Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹ሄኖክም ሆነ መጽሐፈ ሄኖክ ኢትዮጵያዊነት የለባቸውም›› ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ

‹‹ሄኖክም ሆነ መጽሐፈ ሄኖክ ኢትዮጵያዊነት የለባቸውም›› ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ

ቀን:

በኢትዮጵያ ምድር በቀዳሚነት በሥነ ጽሑፍ ቋንቋነቱ የሚታወቀው ግዕዝ ካለው ጽሑፋዊ ሀብት የተነሳ ከአገሬው ይልቅ የባህር ማዶ ምሁራንና ተማሪዎችን ቀልብ ከገዛ ዘመናተ ዘመናትን አስቆጥሯል፡፡ የሩቁን ትተን ከዓመት በፊት ስንኳ በካናዳ የሚገኘው የቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ በግዕዝ ቋንቋ የተጻፉትን ጥንታዊ ድርሳኖች ለማጥናት፣ ለመመርመር ይቻል ዘንድ ፍላጎቱ ላላቸው ተማሪዎች ማስተማር ጀምሯል፡፡

በቅርቡም በኢትዮጵያ ከተመሠረቱ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የሆነው አክሱም ዩኒቨርሲቲ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ለቅድመ ምረቃ ግዕዝን ለማስተማር ዝግጅት እያደረገ መሆኑም ተሰምቷል፡፡ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲም በልሳነ ግዕዝ በድኅረ ምረቃ ትምህርት መሰጠት መጀመሩንም በቅርቡ አብስሯል፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኮመን ኮርስ ከሚሰጠው የግዕዝ ትምህርት ባለፈ በድኅረ ምረቃ በሥነ ድርሳን (ፊሎሎጂ) ትምህርት ትኩረቱን በግዕዝና በዓረብኛ በማድረግ በርካታ ጥናቶች ላለፉት 13 ዓመታት ማሠራቱም ይታወቃል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በበኩሉ ከአራት ዓመት ወዲህ ከአክሱም፣ ባህር ዳር፣ ጅማና ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የግዕዝ ጉባዔን በማካሄድ ለቋንቋውና ለሥነ ጽሑፍ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑም ይታያል፡፡

ይህ የግዕዝ ቋንቋን የማወቅ አስፈላጊነት በየአቅጣጫ በሚሰማበት አጋጣሚ ነዋሪነታቸው በአሜሪካ የሆነው የግዕዝ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ሊቁ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በኒው ዮርክ ከተማ በቅርቡ ያሳተሙት ‹‹ስለግዕዝ ሥነ ጽሑፍ የተሰበሰቡ አንዳንድ ማስታወሻዎች›› አዲስ አበባ ከተማ ውስጥም ለኅትመት በቅቶ እየተሠራጨ ይገኛል፡፡

ከድንጋይ ላይ ወደ ብራና ላይ ሽግግር ያደረገው የግዕዝ ሥነ ጽሑፍ ዘመነ አክሱም በተለይ ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አንስቶ በርካታ መጻሕፍት ተተርጉመውበታል፣ ተደርሶበታል፡፡

‹‹ግዕዝ በቀላሉ ከናሙና ድርሰቶቹ ጋራ›› በሚል ርዕስ በኒው ዮርክና በአዲስ አበባ ከተማ ሃቻምና ያሳተሙት ፕሮፌሰር ጌታቸው በአዲሱ መጽሐፋቸው ስለ ግዕዝ ሥነ ጽሑፍ የተሰበሰቡ ማስታወሻቸው የሥነ ጽሑፉን ጥንተ ነገር፣ በየዓረፍተ ዘመኑ በመከፋፈል የተወሰነ መልኩ አቅርበውታል፡፡ ከአክሱም እስከ አፄ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት የነበረው ገጽታ ከብሔራዊ ሥነ ጽሑፍ አንፃር ተተንትኖበታል፡፡ በመጽሐፉ ከተነሱት የተወሰኑትን ቀንጭበን እዚህ ላይ አቅርበነዋል፡፡

የግዕዝ ሥነ ጽሑፍ የሚባለው ምንድነው?

እንደ ፕሮፌሰር ጌታቸው አገላለጽ፣ የግዕዝ ሥነ ጽሑፍ የሚባለው ምንድነው? እስካሁን ባለው ውሳኔ መሠረት ‹‹በግዕዝ ቋንቋ ተጽፎ የተገኘ ሁሉ ‹‹የግዕዝ ሥነ ጽሑፍ›› አካል ተደርጎ ተወስዷል፡፡ ወሳኙ የጽሑፉ ይዘት ሳይሆን ቋንቋው ግዕዝ መሆኑ ነው፡፡ ጸሐፊው ኢትዮጵያ (አግዓዚ) ይሁን ወይም ግዕዝ ተምሮ በግዕዝ ቋንቋ ይጽፍ የነበረ ደራሲ፣ ወይም የጽሑፉ ጥንት (Origin) በውጭ ቋንቋ ሆኖ ወደ ግዕዝ የተተረጎመ ይሁን ከውይይት የሚገባው ጽሑፎቹ በሚተቹበት ጊዜ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ማን ጻፈው? መቼ ተጻፈ? ጥንቱ በምን ቋንቋ ተጻፈ? ስለምን ተጻፈ? የሚሉት ጥያቄዎች መልስ ያላቸውን ያህል አብረው ይነገራሉ፡፡ አርዕስቱ ታሪክ፣ ጸሎት፣ ሃይማኖት ማስተማሪያ ሁሉ የሰው ልጅ አዕምሮ የወለዳቸው ስለሆኑ የሥነ ጽሑፍ አካል ናቸው፡፡

‹‹በግዕዝ ተጽፎ የተገኘ ሁሉ የግዕዝ ሥነ ጽሑፍ አካል ነው ቢባልም ሁሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥነ ጽሑፍ አይደለም፡፡ እርግጥ የጥንቆላ ጽሑፎችና የነገሥታቱ ታሪክ የተጻፉት በቤተ ክህነት ትምህርት ባደጉ ጸሐፊዎች ነው፡፡ አስተዳደጋቸው ድርሰታቸውን ሁሉ የቤተ ክርስቲያን ሥነ ጽሑፍ አያደርገውም፡፡

‹‹የስደተኞች የታሪክና የሥነ ጽሑፍ ምንጮች›› በሚል ንዑስ ርዕስ እንደጻፉት፣ የተሟላ የግዕዝ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ለመጻፍ መጀመርያ ገዳማቱ የከተቱትን የሥነ ጽሑፍ ቅርስ ማየትና መመርመር ይኖርበታል፡፡ ያንን ገና አድርገን አልጨረስንም፡፡  እስከ ቅርብ ጊዜ ያወቅነውን ያህል እንኳ ያወቅነው ከየአድባራቱ በልዩ ልዩ አጋጣሚዎች ተመዝብረው በውጭ አገር በስደት ያሉትን መጻሕፍት በመመርመር ነው፡፡ ዋና ዋናዎቹም እንደሚከተለው ጠቅሰዋቸዋል፡፡

በግራኝ ጦርነት ጊዜ የኢየሩሳሌምና የግብፅ ገዳሞቻችን ወዳሉበት ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የሚወስደው መንገድ ስለተዘጋ መነኮሳቱን ከማለቅ፣ ገዳማቱን ከመዝጋት የሚያደርስ ከፍተኛ ችግር ደረሰ፡፡ በዚያን ጊዜ ከተበታተኑት ንብረቶች ውስጥ ከኢየሩሳሌም መጻሕፍት አንዳንዱ ቫቲካን፣ ከግብፆቹ መጻሕፍት ብዙዎቹ ፓሪስ ተወስደው ለጥናት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

‹‹ሁለተኛውም ከግራኝ ጦርነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በግራኝ ጦርነት ዕርዳታ ሊሰጡን ከመጡ ፖርቱጋሎች ጋር አብረው የመጡ ኢየሱሳውያን ንጉሥ ሱስንዮስን እስከ ማኮትለክ ደርሰው ነበር፡፡ ሲባረሩ ብዙ የብራና መጻሕፍት ይዘው ሄደው ነበረ፡፡ አብዛኞቹ ቫቲካን ቤተ መጻሕፍት ይገኛሉ፡፡

‹‹ሦስተኛው ከአንድ ጄምስ ብሩስ ከሚባል የስኮትላንድ ሰው ታሪክ ጋራ የተያያዘ ነው፡፡ ይህ ሰው በዘመነ መሳፍንት መጀመርያ ላይ የዓባይን ምንጭ ለማየት መጥቶ እንደነበረ እናስታውሳለን፡፡ ወደ አገሩ ሲመለስ ብዙ የብራና መጻሕፍት ሰብስቦ ይዞ ሄደ፡፡ ዛሬ መጻሕፍቱ በእንግሊዝና በፈረንሣይ አገር ይገኛሉ፡፡ እነዚህም የጥናት የዕውቀት ምንጭ ሆነዋል፡፡

‹‹ቀጥሎ ሁለት ፈረንሣውያን ወንድማማቾች ወደ ዘመነ መሳፍንት ማለቂያ ላይ ኢትዮጵያ መጥተው አንዱ የራስነት ማዕረግ አግኝቶ ኢትዮጵያዊት ሚስት አግብቶ እዚያው ሲኖር፣ ሁለተኛው ጥረቱ መጻሕፍት መሰብሰብ ነበረ፡፡ የሰበሰበውን ሰብስቦ ሌላውን አስቀድቶ ብዙ መጻሕፍት ይዞ አገሩ ገባ፣ ስሙ ዲ’ባዲ ስለነበረ መጻሕፍቱ የዳ’ባዲ ስብስቦች ተብለው በፈረንሣይ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት ይገኛሉ፡፡ ዛሬ ትልቁ የኢትዮጵያ የብራና መጻሕፍት ክምችት ያለው ፈረንሣይ አገር ነው፡፡››

‹‹እንግሊዝ አገር ያለውም ትንሽ አይደለም፡፡ አፄ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ የመድኃኔዓለምን ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት ሲዘጋጁ አንዱ የወሰዱት ዕርምጃ የሌሎቹን አብያተ ክርስቲያን መጻሕፍት እየወሰዱ መቅደላ ላይ ማከማቸት ነበረ፡፡ በጄኔራል ናፒየር የሚመራ የእንግሊዝ የጦር ሠራዊት በሰላይነት ተጠርጥረው የታሰሩትን እስረኞች በኃይል ለማስፈታት በ1860 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ የባህላዊ ቅርሳ ቅርስን በተለይም የመጻሕፍትን ዋጋ የሚያውቅ ሰው አብሮ እንዲመጣ አደረጉ፡፡ ‹‹ለሆዳም በሬ ጭድ ያዝለታል›› እንደሚባለው እንግሊዞች ብዙ ውጣ ውረድ ሳይደርስባቸው ከየገዳማቱ ተወስደው መቅደላ ተራራ ላይ ከተከመሩት መጻሕፍት ውስጥ የመረጡትን ይዘው ሄዱ፡፡

‹‹የኢጣሊያ ኃይል  ከ1888 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 1933 ዓ.ም. ሰሜን ኢትዮጵያ መረብ ምላሽ ውስጥ፣ ከ1928 ዓ.ም. እስከ 1933 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ እንደቆየ እናስታውሳለን፡፡ ወራሪዎቹ በዚህ ጊዜ ውስጥ የዘረፏቸው ናቸው ተብሎ የሚገመቱ የኢትዮጵያ የብራና መጻሕፍት አሁን በኢጣሊያ ቤተ መጻሕፍት ይገኛሉ፡፡

‹‹ታሪካቸው ከላይ ከጠቀስኳቸው መጻሕፍት ጋር ተመሳሳይ ባይሆንም በአገልግሎታቸው ስለሚመሳሰሉ በማይክሮ ፊልም ስለተነሱት መጻሕፍትም መናገር ያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ የማስታውሳቸው ሦስት ናቸው፡፡ ዩኔስኮ፣ የሃምቡርግ ዩኒቨርሲቲ (ጀርመን አገር)፣ እኔ የምሠራበት የቅዱስ ዮሐንስ ዩኒቨርሲቲ (ኮሌጅ ቪል፣ ሚኒሶታ) ብዙ መጻሕፍት ፎቶግራፍ አንስተዋል፡፡ ራሳቸው መጻሕፍቱ ግን በመሀል ቤት ካልጠፉ አሁንም እዚያው በየገዳማቱ ናቸው፡፡

ከአክሱም እስከ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት

‹‹የታሪክ ተመራማሪዎች ኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱሷን በአምስተኛው/ በስድስተኛው ምዕት ዓመት ወደ ግዕዝ ተርጉማ ጨርሳለች ይላሉ፡፡ በአክሱም ዘመነ መንግሥት ብዙ መጻሕፍት ወደ ግዕዝ እንደተተረጐሙ እናያለን፡፡ ቅዱስ ያሬድም የተነሳው በዚያ ጊዜ ነው፡፡ ግን ብሔራዊ ሥነ ጽሑፍ በጠቅላላው የዳበረው የይኩኖ አምላክ ቤተ መንግሥት ከተመሠረተ ከ1263 ዓ.ም. በኋላ ነው፡፡ ሆኖም ከይኩኖ አምላክ ሥርወ መንግሥት መቋቋም አስቀድሞ መጽሐፍ ቅዱስን ተርጉመን ከጨረስንበት ጊዜ ጀምሮ ያላንዳች ሥነ  ጽሑፋዊ እንቅስቃሴ ቁጭ አላልንም፡፡ ብዙ መጻሕፍት እንደተረጐምን እኛም እንደጻፍን (እንደደረሰን) አያጠራጥርም፡፡ ግን መጻሕፍቱ ወዴት እንደደረሱ፣ ምን እንደሆኑ በማስረጃ የምናውቀው ነገር የለንም፡፡ አንድ ምሁር ቢቸግረው በየድንጋዩ ላይ የተጻፈ የጥንት ግዕዝ ጽሑፎች ባላይ ኖሮ ኢትዮጵያውያን ከይኩኖ አምላክ በፊት ጽሕፈት የሚባል ነገር አያውቅም እል ነበር አለ፡፡ ሁኔታው ያን ጊዜም አገሪቷን ዘመናዊ ሥልጣኔ አይታ የማታውቅ አድርጓት የሄደ አንድ አደጋ እንደደረሰበት ያስገምታል የጉዲት አመፅ ይሆን?

መጽሐፈ ሄኖክ የማን ነው?

ደራሲው በግዕዝ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ስማቸውም ሆነ ማንነታቸው ያልታወቀ ባለውለታዎች በአጠቃላይ ‹‹ያልታወቀው ምሁር›› ሊባሉ ይገባል ይላሉ፡፡

‹‹ያልታወቀው ምሁር የተረጐመልንን ቅዱሳት መጻሕፍት ተከታዮቻቸው አባቶቻችን ሱቲ አልብሰው ማኅደር አበጅተው የተቻላቸውን ያህል ተንከባክበው ለእኛ አውርሰውናል፡፡ እንዲያውም ከሌሎች ክርስቲያን ሕዝቦች ያበለጡንም ሁኔታ አለ፡፡ ለምሳሌ የሌሎች ሕዝቦች ኦሪትና ነቢያት ጎደሎዎች ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ከኦሪት ኩፋሌን፣ ከነቢያት ሄኖክን በሕጋዊነት በመቀበሏና እንደ ሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በመንከባከቧ መጽሐፍ ቅዱሳችን ምሉዕ ነው፡፡ ሌሎች አብያተ ክርስቲያን እነዚህ መጻሕፍት የሏቸውም፡፡ አሁን ዛሬ በሕጋዊነት ደረጃ ቢቀበሏቸውም ባይቀበሏቸውም ከግዕዙ ወደየቋንቋቸው መተርጐም ጀምረዋል፡፡ ሌሎችም ከውጭ የተረጐምናቸው፣ የውጭው ዓለም ግን አሁን የጠፉና ፈለጋቸው ብቻ የተገኘ መጻሕፍት አሉን፡፡

‹‹መጽሐፈ ሄኖክ ኢትዮጵያ ውስጥ ተገኘ ማለት የምዕራባውያን አነጋገር ነው እንጂ ድንገት አንድ ወይም ሁለት ቅጂ ተገኘ ማለት አይደለም፡፡ ሄኖክ እኛ ዘንድ ከነቢያት መጻሕፍት አንዱ ነው፡፡ ሄኖክን ቅዱስ ይሁዳ በመልእክቱ (ቁጥር 14) ቢጠቅሰውም ምዕራባውያን መጽሐፈ ሔኖክ የሚባል መጽሐፍ መኖሩን አላመኑም ነበር፡፡ በኋላ ግን ብጥስጣሹ በግሪክኛ ግብፅ ውስጥ ሲገኝ እውነት መሆኑን መቀበል ብቻ ሳይሆን ሌላም የጠፋ ጽሑፍ ይገኝ ይሆናል በማለት ገዳሞቻችን በአክብሮት መጎብኘት ጀመሩ፡፡

መጽሐፈ ሄኖክ ኢትዮጵያ ውስጥ መገኘቱን ዓለም በአድናቆት ሲናገር የሰሙ አንዳንድ ወጣቶች ራሱን ነቢዩን ሄኖክን ሳይቀር ኢትዮጵያዊ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ ሄኖክም ሆነ መጽሐፈ ሄኖክ ኢትዮጵያዊነት የለባቸውም፡፡

‹‹ለምንድነው እነዚህ መጻሕፍት እኛ ዘንድ ሲኖሩ ከሌላው ዘንድ የጠፉት? እያንዳንዱ አገር የራሱ ታሪካዊ ምክንያት ይኖረዋል፡፡ የሃይማኖት ጭቅጭቅ አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ክርስትና ከአይሁድ ሃይማኖት የተለየበት ዘመን የፈተና ዘመን ነበር፡፡ ወንጌሉ እንደሚለው ክርስቶስ ‹‹የእርሱ ወደሆኑት መጣ፣ ግን የገዛ ወገኖቹ አልተቀበሉትም›› ካልተቀበሉ ‹‹ክርስትና›› የሚባል ሌላ ሥርዓት ሊቋቋም ነው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ፣ ሐዋርያትና የእነሱ ተከታዮች ሊቃውንት ያንን አዲስ ሥርዓት መልክ ለማስያዝ የየራሳቸውን ሐሳብ የያዘ ጽሑፍ ያቀርቡ፣ የተለየ የኋለኞቹ ከዚያም አልፈው አንዱ የሌላውን ጽሑፍ ከእነመረጃው ምንጩ ያጠፉ ነበር፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ ከመጥፋታቸው በፊት ወደ ግዕዝ ተተርጉመው እኛ ዘንድ በሰላም ይኖራሉ፡፡ እነዚህ መጻሕፍት ለክርስትና ሃይማኖት ታሪክ የሚፈለጉ ዋና ምንጮች ናቸው፡፡    

የግዕዝ ፊደል የማን ነው?

ለመሆኑ ፊደሉ የማነው? ይሐሔኸ㝕ሐሔኼሔኼነንንንን ኼንን ፊደል ከእኛ በቀር ማንም አይሠራበትም፣ የማን ሊሆን ይችላል? ታሪክ ተመራማሪዎች በተለይም የምዕራብ ሊቃውንት ፊደሉ በመሠረቱ የሳባውያን መሆኑንና ኢትዮጵያውያን ከእነሱ የተዋሱት መሆኑን ያረጋግጣሉ፡፡ ይኼ ‹‹እርግጫ›› ሁለት ችግር አስከትሏል ይላሉ ፕሮፌሰር ጌታቸው፡፡

አንደኛ ፊደሉ የሳባውያን ለመሆኑ በግምት እንጂ በጽሑፍም ሆነ በቃል ሲወርድ ሲዋረድ የደረሰን ተጨባጭ ማስረጃ የለንም፡፡ ሊቃውንቱ ከዚህ ውሳኔ የደረሱት የሳባውያን ቋንቋ የግዕዝን ፊደል በሚመስል ፊደል ተጽፎ ስላገኙ ነው፡፡ ታዲያ ይኼ እንዴት የፊደልን ባለቤት ሊነግረን ይችላል? የሳባውያን ቋንቋ የተገኘው በግሪክኛ ፊደል ተጽፎ ቢሆን ኖሮ የግሪኩን ፊደል የሳባውያን ፊደል እንለው ነበረ ማለት ነው? የሳባውያን ቋንቋ የግዕዝ ፊደል በሚመስል ፊደል ተጽፎ መገኘቱ አያከራክርም፡፡ ግን ይኼ ታሪክ ፊደሉን የሳባውያን አያደርገውም፡፡ የዚህ የዚህ እንግሊዞች ቋንቋቸውን የሚጽፉበት ፊደል ለምን የእንግሊዝ ፊደል አንለውም? በዚህ ግዕዝን ፊደል በመሰለ ፊደል ቋንቋቸውን የጻፉ ሳባውያን ብቻ አይደሉም፡፡ ሌሎችም የደቡብ ዓረብ የጥንት ቋንቋዎች እንደኛና እንደሳባውያን በዚሁ ፊደል ጽፈዋል፡፡ ተቀባይነት ያለው አነጋገር ፊደሉን ሁላችንም (እኛንና ሳባውያንን ጨምሮ) ከአንድ ምንጭ ቀዳነው ማለቱ ነው፡፡ የሳባውያን ቋንቋ የተጻፈበትን ፊደል የሳባውያን ለማድረግ ግን ከዚህ የተሻለ ማስረጃ ያስፈልገናል፡፡

ቢሆንም ባይሆን ፊደሉን የግዕዝ ለማድረግ ግን የተሻለ ማስረጃ እንዳለ ፕሮፌሰሩ እንዲህ ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹በቃል ሲወርድ ሲዋረድ የደረሰን ስሙ ከላይ እንዳመለከትኩ ‹‹ግዕዝ›› ነው፡፡ የፊደላችንን የመጀመርያውን ረድፍ ግዕዝ ያሉት ፊደሉ የግዕዝ መሆኑንና ሌሎቹ ስድስቱ ረድፎች ከግዕዙ ፈደል የተወለዱ መሆናቸውን ለማመልከት ነው፡፡ የቀድሞ አባቶቻችን ፊደሉ የሳባውያን ፊደል መሆኑን ቢያምኑ ኖሮ የሳባውያን ፊደል ይሉት ነበር፡፡ ንግሥተ ሳባ የእኛ ንግሥት ነበረች እንዳሉት ስሙን ‹‹ግዕዝ›› ከማለት ‹‹ሳባ›› ብለው ‹‹የሳባ ፊደል የእኛ ፊደል ነው›› ይሉ ነበር እንጂ ‹‹ግዕዝ›› አይሉትም ነበር፡፡ ሌሎቹ ረድፎች ‹‹ከግዕዝ›› የተወለዱ ናቸው፡፡ እነዚያን ሁሉ አጠቃሎ የሳባ ፊደል ማለት አይቻልም፡፡ ሁለተኛም ምስጢሩ በግልጽ ባይገባኝም እኛ ብቻ ነን ፊደላችንን በ‹‹ሀ›› የምንጀምር፡፡

‹‹የግዕዝን ፊደል የሳባውያን ነው የሚለው አነጋገር ያስከተለው ሁለተኛው ችግር እኛን የፊደል ሥልጣኔ የሌለን አድርጎ ለማየት የሚፈልጉ ወገኖች የሚናገሩት ነውር ነገር ነው፡፡ ምዕራባውያን (ግሪኮች፣ ላቲኖች) እና ሴማውያን (ዓረቦች፣ ዕብራውያን፣ ሶርያውያን) የሚጠቀሙበት እኛም የምንጠቀምበት ፊደል በመሠረቱ የተፈለሰፈው ከአንድ ቦታ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ሁሉም መሠረቱን ከዚያ ወስዶ በየበኩሉ እንደመሰለው አስተካክሎታል፡፡ እኛም ያደረግነው ይኼንን ነው፡፡ በዚህ ረገድ ላቲኖች፣ ግሪኮች፣ ዓረቦች፣ ዕብራውያን፣ ሳባውያን፣ ካደረጉት የተለየ (ያነሰም ሆነ የበዛ) ነገር አላደረግንም፡፡ የግሪኮች ፊደል የግሪኮች፣ የላቲኖች ፊደል የላቲኖች፣ የዓረቦች ፊደል የዓረቦች ከሆነ፣ የግዕዝ ፊደል የአግዓዝያን/የኢትዮጵያውያን ነው፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...