Saturday, April 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበአሶሳ ከተማና አካባቢው የተከሰተውን ግጭት መከላከያ አስቆመው

በአሶሳ ከተማና አካባቢው የተከሰተውን ግጭት መከላከያ አስቆመው

ቀን:

በግጭቱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 15 መድረሱ ተጠቆመ

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በአሶሳ ከተማና በአካባቢው በሚገኙ አነስተኛ ከተሞች ከሰኔ 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ተከስቶ የነበረውን ግጭት፣ የመከላከያ ሠራዊትና የክልሉ የፀጥታ ኃይል በጋራ ማስቆማቸው ተገለጸ፡፡ የግጭቱ ምክንያት በውል ባይታወቅም፣ ከሰኔ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ጀምሮ በመከላከያ ሠራዊትና በክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ሊቆም መቻሉን፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አሻድሊ ሐሰን ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡

ከአሶሳ ከተማ እስከ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኙ መንጌ፣ ኡራ፣ ኮምሻ፣ ሸርቆሌና ማኦኮሞ በሚባሉ ከተሞች በተቀሰቀሰው ግጭት የሰዎች ሕይወት መጥፋቱን፣ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ከመድረሱም በተጨማሪ፣ ግምቱ ያልታወቀ ንብረት መዘረፉን የአካባቢው ነዋሪዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በመሄድ በአሶሳ ከተማና በሌሎች አነስተኛ ከተሞች የሚሠሩ ሰዎችንና ነጋዴዎችን ‹‹አገራችንን ለቃችሁ ውጡ›› በማለት በቡድን ሆነው አካባቢውን የወረሩት ወጣቶችና ጎልማሶች፣ በፈጠሩት ግጭት የበርካታዎች ሕይወት ማለፉን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ በተለይ በአሶሳ ከተማ በርካታ ሱቆች መዘረፋቸውንና የተገደሉ ንፁኃን ዜጎች መኖራቸውን የጠቆሙት ነዋሪዎቹ፣ ድርጊቱ የተፈጸመው በክልሉ መንግሥት መቀመጫ በሆነው አሶሳ ከተማ መሆኑ እንዳስደነገጣቸው ተናግረዋል፡፡

ችግሩ የተፈጠረው ሰኔ 18 ቀን 2010 ዓ.ም. መሆኑን የጠቆሙት ነዋሪዎቹ፣ ግጭቱ የትም አይደርስም በማለት ችላ መባሉን ያስረዳሉ፡፡ ችግሩ አሶሳ ከተማ ደርሶ የሰው ሕይወት በመጥፋቱ፣ ንብረት በመውደሙና የአካል ጉዳት በመድረሱ የክልሉ መንግሥት መጠየቅ እንዳለበትም አስረድተዋል፡፡ ሁሉም የአንድ አገር ዜጋ በመሆኑ፣ ጉዳት የደረሰበት ነዋሪ በአካባቢ ባሉ የጤና ተቋማት እኩል ሕክምና አገልግሎት ማግኘት ሲገባው፣ አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች ለእነሱ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ለማድረግ ጥረት ቢያደርጉም፣ ሐኪሞች እንዳልተባበሯቸው አስረድተዋል፡፡ ይኼም የሕክምና ባለሙያዎቹ የሥነ ምግባራቸው፣ ሕግ አክባሪነታቸው ሊመሰገኑ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በሌሎች አካባቢዎች የተፈጸመው ድርጊት በእነሱም አካባቢ መፈጠሩ እንደዳሳዘናቸው የጠቆሙት ነዋሪዎቹ፣ በአሁኑ ጊዜ እየታየ ያለውን አንፃራዊ ሰላም ለማስቀጠል የክልሉ መንግሥት ጠንክሮ መሥራት እንዳለበት፣ የፌዴራል መንግሥትም በእያንዳንዱን ክልል ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መከታተል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ለደረሰባቸው የሕይወት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት የክልሉ መንግሥትና ሕይወታቸውን የታደጋቸው መከላከያ ሠራዊት ጥፋተኞቹን አድኖ በመያዝ በሕግ ፊት እንዲያቀርቡላቸው ጠይቀዋል፡፡ የግጭቱ ጠንሳሾችና የድርጊቱ ተዋናዮች በፌዴራል እንደሚገኙ፣ በግጭቱ ተሳታፊ የነበሩትም በገንዘብ የተደገፉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎች ያነሷቸውን ቅሬታዎችና ጉዳዮች በሚመለከት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አሻድሊ ሐሰን እንደተናገሩት፣ በክልሉ ተከስቶ የነበረው ግጭት ከሰኔ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ጀምሮ በመርገቡ ሰላም ሰፍኗል፡፡ ከክልሉ የፀጥታ ኃይል በላይ በመሆኑ የመከላከያ ሠራዊት እንዲገባ በመደረጉ የበለጠ ጉዳት ሳይደርስ መቆጣጠር መቻሉን አክለዋል፡፡ የአሥር ሰዎች ሕይወት መጥፋቱንና የአካል ጉዳትና የንብረት ዘረፋ መፈጸሙን ያመኑት ፕሬዚዳንቱ፣ የችግሩ አንቀሳቃሽና ተሳታፊ ናቸው የተባሉ ከ40 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የግጭቱ መንስዔ ምን እንደሆነ ለማወቅ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ገልጸው የአገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሁሉም ነዋሪዎች በየከተማው ውይይት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የግጭቱ መንስዔ ሲታወቅ ለሕዝብ ይፋ ከማደረግ በስተቀር ዝም ብሎ መነሻው ይኼ ነው ማለት እንደማይቻልም ጠቁመዋል፡፡ ጥፋተኞች ከተለዩ በኋላም በሕግ እንደሚጠየቁም አክለዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ የሟቾቹ ቁጥር አሥር ነው ቢሉም፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ግን 15 ናቸው ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...