ከአንድ ዓመት በፊት እንደ አዲስ የተዋቀረው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን፣ በአዲስ አበባ ለሚገኙ የመንግሥት ተሿሚዎችና ሠራተኞች 16,173 የጋራና ለኪራይ የሚውሉ ቤቶች በ33 ቢሊዮን ብር ለመገንባት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቁ፡፡
ኮርፖሬሽኑ የእነዚህን ቤቶች ግንባታ፣ የዲዛይን ሥራዎችና ተያያዥ ተግባራትን አስመልክቶ በቅርቡ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት፣ ከመሐንዲሶች፣ ከቤት አልሚዎች፣ ከትምህርት ተቋማትና ባለሙያዎች ጋር በካፒታል ሆቴል የምክክር ጉባዔ አዘጋጅቶ ነበር፡፡
ከምክክር መድረኩ ጎን ለጎን የኮርፖሬሽኑ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ግሩም ብርሃኑ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ቤቶቹ በተለያዩ የከተማዋ ክፍላተ ከተሞች ይገነባሉ፡፡ ቤቶቹን በሦስት ዓመት ገንብቶ ለመጨረስ መታቀዱንም አስረድተዋል፡፡
ለቤቶቹ ግንባታ 26.4 ሔክታር እንደሚያስፈልግ፣ ገሚሱ በኮርፖሬሽኑ እጅ እንደሚገኝና ቀሪው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንደሚቀርብ አቶ ግሩም ገልጸዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በሚገነባቸው ቤቶች ቀደም ሲል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሚገነባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተመዝግበው እየተጠባበቁ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ተጠቃሚ ይሁኑ አይሁኑ አልተወሰነም፡፡
ለመንግሥት ተሿሚዎችና ሠራተኞች፣ እንዲሁም ለተከራዮች ደረጃቸውን የጠበቁና መሠረታዊ አገልግሎቶች የተሟሉላቸው ቤቶች በመገንባት፣ በከተማው የሚታየውን የቤት እጥረት ለማቃለል ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ኮርፖሬሽኑ ገልጿል፡፡
ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው የአዲስ አበባ የከተማ ነዋሪዎች በአስተዳደሩ ተመዝግበው ቤት ለማግኘት እየተጠባበቁ ናቸው፡፡ ለ10/90 እና ለ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከተመዘገቡ 755,535 ከተመዘገቡ ቤት ፈላጊዎች ውስጥ የመንግሥት ሠራተኞች ብዛት 126,529 ሲሆን፣ የ11ኛውን ዙር ሳይጨምር 14,937 ያህል የመንግሥት ሠራተኞች ቤት ደርሷቸዋል፡፡
ነገር ግን በአጠቃላይ ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ከተመዘገቡ የመንግሥት ሠራተኞች ውስጥ የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች ቁጥር በትክክል ባይታወቅም፣ በተለያዩ የፌዴራል ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ኃላፊዎችና ሠራተኞች እንደሚገኙበት ከኮርፖሬሽኑ ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያሳያል፡፡
የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴርን በመጥቀስ ኮርፖሬሽኑ እንደሚገልጸው፣ የዩኒቨርሲቲዎችና የልማት ድርጅቶችን ሳይጨምር በሰኔ ወር 2008 ዓ.ም. በተለያዩ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ብቻ 86,263 የሚደርሱ ቋሚ ሠራተኞች ነበሩ፡፡