Friday, May 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየአዲስ አበባ አስተዳደርን የሥልጣን ዘመን ለማራዘም የሕግ ማሻሻያ መቅረቡ ጥያቄ አስነሳ

የአዲስ አበባ አስተዳደርን የሥልጣን ዘመን ለማራዘም የሕግ ማሻሻያ መቅረቡ ጥያቄ አስነሳ

ቀን:

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ማሻሻያ ተዘንግቷል

ሚኒስትሮች ምክር ቤት የከተማ አስተዳደሩ ማቋቋሚያ ቻርተር ተሻሽሎ የሥራ ዘመኑን የጨረሰው የከተማዋ አስተዳደር ምርጫ እስከሚካሄድ በሥልጣን ላይ እንዲቆይ መወሰኑ፣ የሕግ ማሻሻያውም ለፓርላማ መቅረቡ የሕጋዊነት ጥያቄ አስነሳ።

ፓርላማው ሐሙስ ሰኔ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅን ለማሻሻል በቀረበለት ረቂቅ አዋጅ ላይ መክሮ፣ ለተጨማሪ ዕይታ ለሕግ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል።ዘንድሮ ምርጫ ከአቅም በላይ በሆነ የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት መካሄድ አልቻለም፡፡ በዚህም ሳቢያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤትና ካቢኔ ከሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. በኋላ ሕጋዊ ሥልጣን የማይኖረው በመሆኑ፣ ምርጫ እስከሚከናወን ድረስ ሥራውን እንዲቀጥል የሚያስችል የሕግ ማሻሻያ ነው ለምክር ቤቱ የቀረበው። ‹‹የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን አምስት ዓመት ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ገጥሞ በአምስት ዓመት ማጠናቀቂያ ወቅት ምርጫ ማካሄድ ያልተቻለ እንደሆነ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የምርጫ ጊዜው ሊራዘም ይችላል፤›› የሚል ማሻሻያ በከተማዋ ማቋቋሚያ ቻርተር አዋጅ 361/1995 አንቀጽ 15 ንዑስ አንቀጽ (1) ላይ እንዲካተት ረቂቅ ማሻሻያ ሕጉ ይጠይቃል። በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 7 ሆኖ እንዲካተት የቀረበው ማሻሻያ አንቀጽ ደግሞ ‹‹በንዑስ አንቀጽ (1) መሠረት የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን የተራዘመ እንደሆነ፣ በሥራ ላይ የሚገኙ በሕግ የተቋቋሙ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት አካላት ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ ተግባርና ኃላፊነታቸውን መወጣት ይቀጥላሉ፤›› የሚል ማሻሻያ ድንጋጌ ቀርቧል።

- Advertisement -

ምክር ቤቱ በረቂቅ ማሻሻያው ላይ በተወያየበት ወቅት ከቀረቡት ጥቂት ጥያቄዎች መካከል ዋነኛው የአስተዳደሩ ምክር ቤት የሥራ ዘመን ማራዘም ብቻ በቂ እንደሆነ፣ ምክንያቱ ካቢኔውን የሚያቋቁመው የአስተዳደሩ ምክር ቤቱ እንደሆነ ቀርቧል። የካቢኔውን የሥራ ዘመን ለማራዘም ፓርላማው ሥልጣን እንደሌለው፣ ጉዳዩ በሚመለከተው የከተማዋ የምክር ቤት ኃላፊነት ላይ ጣልቃ መግባት ሊሆን እንደሚችል ጥያቄ ቀርቧል።

ሪፖርተር በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያ አቶ አብዱ ዓሊ ሒጅራ የቀረበው ማሻሻያ በራሱ የሕግ መሠረት እንደሌለው ይከራከራሉ። የአገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 54 የፌዴራልም ሆነ የክልል የሕዝብ ተወካዮች የሥራ ዘመን አምስት ዓመት ብቻ እንደሆነ መደንገጉን፣ ይኼንን መሠረት በማድረግ የወጣው የምርጫ ሕግም ምርጫ በየአምስት ዓመቱ እንደሚካድ መደንገጉን በምክንያትነት ይጠቅሳሉ።

ከሕገ መንግሥቱ በታች የሆነ አዋጅ ወይም ሌላ ማንኛውም ሕግና የመንግሥት አካል ውሳኔ ከሕገ መንግሥቱ የተጣጣመ መሆን እንዳለበት የሚያስረዱት አቶ አብዱ፣ ከሕገ መንግሥቱ የሚቃረን ሕግ በሕግ መወሰኛ ስለፀደቀ ብቻ ሕጋዊነትን ሊያገኝ እንደማይገባ ገልጸዋል። የአዲስ አበባን ቻርተር አዋጅ ለማሻሻል የቀረበው ረቂቅ ሰነድ ማብራሪያ ሀተታም ሕገ መንግሥቱ በተመሳሳይ የፌዴራልም ሆነ የክልል የሕዝብ ተወካዮች አባላት ምርጫ በየአምስት ዓመቱ እንደሚካሄድ ይደነግጋል። ከሕገ መንግሥቱ ተጣጥሞ የወጣው የተሻሻለው የምርጫ ሕግ በአንቀጽ 28(1) ላይ ጠቅላላ ምርጫ በየአምስት ዓመቱ የሚፈጸም መሆኑን የሚደነግግ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ከተማ ቻርተርም በአንቀጽ 8 ላይ፣ ‹‹በከተማ አስተዳደሩ የሚከናወኑ ምርጫዎች በአገሪቱ የምርጫ ሕግ ይከናወናል፡፡ በመሆኑም የአዲስ አበባ ምርጫ በየአምስት ዓመቱ መከናወን ይኖርበታል፤›› በማለት ያብራራል። ‹‹ይሁን እንጂ ምርጫውን ለማካሄድ ችግር በሚገጥምበት ወቅት ምን ሊደረግ እንደሚገባ መፍትሔ የሚሰጥ የተለየ ድንጋጌ ያስፈልግ ነበር። ይህ ባለመሆኑ ሌላ ምርጫ ተከናውኖ አዲስ ምክር ቤት እስከሚደራጅ ድረስ፣ አሁን ያለው ምክር ቤትና የሥራ አስፈጻሚ አካል ሥራውን ይዞ እንዲቀጥል ለማድረግ ይህ ማሻሻያ አዋጅ እንዲወጣ አስፈልጓል፤›› በማለት ያክላል።

ከሕገ መንግሥቱ የሚቃረን ሕግ ሕጋዊነት ሊኖረው እንደማይችል የሚያስረዱት የሕግ ባለሙያና የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኙ አቶ አብዱ፣ ‹‹ለእግር ተስማሚ ጫማ መስፋት ሲገባ፤ጫማው እንዲስማማ እግሩን ቁረጡት እንደሚባለው ዓይነት ነው የተደረገው፤›› ሲሉ ተችተውታል። ፓርላማው ሚያዚያ 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ ዘንድሮ መካሄድ የነበረበትን የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተሞች ምክር ቤትና የአካባቢ ምርጫን፣ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባቀረበለት የውሳኔ ሐሳብ በማፅደቅ ወደ 2011 ዓ.ም. እንዲዘዋወር ማድረጉን ያስታወሱት አቶ አብዱ፣ ይኼም የሕግ ስህተት እንደነበር ይገልጻሉ።

ሕገ መንግሥቱ ሥልጣን የሚመሠረተው በየወቅቱ በሚካሄድ ምርጫ እንደሆነ በአንቀጽ 38 ላይ መደንገጉን ያስረዱት አቶ አብዱ፣ በማናቸውም ደረጃ በየጊዜው በሚካሄድ ምርጫ የመምረጥና የመመረጥ መብት ዜጎች እንዳላቸው፣ እንዲሁም ምርጫ መራጩ ፈቃዱን በነፃነት የሚገልጽበትና ዋስትና የሚሰጥበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ፓርላማው ይኼንን በየወቅቱ የሚካሄድ ምርጫ ዛሬስ ይለፈን ብሎ ነው የወሰነው፤›› ሲሉ ተችተዋል፡፡ ይህ መሆኑም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 13 ሥር ተቀባይነት ካገኙ የሰብዓዊ መብቶች ጋር ጭምር እንደሚጣረስ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከምርጫ መሠረታዊ መርሆዎች አንዱ በየጊዜው (Periodic) መሆኑ ነው፤›› ያሉት አቶ አብዱ፣ ‹‹ይኼንን መርህ እስቲ ዛሬ ተውኝ፣ ይለፈኝ እንደ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከማንም እንዳይመጣ የሚፈራ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክር ቤትናካቢኔ የሥራ ዘመን እንዲራዘም የሕጋዊነት ጥያቄ የተነሳበትን የሕግ ማሻሻያ ለማፀደቅ ለፓርላማው ሲልክ፣ በተመሳሳይ ጊዜ የሥራ ዘመኑን የሚያጠናቅቀው የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤትንና ሥራ አስፈጻሚ ካቢኔውን እንደዘነጋ ለማወቅ ተችሏል። በዚህም ምክንያት የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ አቶ ኢብራሒም ዑስማን ዓርብ ሰኔ 22 ቀን 2010 ዓ.ም. አዲስ አበባ ተገኝተው ከፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ጋር መነጋገራቸውን ከንቲባው ለሪፖርተር ገልጸዋል።

 የሚኒስትሮች ምክር ቤት የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርና ካቢኔን የሥልጣን ዘመን ለማራዘም፣ ተመሳሳይ የሕግ ማሻሻያ በቀጣዩ ሳምንት ለፓርላማ እንደሚልክ ከንቲባው አክለዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ