የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፀረ አበረታች ቅመሞች ጽሕፈት ቤት፣ ችግሩን በዘላቂነት ለመቆጣጠር እያደረገ ካለው ጥረት ጎን ለጎን ከሰሞኑ በስፖርት የፀረ አበረታች ቅመሞች የሕግ ጥሰት በፈጸሙ አትሌቶችና የመድኃኒት መደብር ላይ የቅጣትና ዕገዳ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ጽሕፈት ቤቱ ሰኔ 22 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ ውሳኔውን ዝርዝርና ሒደት አስመልክቶ ማብራሪያም ሰጥቷል፡፡
እንደ ጽሕፈት ቤቱ ከሆነ፣ በኢትዮጵያ ንፁህ ስፖርት ለማስፋፋትና ውጤታማነቱን ለማጎልበት በየደረጃው የተጠናከረ ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በተለይም የአትሌቶች ምርመራና ቁጥጥር እንዲሁም የደኅንነት ተግባራት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ስለመሆኑም አስታውቋል፡፡
በዚሁ መሠረት ሁለት አትሌቶችና ዮሐና የተባለው የመድኃኒት መደብር የስፖርት አበረታች ቅመሞችን በመጠቀም፣ ያለ አግባብ በመሸጥና በማዘዋወር ተጠርጥረው ጉዳያቸው ሲጣራ ቆይቶ፣ ጥፋተኝነታቸው በመረጋገጡ ውሳኔ ተላልፎባቸዋል፡፡ በመሆኑም ከአዲስ አበባ የምግብ፣ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ ቁጥጥር ባለሥልጣን ጋር በመሆን በተካሄደው የኢንቴለጀንስና ኢንቨስትጌሽን ተግባር ዮሐና የመድኃኒት መደብር ቴስቴስትሮን የተባለውንና በስፖርት የተከለከለውን መድኃኒት ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ይዞ በመገኘቱ፣ እንዲሁም ያለ ሐኪም ትዕዛዝ ለአትሌቷ መሠረት ታየ አሳልፎ መሸጡ በመረጋገጡ፣ ለሁለት ዓመታት ምንም ዓይነት መደበኛ አገልግሎት እንዳይሰጥ ታግዷል፣ የብቃት ማረጋገጫ ፈቃዱም እንዲመለስ ተደርጓል፡፡
ከዚህ ባሻገር አትሌት መሠረት ታየ አሰፋ፣ ደቡብ አፍሪካ ላይ በተካሄደው የኬፕታውን ማራቶን ላይ መስከረም 7 ቀን 2010 ዓ.ም. በተደረገላት ምርመራ ቴስቴስትሮን ተባለውን የተከለከለ አበረታች መድኃኒት መጠቀሟ በመረጋገጡ፣ ጊዜያዊ ዕገዳ ከተጣለባት ከታኅሳሥ 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለተከታታይ አራት ዓመታት በማንኛውም ውድድር ላይ እንዳትሳተፍ፣ በዚህ ውድድር ያገኘቻቸው ውጤቶችና ሽልማቶች ሁሉ እንዲሰረዙ ቅጣት ተጥሎባታል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ መቅደስ ፈቀደ ቸገን፣ ቻይና ላይ በተካሄደው የቴላን ማራቶን ሚያዝያ 14 ቀን 2009 ዓ.ም. በተደረገላት ምርመራ ክሌንቡቴሮ የተባለውን የተከለከለ አበረታች መድኃኒት መጠቀሟ ስለተረጋገጠ፣ ጊዜያዊ ዕገዳ ከተጣለባት ከኅዳር 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለተከታታይ ሁለት ዓመታት በማንኛውም ስፖርታዊ ውድድር ላይ እንዳትሳተፍ፣ እንዲሁም በዚህ ውድድር ያገኘቻቸው ውጤቶችና ሽልማቶች እንዲሰረዙ ቅጣት ተላልፎባታል፡፡