Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክፈተና ላይ የወደቀው የንግድ ሕግ ነፃነት

ፈተና ላይ የወደቀው የንግድ ሕግ ነፃነት

ቀን:

በአፈወር ቅጣው

የአንድ አገር የሕግ አደረጃጀት በሰፊው ሲታይ የሕዝብና የግል ሕግ ተብሎ ይከፈላል፡፡ እነዚህ ራሳቸው ደግሞ የተለያዩ ክፍልፋዮች ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ከእነዚህ ሕጎች መካከል በአብዛኛው በግል ሕግ የሚመደበው የንግድ ሕግ ነው፡፡ የንግድ ሕግ የሲቪል ሕግ አካል ሆኖ ያደገና ቤተሰብ የሆነ ነው፡፡ የንግድ ሕጉ የሲቪል ሕግ አብሮ አደግና ቤተሰብ ቢሆንም፣ የራሱ ባህሪ ያለውና ራሱን ችሎ የቆመ የሕግ ዘርፍ ነው፡፡ ይህም ከፍትሐ ብሔር ሕግ፣ ከቤተሰብ ሕግ፣ ከባህር ሕግና ሌሎች መሰል ሕጎች በንፅፅር ሲታይ ነው፡፡ የንግድ ሕግ ሊያሳካው ከሚፈልገው ዓላማ፣ በሥሩ ስላጠቃለላቸው ዝርዝር ተግባራትና ከተፈጻሚነቱ ወሰን አንፃር ከሌሎች ሕጎች ማለትም ከፍትሐ ብሔር ሕግ፣ ከቤተሰብ ሕግ ወይም ከባህር ሕግ የተለየና ነፃ ነው፡፡ የንግድ ሕጉ ተፈጻሚ በሚደረግበት ጊዜም ከእነዚህ ህጎች ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ፣ ሕጉ ሊያሳካው ባሰበው መርህ ብቻ የሚመራ ነው፡፡ ንግድ ሕግ የንግድ እንቅስቃሴን፣ ኢንቨስትመንትን ብሎም የአገር ዕድገትን ለማምጣት የሚሠሩትን ነጋዴዎች ወይም ኢንቨስተሮችን ጉዳይ የሚዳኝ ስለሆነ፣ ሒደቱ ፍጥነትን ይጠይቃል፡፡ ለባለገንዘቦችም ፈጣን ጥበቃ ይሰጣል፡፡ በዚህም ምክንያት የንግድ እንቅስቃሴው ዋስትና የሚያገኝ ስለሆነ፣ ለነጋዴዎች ብሎም የአገር ኢኮኖሚ ዕድገት አስተማማኝነት ይኖረዋል፡፡ ሌሎች ሕጎች ግን ትኩረት የሚያደርጉት በግለሰቦች የግል ጥቅምና ዋስትና ላይ ነው፡፡ የሁለቱ የሕግ ክፍሎች የትኩረት አቅጣጫና የሚጠብቁት ጥቅም እንዲህ ከሆነ፣ የሁለቱ ሕግ ዓይነቶች አፈጻጸምና ነፃነትም የተለየ እንዲሆን ግድ ይላል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ የንግድ ጉዳዮችን የሚገዛው የንግድ ሕግ ራሱን ችሎ በነፃነት ሊተገበር ይገባዋል፡፡ ሲተረጎምም ከሕጉ ዓላማ አንፃር በራሱ መለኪያ እየተለካ መሆን ይኖርበታል፡፡ ከሌሎች የሲቪል ሕጎች ጋር ልዩነት ወይም ግጭት ቢኖር እንኳ ለንግድ ጉዳዮች የንግድ ሕጉ ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡ ከሌሎች የሲቪል ሕጎች ተለይቶ በነፃነት ተፈጻሚ የሚሆን የንግድ ሕግ በበርካታ አገሮች የሕግ ሥርዓት ውስጥ የተካተተ ነው፡፡ ይኽም ፈረንሣይን፣ ጀርመንን፣ ቤልጄምን፣ ኦስትሪያን፣ ስፔንን፣ ቱርክንና ግብፅን ያካትታል፡፡ እነዚህ አገሮች በተጻፈ ሕግ የሚመሩ የሮማኖ ጀርመኒካ ሕግ መሠረትን የሚከተሉ ናቸው፡፡ የንግድ ሕጎቻቸውንም ነፃ ሆነው ለንግድ ጉዳዮች ተፈጻሚ ይሆናሉ፡፡ የኢትዮጵያ የንግድ ሕግም በፈረንሣይ የሕግ ምሁራን የተረቀቀና የፈረንሣይ ሕግ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያለበት ስለሆነ፣ በዚሁ የሕግ ቤተሰብ ሥር የሚመደብ ነው፡፡ ይህ የንግድ ሕግ በኮድ መልክ የወጣው በ1952 ዓ.ም. ሲሆን፣ የ58 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ነው፡፡

በእርግጥ ይህ የንግድ ሕግ ከመውጣቱ በፊት በተናጥል የወጡ የንግድ ማኅበራትና የኪሳራ ሕጎች ከዚህ ዘመን በፊት መኖራቸው ይታወሳል፡፡ ይህ ሰፊና የተጠቃለለ የንግድ ሕግ ሥራ ላይ ከዋለ ረዥም ዓመት የሆነው ቢሆንም፣ በተግባር ምን ያህል ተፈጻሚ ነው? የሚለው አንድ ጥያቄ ነው፡፡ ሕጉ ከወጣበት ዘመን አንፃር ሲታይ ዘመናዊና ውስብስብ ሲሆን፣ ይህን ሕግ ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስችል ነባራዊ የኢኮኖሚ ሁኔታና አስተሳሰብ፣ ሕጉን ለመረዳት የሚችል የኢኮኖሚ ማኅበረሰብና የሕግ ባለሙያዎች በበቂ ሁኔታ አለመኖር ሕጉ በተግባር እንዳይፈተን ምክንያቶች ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን በአገሪቱ የተነቃቃ ኢኮኖሚ በመኖሩ፣ ስለንግድና ስለሕጉ የተሻለ ግንዛቤ በኅብረተሰቡ በመፈጠሩ፣ የሕጉ ተፈጻሚነት በየቀኑ እየጎለበተ ነው፡፡ የንግድ ሕጉ ራሱን ችሎ የወጣበት ምክንያትም በሕጉ መቅድም ላይ እንደሚከተለው ተገልጾ ይገኛል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹በዛሬ ጊዜ የምንገኝበት ዘመናዊ ዓለም ማንኛውም ሕዝብ ለንግዱ ሥራ አቋምና ዋስትና አስፈላጊ የሆኑት ነገሮች የሚረጋገጡበት ጽኑ የሕግ መሠረት ከሌለው ንግዱንና ኢኮኖሚውን የማስፋት ተስፋ ሊኖረው አይችልም፤›› ይላል፡፡ ሕጉ ራሱን ችሎ ሲደራጅ ሊያሳካው ያሰበው ዓላማ የንግድ ሥራን አቋም ዋስትና በመስጠት ንግድና ኢኮኖሚውን ለማስፋት ከሆነ ተፈጻሚ መሆን የሚገባውም ራሱን ችሎና ከሌሎች ሕጎች ተለይቶ ነው፡፡ የንግድ ሕግ ነፃነት ማለትም ይኸው ነው፡፡ የንግድ ሕጉ በንግድ ጉዳዮች ላይ ራሱን የቻለ ተፈጻሚነት ያለው ለመሆኑም ንግድ ሕጉን ባህሪ፣ ምንጩንና ይዘቱን በማየት መረዳት ይቻላል፡፡ እነዚህን ነጥቦች በአጭሩ ማየቱ ጠቃሚ ስለሆነ እንደሚከተለው ተቀምጠዋል፡፡

የንግድ ሕግ ባህሪ

የንግድ ሥራ በሰው ልጅ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ከሚያሳድሩ የኢኮኖሚ እንቅስቀሴዎች አንዱ ነው፡፡ የእንቅስቃሴው መጠን ይለያይ እንጂ የንግድ ሥራ በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ ይካሄዳል፡፡ ጦርነት ቢነሳ፣ አገር በችጋር ቢመታ ወይም ሌላ አስቸጋሪ ሁኔታ ቢፈጠር እንኳ የንግድ ሥራ መካሄዱ አይቀርም፡፡ ይህን በማንኛውም ጊዜና ቦታ የሚካሄድ አይቀሬ የንግድ ሥራ የሚገዛ ሕግ ደግሞ አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገሮች የንግድ ሕግ በማውጣት በሥራ ላይ ያዋሉት፡፡ የንግድ ሕግ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ግን አንድ ወጥ የሆነ አረዳድ የለም፡፡ ይሁን እንጂ የንግድ ሕግ የዕቃና አገልግሎት ግብይትን ወይም ንግድን መነሻ በማድረግ የሚነሱ መብትና ግዴታዎችን የሚገዛ የሕግ ክፍል እንደሆነ ብዙዎቹ ይስማማሉ፡፡ የንግድ ሕግ ስለሚሸፍናቸው ጉዳዮች ግን የተለያየ አረዳድ አለ፡፡ የሲቪል ሕግ ሥርዓት ተከታይ የሆኑ አገሮች በአብዛኛው ራሱን የቻለ የመደበኛው የፍትሐ ብሔር ሕግ የተለየ የንግድ ሕግ አላቸው፡፡ የኮመን ሎው ሕግ ሥርዓት ተከታዮች እንግሊዝን ጨምሮ ራሱን የቻለ የንግድ ሕግ የላቸውም፡፡ የንግድ ክርክሮች የሚታዩት በመደበኛው የፍትሐ ብሔር ሕግ መሠረት ነው፡፡ ይህ ማለት ግን በመደበኛው የፍትሐ ብሔር ሕጋቸው ውስጥ ነጋዴዎችን የሚመለከቱ የሕግ ክፍሎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ግን ከመደበኛው የፍትሐ ብሔር ሕግ የተለየ ራሱን የቻለ የንግድ ሕግ አላት፡፡ ከንግድ ግንኙነት የሚመነጩ መብትና ግዴታዎች ራሱን በቻለ ሕግ መገዛታቸው የራሱ ጠቀሜታ አለው፡፡ መደበኛው የፍትሐ ብሔር ሕግ የቆመበት ዋናው ነገር ለተዋዋዮች ግንኙነትና ለፈጸሙት ውል ዋስትና ለመስጠት ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ በሕጉ የሚቀመጠው መሥፈርት ጥብቅ ነው፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ የፍትሐ ብሔር ሕግ አንቀጽ 1723 መሠረት የማይንቀሳቀስ ንብረት ለመሸጥ፣ ለመለወጥ፣ ለማስተላለፍ ወይም በመያዣ ለመስጠት ውሉ በሚገባ አኳኋን በጽሑፍ መደረግና በውል አዋዋይ ፊት ወይም በፍርድ ቤት ፊት መደረግ እንደሚገባው ተደንግጓል፡፡ የንግድ ሥራ ግብይቶች በዚህ መልክ ይደረጉ ቢባል፣ የንግድ ሥራን መሥራት አይቻልም፡፡ በዚህም ምክንያት ይመስላል የዚህ ዓይነት ጥብቅ የግብይት ደንብ በንግድ ሕጋችን አልተካተተም፡፡ ስለዚህ ከንግድ ባህሪ ጋር የሚስማማውን ለብቻው ለመደንገግ ይቻል ዘንድ የንግድ ሕግ አስፈላጊ ነው፡፡ ሌላው ጠቀሜታ የንግድ ሥራ በባህሪው በየቀኑ የሚለወጥና የሚሻሻል ነው፡፡ ይህ ሁኔታ የሚመነጨውም የአገሮች ኢኮኖሚ እየተሻሻለና እየተለወጠ ስለሚመጣ ነው፡፡ የዓለም አገሮች ኢኮኖሚም በዘመነ ግሎባላይዜሽን እየተጠጋጋና እየተቀራረበ ይገኛል፡፡ የንግድ ሥራ ደግሞ የአንድ አገር የኢኮኖሚ ዕድገት የደም ሥር ነው፡፡ ይህን ያህል ጠቃሚ የሆነን የሥራ ዘርፍ ደግሞ ሊያሠራ የሚችልና ተለማጭ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ መዘርጋት ተገቢ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ንግድ ሕግ መቅድም ላይ እንደተገለጸውም የንግድ ሕጉ ዓላማ ንግድና ኢኮኖሚን ለማስፋፋት ለንግዱ ሥራ ብቻ በሚገባ የተዘጋጁ፣ ዋስትና የሚሰጡና ተለማጭ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ ለማቆም ነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ንግድ ሕግ ባህሪ የንግድ ሥራን መነሻ ያደረጉ ግብይቶች ቀለል ባለ ሥርዓት እንዲፈጸሙና በተጨማሪም ግብይቶቹ ዋስትና እንዲኖራቸው በማድረግ የአገሪቱን ንግድና ኢኮኖሚ ለማስፋፋት ያለመ ነው፡፡ 

የንግድ ሕግ ምንጭ

የንግድ ሕግ የጠቅላላው ሕግ አንድ አካል እንደመሆኑ መጠን የጠቅላላው ሕግ ምንጭ ለንግድ ሕጉም መነሻ ነው፡፡ በአብዛኛው የንግድ ግብይት የሚካሄደው ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች በሚያደርጉት ስምምነት መነሻነት ነው፡፡ ስለዚህ የንግድ ሕግ ዋናው ምንጭ ውል (ስምምነት) ነው፡፡ የውለታው ዓይነት በግልጽ ወይም በሁኔታ የተደረገ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜም ከባህል ወይም ከልማዳዊ አሠራር ሊመነጭ ይችላል፡፡ እነዚህን ነገሮች አካቶ ወይም ሳያካት የሚወጣ ብሔራዊ ሕግም የንግድ ሕግ ምንጭ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽኖች የንግድ ሕግ ምንጭ ይሆናሉ፡፡ አስገዳጅ የሆኑ የፍርድ ቤት ውሳኔዎችም እንደ ንግድ ሕግ ምንጭ ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡

የኢትዮጵያ የንግድ ሕግም ከሞላ ጎደል እነዚህን ምንጮች መነሻ ያደረገ ነው፡፡ በሕጉ መቅድም ላይ ንግድ ሕጉ የኢትዮጵያን የጥንት ሕጎችና ልማዶች ላይ የተመሠረተ ሆኖ የሌሎችን ታላላቅ የንግድ አገሮች ሕግ በመውሰድ እንደተረቀቀ ተጠቅሷል፡፡ የንግድ ሕጉ አምስት ዋና ዋና ክፍሎች (መጽሐፎች) ያሉት ሲሆን፣ የሁሉም ክፍሎች አርቃቂ አንድ ሰው አይደለም፡፡ ክፍል ሁለት፣ አራትና አምስት የተረቀቀው በታዋቂው የፓሪስ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ጂን ኢስካራ ሲሆን፣ ክፍል አንድና ሦስት የተረቀቁት ደግሞ እሳቸውን በተኩት ፕሮፌሰር አልፍሬድ ዦፍሬ ነው፡፡ በክፍል ሁለት ውስጥ የተካተተው የንግድ ማኅበሮችን የሚመለከት ሲሆን፣ ስለተራ ሽርክና ማኅበር የሚገልጸውን ክፍል ብቻ ያረቀቁት የፍትሐ ብሔር ሕጉ አርቃቂ ፕሮፌሰር ሬኒ ዳቪድ ናቸው፡፡ ሁሉንም ረቂቆች በመጨረሻ የመረመረውና ለአርቃቂ ኮሚሽኑ ሪፖርት ያቀረቡ ግን ፕሮፌሰር አልፍሬድ ዦፍሬ ናቸው፡፡ አርቃቂዎቹ የኢትዮጵያን ንግድ ሕግ ሲያረቁ በምንጭነት የኮመን ሎውና ሲቪል ሎው የሕግ ሥርዓት ተከታዮችን ሕጎች እንደ አግባብነቱ በመምረጥ እንደ ግብዓት መጠቀማቸውን ይናገራሉ፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ንግድ ሕግ ይዘት የሁለቱም የሕግ ሥርዓቶች ንክኪ ያለው ነው፡፡ በዋናነት የሕጉ ምንጭ የሆኑት ግን የፈረንሣይ፣ የጀርመንና የስዊዝ ሕጎች እንደሆኑ፣ የ1921 ዓ.ም. የዋርስ ኮንቬሽን፣ በ1923 እና 1924 ስለተስፋ ሰነድ፣ ስለቼክና ተላላፊ ሰነዶች የወጣው የጄኔቫ ኮንቬሽን፣ የ1940 ዓ.ም. የእንግሊዝ የንግድ ማኅበር ሕግ፣ በሰነድ ስለሚደረጉ ባንክ ክፍያዎች፣ እ.ኤ.አ. በ1953 ዓ.ም. የተደረገው የሊዝበን ውል በምንጭነት እንዳገለገሉ አርቃቂዎቹ ባቀረቧቸው መግለጫዎች አመላክተዋል፡፡ ከዚህ መረዳት የሚቻለውም የንግድ ሕጉ ምንጭ የሲቪል የሕግ ሥርዓት ከሚከተሉ አገሮች እንደሆነ ነው፡፡ የንግድ ሕጉን ዓላማና አደረጃጀት ሲታይም፣ ሕጉ የወጣው ራሱን ችሎ ለንግድና ነጋዴዎች ጉዳይ ተፈጻሚ በሚሆን መልኩ ነው፡፡ የአገሪቱን ሕገ መንግሥት እስካልተቃረነ ድረስም ከሌሎች ሲቪል ሕጎች ነፃ ሆኖ ተፈጻሚ መሆን የሚገባው ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች የንግድ ሕጉን ተፈጻሚ እያደረጉ ያሉት ነፃነቱን በጠበቀ መልኩ ነው ወይም የሚለው ግን የጊዜው አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች የንግድ ሕጉን ተፈጻሚ እያደረጉ ያሉት ልዩ ባህሪውንና ሊያሳካ ያሰበውን ዓላማና ነፃነቱን ግምት ውስጥ ባላስገባ መልኩ ነው፡፡ እንዲያውም ከሌሎች የሲቪል ሕጎች ያነሰ ደረጃ እየተሰጠው ይገኛል፡፡ በአገሪቱ የዳኝነት ሥርዓት ከፍተኛ ሥልጣን ያለው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በዚህ ረገድ እየሰጠው የሚገኘው የሕግ ትርጉም ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ለምሳሌ ፍርድ ቤቱ በመዝገብ ቁጥር 132129፣ 128760፣ 102652 እና 135326 የሰጣቸውን የሕግ ትርጉሞች ማየቱ በቂ ነው፡፡ በእነዚህ መዝገቦች  በንግድ ሕጉ የሚገዙ ኃላፊነታቸው የተወሰነ የግል ኩባንያዎች ማለትም ኢትዮ የአሽከርካሪዎችና መካኒኮች ማዕከል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ፣ ኒው ወርልድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ፣ ኖህ ኢንተርናሽናል ጠቅላላ ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ፣ ሸዋ ዳቦና ዱቄት ፋብሪካ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያና ኤስ.ኤ. ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ በየመዝገቦቻቸው የክርክሩ አካል ናቸው፡፡ ኃላፊነቱ የተወሰነ የንግድ ማኅበር በኢትዮጵያ ንግድ ሕግ ውስጥ ከተካተቱ የኩባንያ ዓይነቶች አንዱ ነው፡፡ ይህ ማኅበርም ራሱን የቻለ፣ መክሰስና መከሰስ የሚችል ሕጋዊ ሰውነት ያለው ሲሆን፣ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች በስምምነት የሚፈጥሩት ነው፡፡ ማኅበሩ የራሱ መመሥረቻና መተዳደሪያ ደንብ የሚኖረው ነው፡፡ የማኅበሩ ጉዳዮች የሚመሩትም በንግድ ሕጉና ማኅበርተኞች ባወጡት መመሥረቻና መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ነው፡፡

ከላይ እንዳየነው የንግድ ሕጉ ራሱን ችሎ የተደራጀው ንግድ ጉዳዮችን በተለይ ለማስተዳደርና ለመዳኘት ነው፡፡ በዚህ ጊዜም ከሌሎች የሲቪል ሕጎች ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ ተግባራዊ መደረግ አለበት፡፡ የሕጉ የራሱ ዓላማ በመግቢያው ላይ ሲቀመጥም ይህን በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ ሕጉ በዝርዝር ሲታይም በንግድ ጉዳዮች ላይ ከሌሎች ሕጎች በቀዳሚነትና በብልጫ ተፈጻሚነት እንዳለው መረዳት ይችላል፡፡ ለምሳሌ ያገቡ ሰዎች ልክ እንዳላገቡ ሰዎች ሆነው የንግድ ሥራቸውን መሥራት ይችላሉ በማለት ንግድ ሕጉ ይደነግጋል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ግን ከላይ በተጠቀሱት መዝገቦች ንግድ ሕጉን የቤተሰብ ሕጉ የበታች አድርጎ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት የንግድ ማኅበራት ቅርበት ባላቸው የቤተሰብ አባላት  የተመሠረቱ ስለሆነ በማለት፣ የንግድ ማኅበራቱ አባላት መብትና ጥቅም በቤተሰብ ሕግ እንዲታይ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ የንግድ ማኅበራት የሚቋቋሙት በመመሥረቻና መተዳደሪያ ደንብ ሆኖ በንግድ ሕግ መሠረት ነው፡፡ ማኅበራቱን የመሠረቱት አባላት ባልና ሚስት፣ ወላጆችና ልጆች ወይም ዝምድና የሌላቸው ሰዎች መሆናቸው የሕጉን የተፈጻሚነት ወሰን አይቀንሰውም፡፡ የንግድ ሕጉም ቢሆን ኩባንያ ቤተሰባዊ ግንኙነት ባላቸው ሰዎች መካከል ከተመሠረተ ተፈጻሚ የሚሆነው የቤተሰብ ሕግ ነው የሚል ድንጋጌ የለውም፡፡ ከላይ በተጠቀሱት ንግድ ማኅበራት መመሥረቻና መተዳደሪያ ደንብ ላይም አባላቱ ለመገዛት የተስማሙት በደንባቸውና በንግድ ሕጉ መሠረት ለመሆኑ አረጋግጠው በውል አዋዋይ ፊት ፈርመዋል፡፡ ጉዳዩ የንግድ ማኅበር አባልነትንና ጥቅምን የሚመለከት እስከሆነ ድረስም ሊታይ የሚገባው በንግድ ሕጉ ነው፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ግን በመዝገብ ቁጥር 34945 የንግድ ማኅበር በቤተሰብ የተመሠረተ ቢሆንም፣ ራሱን የቻለ የሕግ ሰውነት ያለው ስለሆነ እንደ ሌሎቹ በጋብቻ እንደተፈሩ ንብረቶች በዓይነት ሊካፈል የሚችል አይደለም፡፡ ጉዳዩ በንግድ ሕጉ መሠረት የሚታይ ነው በማለት አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ከሰጠ በኋላ በመ/ቁ. 132129፣ 128760፣ 102652፣ 135326 ግን ያለበቂ ምክንያት ከዚህ ትርጉሙ ሸሽቷል ወይም አፈግፍጓል፡፡ ፍርድ ቤቱ አስቀድሞ የሰጠውን ትርጉም በሰባት ዳኞች አልቀየረውም፡፡ የሕግ ትርጉሙን ሳይቀይር በእነዚህ ውሳኔዎች የንግድ ማኅበርተኝነት ፈቃድን መሠረት ያደረገ ሆኖ እያለ፣ ከመሥራች ማኅበሩ አባላት ፈቃድ ውጭ አዲስ ማኅበርተኞች ወደ ማኅበሩ እንዲገቡ ተደርጓል፣ ራሳቸውን የቻሉ ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው የንግድ ማኅበራት ጉዳይ በባልና ሚስት የክርክር መዝገብ በቤተሰብ ሕግና ችሎት እንዲታይ ተደርጓል፣ በባልና ሚስት የክርክር መዝገብ በንግድ መዝገብ የገባው የማኅበር ካፒታል እንዲቀነስ ተደርጓል፡፡ የማኅበራቱ ቀጣይ ህልውና በባልና ሚስት የክርክር መዝገብ በቤተሰብ ሕግና ችሎት እንዲታይ ወስኗል፡፡ እነዚህ ውሳኔዎች በዝርዝር ሲታዩ ውጤታቸው የሕገ መንግሥት ጥሰት ያለባቸውና የአገሪቱን ኩባንያዎች ህልውና አደጋ ላይ የጣሉ ናቸው፡፡

የንግድ ሕግ የሚወጣው በሕግ አውጪ ፓርላማ ነው፡፡ የንግድ ማኅበራት ዓይነቶች፣ አመሠራረታቸው፣ የአባልነትና የአክሲዮን ዝውውር አፈጻጸም፣ ካፒታል የሚቀነስበትና የሚያድግበት ሥርዓት፣ ማኅበራቱ የሚፈርሱበት ሥርዓትና ሌሎችም ጉዳዮች በዝርዝር የተደነገጉትም በዚሁ ሕግ ነው፡፡ ሕጉ ይህን ያህል ግልጽ ሆኖ እያለ ፍርድ ቤቱ ግን በውሳኔው አዲስ አባላትን ወደ ማኅበር ያስገባል፣ የአክሲዮን ድልድል ያደርጋል፣ የካፒታል ቅነሳ ያደርጋል፣ የንግድ ማኅበር ህልውና በባልና ሚስት የፍች ክርክር መዝገብ እንዲታይ ይወስናል፡፡ ይህ ሒደትም ሕግ አውጪው የንግድ ጉዳዮች በንግድ ሕግ መሠረት ይታያሉ ብሎ የወሰነው የሚጥስና ፍርድ ቤቱ የሕግ አውጪነት ሚና የወሰደበት ነው፡፡ የንግድ ማኅበራት አመሠራረት፣ የአባልነት መብትና ጥቅም፣ ህልውና የሚመራው በንግድ ሕግ መሆኑን ሕግ አውጪው ደንግጎ እያለ፣ ፍርድ ቤቱ በተጋቢዎች የፍች መዝገብ በቤተሰብ ሕግ መሠረትም ሊታይ ይችላል ብሎ መወሰኑ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 50 የተመለከተውን የሥልጣን ክፍፍል የሚጥስና በአገሪቱ እየሠሩ ያሉ ኩባንያዎች ለከፋ ችግር የሚጥል ነው፡፡

የንግድ ማኅበር የሚመሠረተውም ሆነ ማሻሻያ የሚያደርገው የንግድ ሕጉን ተከትሎ በማኅበርተኞች ስምምነት ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች ማኅበር እንዲመሠረትም ሆነ የአክሲዮን ድልድል በማኅበርተኞች መካከል እንዲደረግ፣ የንግድ ማኅበርን ካፒታል ለመቀነስ ወይም ለመጨመር የሕግ ሥልጣን የላቸውም፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 37 መሠረት ፍርድ ቤቶች በዳኝነት ማየትና መወሰን የሚችሉት በፍርድ ሊታይ የሚገባውን ነገር ብቻ ነው፡፡ በመሠረቱ በቤተሰብ ወይም በባልና ሚስት በተቋቋመ የንግድ ማኅበር ላይ መብት ያለው ቤተሰብ ወይም ተጋቢ ያለው መብት መከበር አለበት፡፡ መብቱ ሲከበር ግን የንግድ ሕጉ ተጥሶ ሳይሆን፣ የንግድ ሕጉን ተከትሎ መሆን ይገባዋል፡፡ የንግድ ሕጉን የቤተሰብ ሕጉ የበታች ሕግ አድርገን ከወሰድነውና ከተረጎምነው ግን የዕድገትና የልማት መሣሪያ የሆኑትን የንግድ ኩባንያዎች አደጋ ላይ የሚጥል ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ የንግድ ኩባንያዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ ቤተሰብን መሠረት አድርገው የተቋቋሙ ኃላፊነታቸው የተወሰነ የግል ማኅበራት ሲሆኑ፣ በማኅበርተኞች መካከል ወይም በማኅበርተኛውና ሌላ ሦስተኛ ወገን መካከል አለመግባባት ሲፈጠር፣ ጉዳዩ በቤተሰብ ሕግና በቤተሰብ ችሎት የሚታይ ከሆነ፣ የማኅበራቱ ህልውና አደጋ ላይ ይወድቃሉ፡፡ በአለመግባባት በፈረሰ የትዳር ውጤት ክርክር ውስጥ የሚጠቃለል የንግድ ማኅበራት የህልውና ጥያቄም ተስፋ የለውም፡፡ በአብዛኛው ትዳራቸውን ያፈረሱ ተጋቢዎች ለንግድ ማኅበሩ ህልውና የሚጨነቁበት አመክንዮ የለም፡፡ ስለዚህ የንግድ ማኅበራት ህልውና ጉዳይ በቤተሰብ ሕግና በቤተሰብ ችሎት ይታይ ማለት ማኅበራቱን ከማፍረስ አይተናነስም፡፡

የዕድገትና የልማት መሣሪያ የሆኑት የንግድ ማኅበራት ሲፈርሱ ደግሞ በርካታ ሠራተኞች ይበተናሉ፡፡ በዚህም ሥራ አጥነት ይበራካታል፡፡ በኩባንያዎቹ ላይ ጥቅም ያላቸው ባንኮች፣ የታክስ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶችና ሌሎች ሦስተኛ ወገኖች መብት በእጅጉ ይጎዳል፡፡ ከሁሉም በላይ በተሳሳተ የሕግ ትርጉም ኩባንያዎች ሲፈርሱና ሲበተኑ፣ አገሪቱ ልታሳካው ያሰበችው ዕድገትና ልማትም ፈተና ላይ ይወድቃል፡፡  በአጠቃላይ በአሁኑ ጊዜ ንግድ ሕጉ የተፈጻሚነት ወሰን ፈተና ላይ ወድቋል፡፡ የንግድ ሕጉ ተፈጻሚነትም ከዓላማው ውጭ ሌሎች የሲቪል ሕጎች የበታች ሕግ ተደርጎ እየታየና እየተተረጎመ ነው፡፡ ይህ ትርጉም ደግሞ የአገሪቱን ሕገ መንግሥት የሚቃረን፣ የዕድገትና የልማት መሣሪያ የሆኑትን የንግድ ኩባንያዎች ህልውና በእጅጉ የሚፈታተን ስለሆነ፣ ንግድ ሕጉ ነፃነት ሊጠበቅ ይገባል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ሆነ ሌሎች የዳኝነት አካላት ንግድ ሕጉ ለአገሪቱ ዕድገትና ልማት ያለውን ከፍተኛ ሚና ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ለንግድ ጉዳዮች በተለይ ለኩባንያዎች ያለውን የተፈጻሚነት ነፃነት ወደፊት በሚሰጧቸው ውሳኔዎች እንደሚጠብቁት ተስፋ አለኝ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...