Friday, October 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊበአንዋር መስጊድ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ በርካታ መደብሮች ወደሙ

  በአንዋር መስጊድ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ በርካታ መደብሮች ወደሙ

  ቀን:

  የንብረት ግምት ገና እየተጣራ ነው ተብሏል

  መርካቶ በአንዋር መስጊድ በከለላቸው የንግድ መደብሮች ላይ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረት መውደሙን የንብረቶቹ ባለቤቶች ገለጹ፡፡

  የአንዋር መስጊድ አስተዳደር ካከራቸው 300 ያህል መደብሮች ውስጥ 50 ያህሉ መቃጠላቸውን የተገለጸ ቢሆንም፣ ንብረቶቻቸው የእሳቱ ሰለባ የሆኑባቸው ባለንብረቶች ግን የሱቆቹ ብዛት ከ163 በላይ መሆናቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

        አቶ ከድር መሐመድ የተባሉ የተለያዩ ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች መሸጫ መደብር ባለቤት እንደተናገሩት፣ መርካቶ ውስጥ ሦስት በአራት የሆነ ክፍል ሰባትና ስምንት ሱቆችን አካቶ እንደሚይዝ ገልጸው፣ የእሳቸው ሱቅ በውስጡ ከ200 ሺሕ ብር በላይ የሚገመት ንብረት ነበረው ብለዋል፡፡ ስፋቱ ግን ሁለት በሁለት ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

        በመሆኑም ሃምሳም ይሁኑ መቶ መደብሮችን የመስጊዱ አስተዳደር ማከራየቱን ቢገልጽም፣ በነፍስ ወከፍ ተይዘው ይሠራባቸው የነበሩ ሱቆች ግን ሁለት መቶ ሊደርሱ እንደሚችሉ አቶ መሐመድ ጠቁመዋል፡፡

        ረቡዕ ሰኔ 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት አካባቢ እሳቱ መነሳቱን የገለጹት ባለመደብሮቹ፣ በወቅቱ ሁሉም መደብሮች ዝግ ነበሩ ብለዋል፡፡ የተወሰነ እንኳን ማትረፍ እንዳይችሉ ተደውሎላቸው የደረሱት ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓትና ከዚያ በኋላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ምንም ዓይነት ንብረት ማትረፍ አለመቻሉን፣ አንዳንዶቹ አዳዲስ ግዥ ፈጽመው መደብሮቻቸውን የሞሉ በመሆናቸው ማካካሻ እንኳን እንደሌላቸው አስረድተዋል፡፡

         የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መቆጣጠር ባለሥልጣን ተደውሎለት ከሌሊቱ 7፡30 ሰዓት በቦታው መገኘቱን፣ ከ15 በላይ የአደጋ መከላከያ ተሽከርካሪዎችና 112 ሠራተኞቹን በማሠማራት እሳቱ ወደ ሌላ እንዳይዛመት ባለበት ለመቆጣጠር መቻሉን አስታውቋል፡፡

        የባለሥልጣኑ የኮሙዩኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሰለሞን መኮንን ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በመስጊዱ አስተዳደር መረጃ መሠረት የተቃጠሉት 50 መደብሮች ናቸው፡፡ መደብሮቹ በተቀጣጣይ ሸቀጣ ሸቀጦች የተሞሉ በመሆናቸው እሳቱ በቀላሉ ስለሚዛመት፣ ወደ ሌላ እንዳይስፋፋ በመከላከል እዚያው እንዲቀር ተደርጓል፡፡ በሕዝቡ ትብብር እስከ ንጋት ድረስ በተደረገው ርብርብ እሳቱ ሳይዛመት ለመቆጣጠር ቢቻልም፣ መደብሮቹን ማዳን አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡

        የደረሰውን የጉዳት መጠን ለማወቅ ባለሥልጣኑ ከፖሊስ ጋር በመተባበር እየሠራ በመሆኑ፣ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ መግለጽ እንደማይቻልም ተናግረዋል፡፡

        የእሳቱ መንስዔም ምን እንደሆነ ለማወቅ ጥረት እየተደረገ ነው ሲሉ አቶ ሰለሞን አክለዋል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img