ወደ ራሳችሁ ተመለሱ! ራሳችሁን ሁኑ! ሰው መሆናችሁን አትርሱ!
በአብዱልፈታህ አብደላህ
‹‹ኬር ይሁን ኬር!›› ይህ ቃል በጉራጌ ዞን በሚገኙ (የሰባት ቤት ጉራጌ፣ የቀቤና፣ የወለኔ፣ የክስታኔ፣ የመስቃን፣ የዶቢ፣ የማረቆ) ሕዝቦች በስፋት ይታወቃል፡፡ ለረዥም ክፍለ ዘመናትም የሕዝብ ለሕዝብ ሰላማዊ ግንኙነትን ለመጠበቅና ለመቆጣጠር ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ አካባቢው ወደ ማዕከላዊ መንግሥት ከገባ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ ግን ዕሴቱ እየተዳከመ ሄዶ ቃሉ ብቻ የቀረ ይመስላል፡፡ የቃሉ ትርጉም “ሰላም ይሁን ሰላም” ማለት ነው፡፡ ሰውና እንስሳቱ፣ ሣር ቅጠሉ በአጠቃላይም ሰማይና ምድሩ ሰላም እንዲሆን የሚያስችል ቃል፣ ዕሴትና ሥርዓት ሆኖ ይታወቃል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰኔ 15 ቀን 2010 ዓ.ም. በወልቂጤ ከተማ ተገኝተው ነበር፡፡ የተገኙበት ለጉብኝት ሳይሆን በጉራጌና በቀቤና ሕዝቦች መካከል ተፈጥሮ በነበረው የሰላም መደፍረስ ምክንያት ነበር፡፡ የሰላም መደፍረሱ በአካባቢው ባህልና ወግ መሠረት እንዲፈታ አበክረው ሲያስተምሩና ሲያሳስቡ ሰንብተዋል፡፡ ለጉራጌና ለቀቤና ብቻ ሳይሆን በዚህ በሰኔ ወር በሲዳማ፣ በወላይታ፣ በጉጂ ኦሮሞና በጌድኦ አካባባቢዎች የተከሰተው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ችግር በአካባቢዎቹ የባህል የሰላምና የዕርቅ ሥርዓት መሠረት ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው መመለስ እንደሚገባቸው አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ችግሮች ሲከሰቱ የተለመደውና ሲዘወተር የነበረው ብዛት ያላቸው የፀጥታ ኃይሎችን በአካባቢው በማሰማራት፣ በመንግሥት ሕግና በአስተዳደር ሥርዓት ለመፍታት መሞከር ነበር፡፡ ይህ አሠራር አራት መሠረታዊ ችግሮች ነበሩበት፡፡
- የሚመደበው ብዛት ያለው የመንግሥት የፀጥታ ኃይል በአመዛኙ ማስፈራራት፣ አንዳንዴም ከፍ ያለ ኃይል ስለሚጠቀም በአካባቢው ተጨማሪ ችግር በመፍጠር አለመግባባቱን ይበልጥ ሲያወሳስበው ቆይቷል፡፡
- የመንግሥት ሕግና የፍትሕ ሥርዓት ፍትሐዊነቱ አጠራጣሪ ስለነበር በአብዛኛው ተቀባይነት አያገኝም ነበር፡፡ ስለሆነም ችግሩ እንኳን ሊፈታ ይበልጥ እያመረቀዘ እንዲሄድ ሲያደርገው ይስተዋላል፡፡
- ሕግና የአስተዳደር ሥርዓት ችግሮቹን በአሸናፊነትና በተሸናፊነት የሚጨርሱ በመሆናቸው የበለጠ ጊዜና ቦታ ጠብቆ ቂም በቀል እንዲስፋፋ አድርጓል፡፡
- የአካባቢው የባህልና የሕዝብ መሪዎችን ከጨዋታው ውጪ የሚያደርግም አካሄድ ስለነበር የነሱ ሙሉ ልብና ትብብር አልነበረበትም፡፡
አሁን በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እየተሰማ ያለው አካሄድ ካለፈው ሁሉ ለየት የሚል ነው፡፡ በአካባቢው ባህልና ወግ መሠረት አለመግባባቶችን መፍታትና መቆጣጠር ይቻላል እያሉን ነው፡፡ ስለሆነም ሕዝቦች ወደ ቀድሞ ማንነታቸው፣ ወግና ባህላቸው መመለስ አለባቸው ብለውናል፡፡ “ሲዳማ ሁኑ፣ ጉራጌ ሁኑ፣ ወላይታ ሁኑ፣ ቀቤና ሁኑ በአጠቃላይም ወደ ራሳችሁ ተመለሱ፣ ራሳችሁን ሁኑ፣ ባህላችሁን ምሰሉ፣ ሰው ሁኑ፣ ኢትዮጵያን ምሰሉ፤” በማለት አስተምረዋል፡፡ እንደሚታወቀው በሰባት ቤት ጉራጌ (የጆካ ቅጫ)፣ በቀቤና (ቦበኒ-ገልቲተ)፣ በወለኔ (የጎርደነ-ሴረ)፣ በክስታኔ (የጎርደና-ሴራ)፣ በመስቃን (ፈረስ-አገኘ)፣ በዶቢ (የስናኖ-ሴራ፣ በሲዳማ (የሲዳማ-ሴራ)፣ በጉጂ ኦሮሞ (የገዳ ሥርዓት)፣ በጌድኦ (የባሌ ሥርዓት)፣ በወላይታና በሌሎችም አካባቢዎች የየራሳቸው የሰላምና የዕርቅ ሥርዓቶች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም ሥርዓቶች የጥንት የጠዋት የሆኑ፣ የዳበረ የሕዝብ ለሕዝብ ግጭቶችን የመፍታትና የመቆጣጠር አቅም ያላቸው ዕሴቶች ናቸው፡፡ እነርሱን ተጠቅሞ የሕዝብ ለሕዝብ ዘለቄታዊ ሰላምንና ዕርቅን ማስፈን እንደሚቻል ይታመናል፡፡
እስካሁን ችግር የነበረው እነዚህን ዕሴቶች ተጠቅሞ የመሥራትና የመምራት ሚና የነበረው የመንግሥት አመራርና አሠራር አለመኖር ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ይህንን አመራርና አሠራር ለማምጣት ነው በመትጋት ላይ የሚገኙት፡፡ በሶማሌና በኦሮሚያ መካከል የተከሰተው አለመግባባት ጭምር በሔራና በገዳ ሥርዓቶች አግባብ እንዲፈታ ከማስተማር ቦዝነው አያውቁም፡፡ ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ የሰላምና የዕርቅ መንገድ በምሁራንና በመንግሥት ባለሥልጣናት ዘንድ ምን ያህል ታውቆላቸዋል? የሚለው ነጥብ ያሳስበኛል፡፡ በበኩሌ ሰፊ የግንዛቤ እጥረት እንዳለ እገምታለሁ፡፡ አብዛኛዎቹ ምሁራንና የመንግሥት ባለሥልጣናት የአገር በቀል የሰላምና የዕርቅ ሥርዓቶቻችንና ዕሴቶቻችን ዙሪያ በቂ ዕውቀት እንደሌላቸው ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ስለሆነም ዕውቀትና ግንዛቤ በሌላቸው ጉዳይ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በምን ደረጃ ሊያግዟቸው ይችላሉ? የሚለው ጥያቄ አግባብነት ይኖረዋል፡፡ ስለሆነም የጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ የሰላምና የዕርቅ መንገድ ሳይሳካ እንዳይቀር ሥጋት አለኝ፡፡
በመሠረቱ ዘላቂ የሕዝብ ዕርቅና ሰላም ማስፈን መንገዱ ሩቅና ከባድ አይደለም፡፡ ነገር ግን ትክክለኛ አመራርና አሠራር መምረጥን ይፈልጋል፡፡ ትክክለኛው መሪ ከላይ መጥቷል፡፡ በክልል፣ በዞንና በወረዳ ደረጃም እንዲገኝ ያስፈልገዋል፡፡ አሠራሩ የሕዝቡ ባህልና ወግ ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱ ቁም ነገሮች ከተገናኙ በየትኛውም አካባቢ የሕዝብ ሰላምና መልካም ግንኙነትን ዘላቂ በሆነ መንገድ ማስፈን ቀላል ጉዳይ ነው፡፡
በመሆኑም ከላይ በተጠቀሱ ሕዝቦች መካከል የተከሰተው አለመግባባት በእርግጥ በተባለው መንገድ ለመፍታት እየተሄደበት ነው? ሒደቱ በትክክል በባህሉ መሠረት እየተፈጸመ ይሆን? የሚለው መታየትና መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ችግሩ የግንዛቤ እጥረት ብቻ አይደለም፡፡ በሕዝቦች ግንኙነት ነግደው ማትረፍ የለመዱና የወደዱ አያሌ ባለሥልጣናት ላለፉት አንድ መቶ ዓመታት በተከታታይ አገሪቱ አፍርታለች፡፡ ይኽም አንዱ እንቅፋት ነው፡፡ በእርግጥ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለዚህም ፍቱን መድኃኒት ዘይደዋል፡፡ የሕዝብ ለሕዝብ አለመግባባት የተከሰተባቸው አካባቢዎች ባለሥልጣናት ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው እንዲለቁ የሚለው መርሐቸው ጠቃሚ ነው፡፡ ከእንግዲህ ወዲያ እንደ ዓይናቸው ብሌን የሚመለከቱት ወንበራቸው ከፈለጉ የሕዝብ ለሕዝብ ሰላማዊ ግንኙነትን መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡
ስለሆነም የሕዝብ ለሕዝብ ሰላማዊ ግንኙነትን ዘለቄታዊ በሆነ መንገድ ለመምራት የሕዝቦች የሰላምና የዕርቅ ሥርዓቶችና ዕሴቶች ዓይነተኛ መንገዶች ናቸው፡፡ ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ፣ ትምህርትና ግሳፄ ከግብ እንዲመታ ሁላችንም መሥራትና ትብብር ማድረግ ይኖርብናል፡፡ እኛም እስካሁን ከ15 በላይ ያጠናናቸውን የአገር በቀል የሰላምና የዕርቅ ሥርዓቶች ጥናት ለዚህ አገራዊ፣ ሕዝባዊና መንግሥታዊ ዓላማዎች እንዲውሉ የተቻለንን እናደርጋለን፡፡
ከአዘጋጁ፡- አቶ አብዱልፈታህ አብደላህ የኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓቶች ማዕከል ሥራ አስኪያጅ ሲሆኑ፣ በማዕከላቸው አማካይነት የተለያዩ ብሔረሰቦች የባህል ሕግ ሥርዓቶች በማጥናት አሳትመዋል፡፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡