ኢትዮጵያ ይኼንን በመፍቀዷ ለ200 ሺሕ ሥራ አጦች ዕርዳታ ታገኛለች
ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የውጭ አገሮች ስደተኞች ከመጠለያ ካምፖች ወጥተው መኖር፣ መዘዋወርና ተለይተው በሚፈቀዱ የሥራና የንግድ እንቅስቃሴዎች እንዲሳተፉ የሚፈቅድ ረቂቅ የሕግ ሰነድ ለፓርላማ ቀረበ፡፡
ረቂቅ ሰነዱ በሥራ ላይ የሚገኘውን የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ አሻሽሎ እንደ አዲስ የሚደነግግ ሲሆን፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ሐሙስ ሰኔ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. በረቂቁ ላይ ተወያይቶ ለዝርዝር ዕይታ ለቋሚ ኮሚቴ መርቶታል፡፡
ረቂቁ በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞች ከመጠለያ ካምፖች ውጪ ለመኖር እንዲችሉ፣ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የመዘዋወር ነፃነትን የሚያጎናፅፍ ድንጋጌ ይዟል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የባንክ ሒሳብ የመክፈት፣ መንጃ ፈቃድና መታወቂያ ማውጣት እንዲችሉ መብት የሚሰጥ ድንጋጌ የያዘ ሲሆን፣ ከ20 ዓመት በላይ በኢትዮጵያ የኖሩ ስደተኞች አግባብ ባለው ሕግ የኢትዮጵያ ዜግነትን እንዲያገኙም በሰነዱ ተካቷል፡፡
የሥራ ዕድልን በተመለከተም ለውጭ አገር ዜጎች ከተሰጡ መብቶች እጅግ የተሻለውን ያህል ተጠቃሚ እንዲሆኑ መብት የሚሰጥ ድንጋጌ በረቂቁ ተካቷል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በተለየ ሁኔታ ለስደተኞች የሚፈቀዱ የሥራ ዘርፎች ተለይተዋል፡፡ እርሻ፣ ኢንዱስትሪ፣ አነስተኛና ጥቃቅን የዕደ ጥበባትና የንግድ ዘርፎች ተዘርዝረዋል፡፡
ንብረት የማፍራትና የማስተላለፍ፣ የአዕምሮ ውጤቶች ጥበቃ እንዲያገኙ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያውያንና በስደተኞች መካከል መድልኦ እንደማይደረግ የሕግ ሰነዱ ይዘረዝራል፡፡
መንግሥት ይኼንን የሚፈቅድ ከሆነ ለኢትዮጵያውያን ሥራ አጦች የጋራ ተጠቃሚነትን የሚውል የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ዕርዳታ እንደሚገኝ የሰነዱ ማብራርያ ይገልጻል፡፡
ከእነዚህም መካከል ለ100 ሺሕ ሰዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በተመሳሳይ 100 ሺሕ ሰዎችን በመስኖ የታገዘ የእርሻ ልማት እንዲያለሙ እንደሚያስችል እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ለዚህም ሲባል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የዓለም ባንክ፣ የአውሮፓ ኅብረትና ሌሎች አገሮች የኢንቨስትመንት ካፒታል በዕርዳታ ለመስጠት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ስምምነት ማድረጋቸውን ያስረዳል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ሲጠናቀቁ ከሚፈጠረው ለ100 ሺሕ ሰዎች የሚሆን የሥራ ዕድል ውስጥ 70 በመቶ (70 ሺሕ) ለኢትዮጵያውያን የሚደለደል ሲሆን፣ ቀሪው 30 በመቶ (30 ሺሕ) ለስደተኞች እንደሚሆን ማብራርያው ይገልጻል፡፡
በተመሳሳይ በእርሻ ልማት የሥራ ዕድል ለመፍጠር 10 ሺሕ ሔክታር መሬት የተዘጋጀ መሆኑን፣ በዚህም ከሚፈጠረው 100 ሺሕ የሥራ ዕድል 70 በመቶ ለኢትዮጵያውያን ቀሪውን 30 በመቶ ደግሞ ለስደተኞች እንደሚደለድል ይገልጻል፡፡
በመሆኑም በሁለቱ የሥራ ዘርፍች ከሚፈጠረው የሥራ ዕድል ውስጥ 60 ሺሕ ስደተኞች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡