Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

  የሳምንቱ ገጠመኝ

  ቀን:

  ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ወደ ስታዲዮም ስጓዝ ታክሲ ውስጥ የሰማሁት ወግ ነው መነሻዬ፡፡ ወያላና ሾፌር የታክሲው መጨረሻ ስታዲዮም መሆኑን ወስነው ተሳፋሪን የሚጭኑት ስታዲዮም ብቻ እንደሆነ ቀጭን ትዕዛዝ ሰጡን፡፡ አንዲት ወጣት በውሳኔው በመከፋት፣ ‹‹ፒያሳ እንሄዳለን ብላችሁ እንዴት ስታዲዮም ላይ ታበቃላችሁ?›› አለች፡፡ ወያላው ቀብረር ብሎ፣ ‹‹ብለን ነበር ሐሳባችንን በመቀየራችን አንሄድም፡፡ ስለዚህ ማንም ሊያስገድደን አይችልም፤›› ማለት፡፡ የወያላው በትዕቢት የተሞላ መልስ ያናደደው አንድ ጎልማሳ፣ ‹‹ግዴለም የከተማው ትራንስፖርት ሲስተም በዘመናዊ ተቀይሮ አሮጌ ሚኒባስህ ወደ ማቅለጫ እስኪላክ ድረስ ተንቀባረር፤›› አለው፡፡ ሾፌርና ወያላ አሪፍ ቀልድ የሰሙ ይመስል ከጣሪያ በላይ ይስቁ ጀመር፡፡

  ታክሲው ውስጥ ይሰማ የነበረው ሙዚቃ አልቆ ስለታክሲ ስምሪት የተዘጋጀው ፕሮግራም እንደሚቀርብ ሲበሰር፣ ተሳፋሪዎች በሙሉ ማለት ይቻላል ከሾፌሩና ከወያላው በላይ ሳቅን፡፡ ጨዋታው አንድ ለአንድ ሆነ ማለት ነው፡፡ የሬዲዮው ፕሮግራም ከትራንስፖርት ባለሥልጣን፣ ከታክሲ ሾፌሮች፣ ከተራ አስከባሪዎችና ከተሳፋሪዎች ጋር በየተራ ገባ ወጣ እያለ ሲያወያይ ወያላና ሾፌር ፀጥ ብለዋል፡፡ የሚሰማው ውይይት የተዋጠላቸው አይመስሉም፡፡ የቅድሙ ጎልማሳ ዘብነን እያለ፣ ‹‹ወያላው ምነው አሁን አፍህ ተለጎመ?›› ሲለው ብልጡ ወያላ እየሳቀ፣ ‹‹ዝምታ ወርቅ ነው፡፡ አሁን አፍ መካፈት ጥሩ አይደለም፤›› ሲለው ስታዲዮም ደርሰን ሁላችንም ወረድን፡፡ ይኼ ለከተማ የማይመጥን የትራንስፖርት ሲስተም በዘመናዊ ተተክቶ የሚሆነውን እስከምናይ ድረስ በዝምታ መታገሱ ሳይሻል አይቀርም፡፡

  ይኼንኑ የታክሲ ወግ እያብሰለሰልኩ ወደ አንድ መንግሥታዊ ተቋም ደረስኩ፡፡ በር ላይ የተቀመጡት የተሰላቹ ጥበቃዎች እንደነገሩ ፈትሸውኝ ከገባሁ በኋላ የምፈልገውን ቢሮ ብጠይቅ የሚያሳየኝ አጣሁ፡፡ ችግሩ ምንድነው ብዬ ስጠይቅ እንዲያው በደፈናው ጉዳይህን ተናገር ተባልኩ፡፡ ጉዳዬን ብናገርም ማስፈጸም አልቻልኩም፡፡ ከአንዱ ቢሮ ወደ ሌላው እንደ ኳስ ቢቀባበሉኝም የሚፈለጉት ሰዎች ሊገኙ አልቻሉም፡፡ በቃ ሥራ ቆሟል ማለት ይቻላል፡፡ በፊት የማውቀው በመጠኑም ቢሆን ቀልጣፋ የነበረ መሥርያ ቤት እንደ አዲስ የሚደራጅ መስሏል፡፡ አንዱን ሠራተኛ ጠጋ ብዬ ‹‹ምን ችግር ተፈጠረ?›› ስለው አንገቱን እያወዛወዘ፣ ‹‹ዝም ማለት ይሻላል፤›› አለኝ፡፡ የታክሲው ወያላ የመረጠው ዝምታ እዚህም ሰፍኗል ማለት ነው፡፡ ሰሞኑን እንደተባለው አሻጥሩ መሠረት የያዘ ይመስላል፡፡ አኩራፊ በየቦታው ካጋጠመን እኮ የሆነ ሴራ አለ ማለት ነው፡፡

  ትክት እንዳለኝ ምሳ ለመብላት ዘወትር የምሄድበት ምግብ ቤት ገባሁ፡፡ እዚህ ይሻላል ሰው ምሳውን እየበላ እንደ ጉድ ያወራል፡፡ በተለይ ድፍድፍ ነዳጅ ተገኘ መባሉ ትልቁ ርዕስ ነበር፡፡ የአስተናጋጆች ፈጣን እንቅስቃሴና የተመጋቢው ሁኔታ ዛሬ ልዩ ይመስላል፡፡ ሁሉም ፊት ላይ ፈገግታ ይታያል፡፡ እኔም እፎይ ብዬ አረፍኩ፡፡ የምግብ ሜኖውን ከፍቼ ስመለከት በርካታ የምግብ ዓይነቶች ተደርድረዋል፡፡ አንዱን ያማረኝን ምግብ አዝዤ መመገብ ጀመርኩ፡፡ በዚህ መሀል ሁለት ጓደኞቼ መጥተው ተቀላቀሉኝ፡፡ ወጋችንን እየሰለቅን ተመገብን፡፡ በወሬያችን ጣልቃ ሁለቱን ገጠመኞቼን ነገርኳቸው፡፡ እነሱ ያን ያህል ሳይገርማቸው አንዳንዴ የሚያጋጥም መሆኑን ነግረውኝ ወደሌላ ገጠመኝ አመራን፡፡

  አንደኛው ጓደኛችን የሰማውን ገጠመኝ እንዲህ ተረከልን፡፡ እሱ የሚሠራበት ድርጅት አካባቢ ሁለት የታወቁ ደላሎች አሉ፡፡ አንደኛው የቆየ ደላላ ሲሆን፣ አንደኛው ግን በቅርብ ጊዜ ሥራውን ተቀላቅሎ መኪና መግዛት የቻለ ነው፡፡ ነባሩ ደላላ ጠቀም ያለ ገቢ ቢያገኝም በየምሽቱ መሸታ ቤት ስለሚታደም ቅርስ አልያዘም እንጂ በርካታ ደንበኞች አሉት፡፡ በአባካኝነቱ ወደር የለውም፡፡ አዲሱ ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ እየተሯሯጠ ያገኘውን ቁምነገር ላይ የሚያውል ሲሆን፣ በርካታ ደንበኞችን እያፈራ ነው፡፡ በአዲሱና በወጣቱ ደላላ ስኬት ጥሩ ስሜት ያልተሰማው ነባሩ ደላላ ሁሌም በነገር ይተነኩሰዋል፡፡ አዲሱ ደግሞ ‹‹አርፈን ሥራችንን እንሥራ፤›› ይላል፡፡ አንድ ቀን ነባሩ ደላላ አዲሱን፣ ‹‹የእኛ ቢል ጌትስ ሥራ እንዴት ነው?›› በማለት ለማሽሟጠጥ ይሞክራል፡፡ አዲሱ ደላላ እየሳቀ፣ ‹‹ሥራ በጣም አሪፍ ነው፡፡ ግን የዘመኑ ሥራ የሚወደው አካውንት መክፈት እንጂ አፍ መክፈት አይደለም፤›› ሲለው በኃፍረት የሚገባበት ጠፋው፡፡ ምናለ ዝም ቢል?

  ከጓዋደኞቼ ጋር ምሳዬን በልቼ ወደ ጉዳዬ ሳመራ አንድ የማውቀው ሰው ደወለልኝ፡፡ ስለድፍድፍ ነዳጅ መገኘት መስማት አለመስማቴን ሲጠይቀኝ መስማቴን ነገርኩት፡፡ ‹‹በቃ ይኼ ሰበር ዜና ባንዴ ነው እንዴ የሚናኘው?›› ሲለኝ፣ ዋናው አለመቀደም መሆኑን ነገርኩት፡፡ ሳቅ እያለ፣ ‹‹እንዴት አገኘኸው?›› በማለት ሌላ ጥያቄ አቀረበልኝ፡፡ እኔስ ምኔ ሞኝ ‹‹ደስ ብሎኛል!›› ማለት፡፡ ይኼ ሰው ግን ውስጡ ከተከፋ የሰነበተ ይመስል በለበጣ፣ ‹‹ላም አለኝ በሰማይ ወተቷንም አላይ ሲባል የት ነበርክ?›› እያለ ሲሳለቅ እኔ ለእሱ አዘንኩ፡፡ ይህ ሰው ፍፁም ሰላማዊና ትሁት ሆኖ ነው የማውቀው፡፡ ክፉም ደግም ላለመናገር ብዬ ተሰናብቼው ስልኩን ዘጋሁት፡፡ አመሻሽ ላይ የገጠመኝን ለባለቤቴ ስነግራት ከት ብላ ሳቀችብኝ፡፡ ‹‹አይ አንተ የተባለውን አልሰማህም እንዴ?›› ብላኝ፣ ‹‹ወቅት ሲቀያየር የሰው ባህሪም ቀያየራል፡፡ ትናንት ጠባብ የተባለው ዛሬ ትምክህተኛ፣ የትናንቱ ትምክህተኛ አሁን ጠባብ፣ የሥርዓቱ ዘብ የነበረው ዛሬ የለየለት ተቃዋሚ፣ ፀረ ሰላም ተብሎ የተፈረጀው የሰላም ሰባኪ፣ ሌባ የነበረው እምነት የሚጣልበት፣ ታማኝ ተብዬው ዘራፊ…›› ስትለኝ ግራ ገባኝ፡፡ ‹‹ሰውዬውን ከዚህ ጋር ምን ያገናኘዋል?›› ስላት፣ ‹‹ሰውን ባስቀመጠክበት ለማግኘት አይቻልም ለማለት ነው …›› ብላኝ ያልገባኝን ግልጽ አደረገችልኝ፡፡ ለካ ትናንት ሥርዓቱን ሲቃወሙ የነበሩ ዛሬ ገርገብ ያሉት ከሥርዓቱ ደጋፊዎች ጋር ቦታ ተለዋውጠው ነው? ወይ ጊዜ? ‹‹የዘመኑን ነገር ለባለ ዘመኑ መተው ነው…›› እንዲሉ፣ ጊዜ እንደ ባቡር ፉርጎ ተቀጣጥሎ ሲጓዝ መታዘብን የመሰለ ነገር የለም፡፡

  (እስክንድር ወግደረስ፣ ከልደታ) 

  spot_img
  Previous articleዝንቅ
  Next articleተስፍሽ ና ገብርሽ
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...