Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ዓረሙ ይነቀል!

ሰላም! ሰላም! የተወደዳችሁ ወገኖች! በያላችሁበት አንዳንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ይድረስልኝ፡፡ ባሻዬ ልጃቸውን፣ ‹‹አሁንስ ህልም እያየሁ እየመሰለኝ ነው፡፡ ህልምም ከሆነ እባክህ እንዳትቀሰቅሰኝ፤›› በማለት ደስታቸውን ሲገልጹ ነበር፡፡ ነገርዬው ምን ያህል እውነት እንደሆነ የተገለጸልን ነገር ባይኖርም፣ ቢያንስ ዜናው ቦምብ ፈነዳ የሚል ስላልሆነ በመልካም ገጽታው ተመልክተን እንንበሽበሽበት፡፡ የምሥራች ስንባል የምን ፈዞ መቆም ነው? ይልቁንስ ድፍድፉ ተጣርቶ እስኪደርሰን ድረስ ነገን በፈገግታ እንጠብቀው እንጂ? ‹አይደለም እንዴ . . . › ያለው ማን ነበር?

ባሻዬም እንደገና፣ ‹‹አሁንስ የሰበር ዜና ሱስ ሳይዘኝ አይቀርም . . . ›› እያሉ ቀለዱ፡፡ ምሁሩ ልጃቸው የአባቱን ቀልድ ተንተርሶ፣ ‹‹ቢያንስ አንድ ቡና በአንድ ሰበር ዜና እናጣጥማለን፤›› አለ፡፡ ውዷ ማንጠግቦሽ ደግሞ፣ ‹‹ነዳጅ ውስጤ ነው፤›› በማለት አስቃኛለች፡፡ ውዷ ማንጠግቦሽ ከኤርትራ በመጡ ልዑካን ምክንያት የተሰማት ደስታ ጣሪያ ነክቷል፡፡ በትግርኛ ለመናገርም እየቃጣት ነበር፡፡ እኔም፣ ‹‹ዋናው ልብሽ ነው፡፡ ቋንቋውን እንኳን ለጠቅላያችን ተይላቸው . . . ›› በማለት ከመንተባተብ አዳንኳት፡፡

ማንጠግቦሽ ገና ድሮ ነው፣ ‹‹ዕርቅ ሲወርድ አስመራ ላይ ‹ሠልፊ› እንነሳለን . . .›› ብላ ቃል ያስገባችኝ፡፡ ‹‹እንኳንስ ‹ሠልፊ› ከፈለግሽ ቬሎ በድጋሚ ለብሰሽ በውቧ የአስመራ ጎዳና ላይ መዘዋወር ትችያለሽ . . . ›› በማለት ልቧን አሞቅሁላት፡፡ ካሁኑ አዲስ የቢዝነስ ዕቅድ ነድፈው አስመራ ለመጓዝ ከእግራቸው በፊት ልባቸው የቀደመ ሰዎች መኖራቸውን ስሰማ፣ እንኳንስ አስመራ ዓለም ድንበር አልባ የምትሆንበት ዘመን እነሆ በደጅ ነው አልኩ፡፡ ምን ይባላል ታዲያ? ዘመኑ የሰላምና የብልፅግና እንዲሆን ከመመኘት በላይ ምን ሊኖር ይችላል? እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ሥራዬ የሚሰፋውና ኑሮዬ የሚቃናው እኮ ሰላም ሲሰፍን ብቻ ነው፡፡

የባሻዬ ልጅ እንዳለኝ የድለላ መረቤን ወደ አስመራ ለመዘርጋት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ የሚጀምርበትን ቀን በናፍቆት እየተጠባበቅሁ እገኛለሁ፡፡ ያኔ ከቀይ ባህር ዓሳ አጥምደን ለእራት አዲስ ይዘነው ከተፍ እንላለን ማለት ነው፡፡ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ዳህላክ ላይ ልሥራ ቤቴን . . . የሚለውን ዘፈን አሻሽለን፣ ሁለተኛ ቤታችንን የምንሠራው ከቀይ ባህር ገባ ብሎ ነው . . . ›› አለኝ፡፡ ዘመን የማያሳየን የለም፡፡ ባሻዬ፣ ‹‹ይኼ ሰው ሦስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ይህን ሁሉ ማዕረግ ካሳየን፣ 27 ዓመት ቢሰጠው እንዴት ሊያደርገን ነው?›› በማለት ላነሱት ጥያቄ ልጃቸው ሲመልስ፣ ‹‹እርሱ ያረጀ አስተሳሰብ ነው፡፡ ትንሽ እያዩ በገዛ ፈቃዳቸው እንዲለቁ መጠየቅ ነው፤›› በማለት በነገር ተንኮስ አደረጋቸው፡፡ የባሻዬ ልጅ አባቱን፣ ‹‹አባዬ? እሳቸውም ቢሆኑ ከተናገሩት ነገር አንዲት ነገር ዝንፍ አድርገው ብናገኛቸው . . . ›› ሲል ባሻዬ የልጃቸው ነገር አንገብግቧቸው እስከሚጨርስ እየተጠባበቁት ነበር፡፡ እሱም ቢሆን የአባቱን ሁኔታ ባላየ ‹ላሽ› ብሎ ወሬውን ቀጠለ፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ደብዳቤ ይልክላቸዋል!›› ሲላቸው ባሻዬ እንደ ተኮሳተሩ፣ ‹‹ምን የሚል ደብዳቤ ነው ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚልክላቸው? ሕዝቡማ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ላይ የጻፈላቸውን ደብዳቤ አንብበኸዋል፤›› ሲሉት እሱም፣ ‹‹መልካም ነው፡፡ ዳሩ ግን ከፊት ለፊታቸው ገና በርካታ ሰኔ አሥራ ስድስቶች አሉ፤›› ብሎ መለሰላቸው፡፡ ይኼን ጊዜ ባሻዬ፣ ‹‹ምን የሚል ደብዳቤ ነው? ተናገር ደም ፍላቴን አታምጣው . . . ›› ብለው ተቆጡት፡፡ ይኼን ጊዜ ልጃቸው ደንገጥ ብሎ፣ ‹‹ኧረ ለጨዋታ ነው አታምርር! ዘመኑ እኮ የማምረር አይደለም፤›› እያለ አባቱን ለማረጋጋት ቢሞክርም፣ ዳሩ ግን አባትዬው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለጠቅላዩ ይጽፋል የተባለው ደብዳቤ አንጀት አንጀታቸውን በልቷቸዋል፡፡ እሳቸው ደግሞ በእስተርጅናቸው ወጣትነት እየገነነባቸው ያሉ ይመስል የጠቅላዩ ነገር የገዛ ጉዳያቸው መስሏል፡፡ በገቡ በወጡ ቁጥር፣ ‹‹ይኼ ልጅ እንዴት ዋለ? ዛሬ ደግሞ ምን አድርጎ ያስደምመን ይሆን? ወይ ፈጣሪዬ በእስተርጅናዬ ወጣትነቴን መልሰህ ትሰጠኝ . . . ›› እያሉ በደስታ ጮቤ ይረግጣሉ፡፡

ልጃቸው አባቱን፣ ‹‹አባቴ አንተው በነገርከኝ ታሪክ ውስጥ እስራኤላዊያን እንደዚያ የሚወዱትን መሪያቸውን ዳዊትን፣ በመጨረሻ ዳዊት ሆይ ቤትህን ጠብቅ እንዳሉት አስተምረኸኝ አልነበር እንዴ?›› በማለት ሌላ ጥያቄ አቀረበላቸው፡፡ ባሻዬ፣ ‹‹ቀጥተኛ ጥያቄ ነው የጠየቅኩህ ቀጥተኛ መልስ ስጠኝ?›› በማለት አፈጠጡበት፡፡ ይኼን ጊዜ ልጃቸው፣ ‹‹አባዬ ያው ደብዳቤው የሚለውማ በገዛ ፈቃድህ ሥልጣንህን ልቀቅ ነዋ የሚባለው፤›› በማለት አፈረጠው፡፡ ባሻዬ የሚሉትን ስላጡ ተነስተው ጥለውት ወጡ፡፡ ብቻቸውን ሆነው፣ ‹‹ይኼ አንዴ እንኳ የፈሰሰ ውኃ አቃንቶ የማያውቅ ተቺና ዘባራቂ ሁሉ፣ የሚመራ ሲያይ ዓይኑ እየቀላ ማንንም ብሎት የማያውቀውን የመልቀቂያ ደብዳቤ ይለኛል፡፡ ሥራ ፈት ሁሉ . . . ›› እያሉ ተንገበገቡ፡፡ ወይ ባሻዬ?

ማንጠግቦሽም ስለነዳጅ በሰማችው የምሥራች ተደስታ፣ ‹‹እነሆ አናዳጅ ሲቀንስ ነዳጅ መውጣት ጀምራል፤›› ብላ ቀለደች፡፡ በዚህ ብቻም አላበቃች፣ ‹‹ገና ሮኬት ማምጠቃችን የማይቀር ነው፤›› አለች፡፡ እርግጠኝነት በተሞላበት ስሜት ስትናገር ልቃወማት አልፈለግኩም፡፡ ይህንን የሰማው የባሻዬ ልጅ ግን፣ ‹‹ሚስትህ ስለሮኬት ማውራት ጀምራለች፣ አንተ ግን ዝም ብለህ ተኛ፤›› በማለት አላገጠብኝም፡፡ ዘንድሮ ሴቶቹ ቀድመውን እየገሰገሱ ነው፡፡ መቼም እርሷ ስለሮኬት አስባለችና ቢያንስ ስለሚሳይል ማሰብ ልጀምር ነው፡፡ የባሻዬ ልጅ ግን፣ መልካም ዜና በመሆኑ ብቻ ደስ እንሰኝበት . . . ›› እያለ ሲቀልድ ነበር፡፡ ቁም ነገራችን መሀል ቀልድ ደብለቅ ካላለ እኮ ይደብራል፡፡

ቀጣዩ ሰበር ዜና ምን ይሆናል ብለን ያሰብነው ቤተሰባዊ ትንበያ ይህን ይመስል ነበር፡፡ ያው የእኔንና የማንጠግቦሽን ሰምታችኋል፡፡ ባሻዬ፣ ‹‹ቀጣዩ ሰበር ዜና የሚሆነው ስለአዲስ ተሸኚ ባለሥልጣናት ነው፤›› ሲሉ ልጃቸው ደግሞ፣ ‹‹ሌላ የሚሸጥ ነገር ይዘውልን ይመጣሉ፤›› በማለት የቅድመ ትንበያ ፕሮግራማችን ተጠናቀቀ፡፡ ‹‹በሰበር ዜና ስብርብር አልን እኮ፤›› እንዳለው አሽሟጣጩ፣ አዳዲስ ነገሮችን መጠበቅ ለምደን ይኼው እያንጋጠጥን ነው፡፡ ወይ ጊዜ?

ደላላው ወዳጄ ያጫወተኝ ግን አስፈግጎኛል፡፡ በቅርቡ ሊዘጋ እንደሆነ የተወራበት አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ፣ አምስት መቶ ሚሊዮን ብር ሊበደር አስቦ ነበር የሚለውን ዜና ከሆነ ቦታ እንደሰማ ነግሮኝ፣ ‹‹ይኼ ቲቪ ጣቢያ ቴሌቪዥናችንን ወደ ኤቲኤም ማሽንነት የመቀየር አጀንዳ ይዞ ነው እንዴ ወደ ሥራ የገባው?›› በማለት አሳቀኝ፡፡ ‹‹ለነገሩ በዚህ ወቅት ከኢቲቪ ውጪ ምንም የሚታመን ጣቢያ አታገኝም፤›› የሚል አስተያየት የሰማሁት ደግሞ ከባሻዬ ልጅ ነበር፡፡ በዚህ ብቻም አላበቃም፡፡ ‹‹እግዜሩ ታሪካችንን እንደ ኢቲቪ ይቀይርልን፤›› በማለት አስቆኛል፡፡ ‹‹ለሁሉም ጊዜ አለው . . . ›› ተብሎ የለ?

ሰሞኑን ለመጀመርያ ጊዜ ከደላላነት ወጥቼ ሌላ ሥራ ውስጥ በገባሁ አሰኘኝ፡፡ ለነገሩ ደላሎችም ቤተ መንግሥት እንደሚጠሩ አልጠራጠርም፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው፡፡ ካልሆነም ችግር የለውም፡፡ እኛ ደላሎች እርስ በርሳችን እንጋጭና ጠቅላዩን እንዲያስታርቁን በሚል ሰበብ እንጠራቸዋለን፡፡ ያን ጊዜ ለአገር ያለን አስተዋጽኦ ይታወቃል፡፡ አንዳንዴ ሳስበው ግን በየቦታው እየተጋጨንና እየተጋደልን የአገር መሪን አላሠራም ማለት አይደብርም? ከቦምብ ፍንዳታ እስከ ኢኮኖሚ አሻጥር ድረስ ምን የሚሉት በሽታ ነው? ኧረ እንረጋጋ? አገር አናጥፋ!

ባሻዬ አሶሳ በተፈጠረው ነገር አዝነው ቤተ ክርስቲያን ደርሰው ፀሎታቸውን አድርሰው ነው የተመለሱት፡፡ አዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ጥላቻ፣ መገፋፋትና አመፃ ሥፍራ የሌላቸው መሆናቸውን ያልተገነዘቡ ግለሰቦች ያስነሱት ነገር፣ ለባሻዬ ዋነኛ የፀሎት ምክንያት ሆኗቸው ነበር የቆየው፡፡ ለማንኛውም ባሻዬ፣ ‹‹አሶሳ ውስጤ ነሽ! ሰላምሽ ሰላሜ ነው! ሸረኛውንና ተንኮለኛውን ይያዝልሽ! ነዳጅ ተገኘባት ይበሉኝ! በወርቅ ተንበሸበሸች ይበሉኝ! ሰላምሽን ይንገሩኝ!›› እያሉ ሲማልዱ ነበር፡፡ አዛውንቶች ይኑሩልን፡፡ ቢያንስ የእነሱ ምርቃት፣ ፀሎትና ተግሳፅ ገርገብ ያደርገናል፡፡ በዚህ በእኛ ጊዜ የገዛ ወገኑን የሚገድል፣ የሚያሳድድ፣ ንብረቱን የሚያወድምና መድረሻ የሚያሳጣ በየቦታው እንደ ዓረም ሲበቅል ማየት ያማል! በጣም ያማል! ዓረሙ ይነቀል! መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት