Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊመፍትሔ የራቀው የትምባሆ ጭስ መዘዝ

መፍትሔ የራቀው የትምባሆ ጭስ መዘዝ

ቀን:

የትምባሆ ምርት ማሸጊያ ላይ የሚወጣ ማስጠንቀቂያ ከጽሑፍ ባለፈ የሚያስከትለውን የውስጥ ደዌ ከሚያሳይ ሥዕላዊ መግለጫ ጋር ቢወጣ የበለጠ ተፅዕኖ መፍጠር እንደሚችል ይነገራል፡፡ ካንሰር እንደሚያስከትል በካንሰር የተጠቃ ባለቀለም የልብና የሳምባ ምሥል መኖር የሚያስከትለውን የጤና ቀውስ በተግባር የማየት ያህል ክብደት አለው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከ115 በላይ የሚሆኑ አገሮች ማንኛውም ዓይነት በትምባሆ ማሸጊያ ላይ የትምባሆ የጤና ማስጠንቀቂያ በጽሑፍ ብቻ ሳይሆን በሥዕል የተደገፉ እንዲሆን ማድረጋቸውንና በዚህም የተሳካ ውጤት መቀዳጀታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ምሥልን በጽሑፍ ያስደገፈ የጤና ማስጠንቀቂያ ውጤታማ ስለመሆኑ በጥናትም ተረጋግጧል፡፡

ይህ ዓይነቱ ማስጠንቀቂያም የዓለም ጤና ድርጅት የትምባሆ ቁጥጥር ቃል ኪዳን ስምምነትን ስኬታማ በሆነ መንገድ ለመጠቀምና ለመተግበር የሚያስችል መሆኑንም ታምኖበታል፡፡

የትምባሆ ኢንዱስትሪዎች የትምባሆ ፓኬትን (ማሸጊያ) የሚጠቀሙት እንደ አንድ የማስታወቂያ መንገድ ነው፡፡ ይኼንንም ተግባራዊ የሚያደርጉት በልዩ ልዩ አሸብራቂ ቀለሞች በማስዋብ፣ በተለይም ሕፃናትን፣ ታዳጊ ወጣቶችንና ሴቶችን በሚያማልልና አጓጊ በማድረግ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ትምባሆ የሚጠቀሙ ወይም የማጨሱ ሁኔታ በእጅጉ ተስፋፍቶ የሚገኘው ከከተሞች ይልቅ በገጠሩ አካባቢዎች መሆኑን አንዳንድ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ከዚህ አኳያ ማንበብ የሚችለው የገጠሩ የኅብረተሰብ ክፍል ምን ያህል ነው? የሚል ጥያቄ ይስነሳል፡፡ ለዚህም የተሻለውና መልዕክቱን ለማስተላልፉ ውጤታማ የሆነው መንገድ በሥዕል መጠቀም ብቻ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የምግብ የመድኃኒትና ጤና እንክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን የሕግ አማካሪው አቶ ደረጀ ሽመልስ፣ በፓኬት ላይ የሚደረገው የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ የፓኬቱን 30 በመቶ ክፍል የሚሸፍን እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት የትምባሆ ማሸጊያ ሊያስቀምጥ የሚገባው የጤና ማስጠንቀቂያ በጽሑፍ ብቻ የተገደበ ነበር፡፡ ይህም ከነበረው አንፃር እንደ አንድ መሻሻል የሚታይ ሲሆን፣ ውጤታማነቱ ግን በሥዕል ከተደገፈው የጤና ማስጠንቀቂያ ጋር አይገናኝም፡፡

ባለሥልጣኑና የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በ2008 ዓ.ም. በጋራ ባካሄዱት ጥናት መሠረት፣ ከነባር አጫሾች ውስጥ የሲጋራ ፓኬት ላይ ያለውን ማስጠንቂያ ተመልክተው ለመተው የወሰኑት የአጫሾች ቁጥር ከ23 በመቶ ያልበለጠ ነበር፣ ይህም የሚያሳየው ነገር ቢኖር ውጤታማነቱ ሩብ ወይም አንድ ሦስተኛ እንኳን እንዳልደረሰ ነው፡፡

በምሥል የተደገፈ የጤና ማስጠቀቂያ ሥራ ላይ ቢውል ግን ከ75 በመቶ በላይ የሚሆኑ አጫሾች ለመተው እንደሚነሳሱ ነው አማካሪው የተናገሩት፡፡ ‹‹ዛሬ ባይተዉም እንኳን ከሁለት ወራት በኋላ የሚተዉ ቁጥር እየጨመረ እንደሚመጣና በተደጋጋሚም እንዲያስቡበት ውስጣቸውን ይቀሰቅሳል፤›› ይላሉ፡፡

በሲጋራ ፓኮ ላይ ከሚደረግ የጤና ማስጠንቀቂያ ባሻገር ሕዝብ የሚሰበሰብባቸውንና የማይጨስባቸውን ቦታዎች የመለየት ሥራ መከናወን አለበት፡፡ የሕዝብ መሰብሰቢያ ማለት ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ለአገልግሎት ወይም ለተለያዩ የግል አገልግሎቶች የሚውሉ ሕንፃዎች ወይም መዋቅር ሲሆን፣ በቤት ውስጥም ፈጽሞ ማጨስ እንደተከለከለ፣ ከበር መልስ ያሉ ቦታዎች ሁሉ ከትንባሆ ነፃ መሆን እንዳለባቸው ግድ ይላል፡፡

የትምህርትና የጤና ተቋማት እንዲሁም በዋናነት ለሕፃናትና ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ ታዳጊዎች አገልግሎት በሚሰጡ ማንኛውም ተቋማት ቅጥርም ከትምባሆ ጭስ ነፃ መሆን ይገባቸዋል፡፡

እንደ አቶ ደረጀ ማብራሪያ በዓለም ላይ በሲጋራ ብቻ የሚሞተው የሕዝብ ቁጥር በአሁኑ ሰዓት ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሟቾች ለትምባሆ የጭስ ተጋላጭ ወይም ደባል አጫሽ በመሆናቸው የሚሞቱ ናቸው፡፡ የሥራ ቦታቸው የሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች በተለይም  ቡና ቤቶች፣ ሬስቶራንቶች፣ ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች ከስምንት ሰዓትና ከዛም በላይ ለትምባሆ ጭስ ተጋላጭ ናቸው፡፡ ይህም ማለት ከአጫሹ በላይ ለካንሰርና ለተለያዩ አደገኛ ንጥረ ነገሮች ለረዥም ጊዜ ተጋላጭ እንደሚሆኑ ነው አቶ ደረጀ የተናገሩት፡፡

አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፣ ከትምባሆ ጭስ ቀጥታ አጫሹ ወደ ሳምባው የሚያስገባው ከ15 በመቶ የበለጠ አይደለም፡፡ 85 በመቶ ውጪ ነው የሚቀረው፡፡ ሲጋራ ቤት ውስጥ ሲጨስ አብዛኛው ጭስ ቤት ውስጥ ነው የሚቀረው፡፡ 10 ወይም 15 አጫሾች በአንድ ሬስቶራንት ውስጥ ቢያጨሱ የማያጨሰው የሬስቶራንቱ ሠራተኛ ሁሉ ለትምባሆ ጭሱ ተጋላጭ ነው የሚሆነው፡፡

እንደ አቶ ደረጀ አባባል ወደ 36 የሚደርሱ የአፍሪካ አገሮች የሕዝብ መሰባሰቢያዎችን ሙሉ ለሙሉ ከትምባሆ ጭስ ነፃ አድርገዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሕግ የሚጨስበት ቦታ ይለይ የሚል ድንጋጌ ቢኖርም አፈጻጸም ላይ ግን ከፍተኛ ክፍተት አለ፡፡ የትምባሆ ኢንዱስትሪዎችም ይህን አጋጣሚ እየተጠቀሙበት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ዓምና ለመጀመርያ ጊዜ የተካሄደው ‹‹ግሎባል አዳልት ቶባኮ ሰርቨይ›› የተባለው ጥናት ይኼንን በሚመለከት ያገኘው ውጤት በአሁኑ ጊዜ ከ6.5 ሚሊዮን ወይም 29.3 በመቶ በላይ ኢትዮጵያውያን አጫሽ ሳይሆኑ ለደባል አጫሽነት መጋለጣቸውን ነው፡፡ ከሰባት ሰዎች መካከል አንዱ የሚሞተው በቀጥታ ሲጋራውን በማጨስ ሳይሆን ስለተጨሰበት ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት የኅብረተሰቡን ጤና መጠበቅ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

ይህም ሆኖ ግን ለረጅም ሰዓት ለሲጋራ ጪስ ተጋላጭ የሆኑትን የማኅበረሰብ ክፍሎች ማዕከል ያደረገና መብትና ጤንነታቸው ሊጠበቅ የሚችል የሕግ ማዕቀፍ ተቀርፆ ጉዳዩ ለሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ቀርቧል፡፡

 የኅብረተሰቡን ጤና ማስጠበቅ የሚችሉ የጤና ፖሊሲዎችና ሕጎች በሚወጡበት ጊዜ ትልቅ ተግዳሮት የሚሆነው ከትምባሆ ንግድ ጥቅም የሚያገኙ ነጋዴዎች ሕጉ በሚፀድቅበት ወቅት፣ ከፀደቀም በኋላና በመፈጸምም እያለ ጣልቃ ገብነታቸው አይቀሬ መሆኑን ያመለከቱት የሕግ አማካሪው፣ ይህም ሆኖ ግን ማዕቀፉ ፀድቆ በሚወጣበት ጊዜ የትምባሆ ኢንዱስትሪ ጣልቃ ገብነት በቀጣይ ይታያል ብለዋል፡፡

የትምባሆ ኢንዱስትሪ ለጣልቃ ገብነቱ እንደ ምክንያት የሚያቀርበው በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሕገ ወጥ የትምባሆ ንግድ በጣም ከፍተኛ ስለሆነ ጠንካራ ሕግ ቢወጣ ተጠቃሚው ሕገ ወጥ የሆነው ነጋዴው ነው፡፡ እንጂ በሕጋዊ መንገድ የሚነግደው ነጋዴ አይደለም፡፡ ስለዚህም ሕጉ ትንሽ ላላ ቢል ይመረጣል የሚሉ አሉ፡፡ ሕጉ ተወካዮች ምክር ቤት ባፀደቀው የትምባሆ ኮንቬንሽን ውስጥ ሕገ ወጥ ትምባሆ ንግድን መቆጣጠር አንዱ መሠረታዊ የቁጥጥር መሥፈርት እንደሆነ፣ ይህም ከሌሎች የትምባሆ ቁጥጥር መሥፈርቶች ጋር አብሮ እንደሚሄድ፣ ሌሎች የቁጥጥር ሐሳቦች በሕጉ ውስጥ ተካተቱ ማለት ሕገ ወጥ የትምባሆ ንግድ አደገ ማለት እንዳልሆነ ከአማካሪው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የማቴዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ባለሙያ፣ አቶ ዘላለም መንግሥቱ  ትምባሆ በዓለም ውስጥ በወረርሽኝ ደረጃ እንዳለ፣ ወረርሽኙም አራት ዓይነት ደረጃዎች እንዳሉት፣ የአፍሪካ አገሮች የወረርሺኝ ደረጃ ገና በጅምር ላይ እንደሆነና በዚህም የተነሳ ሥርጭቱ ሲታይ አነስተኛ መስሎ እንደሚታይ አስረድቷል፡፡

የኢትዮጵያ ሥርጭት ሲታይ ደግሞ አንድ በመቶ እንደሆነ ሥርጭቱ  አነስተኛ በሆነበት በአሁኑ ወቅት ነው የመከላከያ ዕርምጃው መወሰድ ያለበት፤ አለበለዚያ ዕርምጃው አሁን መወሰድ ካልተቻለና የሥርጭቱ ደረጃ እየጨመረ ቢሄድ ከፍተኛ የሆነ መስዋዕትነት እንደሚያሰከፍል ይናገራሉ፡፡

የትምባሆ ምርትና ፍጆታ በተለይ በታዳጊ አገሮች ውስጥ በጣም እየጨመረ እንደመጣ ይህም የትምባሆ ኢንዱስትሪዎች በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ የተለየ ማርኬቲንግ ስትራቴጂን እየተከተሉ ስለመጡ ነው፡፡ የአገራችንም የትምባሆ ኢንዱስትሪ ለጃፓን ቶባኮ ኢንተርናሽናል በከፍተኛ ኢንቨስትመንት መሸጡ የሚታወስ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና ጤና ክባካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ የሁሉ ደነቀው፣ ‹‹ትምባሆ እንዳይስፋፋ ከሱሱ እንዲላቀቁ ለማስቻል በሱሱ የተቀየሰውን ሥልትና ሥልቱን ዕውን ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም ውጤቱ ግን በተፈለገው መንገድ እየሄደ አይደለም፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት የሕግ ማዕቀፎች ቅደም ተከተል አለመኖር ነው፤›› ብለዋል፡፡

ስለዚህ አንድን ሰው ትምባሆ እያስጨስክና እያጨስክ ነው፡፡ ይህን ያህል ትቀጣለህ ለማለት አይቻልም ሲሉም ያለውን የሕግ ክፍተት አሳይተዋል፡፡ ትምባሆም ምንም እንኳን የጤና ጎጂ ቢሆንም ሕጋዊ  ዕርምጃ ለመውሰድ የሕግ ሥልጣን ሊኖር ይገባል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...