Saturday, April 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የ70 ዓመታት የነዳጅ ፍለጋ ጥረት ፍሬ እያፈራ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ፖሊጂሲኤል ነዳጅ ለፋብሪካዎች ማቅረብ ጀመረ

አዲስ የጋዝ ክምችት አገኘ

ላለፉት 70 ዓመታት በኦጋዴን ቤዚን ሲካሄድ የቆየው የነዳጅ ፍለጋ ሥራ ፍሬ እያፈራ እንደሆነ ተገለጸ፡፡

ፖሊጂሲኤል ፔትሮሊየም ኢንቨስትመንት የተባለው የቻይና ሂላላ በተባለው ሥፍራ ያገኘውን የተፈጥሮ ዘይት ሐሙስ ሰኔ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. የሙከራ ምርት ማውጣት ጀምሯል፡፡ በዕለቱ የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር አቶ መለስ ዓለሙ፣ ሚኒስትር ዴኤታው ኮአንግ ቱትልም (ዶ/ር)፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ፣ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐሙድ ዑመርና የፖሊጂሲኤል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተው የሙከራ ምርት መጀመሩን አብስረዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው ኮአንግ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ላለፉት 70 ዓመታት ሲካሄድ የቆየው የነዳጅ ፍለጋ ሥራ ከፍተኛ ውጤት እያስገኘ ነው፡፡ ‹‹ይህ በ70 ዓመታት ኢትዮጵያ የነዳጅ ፍለጋ ታሪክ እመርታ ነው፡፡ እኔም የዚህ ታሪክ አካል በመሆኔ ደስተኛ ነኝ፤›› ብለዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2013 ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር የነዳጅ ልማት ስምምነት የተፈራረመው ፖሊጂሲኤል ከ2014 ጀምሮ የተፈጥሮ ዘይትና ጋዝ ፍለጋ ሥራ ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ኩባንያው በዋነኛነት በካሉብ፣ በሂላላና በገናሌ የሚገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ለማልማት የመጣ ቢሆንም፣ ተጨማሪ የጋዝና የተፈጥሮ ዘይት ፍለጋ ሥራ ለማካሄድ ተስማምቷል፡፡ በመሆኑም ከጋዝ ልማቱ ጎን ለጎን የነዳጅ ፍለጋው ሥራ 93,000 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ባለው ይዞታ ላይ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

በሂላላ በቆፈራቸው ሂላላ 6፣ 7፣ 8 ጉድጓዶች ድፍድፍ ነዳጅ እንዳገኘ ኮአንግ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ይህን ተከትሎ የድፍድፍ ነዳጁን ክምችት መጠን ለማወቅ የሙከራ ምርት ማካሄድ እንዳስፈለገ ገልጸዋል፡፡

‹‹ቀደም ሲል የተገኘ የጋዝ ክምችት አለ፡፡ እስካሁን ሳይለማ ቆይቷል፡፡ ድፍድፍ ነዳጅ ምናልባት አንድ ጠርሙስ ተገኝቶ ይሆናል፡፡ አሁን ግን በርካታ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ በመፍሰስ ላይ ይገኛል፤›› ብለው፣ የተገኘው ድፍድፍ ነዳጅ መጠን ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ የተራዘመ የፍተሻ ሥራ እንደሚከናወን አስረድተዋል፡፡

‹‹በአሁኑ ጊዜ የክምችቱ መጠን አይታወቅም፡፡ የነዳጁ መጠን በኢኮኖሚያዊ ሥሌት አዋጭ ነው አይደለም የሚለውን ለመለየት የሙከራ ምርት ተጀምሯል፡፡

ኩባንያው አጥጋቢ የሆነ መጠን መኖሩን ሲያረጋግጥ ወደ ልማት ይገባል፤›› በማለት የሙከራው ውጤት ሲታወቅ ለሕዝብ እንደሚገለጽ ጠቁመዋል፡፡

አንድ የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ከፍተኛ የፔትሮሊየም ባለሙያ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ፖሊጂሲኤል መካከለኛው ሃማሌ ፎርሜሽን ላይ በቆፈራቸው ሦስት ጉድጓዶች ነዳጁን ሊያገኝ ችሏል፡፡

      ‹‹ሦስቱም ጉድጓዶች ውስጥ የጋዝ ምልክት ታይቷል፡፡ ሁለቱ ውስጥ ድፍድፍ ነዳጅ ተገኝቷል፡፡ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ነው እየተገኘ ያለው፤›› ያሉት ባለሙያው፣ የሙከራ ድፍድፍ ነዳጅ ምርት ከሁለቱ ጉድጓዶች እየተመረተ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ፖሊጂሲኤል በአሁኑ ወቅት አራተኛ ጉድጓድ በሂላላ በመቆፈር ላይ እንደሆነ ታውቋል፡፡

      እንደ ኮአንግ (ዶ/ር) ገለጻ ፖሊጂሲኤል ለሙከራ በቀን 450 በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ እያመረተ ለአገር ውስጥ ፈርነስ ነዳጅ ለሚጠቀሙ ፋብሪካዎች ያቀርባል፡፡ ኩባንያው ሃንሰን ኢንተርናሽናል ለተባለ የቻይና መስታወት ፋብሪካ ቀላል የተፈጥሮ ዘይት ለማቅረብ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ ነዳጁን ለሲሚንቶ ፋብሪካዎችም እንደሚያቀርብ ተገልጿል፡፡

      ድፍድፍ ነዳጁ ቤንዚን፣ ናፍጣና ነጭ ጋዝ ምርቶችን የያዘ በመሆኑ በቀጣይ በፈርነስ ነዳጅነት ብቻ መሸጡ አዋጭ ስለማይሆን የሙከራ ምርት ሒደቱ የተራዘመ መሆን እንደሌለበት ባለሙያዎች ያሳስባሉ፡፡

ፖሊጂሲኤል ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ጋር በቅርቡ ተወያይቷል፡፡ የኩባንያው ኃላፊዎች ያገኙትን ድፍድፍ ነዳጅ አነስተኛ ተንቀሳቃሽ የነዳጅ ማጣሪያ በመገንባት አጣርተው፣ የነዳጅ ውጤቶቹን ለኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ቢያቀርቡለት ይቀበላቸው እንደሆነ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ፖሊጂሲኤል ድፍድፍ ነዳጁን አጣርቶ ውጤቶቹን ቢያቀርብ ድርጅታቸው በደስታ ይቀበላል፡፡ ይሁን እንጂ የነዳጅ ምርቱ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የሚያወጣውን የነዳጅ ጥራት ደረጃ መሥፈርት ሟሟላት ይጠበቅበታል፡፡ ‹‹የሰልፈር ይዘትና ሌሎች መመዘኛዎችን ካሟላ በብር የምንገዛው በመሆኑ የውጭ ምንዛሪ የሚያድንልን በመሆኑ በደስታ እንቀበላለን፤›› ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ፖሊጂሲኤል ከነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ጋር የጀመረውን ድርድር ብዙም ሳይገፋበት፣ ያልተጣራውን ድፍድፍ ነዳጅ በቀጥታ ለፋብሪካዎች ማቅረብ ጀምሯል፡፡ አቶ ታደሰ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ኩባንያው አሁን በሙከራ ደረጃ ማምረት በመጀመሩ የምርቱ መጠን አነስተኛ ነው፡፡

‹‹እያመረቱ ያሉት በቀን 400 በርሜል ነው፡፡ የአገራችን ዕለታዊ የነዳጅ ፍጆታ 80,000 በርሜል ነው፡፡ ኩባንያው የፍለጋ ሥራው እንደቀጠለ በመሆኑ ከፍተኛ መጠን ያለው ድፍድፍ ነዳጅ ሊያገኝ ይችላል፡፡ የሙከራ ምርቱም እያደገ ሊሄድ ይችላል፤›› ያሉት አቶ ታደሰ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ለነዳጅ ግዥ በዓመት ሦስት ቢሊዮን ዶላር እንደሚያወጣ በመጠቆም፣ አሥር በመቶውን እንኳ በአገር ውስጥ ምርት መተካት ቢቻል ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡

የአገር ውስጥ ፋብሪካዎች የፈርነስ ነዳጅ በስፋት ይጠቀሙ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ታደሰ፣ አብዛኞቹ ፋብሪካዎች ወደ ድንጋይ ከሰል በመቀየራቸው የፈርነስ ነዳጅ ፍላጎት እየቀነሰ እንደመጣ ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ዕለታዊ ከባድ ጥቁር ናፍጣ ፍጆታ 125,000 ሊትር፣ ቀላል ጥቁር ናፍጣ 110,000 ሊትር መሆኑን ገልጸው፣ ይህን በአገር ውስጥ ምርት መተካት ቢቻል ከፈርነስ ነዳጅ ብቻ በወር 1.2 ሚሊዮን ዶላር ማዳን ይቻላል ብለዋል፡፡

ኮአንግ (ዶ/ር) ፖሊጂሲኤል ያገኘው ድፍድፍ ነዳጅ መጠን አዋጭ መሆኑን ሲረጋግጥ፣ የነዳጅ ልማት ዝርዝር ዕቅድ ለሚኒስቴሩ እንደሚያቀርብና ሲፀድቅለት ወደ ልማት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ሙሉ በሙሉ ወደ ምርት የሚገባበትን ጊዜ አሁን መናገር እንደማይቻል አክለዋል፡፡

‹‹ወደ ሽያጭ ምርት ለመግባት የድፍድፍ ነዳጁን ክምችት መጠን መታወቅ አለበት፡፡ አዋጭነቱ በጥናት ሲረጋገጥ ነው ወደ ሽያጭ ምርት መግባት የሚችሉት፤›› ብለዋል፡፡ ወደ ልማት ለመግባት ጊዜ እንደሚወስድ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹አዋጭነቱ ከተረጋገጠ በኋላ የልማት ዕቅድ አዘጋጅቶ አስፈላጊውን መሠረተ ልማት በመገንባት ወደ ምርት እስኪገባ ጊዜ ይወስዳል፤›› ብለዋል፡፡

ፖሊጂሲኤል የፔትሮሊየም ልማት ስምምነትና የምርት ክፍፍል ስምምነት ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ሲፈራረም ለካሉብ፣ ለሂላላና ለገናሌ የጋዝ መሬቶች 100 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ተስማምቷል፡፡ ከነዳጅ ልማቱ ላይ 85 በመቶ የኩባንያው ሲሆን፣ የመንግሥት ድርሻ 15 በመቶ ነው፡፡ ከምርት ድርሻው በተጨማሪ መንግሥት የገቢ ግብር፣ የባለቤት (ሮያሊቲ) ክፍያና የመሬት ኪራይ ይሰበስባል፡፡

በሙከራ ደረጃ የሚመረተውን ድፍድፍ ነዳጅ ሽያጭ ለመካፈል መንግሥትና ፖሊጂሲኤል ተስማምተዋል፡፡ የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር የመንግሥትን የነዳጅ ድርሻ እንዲያስተዳደር የማዕድን፣ ነዳጅና ባዮፊውል ኮርፖሬሽንን ወክሎታል፡፡

ፖሊጂሲኤልና ኮርፖሬሽኑ የትብብርና የገቢ ክፍፍል ስምምነት ያረቀቁ ቢሆንም፣ ውሉ ገና እንዳልተፈረመ ሪፖርተር አረጋግጧል፡፡

በተያያዘ ዜና ፖሊጂሲኤል ከዚህ ቀደም ያልተገኘ አዲስ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ዶሃር በተባለ ሥፍራ እንዳገኘ ታውቋል፡፡ በማዕድን ሚኒስቴር የሚገኙ ከፍተኛ የፔትሮሊየም ባለሙያ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ዶሃር የተገኘው የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ከሦስት ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ በላይ ይገመታል፡፡ ዶሃር የተባለው ሥፍራ በካሉብና በሂላላ መካከል እንደሚገኝ ታውቋል፡፡

ኮአንግ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ፖሊጂሲኤል ዶሃር ውስጥ በቆፈራቸው ሁለት ጉድጓዶች የጋዝ ክምችቱን ሊያገኝ ችሏል፡፡ ሦስተኛውን ጉድጓድ በመቆፈር ላይ እንደሆነ ገልጸው፣ የክምችቱ መጠን ላይ በቀጣይ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በሁለቱ ጉድጓዶች ላይ ሙከራ እየተካሄደ ነው፡፡ አዲስ የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት መጠን ለማወቅ ትንሽ ጊዜ ይወስዳል፤›› ብለዋል፡፡

ፖሊጂሲኤል በካሉብ፣ በሂላላ፣ በገናሌና በዶሃር የሚገኘውን ስምንት ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ የሚገመተውን የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ለማልማት የሚያስችለውን ዕቅድ ለሚኒስቴሩ አቅርቦ አፅድቋል፡፡ በመጪው መስከረም ወር የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ ዝርጋታ ሥራ እንደሚጀመር፣ በጂቡቲ ወደብ የጋዝ ማጣሪያ እንደሚገነባ ኮአንግ (ዶ/ር)  ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጪ አራት ቢሊዮን ዶላር ይገመታል፡፡

የመሠረተ ልማት ግንባታው እ.ኤ.አ. በ2020 መጨረሻ እንደሚጠናቀቅ፣ የጋዝ ምርቱ በ2021 እንደሚጀመር ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የነዳጅ የሙከራ ምርት መጀመሩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ ከጋዝ ኤክስፖርት በዓመት አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደሚገኝ ገልጸው፣ የሥራ ዕድልና ለአገሪቱ እጅግ አስፈላጊ የሆነውን የውጭ ምንዛሪ እንደሚያስገኝ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች