[ለክቡር ሚኒስትሩ በጣም ተናደው መኪናቸው ውስጥ ሲገቡ ሾፌራቸው እያነጋገራቸው ነው]
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- ምነው?
- ፊትዎ በጣም ጠቋቁሯል፡፡
- ዛሬ እኮ ስንትና ስንት ስልክ ነው የተቀበልኩት፡፡
- የምን ስልክ?
- ሁሉም የሚደውልልኝ የቀን ጅብ ተባልኩ ምናምን ሲለኝ ግራ ገብቶኝ ነው፡፡
- ለምን ግራ ገባዎት?
- ይኼ ነገር እኔንም ይመለከተኛል ወይ ብዬ ነዋ?
- እሱን እንኳን እኔ አላውቅም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው ግን ይኼ የቀን ጅብ?
- እሱ እውነት ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት?
- ክቡር ሚኒስትር ብዙ ጊዜ ቢሮ ስለሚውሉ አያውቁም ማለት ነው፡፡
- ምኑን ነው የማላውቀው?
- ከተማዋ እኮ በቀን ጅቦች ተወራለች፡፡
- ምን ማለት ነው?
- በየሄዱበት የቀን ጅብ ብቻ አይደለም እንዴ ያለው?
- አልገባኝም?
- ዝም ብለው ቀበሌ ሲሄዱ ቀጠን ቀጠን ያሉ የቀን ጅቦች ያገኛሉ፡፡
- ምን ማለት ነው?
- መታወቂያ ለማሳደስም ሆነ ለማውጣት ወይም የሆነ ማስረጃ ለማግኘት ኪስዎን ካልዳበሱ አገልግሎት ማግኘት አይችሉም፡፡
- እሱን እንኳን አውቃለሁ፡፡
- ስለዚህ እነዚህ የሕዝብ ስልኮች የቀን ጅብ ነው የሚባሉት፡፡
- እነዚህን ነው እንዴ ሰው የቀን ጅቦች የሚለው?
- እዚህ ብቻ አይቆምም፡፡
- ሌላ ደግሞ ምን አለ?
- ለምሳሌ ሚስትዎ ልትወልድ ብላ ሆስፒታል ሲሄዱ በቀዶ ጥገና እንጂ በምጥ መውለድ አትችልም የሚሉ አሉ፡፡
- ይኼ እኮ የእነሱ ሙያ ነው፡፡
- እንዳይሳሳቱ ክቡር ሚኒስትር በቀዶ ጥገና የምትወልደው ሴት በምጥ ከምትወልደው የምትከፍለው ገንዘብ ከእጥፍ በላይ ስለሆነ አውቀው ነው እንዲህ የሚሉት፡፡
- ኧረ በሰው ሙያ አትግባ?
- ክቡር ሚኒስትር ነገርኩዎ እነዚህ ሐኪሞችም የቀን ጅቦች ናቸው፡፡
- ስማ ታዲያ ሐኪምና የቀበሌ ጉዳይ ፈጻሚን ነው ሰው የቀን ጅብ እያለ የሚያወራው?
- ከአስኮ እስከ መርካቶ ያለው ነጋዴ ሕዝብ ላይ 500 ፐርሰንት አትርፎ አይደል እንዴ የሚሸጠው?
- ይኼ እኮ የነፃ ገበያ መርህ ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ይኼ የቀን ጅብነት ነው፡፡
- ወይ ጣጣ?
- ሌላ ልጨምርልዎ ክቡር ሚኒስትር?
- እሺ ቀጥል፡፡
- የፍትሕ ሥርዓቱን መለከቱ ገንዘብዎ ነው ፍትሕ የሚያመጣልዎት፡፡
- እ. . .
- እንዲያውም የፍትሕ ሥርዓት ከሚባል የገንዘብ ሥርዓት ቢባል ይቀላል፡፡
- እና በየዘርፉ ነው የቀን ጅቦች ያሉት?
- ክቡር ሚኒስትር የቀን ጅብ ሃይማኖት፣ ብሔርና ዜግነት የለውም፡፡
- ምን ማለት ነው?
- የቀን ጅብ ማለት የማይገባውን ጥቅም ባልተገባ መንገድ ለማግኘት የሚጥር ሰው ማለት ነው፡፡
- እ . . .
- ክቡር ሚኒስትር የቀን ጅብ ነጭ ወይም ጥቁር፣ ወንድ ወይም ሴት፣ ትንሽ ወይም ትልቅ ሳይመርጥ ብቻ በየትኛውም ማንነት ሊኖር የሚችል ነው፡፡
- አሁን ገባኝ፡፡
- ለማንኛውም እርስዎም ከቀን ጅቦች ቢጠነቀቁ ጥሩ ነው፡፡
- እነዚህ ጅቦች ግን ማታ ማታ ይወጣሉ?
- ክቡር ሚኒስትር አይቀልዱ እንጂ?
- ኧረ እኔ እየቀለድኩ አይደለም፡፡
- ለነገሩ ሁኔታዎን ሳየው እርስዎም እየመሰሉኝ ነው፡፡
- ምን?
- የቀን ጅብ!
[ክቡር ሚኒስትሩ በጣም ተናደው ከሚስታቸው ጋር እያወሩ ነው]
- ወይ ጉድ፡፡
- ምን ሆንክ?
- በተከበርኩበት አገር እንደዚህ ልዋረድ?
- ምን ሆንክ?
- ይኼው የራሴ ሾፌር የቀን ጅብ ብሎኝ አረፈ፡፡
- መቼ?
- አሁን በመኪና እየመጣን፡፡
- ምን አለህ?
- ሳይህ ሳይህ የቀን ጅብ ትመስላለህ አይለኝ መሰለሽ?
- ከእሱ ጋር መቀላለድህ እኮ ነው እንዲህ ያስደፈረህ?
- የተደፈርኩትማ በሌላ በመደፈሬ ነው፡፡
- ማን ደፈረህ?
- ስሚ እኔ ለዚህች አገር ሰለቸን ደከመኝ ሳልል ሠርቼ የተረፈኝ አንድ ነገር ነው፡፡
- ምን?
- በሽታና ስድብ፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- ስኳርና ደሜን ተሸክሜ ባገለገልኩ ይኼው ስድብ ተጨመረልኝ፡፡
- ሾፌር ሰደበኝ ብለህ ነው?
- አለቃችንስ ቢሆኑ በአደባባይ አይደለም እንዴ የቀን ጅብ ያሉን?
- አለቃችሁ እኮ ሥራችሁን አይቶ ነው የቀን ጅብ ያላችሁ፡፡
- አሁን ግን በዛ፡፡
- እንዴት ማለት?
- የቀን ጅቡን ተቀብዬ ብቀመጥ ሌላ ተጨመረልኝ፡፡
- ሌላ ምን?
- ይኼው ነገ ደግሞ እሾህ ሊለኝ ነው፡፡
- እሱስ ልክ ነህ፡፡
- ከነገ ወዲያ ደግሞ ጠማማ ዛፍ ልባል ነው፡፡
- ምን ይደረግ ታዲያ?
- ሳምንት ደግሞ አይጥ ልባል ነው፡፡
- ምነው እንደዚህ ከነከነህ ግን?
- ስሚ ይችን አገር ባቀና ጠማማ ዛፍ ልባል?
- እሱን እንኳን ተወው፡፡
- ምነው?
- አገሪቱን ስላጣመምካት እኮ ነው ጠማማ ዛፍ የተባልከው፡፡
- እሺ ሌላው ቢቀር አገሪቱ ላይ እሾህ የሆኑባትን እነ ድህነት እየነቀልኩ እሾህ ልባል?
- አሁን አንተ ድህነትን ነቀልክ ወይስ ተከልክ?
- አንቺም ከእነሱ ጋር ተደመርሽ?
- ሥራህን ታውቀዋለህ ብዬ ነው፡፡
- እሺ ሁሉም ይቅርና እኔን ክብር ያለኝን ሰው አይጥ ብሎ ማዋረድ አይከብድም?
- እሱንም እኮ ያገኘኸው በይቅርታ ነው፡፡
- የምን ይቅርታ?
- ከጅብነት ወደ አይጥነት የተደረገልህ በይቅርታ መርህ ነው፡፡
- አንቺ ራሱ የምታወሪውን አታውቂም፡፡
- ለማንኛውም እኔንም አንድ የአይጥና የድመት ፊልምን አስታወስከኝ፡፡
- የምን ፊልም?
- ፊልሙ ላይ አይጧ ልክ እንደ አንተ ሌባ፣ አጥፊ፣ ተንኮለኛና ሴረኛ ነች፡፡
- ምንድነው የምታወራው?
- ስለዚህ እኔም ከዚህ በኋላ አዲስ የቤት ስም አውጥቼልሃለሁ፡፡
- ማን ልትይኝ?
- ጄሪ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከደላላ ወዳጃቸው ጋር ቢሮ ተገናኝተው እያወሩ ነው]
- ክቡር ሚኒስትር ሰሞኑን በጣም ብፈልግዎም ላገኝዎ ግን አልቻልኩም፡፡
- ሰውዬ በዚህ ጊዜ ከአንተ ጋር መገናኘት የለብኝም፡፡
- ለምን ክቡር ሚኒስትር?
- ስማ እኔ ሌላ ጣጣ ውስጥ መግባት አልፈልግም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እኔ ምን ያህል በጥንቃቄ እንደምንቀሳቀስ መቼም ያውቃሉ?
- ምን ፈልገህ ነው ቢሮ የመጣኸው?
- አዲስ ለምንከፍተው ድርጅት የብቃት ማረጋገጫ ያስፈልጋል፡፡
- የምን የብቃት ማረጋገጫ?
- ድርጅቱን ለመክፈት ኃላፊው ሦስት ማስተርስ ሊኖረው ይገባል፡፡
- ምን አሰብክ ታዲያ?
- ያው በዚህ በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ ለእርስዎ ሦስተኛ ማስተርስ አመጣለሁ፡፡
- ከየት ነው የምታመጣው?
- ከሚመጣበት ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እ . . .
- ባለፈው ያስመጣሁልዎት የምን ነበር?
- ትራንስፎርሜሽናል ሊደርሽፕ፡፡
- የበፊቱ ኤምቢኤ ነበር አይደል?
- በትክክል፡፡
- ስለዚህ አሁን በሲስተማቲክ ማኔጅመንት አመጣልዎታለሁ፡፡
- እንደዚያ የሚባል የትምህርት ዘርፍ አለ እንዴ?
- ባይኖርም እንፈጥራለና፡፡
- ካልክማ ይሁን፡፡
- ባይሆን ቤት ትንሽ ዝግጅት አድርገው ጋዋን ለብሰው መነሳት አለብዎ፡፡
- ድግስ ያስፈልጋል ብለህ ነው?
- እሱማ ወሳኝ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለምን?
- አዩ አገሪቱ እንደዚህ እየጦዘች እርስዎ ሦስተኛ ማስተርስ መያዝዎ የዓላማ ፅናት እንዳለዎት ነው የሚያሳው፡፡
- የአንተ አስተሳሰብ እኮ ይገርመኛል፡፡
- ለሌላ ኃላፊነትም ሊያበቃዎ ይችላል፡፡
- እሱስ ልክ ብለሃል፡፡
- አሁን ወደ ዋናው ቁም ነገሮች እንሂድ፡፡
- ምንድነው እሱ?
- ሲመረቁ እኮ የሚያገኙት ሁለት ነገሮች ነው፡፡
- ምንድን ናቸው፡፡
- አንደኛው ዲግሪዎን ነው፡፡
- እሺ፡፡
- ሁለተኛው ደግሞ ፕሮጀክቱ ሲፈጸም ዕድገትዎን ያገኛሉ፡፡
- የምን ዕድገት?
- የታክስ ከፋይነትዎ ዕድገት ያመጣል፡፡
- እኮ ምን ዓይነት ዕድገት?
- ያው ከፍ ማለትዎ አይቀርማ፡፡
- ወደ ምን?
- ወደ ደረጃ ሀ!
[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን ቢሯቸው ያስጠሩታል]
- ያስጠራሁህ አንድ ጉዳይ ላይ እንድንወያይ ነው፡፡
- የምን ጉዳይ ክቡር ሚኒስትር?
- የሚኒስቴር መሥሪያ ቤታችን የሚሠራቸውን ሥራዎች ለምን ለሚዲያ ይፋ አናደርግም?
- ባለፈው ከነገርናቸው ውጪ የሠራነው ሥራ የለም እኮ?
- ቢሆንም ከሚዲያ ጋር ግንኙንት መፍጠሩ መልካም ነው፡፡
- ያው በኋላ ላይ ሚዲያዎቹ ራሳቸው እንዳያፋጥጡን ብዬ ነው፡፡
- ልማታዊ ሚዲያዎቹን ጥራልኝ፡፡
- የትኞቹን ሚዲያዎች?
- ለነገሩ አሁን ልማታዊ ሚዲያ የት አለ?
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- አንዴ ሠልፍ ነው፣ ሌላ ጊዜ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው፣ ወይም ደግሞ ግጭት ነው የሚዘግቡት፡፡
- ታዲያ ይኼን መዘገብ ምን ችግር አለው?
- አገሪቱ ውስጥ እኮ ከዳር እስከ ዳር ልማት ነው እየተካሄደ ያለው፡፡
- ኧረ ይተው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለምንድነው የምተወው?
- ስለእንደዚያ ዓይነት ልማት ሰው መስማት አይፈልግም፡፡
- ታዲያ መስማት የሚፈልገው ስለደም ልገሳና ሠልፍ ነው?
- ምን ሆኑ ክቡር ሚኒስትር?
- ምን ሆንኩ?
- ሰው መስማት የሚፈልገው ስለአንድነት፣ ስለፍቅር፣ ስለይቅርታና ስለመደመር ነው፡፡
- የምን ፍቅር ነው በየቦታው ግጭት አይደል እንዴ ያለው?
- ክቡር ሚኒስትር አገሪቱ ለመፍረስ አፋፍ ላይ ደርሳ ነው የተረፈችው፡፡
- እስኪ ተወኝ፡፡
- ለማንኛውም ጊዜው የፍቅር፣ የአንድነት፣ የይቅርታና የመደመር ነው፡፡
- ኦ ኦ . . . ሰውዬ?
- እኔ የምመክርዎ እንዲደመሩ ነው፡፡
- የምን መደመር ነው?
- የማይደመሩ ከሆነ የሚጠብቅዎ ምን እንደሆነ ያውቁታል፡፡
- ምንድነው የሚጠብቀኝ?
- መቀነስ!