ የቀሩ የፕሮጀክት አፈጻጸሞችን አካቷል፡፡ በ2005 ዓ.ም. የወጣው የመጀመርያው ዕቅድ አፈጻጸም ለአብነት ካካተታቸው ሰፋፊ ፕሮጀክቶች መካከል የባቡር ዘርፍ ልማት አፈጻጸም በዋቢነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ በወቅቱ በቀረበው ሪፖርት መሠረት ይገባል፡፡ የተባለው የባቡር መስመር አገራዊ የባቡር ኔትወርክ 2,400 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን፣ ይህም በመጀመርያው ዕቅድ ዘመን በሦስት ኮሪደሮችና በአምስት መስመሮች የሚገነቡትን የሚሸፍን ነበር፡፡ ይሁንና በዚያን ወቅትም የማስፈጸምና የፋይናንስ አቅም ችግር እንደነበር በመታመኑ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው የተደረጉት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት፣ የአዲስ አበባ ሰበታ ሚኤሶ ፕሮጀክት፣ የሚኤሶ ደወሉ ፕሮጀክት ግንባታዎች እንደነበሩና አፈጻጸማቸውም ከፊሎቹ በጅምር የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ግን 43 በመቶ የደረሰበት የግንባታ ደረጃ በሪፖርት ለመንግሥትና ለለጋሾች ሪፖርት ተደርጎ ነበር፡፡ አዋሽ ወልዲያ ሃራ ገበያ፣ ወልዲያ ሃራ ገበያ መቀሌ፣ ወልዲያ ሃራ ገበያ ሰመራ አሳይታ፣ እንዲሁም አሳይታ ታጁራ የመንገድ ፕሮጀክቶች የአዋጭነት ጥናት የተፈረመባቸው ነበሩ፡፡ ሌሎችም በቅደመ ዝግጅት ደረጃ እንደሚገኙ የተጠቀሱ የባቡር ፕሮጀክቶች በ2005 ዓ.ም. ሪፖርት ቀርቦባቸው ነበር፡፡

ፕላን ኮሚሽን ባቀረበው ሪፖርት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ሥራ መጀመሩን ይጠቅሳል፡፡ ይሁንና ምን ያህል የታሰበውን ያህል የትራንስፖርትና የገቢ ፍሰት እያስመዘገበ እንደሚገኝ ከመጥቀስ የሚቆጠበው ይህ ሪፖርት፣ በተያዘው ዓመት ወደ ሥራ የገባውን የአዲስ አበባ ሰበታ፣ ሚኤሶ ባቡር ፕሮጀክትን ይጠቅሳል፡፡ የአዋሽ ወልዲያ ሃራ ገቤ ፕሮጀክት እስካለፈው መንፈቀ ዓመት ድረስ 65 በመቶ ገደማ መገባደዱን ይጠቅስና፣ በሁለት ዓመት ተኩል ውስጥ ‹‹የባቡር ዘርፍ ልማት በታቀደውና በተጠበቀው ልክ አልተፈጸመም፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት የፋይናንስ አቅም ውሱንነት እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፤›› በማለት የባበሩን ዘርፍ አፈጻጸም በግርድፉ ይደመድማል፡፡

ሌላኛው መንግሥት ያቀደውን ያህል መተግበር ካልቻለባቸው መስኮች ውስጥ የሚመደቡት የታክስ አሰባሰብና የዕድገት ደረጃው፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ የትምህርት ጥራት፣ የመጀመርያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትና ተማሪዎች ጥመርታና ሌሎችም ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ በአገሪቱ የታሰበውን ያህል ዓመታዊ ዕድገት ማስመዝገብ ባይቻልም፣ አሁንም ድረስ ፈጣን የሚባል የኢኮኖሚ ዕድገት ስለመኖሩ የሚያትተው ሪፖርት፣ በ2008 ዓ.ም. የስምንት በመቶና በ2009 ዓ.ም. የ10.9 በመቶ የተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት ይመዘገባል ተብሎ ከታቀደው የ11.2 እና የ11.1 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት አኳያ ዝቅተኛ መሆኑን አመላክቷል፡፡ ለዚህ ምክንያት የተደረገውም በ2008 ዓ.ም. ተከስቶ የነበረው ድርቅና የወጪ ንግድ ሸቀጦች የዓለም ገበያ ዋጋ መውረድ በአገሪቱ የወጪ ንግድ ገቢ ላይ ተዕኖ ማሳደራቸው በዋናነት እንደሚጠቀሱ ያትታል፡፡ ይህም ሆኖ በ2009 ዓ.ም. የአገሪቱ ኢኮኖሚ መጠን ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ ወደ 1.9 ትሪሊዮን ብር ከፍ ማለቱ ሲጠቀስ፣ በ2007 ዓ.ም. (የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተጀመረበት) ግን 1.2 ትሪሊዮን እንደነበር በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡ በዚህም ሳቢያ በ2009 ዓ.ም. የአገሪቱ የነፍስ ወከፍ ገቢ 863 ዶላር መድረሱ ሲጠቀስ፣ ይህም በ2007 ዓ.ም. 693 ዶላር እንደነበር አስታውሷል፡፡

ይህ ይባል እንጂ መንግሥት ከውጭና ከአገር ውስጥ ምንጮች ሲበደር የቆየው የገንዘብ መጠን አሁን ላይ ማነቆ እንደሆነበት አምኗል፡፡ የብድር መክፈያ ጊዜዎቹ በመድረሳቸው በርካታ አገር አቀፍ ፕሮጀክቶች እንዲታጠፉ ወይም ባሉበት በዕቅድ ደረጃ እንዲቆዩ እያስገደደው እንደሆነ ይታያል፡፡ ለአብነትም የስኳር ልማት ፕሮጀክቶችና የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ምዕራፍ ሁለት ፕሮጀክት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

ብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ባስቀመጠው መሠረት፣ በ2010 በጀት ዓመት የመጀመርያ ስድስት ወራት በድምሩ 1.345 ቢሊዮን ዶላር (697.1 ሚሊዮን ዶላር የማዕከላዊ መንግሥት ብድር፣ 464.7 ሚሊዮን ዶላር በመንግሥት ዋስትና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ብድር፣ እንዲሁም 183.7 ሚሊዮን ዶላር ከመንግሥት ዋስትና ውጭ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ብድር) የውጭ ብድር ፈሷል፡፡

በዘንድሮው ዓመት የመጀመርያው ስድስት ወራት ውስጥ ከአገር ውጭ ከተለያዩ ተቋማት በማዕከላዊ መንግሥት፣ በመንግሥት ዋስትናና ያለመንግሥት ዋስትና ለተገኙ ብድሮች ክፍያ ማለትም ለዋና ብድር፣ ለወለድና ለባንክ ማስተላለፊያ በጥቅሉ 688.6 ሚሊዮን ዶላር የብድር ዕዳ  ክፍያ ተፈጽሟል፡፡ ከዚህ ውስጥ 66.9 በመቶ ለዋና ብድር፣ ቀሪው 33.1 በመቶ ለወለድና ለባንክ ክፍያ ማስተላለፊያ ስለመዋሉም መንግሥት ይፋ አድርጓል፡፡

በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ከ24 ቢሊዮን ዶላር በላይ የብድር ዕዳ ያለባት በመሆኑና መንግሥት ለብድር ዕዳ ክፍያ የሚያውለው የወጪ ንግድ ገቢም እንደሚታሰበው ባለማግኘቱ ሳቢያ፣ እንደ አየር መንገድ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት፣ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎችን በከፊል ወደ ግል እንዲዛወሩ መወሰኑን ይፋ አድርጓል፡፡ ሌሎችም የባቡር ኮርፖሬሽንና የስኳር ልማት የመሳሰሉትን ድርጅቶች በከፊልና ሙሉ በሙሉ ወደ ግል ለማዛወር መወሰኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

ይህንን ውሳኔ ተከትሎም የአገሪቱ ጉምቱ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ባለሙያዎች በሰፊው የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦችንና የጥንቃቄ መልዕክቶችን ሲያስተጋቡ ከርመዋል፡፡ መንግሥትም እንደ ከዚህ ቀደሙ ‹‹ሜጋ ፕሮጀክቶችን›› የመገንባት ሳይሆን፣ አደጋ የመቀልበስ አጣዳፊ የቤት ሥራ ላይ እንዲጠመድ ያስገደደው የአገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ ላይ የተጋረጠው ቀውስ ነው፡፡

አብዛኞቹ ፕሮጀክቶች የሚያስፈልጋቸው ፋይናንስ መጠን፣ የሚጠይቁት የፕሮጀክት ክትትልና የሰው ኃይል፣ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ተገንብተውና ተጠናቀው ወደ ሥራ በመግባት አስፈላጊውን ገንዘብና አገልግሎት በመስጠት የአገሪቱን ዕዳ ይመልሳሉ የሚለው ጉዳይ በአግባቡ ሳይታይ በድፍረት የተገባባቸው ሥራዎች፣ አገሪቱ አሁን ለምትገኝበት የኢኮኖሚ መንገጫገጭ ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱ ባለሙያዎቹ አበክረው ይገልጻሉ፡፡ ይህንን የተረዳው መንግሥት መሠረታዊ ለውጥችን ማድረግ ጀምሯል፡፡ የአገሪቱን የፋይናንስ ዘርፍ የሚመራውን ተቋም ማኔጅመንት በአዲስ የመተካት ዕርምጃ ወስዷል፡፡ ሆኖም ተቋሙ ሲመራበት የነበረው አሠራር ተቀይሮ በአዲስ አደረጃጀት እንዲዋቀር እየተጠየቀ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች