Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  እኔ የምለዉ‹‹ሁለተኛው የጫጉላ ሽርሽር›› የመጀመርያውን ጥፋት እንዳይደግመው የሉዓላዊ ባህር በር መብታችን ጉዳይ

  ‹‹ሁለተኛው የጫጉላ ሽርሽር›› የመጀመርያውን ጥፋት እንዳይደግመው የሉዓላዊ ባህር በር መብታችን ጉዳይ

  ቀን:

  በአበበ ተክለ ሃይማኖት (ሜጄር ጄኔራል)

  የመጀመርያው ‹‹የጫጉላ ሽር ሽር›› (Honeymoon) ከ1983 እስከ 1990 ዓ.ም. የነበረውና ወደ ጦርነት ያመራው ነው፡፡ ኤርትራዊያን ነፃነታቸውን በትግል አረጋግጠዋል፡፡ ዕውቅና መስጠት የመርህና የቁርጠኝነት ውሳኔ ነበር፡፡ ኤርትራ በሌሎች አገሮችና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕውቅና እንድታገኝ ኢትዮጵያ ቀድማ ዕውቅናም በመስጠት ሚናዋ የላቀ ነበር፡፡ ‹‹የጫጉላ ሽርሽር››  እዚህ ይጀመራል (ቀደም ሲል በሻዕቢያና በኢሕአዴግ በተለይም ከሕወሓት ጋር አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ወደ ግጭት የሚያመራ የሚመስል ግንኙነት ነበር)፡፡ በቀዳሚዎቹ የነፃነት ዓመታት ኢትዮጵያና ኤርትራ የነበራቸው ግንኙነት ለሌሎቹም በምሳሌነት ሲደነቅ የነበረ ነው፡፡ ምንም እንኳን በርካታ ኢትዮጵያውያን ግንኙነቱ ለኤርትራ ጥቅም ያደላ ነው የሚል ቅሬታ ቢኖራቸውም፡፡ ከ1988 ዓ.ም. እስከ 1989 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ ኢትዮጵያ በአገሮቹ መካከል የነበረውን ልቅና ቁጥጥር አልባ ግንኙነት ማጥበቅ ስትጀምር የነበረው ግንኙነት ብዙ ሊዘልቅ አልቻለም፡፡ በኤርትራ መንግሥት በኩል በነበረው የኢትዮጵያን ሀብት የመዝረፍ ፍላጎትና ሲመካበት የነበረው ወታደራዊ አይበገሬነት (Military Invincibility) በመመሥረት በግንቦት 1998 ዓ.ም.  ኢትዮጵያን ወረረ፡፡

  ኤርትራ ኢትዮጵያን የወረረችው በድንበር ጉዳይ አልነበረም፡፡ የሁለቱ አገሮች የድንበር ኮሚሽነሮች የድንበር መካለሉ እንዴት ይሁን? ብለው ለውይይት አዲስ አበባ ተቀምጠው እያሉ ነበር የኤርትራ ታንኮች ሉዓላዊ መሬታችንን የወረሩት፡፡ እንደተለመደው በተዛባ ግምግማ የኢትዮጵያ መንግሥት ፍትሐዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዝምድና እንዲፈጠር የማስተካከያ ዕርምጃ እንዳይወስድ ለማስፈራራትና ብሎም ለማንበርከክ ነበር፡፡ ለኤርትራ ሕዝብ ጭምር ያልረባው ሻዕቢያ ለቡድናዊ ጥቅሙ ሲል በድንበር ስም ኢትዮጵያን ወሮ የሁለቱን ሕዝቦች አንድነት አደፈረሰው፡፡ ኢትዮጵያም ኤርትራ ወታደሮቿን እንድታስወጣ በመጠየቅ ነገሮች ወደነበሩበት እንዲመለሱ ጠየቀች፡፡ ‹‹ከባድመ መውጣት ማለት ፀሐይ ጠልቃ ትቀራለች ማለት ነው፤›› በሚል ትዕቢት አሻፈረኝ አለች፡፡ ከዚያም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የናዚ ኃይል ግብፅን ለቆ ከወጣ በኋላ በአፍሪካ ምድር እንደተደረገው የሁለት ዓመት ጦርነት፣ በ2000 .ም. ኢትዮጵያ የኤርትራን ሠራዊት በከፍተኛ ደረጃ በመደምሰስ ሁሉንም የተያዙ አካባቢዎች ነፃ አወጣች፡፡ በኋላም ኤርትራ በአልጀርስ ስምምነት መሠረት በራሷ ይዞታ ነፃ ቀጣና እንዲቋቋምና የተኩስ አቁም ስምምነትን ሳትወድ በግድ ለመቀበል ተገደደች፡፡ ‹‹ቀድሞ ነበረ እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ›› እየተባለ ወደ ባሰ የከበባ ሥነ ልቦና (Siege Mentality) ውስጥ ተዘፈቀ፡፡

  በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ማንም ያሸንፍ ማን ሁለቱም ሕዝቦች ተጠቃሚ አልነበሩም፡፡ ሊሆኑም አይችሉም፡፡ በኢትዮጵያ ተፈጥሮ የነበረው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መነቃቃት ለጊዜውም ቢሆን ተቀዛቅዞ ነበር፡፡ በአሥር ሺዎች የሚጠጋ የኢትዮጵውያን ወጣቶች ሕይወት መቀጠፍ፣ የተፈናቀለው ሕዝብ፣ የወደመው ንብረት ግዙፍ ነው፡፡ መመለስ የማይቻል ነው፡፡ ለአገር ሉዓላዊነት ሲባል የጠፋ ቢሆንም፡፡

  ከኤርትራ መንግሥት ባህሪ ተነስቶ የኢትዮጵያ መንግሥት መዘጋጀት ነበረበት፡፡ ‹‹የጫጉላ ሽርሽር››  ሊያሞኘው አይገባም ነበር፡፡ ምናልባትም በዓለም ላይ ምንም ዓይነት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በሌላት ብቸኛ አገር በጣም ጨቋኝ ሥርዓት የኤርትራ ሕዝቦችን እያተራመሰና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያቃወሰና እየደቆሰ፣ ብቸኛ አማራጭ ይመስል ወደ ስደት እያመሩ አገሪቷ ከመንገዳገድ አልፋ ለመሆኑ እንደ አገር ትቀጥላለች? ወይስ አትቀጥልም? ወደሚል ደረጃ የሚያደርስ መንግሥትን ተማምኖ ንዝህላልነት ማሳየት አይገባም ነበር፡

  ግጭት የማስወገድ ተፈጥሯዊ ባህሪውን ያጣ ስምምነት መረጋጋትና መቋጫ ሊያመጣ አይችልም፡፡ መረጋጋት ሊመጣ የሚችለው ሊፈጸም የሚችልበት ሁኔታ ሲኖር ነው፡፡ ተፈጻሚነቱ ደግሞ የቀረበውን ስምምነት ለመፈጸም አቅሙና ተነሳሽነቱ ያላቸው ተዋናዮች መኖርን በቅድሚያ ይፈልጋል፡፡ አሁን ያለው የኤርትራ መንግሥት በሌሎች ሀብት ለመኖር የሚፈልግ መዥገር ነው፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ልማት እንዳትጎናፀፍ ከሚፈልጉ ኃይሎች ጎን በመሠለፍ ተመፅዋች ሆኖ የተላላኪ ሥራ የሚሠራም ነው፡፡ በገልፍ ቀወስ (Gulf Crisis) አሠላለፉ እንዴት እንደተገለበጠ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ሰላም የማይፈልግ በሁከት ንግድ የተሰማራ ተላላኪ መንግሥት ራሱ በድርጊቱ የሻረውን የአልጀርስ ስምምነት ተግባራዊ በማድረግ ሰላም ይመጣል ብሎ ማስብ ቂልነት ነው።  የባህር በር መብትን አስረክቦ፣ ባድመና ኢሮብን ሰጥቶ ሰላም እናገኛለን ማለት ሞኝነት ነው፡፡ በቂ ጥናትና ዝግጅት የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው፡፡

  ‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ራስ ምታት›› ተበሎ የሚጠራው የባህር በር አልባነት አባዜ (Syndrome) በየጊዜው በውስጥ ፖለቲካዊ ትኩሳት አንዴ ሲደፈጠጥ ሌላ ጊዜ መቃወሚያ ሲሆን ኖሯል፡፡ አሁን የአልጀርስ ስምምነት ተግባራዊ ከሆነ መብታችንን እስከ ወዲያኛው የማጣት ሁኔታ ለፈጠር ይችላል፡፡ የውስጥ ፖለቲካዊ ሥልጣን ከዘላቂ የኢትዮጵያ ጥቅም የሚፃረር በሚያስመስል ሁኔታ ሁሉም መንግሥታት በአንዴ ወይም በሌላ መብታችንን የራሳቸውን ሥልጣን ለማደላደል ሲገፈትሩት ኖረዋል፡፡ ኤርትራ ነፃ አገር ስትሆን የባህር በር በማጣታችን ኢትዮጵያ አንገቷ ተቆርጧል ብለው ሲጮሁ የነበሩት አንዳንድ ምሁራን፣ በወቅቱ ፖለቲካዊ ትኩሳት ታውረው እርግፍ አድርገው ትተውታል፡፡ ትግራይን እስካዳከመ ድረስ (በአልጀርስ ስምምነት ወደ ኤርትራ የተካለሉት የኢትዮጵያ መሬቶች በአብዛኛው ትግራይ ነው የሚገኙት) የባህር በር ጉዳይን ትተውታል፡፡  የትግራይ መዳከም የኢትዮጵያ መዳከም እንደሆነ በሚያሳፍር ሁኔታ የዘነጉት ይመስላል፡፡ ‹‹መደመር›› ይሉሃል ይኼ ነው፡፡  የባህር በር ቀማጣት ጉዳይ የኢትዮጵያ የህልውና እንዳልሆነ እርግፍ አድርገው ትተውታል፡፡  በፖለቲከኞችና በምሁራን ጊዚያዊ ፖለቲካዊ ትኩሳት  የምትነዳ አገር ዘላቂ መብትንና ጥቅሟን ልታጣ ትችላለች፡፡ ከታሪክ ተጠያቂነት እጃችንን እናውጣ፡፡

  አገራችን በጀመረችው አቃፊ ፖለቲካ፣ ፍቅር፣ ይቅርታና መደመር መሠረት የሚደረግ የህዳሴ ጉዞ እደግ ተመንደግ መባል ያለበት ነው፡፡ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ የአገራችንን ህልውና አደጋ ውስጥ ሊከት የሚቺለውን የባህር በር ዕጦት በቸልተኝነት ዘላቂ ማድረግ የህዳሴ ጉዞውን ማደናቀፍ ነው፡፡ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ያለው ‹‹ሁለተኛው የጫጉላ ሽር ሽር›› ሳያዘናጋን ኳታር የባህር በር ባይኖራት ምን ትሆን ነበር? ብለን ዴሞክራሲን እንደ ጠላት የሚፈርጀው፣ ቀይ ባህርን ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠር ፍለጎት ያለው፣ የኢትዮጵያ ትልቅነት እንደ ሥጋት የሚመለከት ፔትሮ ዶላር ያሰከረውና በወታደራዊ አቅሙ ተማምኖ የመንን የወረረ የቅንጅት ኃይል ባለበት የመካከለኛው ምሥራቅ ተዝረክረከን መቆየት ይቅርታ የማይሰጠው ነው፡፡

  የኢትዮጵያ ሉዓላዊ የባህር በር መብት

  በዚህ ጽሑፍ ከዓለም ሕግ አኳያ ኢትዮጵያ ሉዓላዊ የባህር በር መብት እንዳላትና የአልጀርስ ስምምነት የአገራችን መብትና ጥቅም የሚያሳጣ መሆኑን፣ ስምምነቱን ለመሻር ሕጋዊ መበት እንዳለን የሁለተኛ ዲግሪ መመረቂያ ጽሑፍ (1999) መሠረት በማድረግ አቀርባለሁ፡፡ የተያያዝነውን የለውጥ ሒደት ለማስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው ለማድረግ ሉዓላዊ የባህር በር መብት ወሳኝ መሆኑን በማመን፡፡ ኢትዮጵያና ፈረንሣይ እንደ እ.ኤ.አ. በ1897 ባደረጉት ስምምንነት በጂቡቲ በኩል ሊኖረን የሚችለውን የባህር በር ጥያቄ በይፋ አሳልፈን ሰጥተናል፡፡ በተለያዩ የውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ ምክንያት በኤርትራ በኩል ባሉት ወደቦች እንደፈለግነው ባንጠቀምባቸውም፣ ኢትዮጵያ ሉዓላዊ የባህር በር መብት እንደሚገባት ደምቆ የሚነገርላት ነበረች፡፡ በቅኝ ገዥዋ ጣሊያንና በኢትዮጵያ መካከል እንደ እ.ኤ.አ. በ1900፣ በ1902 እና በ1908 የተደረጉ ስምምነቶች ግን አትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ ያውም በጦርነት አሸንፋ ሉዓላዊ የባህር በር መብቷን አሳልፋ ሰጥታለች፡፡ ኤርትራ በፌዴሬሽን ወደ ኢትዮጵያ ከተቀላቀለች በኋላ እንደገና ሉዓላዊ የባህር በር መብት ማረጋገጥ ችለን ነበር፡፡ ከ40 ዓመታት ባለመብትነት በኋላ ኤርትራ ነፃነቷን ስትጎናፀፍ አገራችን እንደገና ያላግባብ ወደብ የለሽ ሆነች፡፡ በጦርነት አሸንፈን መብታችንን አሳልፍን መስጠት ባህላችን እስኪመስል ድረስ፣ የኤርትራን ወረራ ከቀለበስን በኋላ  የአገራችን መብትና ጥቅም የሚያሳጣውን የአልጀርስ ስምምነት ተዋዋልን፡፡ አገራችን እስከ ወዲያኛው የባህር በር በምታጣበት ጫፍ ላይ ትገኛለች፡፡ ለኢትዮጵያ ህልውና የባህር በር የማግኘት ጉዳይ መፍትሔ የሚሻ ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ጉዳዩም በሥልጣን ላይ ካለው መንግሥት ባሻገር ሊታይ ይገባዋል፡፡ ለኤርትራ ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትና ነፃነትም ዕውቅና እሰጣለሁ፡፡ ነገር ግን  የኤርትራ ነፃነትና የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ሉዓላዊ መብት አንዱ ሌላውን የሚተካ (Exclusive) እንዳልሆነ አምናለሁ፡፡

  1900፣ የ1902 እና የ1908 ዓ.ም. ስምምነቶችች ጣሊያን የጣስቻቸው ኢትዮጵያ በሕግ የሻረቻቸው ናቸው፡፡ የአልጀርስ ስምምነት የተሻሩትን በ1900፣ በ1902 እና በ1908 ዓ.ም.  የተደረጉ ስምምነቶችን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ በእነዚህ ስምምነቶች መሠረት በኢትዮጵያ በኩል ይቀርብ የነበረው ተደጋጋሚ የድንበር ማካለል ጥሪ በጣሊያን በኩል ሰሚ አላገኘም፡፡ ይልቁንም በተለያዩ አካባቢዎች ጦሯን ታደራጅ ነበር፡፡ ጣሊያን ስምምነቶችን በቀና መንፈስ ለመፈጸም ዝግጁ አልነበረችም፡፡ በዚህም መሠረት በ1928 ዓ.ም. ኢትዮጵያን ስትወር የነበራት ድብቅ ዓላማ ተጋለጠ፡፡ ኢትዮጵያን መውረር ብቻ ሳይሆን የጣሊያን ምሥራቅ አፍሪካን ቅኝ ግዛትን ለመመሥረት በነበራት ዕቅድ የሶማሊያ፣ የኤርትራና የኢትዮጵያ ድንበሮችን ደባልቃ አምስት ግዛቶች ያሉት የጣሊያን የምሥራቅ አፍሪካ ቅኝ ግዛት ተመሠረተ፡፡ በዚህ አረመኔያዊ ውሳኔ ጣሊያን ኢትዮጵያን እንደ አገር የማጥፋትና ስሟንም ከታሪክ ማኅደር እንዲፋቅ ፈልጋ ነበር፡፡ በአምስቱ ዓመታት  የጣሊያን ወረራ ዘመን እነዚያን የ1900 ውሎች የሚያስፈጽም አንዱ ወገን (ኢትዮጵያ) ህልውና እንዳይኖረው ተደርጓል፡፡ የቪየና ድንጋጌ የስምምነቶች ሕግ በአንቀጽ 60 በሁለትዮሽ ስምምነት ውስጥ በአንዱ አካል የሚፈጸም የሕግ ማፍረስን የተመለከቱ ጉዳዮች፣ በሌላኛው አካል ስምምነቱን ለማቋረጥ ወይም ተፈጻሚነቱን በከፊልም ሆነ በሙሉ ለማቆም መብት ይሰጣል ይላል፡፡ በሌላ አነጋገር አንዱ ወገን ስምምነት በመጣሱ ምክንያት ተግባራዊነቱ እንዲቆም ወይም እንዲቋረጥ ሲደረግ፣ የስምምነቱን ዋነኛ ጥሰት ስለሚያሳይ ሌላው ወገን ሊሽረው (Null and Void) ይችላል ማለት ነው፡፡ የሁሉም ስምምነቶች መሠረት የሆነው የ1900 ዓ.ም. ውል አንቀፅ ሁለት፣ ‹‹የጣሊያን መንግሥት ቀጥሎ በተዘረዘሩት አካባቢዎች ለየትኛውም ሌላ ኃይል ላለመሸጥ፣ ላለመስጠት ራሱን ያስገዛል፤›› ይላል፡፡ በዚህ መሠረትም ጣሊያን በሁለተኛ ዓለም ጦርነት ስትሸነፍ ግዛቶቿን ለኢትዮጵያ ማስረከብ ነበረባት፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግሥት ኤርትራ በፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር ስትቀላቀል (የኤርትራና ኢትዮጵያ ፌዴሬሽን አይደለም) ጣሊያን ያፈረሰቻቸው ስምምነቶች እንደማይሠሩ በማወጅ ውድቅ አድርጓል፡፡ በወቅቱ ተረቆ በታወጀው የኤርትራ ሕገ መንግሥት መሠረት የ1900፣ የ1902 እና 1908 ዓ.ም. የኢትዮጵያና የጣሊያን ስምምነቶች ውድቅና የማይሠሩ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡ እነዚህ የ1900ዎቹሎች እ.ኤ.አ. በ1947 የፓሪሱ የሰላም ጉባዔና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ ሐሳብ መሠረት የማይሠሩ ሆነዋል፡፡ አንድኛው ወገን ውል ሲጥስ ሌላኛው ተዋዋይ ውድቅ የማድረግ መብት እንዳለው በሚመለከት የሙኒክ ስምምነትና የሪጋ ውል በመባል የሚታወቁት ዓለም አቀፍ ውሎች ህያው ምስክሮች ናቸው፡፡ የሙኒክ ስምምነት ታላቋ ብሪታንያ፣ ጀርመን፣ ፈረንሣይና ጣሊያን ከቀድሞዋ ቼኮዝሎቫኪያ የሱድትንላንድ ግዛቷን ወደ ጀርመን መቀላቀል በተመለከተ መስከረም 29 ቀን 1938 ዓ.ም.  በጀርመኗ ሙኒክ ከተማ ያደረጉት ስምምነት ነው፡፡ ስምምነቱ ቼኮዝላቫኪያን ከጀርመን ወረራ ለመታደግ ለተፈጠረው አዲስ ወሰን ዓለም አቀፍ ዕውቅና (ማረጋገጫ) በመስጠት የሁለተኛው የዓለም ጦርነትን ለማስቀረት የተደረገ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ጀርመን ቼኮዝሎቫኪያን በመውረር አገሪቱን በሙሉ ያዘች፡፡ ጀርመን ሆን ብላ ስምምነቶችን በመጣሷ የፈረንሣይና የታላቋ ብሪታንያ መንግሥታት የሙኒክ ስምምነት የማይሠራና ውድቅ መሆናቸውን አውጀል፡፡ ከዚያ ስምምነት ጋር የተያያዘ የትኛውም ተግባር የሚያስከትለው ውጤት (ለውጥ) በሙሉ ውድቅ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም የአገሪቱ ድንበር ከመስከረም 1938 ዓ.ም. በፊት በነበረው የቼኮዝላቫኪያ ሪፐብሊክ ወሰን እንደሚሆን አረጋግጠዋል፡፡

  1921 የሪጋ ስምምነት ሶቪየት ኅብረት ከጥቅምት አብዮትና ከፖላንድ ጦርነት በኋላ ተዳክማ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነበረች፡፡ ወታደራዊ ኃይሏንም ከድንበር አካባቢ የመለሰች በመሆኑ፣ በአወዛጋቢ የድንበር አካባቢዎች የግዛት ማካካሻ ለመስጠት ከፖላንድ ጋር በ1921 የሪጋ ስምምነት ተፈራርመች፡፡ መስከረም 28 ቀን 1939 ዓ.ም.  ሶቪየት ኅብረት የሪጋ ስምምነትን በተናጠል በመጣስ ከጀርመን ጋር ፖላንድን ለመቀራመት ተስማሙ፡፡ ሰኔ 22 ቀን 1941 ዓ.ም. የጀርመን ወታደራዊ ኃይል ሶቪየት ኅብረትን ወረረ፡፡ ሰኔ 30 ቀን 1941 ዓ.ም. ደግሞ ሶቪየትና ፖላንድ ጀርመንን ለመውጋት ሲስማሙ የ1921 ዓ.ም. ሪጋ ስምምነትም ታደሰ፡፡ ሆኖም ከጥር 11 ቀን  1944 ዓ.ም. በኋላ ሶቪየት ኅብረት ከአሜሪካና ከእንግሊዝ ጋር ገብታው የነበረው ውል እንደገና ታድሶ የነበረው የሪጋ ስምምነት በፖላንድ ጭምር ውድቅ እንዲሆን ተደርጎ ተጠናቋል፡፡ ሶቪየቶች ይጠይቁት የነበረው የኩርዘን መስመር የፖላንድና የሶቪየት ድንበር እንዲሆን እንግሊዞች ባቀረቡት ምክረ ሐሳብ የሪጋ ስምምነትን ሻሩት፡፡ ኢትዮጵያ በ1928 ዓ.ም.  በጣሊያን ወረራ ሲፈጸምባትና ስትያዝ የ1900ዎቹ ስምምነቶች ውድቅ የማድረግ መብትን በሚገባ የሚገልጹ ሲሆን፣ የሁለተኛው የዓለም ጦርነትን ለማስቀረት እንዲሁም ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የወሰን መብቶችን ለድርድር ስለማቅረብ፣ እንዲሁም ከጦርነቱ በኋላ በወሰን አከላለል ሥራዎች ውስጥ ወታደራዊ ኃይል ያለውን ሚናና ለፖሊሲ ዓላማዎች እንደ ሁኔታዎች የታዩት መለሳለሶች ከላይ ካነሳናቸው ተግባራት ትምህርት የሚወሰድባቸው ናቸው፡፡

  የ1900ዎቹ ውሎች ውድቅ ከሆኑ ኤርትራ ነፃ ስትወጣ ደንበሩ በየትኛው ዓለማዊ ሕግ ይገዛል?

  የካቲት 10 ቀን 1947 ዓ.ም. ከጣሊያን ጋር የተደረሰው የሰላም ውል ስምምነት ጣሊያን በአፍሪካ ያሏትን ግዛቶች ማለትም ሊቢያ፣ ኤርትራና የጣሊያን ሱማሌላንድ ሙሉ መብትና ባለቤትነት እንድትለቅ የሚያደርገው ይገኝበታል፡፡ ኢትዮጵያ ከአምስት ዓመት ትግል ነፃነቷን በማረጋገጧ ጣሊያን በግዛቶቿ ላይ የነበሯትን መብቶችና ኃላፊነቶች በሰላም ስምምነቱ አንቀጽ 23 መሠረት ስትተው፣ በኢትዮጵያና በጣሊያን መካከል በነበረው ውል ማብቂያ ሆኗል፡፡

  በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚመለከተው ሌላ አዲስ ሕጋዊ ማዕቀፍ ተመሠረተ፡፡ አቃፊው ሕግ ‹‹በተባበሩት መንግሥታትና በኢትዮጵያ መካከል የተደረገ ስምምነት›› ሆነ፡፡ በግልጽ ለማስቀመጥም በ1952 ዓ.ም. ኤርትራን በፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ያዋሀደው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት አሸናፊ ኃያላን መንግሥታትና የኢትዮጵያ ስምምነት ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ምክረ ሐሳቦች ከራሱ ከመንግሥታቱ ድርጅት ውጪ አስገዳጅ ሕጋዊ ውጤት ያላቸው አይደሉም፡፡ ይሁን እንጂ ጣሊያን በቅኝ ግዛቶቿ ላይ ያላትን መብት የወረሱት አሸናፊዎቹ ኃያላን መንግሥታት ለጠቅላላ ጉባዔ ስለወከሉትና ሐሳቡን በመቀበል ስለተገበሩት ነው፡፡ በመሆኑም በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ ኤርትራ 390ኤ መሠረት ኤርትራ ራስ ገዝ ሆና በኢትዮጵያ ዘውድ ሥር በፌዴሬሽን እንድትቀላቀል የተደረገባቸው የፌደሬሽኑ መሠረታዊ መርሆዎችና እምነቶች ናቸው አቃፊው ሕግ የሚሆኑት፡፡

  የውሳኔ የፍላጎት መንፈስ (Intent) ለመረዳት የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ መስከረም 24 ቀን 1948 ዓ.ም. ባካሄደው 143ኛው ስብሰባ፣ የቀረቡ አስተያየቶች በዋናነት ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር ማቀላቀል ላይ ያተኮሩትን ማየት ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን በትክክል የትኞቹ ግዛቶች እንደሚካተቱ ሰፊ አለመግባባት ነበር፡፡ የኤርትራ ምሥራቃዊ ክፍል ከኢትዮጵያ ጋር መቀላቀል አለበት፣ ቀሪው የምዕራቡ ክፍል ሌላ መፍትሔ ይፈለግለታል፡፡ (ታላቋ ብሪታንያና አሜሪካ)፣  ሁሉም የኤርትራ ክፍል በፍጥነት ወደ ኢትዮጵያ መተላለፍ አለበት (ላይቤሪያና ኢትዮጵያ)፣  በባለ አደራ ምክር ቤት በሚሾም አስተዳደር በተባበሩት መንግሥታት ባለአደራነት ሥር ሆኖ በአማካሪ ኮሚቴ ድጋፍ ይደረግ፡፡ ኢትዮጵያ በአሰብ በኩል የባህር በር እንድታገኝ የግዛት ማካካሻ ይደረግላት (ሶቪየት ኅብረት፣ ዩጎዝላቪያ፣ ቼኮዝላቫኪያ፣ ፖላንድ፣ ቤይሎሩስያንና ዩክሬን)፣ የስሜን ኤርትራ ክፍል በጋራ (በኅብረት) ባለአደራ አስተዳደር ሥር ሆኖ ጣሊያን ባለአደራ አስተዳደር ትሁን፡፡ የደቡብ የአገሪቱ ክፍል ወደ ኢትዮጵያ ይጠቃለል (አርጀንቲና ቱርክ)፣ የባህር በር የማግኘት ጉዳይ እንዳለ ሆኖ ዘርንና ሃይማኖትን መሠረት በማድረግ የተወሰነው የኤርትራ ክፍል ወደ ኢትዮጵያ መጠቃለል አለበት፡፡ ቀሪው የአገሪቱ ክፍል ጣሊያን አስተዳዳሪ ሆና በተባበሩት መንግሥታት ባለአደራነት ሥር መሆን አለበት (ቤልጂየም፣ ቺሊ፣ ኮሎምቢያ፣ ኮስታሪካ፣ ዶሚኒካን ሪፐብሊክ፣ ኢኳዶር፣ ኤልሳቫዶር፣ ጓቲማላ፣ ሆንዱራስ፣ ፓናማ፣ ፓራጓይ፣ ፔሩ፣ የደቡብ አፍሪካ ኅብረትና ቬንዙዌላ)፡፡

        የጣሊያን ግዛቶችን በተመለከተ ኃላፊነት የወሰዱት ኃያላን መንግሥታት በተጠቀሱት ግዛቶች መለቀቅ ዙሪያ ድርድር የማድረግና መፍትሔ የማምጣት ኃላፊነት ነበር የወሰዱት፡፡ ነገር ግን በማስለቀቁ ጉዳይ ላይ መስማማት አልቻሉም፡፡

  ታላቋ ብሪታንያ

  ኢትዮጵያ ለአሥር ዓመታት ያህል ኤርትራን ለማስተዳደር መመደብ አለባት፡፡ ከአሥር ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ አስተዳደር በምን ሁኔታ ለዘለቄታው መቀጠል እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ይወስናል፡፡  የኢትዮጵያን አስተዳደር የሚደግፍ የአማካሪዎች ምክር ቤት ይመደባል፡፡ ምክር ቤቱ ኤርትራውያንን፣ የአራቱ ኃያላን ወኪሎችን፣ እንዲሁም ከጣሊያን፣ ከስውዘርላንድ፣ አንድ የስካንድኔቪያን አገርና አንድ የሙስሊም አገርን ያካተተ ይሆናል፡፡

  ፈረንሣይ

  ከዙላ ባህረ ሰላጤ እስከ ፈረንሣይ ሱማሌላንድ ካለው ግዛት ውጪ ያለው የኤርትራ ክልል በጣሊያን ሞግዚትነት መያዝ አለበት፡፡ ከዙላ ባህረ ሰላጤ እስከ ፈረንሣይ ሱማሌላንድ ያሉት ግዛቶች ከሙሉ ሉዓላዊነት ጋር ለኢትዮጵያ መሰጠት አለበት፡፡ ለኢትዮጵያ በተሰጡት ግዛቶችና በጣሊያን ሞግዚትነት ሥር ባሉት ግዛቶች መካከል ያለው ድንበር የአካለ ጉዛይ ምሥራቃዊ አስተዳደራዊ ወሰንን ተከትሎ ከዙላ ባህረ ሰላጤ እስካሁኑ የኢትዮጵያ ድንበር ያለውን የያዘ መሆን አለበት፡፡ ከኢትዮጵያና ከጣሊያን ወገን በኩል በሚወከሉ ሰዎች አማካይነት ወሰን የማካለል ሥራው ከመስከረም 15 ቀን 1949 ዓ.ም. በፊት መጠናቀቅ አለበት፡፡

  አሜሪካ

  የደቡባዊ ኤርትራ ክፍል ወደ ኢትዮጵያ እንዲጠቃለል ሐሳብ ታቀርባለች፡፡ ይህ አካባቢ የደናክል ዳርቻ የአካለጉዛይና ሰራዬ ግዛቶችን በማካተት፣ አዲሱ ድንበር ከዙላ ባህረ ሰላጤ የአካለጉዛይና ሰራዬ ሰሜናዊ ድንበርን ተከትሎ እስከ ኢትዮጵያ ድንበር ያለውን ይይዛል፡፡

  ጣሊያንም ብትሆን ይኼንን መብት ዕውቅና መስጠት ነበረባት፡፡ የመጀመርያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባዔ በለንደን ከመደረጉ አስቀድሞ የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለአሜሪካ አቻቸው ተከታዩን መልዕክት ጽፈው ነበር፡፡ ‹‹በሶማሌላንድ ሞግዚትነት (የባለአደራ ሥርዓት) ላይ የሚመከር እንኳ ቢሆን የረዥም ጊዜ ቅኝ ግዛታችን በሆነችው ኤርትራ የጣሊያን ሉዓላዊነት መጠበቅ ተገቢ ነው፡፡ ይህ የኢትዮጵያን የባህር በር የማግኘት ጥያቄ የሚያካክስ ነው፡፡ ለዚያ ብለንም ከደሴ ወደ አሰብ የሚወስድ መንገድ ገንብተናል፡፡ ይህ መብት ሊረጋገጥ የሚችለው በጣሊያን ግዛት ውስጥ ወይም ጥያቄው ከቀረበ ደግሞ በድንበር ማካለል (Rectifications) ነው፡፡

  በኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ የተባበሩት መንግሥታት ውሳኔ 390v መግቢያ እንደሚከተለው ይላል፡፡ ከዚህ የሚከተለውን ከግምት በማስገባት፣

  በኤርትራ የተለያዩ ብሔረሰቦች፣ የሃይማኖትና ፖለቲካ ቡድኖች አስተያየትና የሕዝቡ ራስን የማስተዳደር አቅምን ጨምሮ የኤርትራ ነዋሪዎች ፍላጎትና ደኅንነትየምሥራቅ አፍሪካ ሰላምና ፀጥታ ሁኔታዎችከመልክዓ ምድር፣ ከታሪክ፣ ከብሔረሰቦችና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች በመነሳት በተለይም የኢትዮጵያን ሕጋዊ የባህር በር የማግኘት ጥያቄና መብቶች፣ የውጭ ኃይሎች ለኤርትራ ኢኮኖሚ ልማት የሚኖራቸውን ቀጣይነት ያለው ትብብር የማረጋገጥ ጠቀሜታን ከግምት በማስገባት፣  የኤርትራ መለቀቅ ከኢትዮጵያ ጋር ቅርበት ያለው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚ ውህደትን መሠረት ማድረግ እንዳለበት ዕውቅና በመስጠትየዚህ የውህደት ስምምነት ፍላጎት ለኤርትራ ነዋሪዎች፣ ተቋማት፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋዎችና ልማዶች ሙሉ ክብርና ጥበቃን ለማረጋገጥ ብሎም ስፋት ያለው ራስን የማስተዳደርና በተመሳሳይ የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥት፣ ተቋማት፣ ልማድና ዓለም አቀፍ ዕውቅናና ተቀባይነት በማክበር ነው ይላል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ በኤርትራ ኮሚሽን ሪፖርት ላይ የጠቅላላ ጉባዔው ጊዜያዊ ኮሚቴ ሪፖርት መሠረት 390-A(V)  የውሳኔ ሐሳብን አሳለፈ፡፡ በዚህ ውሳኔም ኤርትራ ራስ ገዝ ሆና ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን እንድትቀላቀልና በኢትዮጵያ ዘውድ ሉዓላዊነት ሥር እንድትሆን ውሳኔ አሳለፈ፡፡

   የውሳኔ ሐሳቡ (390v) በአጠቃላይ ዓለም አቀፍ ሕግን ተከትሎና በተለይ ደግሞ የቪየና የውሎች ሕግ ድንጋጌን መሠረት ተደርጎ ሊተረጎም ይገባዋል፡፡ የቪየና ድንጋጌ የውሎች ሕግ አንቀጽ 31(1) እንደሚያትተው ‹‹አንድ ውል በመልካም ጎኑ መተርጎም ይኖርበታል፡፡ የውሉ ቃላት በመደበኛ የዓውድ ይዘታቸው፣ እንዲሁም ጭብጥና ፍሬ ነገር መሠረት በማድረግ ሊታይ ይገባል፤›› በአንቀጽ 31(1) የሠፈሩት መሠረታዊ መርሆች የቀናነት መርህ፣ መደበኛ ትርጉም፣ ዓውድ፣ ጭብጥና ፍሬ ነገር ናቸው፡፡

  ከላይ የተጠቀሱት ምሳሌዎች በቪየና ድንጋጌ የውሎች ሕግ አንቀጽ 31 መሠረት የኤርትራን ሁኔታ በተመለከተ በአራቱ ኃያላንና ኢትዮጵያ መካከል የተደረሰው ውል ዋና ዓላማና ተግባር፣ የኢትዮጵያን ሰላም ማስጠበቅና የባህር በር ባለቤትነት መብቷን ያረጋግጣሉ፡፡ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን እስከ ተቀላቀለችበት ጊዜ ድረስም በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኋላም ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩት አክሊሉ ሀብተ ወልድ የሚመራ የኢትዮጵያ ልዑክ ኤርትራን ለማስመለስ ካልተቸለም የአገሪቱን የባህር በር መብት ለማረጋገጥ ታግሏል፡፡ የአዲሱ ስምምነት ተዋዋዮች ማለት ኢትዮጵያና የአሸናፊዎቹ  ኃያላን መንግሥታት ኤርትራን ወደ ኢትዮጵያ በፌዴሬሽን ሲቀላቀሉ አንዱ ታሳቢ የተደረገው የኢትዮጵያ ሉዓላዊ የባህር በር የማግኝት መብት ነው፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ ከኤርትራ ጋር የሚድረግ ማናቸውም ድንበር ማዕከል የሚያደርግ ድርድር፣ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ የባህር በር የማግኝት መብት ማዕከል ያደረገና በድንበር አከባቢ የሚኖሩት የሁለቱ አገር ሕዝቦች ፍትሐዊ ውሳኔ የሚያገኙበት ሊያሠራ የሚያስችል ዓለማዊ ሕግ (Applicable International Law) መሠረት መሆን ይገባዋል፡፡

  የአልጀርስ ስምምነትን ለመሰረዝ ሕጋዊ መብት አለን 

  ይህ ስምምነት ወራሪና ተወራሪን አሸናፊና ተሸናፊን እኩል የሚያደርግ መሆኑ አሳፋሪ ቢሆንም፣ የአገራችንን መብት አሳልፎ የሰጠ በመሆኑ ዘላቂ ሰላም ሊያረጋግጥ አይችልም፡፡ በኢትዮጵያ አጠቃላይ ደኅንነት  በተለይም የኢኮኖሚ ደኅንነትን አደጋ ውስጥ የሚያስገባ  ነው፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክና ክብር የማይመጥን ስምምነት ነው። የኤርትራ መንግሥት ጦርነትን ጫረ፣ ተሸነፈም፡፡ የኤርትራ መንግሥት ባደረሰው ጥፋትና ጦርነቱን በመጀመሩ ተጠያቂ መሆን ነበረበት፡፡ ወራሪ በመሆኑም ሠራዊቱ ለመውረር በማያስችለው ደረጃ መገደብ ነበረበት፡፡ ከዚያ በላይ ለስምምነቱ መነሻ ሐሳብ ሲቀርብ ማዕከሉ የሉዓላዊ ባህር በር ጉዳይ መሆን ነበረበት፡፡ ካልተቀበለ ቅጣቱ ከፍተኛ ይሆን ስለነበር የኤርትራ መንግሥት ከመቀበል ውጪ ሌላ አማረጭ አልነበረውም ፡፡

  የአልጀርስ ስምምነት ሕጋዊ ውል ነው ወይ?

  የፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ አዋጅ ቁጥር 225/1993 ‹‹በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክና በኤርትራ መንግሥት መካከል የተደረገው የሰላም ስምምነት ለማፅደቅ የወጣ አዋጅ›› የሚል ሲሆን፣ የታወጀበት ወቅት ኅዳር 29 ቀን 1993 ዓ.ም. (8/Dec/2000) ነው፡፡ የአልጀርስ ስምምነት የተፈረመው ግን ታኅሳስ 3 ቀን 1993 ዓ.ም.  (12/Dec/2000) ከአራት ቀናት በኋላ ነው፡፡ እንደሚታወቀው የአልጀርስ ስምምነት እስኪቋጭ ድረስ ድርድር ነበረበት፡፡ የሕገ መንግሥታችን አንቀጽ 55 (12) ‹‹የሕግ አስፈጻሚው አካል የሚዋዋላቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ያፀድቃል፤›› ይላል፡፡ ይህ ሕገ መንግሥታችንን ይፃረራል፡፡ ከሕገ ፍልስፍናም (Jurisprudence) አኳያም ሕግ አውጪው ሥልጣኑን አሳልፎ መስጠት የተከፋፈለ መንግሥትን መርህ ይፃረራል፡፡ ተዋዋዮች ሁሉ ስምምነቱን በየአገራቸው ባሉት ሥርዓቶች መሠረት መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ሕጋዊነቱ ላይ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ውሉ ሕጋዊ ቢሆን እንኳን ገና ከመጀመርያው የኤርትራ መንግሥት ማፍረስ በመጀመሩ ኢትዮጵያ ለመሰረዝ (Null and Void) ለማድረግ ሕጋዊ መሠረት አላት፡፡ የአልጀርስ ስምምነት አንኳር በአንቀጽ I (1 እና 2) ናቸው፡፡ ዋና ዓላማው በሁለቱ አገሮች ስላም ማስፈን ነው፡፡ የድንበርና የካካ ወዘተ. ጉዳዮች የመጨረሻ ግባቸው ስላም ማረጋገጥ ነው፡፡ 

  Article I

  1. The parties shall permanently terminate military hostilities between themselves. Each party shall refrain from the threat or use of force against the other.
  2. The parties shall respect and fully implement the provisions of the agreement on cessation of hostilities.

  በንኡስ አንቀጽ ሁለት የተጠቀሰው ጠላትነትን ለማቋረጥ (Cessation of Hostilities)፣ የ25 ኪሎ ሜትር ጊዜያዊ የደኅንነት ቀጣና (Temporary Security Zone)፣  የጦርነት አደጋ ለመቀነስ (Buffer Zone) ተመሥርቶ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም አስከባሪ ኃይል ይጠብቀዋል ይላል፡፡ የኤርትራ መንግሥት ከተወሰኑ ወራት በኋላ የስላም እስከባሪ ኃይሉን በማባረር ጊዜያዊ የደኅንነት ቀጣናውን አፍርሶ ወታደሮቹን አሰፈረ፡፡

  ንዑስ አንቀጽ አንድን በመፃረር የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያን ለማተራመስ በማሰብና በመንቀሳቀስ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ሥጋት ሆነኗል፡፡ በኤርትራ ውስጥ ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎችን በማሰበሰብ፣ በማሠልጠን፣ በማስታጠቅና በማሰማራት ቀጣይነት ያለው ትንኮሳ እየፈጸመ ይገኛል፡፡ በሶማሊያ በኩል የውክልና ጦርነት (Proxy War) በተደጋጋሚ በመክፈት ኢትዮጵያን የማተራመስ ዕቀዱን እስከ ቅርብ ጊዜ ያካሂድ ነበር፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮች በየጊዜው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያሰሙዋቸው የነበሩ ስሞታዎች፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርቶችና እነሱን መሠረት አድርጎ የተጣሉ ማዕቀቦች በቂ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ አንድ ምሳሌ ብንወስድ በፀጥታው ምክር ቤት የውሳኔ ሐሳብ 1676 (2006) መሠረት የቀረበው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሶማሊያ ተቆጣጣሪ ቡድን ሪፖርት እንደሚከተለው ይላል፡፡

  ‹‹ጅቡቲ፣ ግብፅ፣ ኤርትራ፣ ሊቢያና የተወሰኑ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረትን የተለያዩ የፀረ ታንክ፣ ፀረ አውሮፕላንና ሌሎችም መሣሪያዎች በማስታጠቅ እንዲሁም በሎጂስቲክስ (ቁሳቁስ) ድጋፍና ማማከር እያገዙ ናቸው፡፡ የቡድኑን ድጋፍ በማስተባበርና ማስተላለፍ ዋነኛ ድልድይ ሆና እያገለገለች ያለችውም ኤርትራ ነች፡፡ ከላይ በዝርዝር እንደተገለጸው አንዱ ተዋዋይ ወገን ውሉን ካፈረሰ ሌላኛው ወገን የመሠረዝ መብት ስላለው፣ ኢትዮጵያ ስምምነቱን በማፍረስ ሕጋዊ መብት ሰርዣለሁ ብላ ማወጅ አለባት፡፡

  ማጠቃለያ

  ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የምሥራቅ አፍሪካ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኅብረት አስተሳሰብዎ የሚደነቅ ነው፡፡ ይህ ግን በረዥም ጊዜ የሚፈጸም ሥራ ነው፡፡ ከአሁኑ መጀመር ቢኖርበትም ብዙ ውጣ ውረድ አለበት፡፡ የአካባቢያችንን ሀብትና ወታደራዊ አቅም እያፈረጠሙ ያሉት አገሮች ብዙ መሰናክል ይፈጥራሉ፡፡ አብዛኛው በአካባቢያችን ያሉ አገሮች  በእነሱ ተፅዕኖ ሥር የወደቁ ናቸው፡፡ በራሳቸው የሚወስኑ አይደሉም፡፡ የኢትዮጵያ የባህር በር ጉዳይ ከኤርትራ ብቻ ሳይሆን ከጂኦ ፖለቲካ አንፃር መታየት አለበት፡፡

  የአልጀርስ ስምምነት ኢትዮጵያን ከድል መንጋጋ ሽንፈት እንድትወስድ አድርጓል፡፡ ያረጁ የወደቁና የተተኩ የ1900ዎቹ ውሎች በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የድንበር ጉዳይ መደራደሪያ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ አቃፊው ሕግ ‹‹በተባበሩት መንግሥታትና በኢትዮጵያ መካከል የተደረገ ስምምነት›› ነው፡፡ በግልጽ ለማስቀመጥም በ1952 ዓ.ም.  ኤርትራን በፌደሬሽን ከኢትዮጵያ ያዋሀደው ‹‹የሁለተኛው የዓለም ጦርነት አሸናፊ ኃያላን መንግሥታትና የኢትዮጵያ ስምምነት›› ነው፡፡ የአልጀርስ ስምምነት ሕጋዊ ውል አይደለም፡፡ ኤርትራም በተደጋጋሚ የጣሰችው በመሆኑ ኢትዮጵያ የመሰረዝ መብት አላት፡፡ በርካታ ምሁራን የኢትዮጵያን ሉዓላዊ የባህር በር መብት በሚመለከት በጥናታቸው አረጋግጠዋል፡፡  ለጊዜውም ቢሆን ሉዓላዊ የባህር በር የማግኘት መብቷንና ሌሎች የውስጥ ግዛቶቿን አጥታለች፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ ከኤርትራ ጋር የሚደረግ  ማናቸውም ድንበርን ማዕከል የሚያደርግ ድርድር የኢትዮጵያን ሉዓላዊ የባህር በር የማግኝት መብት ማዕከል ያደረገ፣ በድንበር አካባቢ የሚኖሩ የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች ፍትሐዊ ውሳኔ የሚያገኙበት ሊያሠራ የሚያስችል ዓለማዊ ሕግ (Applicable International Law) መሠረት መሆን ይገባዋል፡፡ ለጊዜያዊ ፖለቲካ የአገራችንን ዘላቂ መብትና ጥቅም አናጥፋው፡፡ የአልጀርስ ስምምነት ለማሽቀንጠር ጊዜው አሁን ነውና!

  ከአዘጋጁ፡– ጸሐፊው የቀድሞ የኢሕአዴግ ታጋይና የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ የነበሩ ሲሆን፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...