Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉዘላቂ ጥቅም እንጂ ዘላቂ ጠላት የለም

ዘላቂ ጥቅም እንጂ ዘላቂ ጠላት የለም

ቀን:

በሰለሞን መለሰ ታምራት

ሰውዬው ሞኝ ቢጤ ነበር አሉ፡፡ ሚስቱ የመጀመርያ ልጃቸውን ስታረግዝ ወደ ወላጆቹ ይሄድና የሆዷ እየገፋ መምጣት እንዳሳሰበውና ግራ መጋባቱን ይነግራቸዋል፡፡ ወላጆቹም፣ ‹‹አይዞህ አታስብ ሽል ከሆነ ይገፋል፣ ካልሆነም ይጠፋል፤›› ብለው አፅናንተው መለሱት ይባላል፡፡ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ከሦስት ወራት በፊት ስንመለከተው እንደ ሞኙ ባል ግራ የሚያጋባ ሁኔታ ላይ ነበረ፡፡ እርግጥ ነው ሽል ሆኖ እንዲገፋም፣ ሌላ ሆኖ እንዲጠፋም በየቦታው ያሉ ኢትዮጵያውያን በየግላቸው ሲመኙም ቆይተዋል፡፡ አሁን ግን ወደ አንደኛው ወገን ምኞት እያጋደላ የመጣ ይመስላል፡፡ በእኔ በኩል ሽል ሆኖ ሲገፋ ይታየኛል፡፡

      የኢሕአዴግን ሁለት ታላላቅ ውሳኔዎች አስመልክቼ ባለፈው ሳምንት ባቀረብኩት ኮምጨጭ ያለ አስተያየት (የማልጋፈጠው እውነት መሆኑ አስገድዶኝ እንጂ ባልቀበለው የምወደው ሐሳብ ነበር)፣ የአገራችን የመገናኛ ብዙኃን በተለይ ሬዲዮና ቴሌቪዥኖቹ በቂ ጊዜ አልሰጡትም ብዬ ወቀሳ አቅርቤ ነበር፡፡ ውሎ ሲያድርና ኅብረተሰቡም በራሱ መንገድ ጉዳዩን እየገፋበት ሲመጣ፣ አሁንም በቂ ነው ብዬ ባላስብም የተሻለ የአየር ሽፋን እያገኘ መምጣቱን ታዝቤአለሁ፡፡ ከእነዚህም ውይይቶች ቀደም ሲል ያልተደመጡ ጎላ ጎላ ያሉ አስተያየቶችን ለማዳመጥ በመቻሌ፣ ዛሬ በድጋሚ ከእዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ሳልወጣ ጥቂት በበኩሌ መጥራት አለባቸው ያልኳቸውን ሐሳቦች ለማካፈል ዳግም ልዳስሰው አስቤአለሁ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

      ሁለቱም የግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. የኢሕአዴግ ውሳኔዎች በየራሳቸው ብዙ ብዙ የሚያወያዩ፣ የሚያነታርኩና ራሳቸውን ችለው የአገሪቷን መፃኢ ዕድል ሊወስኑ የሚችሉ ትልልቅ ውሳኔዎች መሆናቸውን እየተረዳን የመጣነው ውሎ አድሮ ይመስለኛል፡፡ ሁሉም በቅርብ ይመለከተኛል የሚለውን ጉዳይ ብቻ እያነሳ ሲጥል ሌላኛውን ውሳኔ የሌለ ያህል እየረሳው መሆኑን ታዝቤአለሁ፡፡ በበኩሌ ሁለቱም ውሳኔዎች በተለያየ ጊዜ ተላልፈው ቢሆን ጥሩ እንደ ነበርና በጥልቀትና በጥንቃቄ እንድንወያይበት ዕድል አግኝተን ቢሆን መልካም ነበር ማለቴ አልቀረም፡፡ ግን አንዴ ውሳኔዎቹ በመተላለፋቸውና ለሕዝብ ውይይትም በመቅረባቸው የፈሰሰ አይታፈስምና እያነታረኩን ይገኛሉ፡፡

      እንግዲህ ሁለቱንም በየተራ መመልከት ይገባል ባልኩት መሠረት ከአልጀርሱ የሰላም ስምምነት ልጀምር፡፡ በእዚህ የኢሕአዴግ ውሳኔ ላይ የሚቀርቡት በርካታዎቹ ተቃውሞዎች ምንጫቸው ከትግራይ ክልል የሚነሱ ከመሆናቸውም በላይ (ቀደም ብዬ ሁሉም ይመለከተኛል የሚለው ውሳኔ ላይ ትኩረት እንደሰጠ ገልጫለሁ፡፡ እናም ትክክለኛ የዴሞክራሲ መገለጫ ነው)፣ ሁሉም የሉዓላዊነትን መገሰስ በመሠረታዊነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የሚቀርቡ ናቸው፡፡ ከሰማኋቸው የመከራከሪያ ነጥቦች መካከልም፣ አንድን ሕዝብ በመነጠል ኢትዮጵያዊነትን የሚገፍፍ ነው፡፡ ቀድሞውንም ለጦርነቱ መነሻነት ድንበር እንደ ምክንያት ቀረበ እንጂ ባድመን ስለሰጠነው ከሻዕቢያ ሰላምን አናገኝም፡፡ የሔጉ ውሳኔ ፍትሐዊ ስላልሆነ ልንቀበለው አይገባም፡፡ ስህተትን በሌላ ስህተት ማረም አይቻልም (ቀድሞ የኢትዮጵያ መንግሥት የአልጀርሱን ስምምነት የተቀበለበት መንገድ የተሳሳተ መሆኑን ዋቢ በማድረግ) የሚሉት ይገኙበታል፡፡ እስቲ አንድ በአንድ እንመልከታቸው፡፡

ኢትዮጵያውያንን ከመሬታቸው (ከአገራቸው) የሚነጥል ውሳኔ ነው

      ከሰማኋቸው የመከራከሪያ ሐሳቦች ሁሉ ስሜት የሚሰጠውና የሔጉን የፍርድ ውሳኔ ለመቀበል ከባድ የሚያደርገው ያለፈቃዳቸው ቀዬአቸውን ለቀው የሚሰደዱ ሰዎችን ማየት ይመስለኛል፡፡ ማንኛውም ሰብዓዊ ፍጥረት ያለውዴታው ከቦታው ላይ በማንኛውም ምክንያት ሲፈናቀል የማየትን ያህል ከባድ ነገር የለም፡፡ የዓለማችን የመገናኛ ብዙኃን በየዕለቱ የሚያሳዩን ዜናም ዋነኛው ትኩረት፣ እነዚህኑ በስደትም ይሁን በጦርነት የሚፈናቀሉ የተለያዩ አገር ዜጎችን ነው፡፡  ሁላችንም ማስተዋል ያለብን ጉዳይ ግን፣ የድንበር ማካለሉ በማንኛውም ሁኔታ ቢከናወን የሚፈናቀሉ ዜጎች በኤርትራም ሆነ በኢትዮጵያ ወገን ሊኖሩ እንደማይችሉ ነው፡፡ የኢሮብም ሆነ ሌላ በድንበር ማካለሉ የሚነካ ሕዝብ ካለ የሚፈጠረው ከባዱ ችግር ዜግነትን መቀየር ነው፡፡ ባሉበት ቦታ ሆነው አዲስ የሚያገኙትን ዜግነት (እሱንም ያለማንም አስገዳጅነት) ይቀበላሉ እንጂ፣ የኤርትራም ሆነ የኢትዮጵያ መንግሥታት እነዚህን ነዋሪዎች ከቦታቸው ሊያፈናቅሏቸው የሚችሉበት ምንም ዓይነት የሕግ አግባብ የለም፡፡ ለነገሩ በየትኛውም የአፍሪካ ግዛት ብንመለከት ድንበር ያላገዳቸውን ጎሳዎች አለማግኘት ከባድ ነው፡፡ ሲጀመርም በአፍሪካ ተመሳሳይ ቋንቋና ባህል ያላቸውን ነገዶች ሁለትና ከዚያም በላይ በሆኑ አገሮች ተበታትነው ማየት የተለመደ ነው፡፡

      በኢትዮጵያም የሔጉ ውሳኔ ተግባር ላይ ቢውል ይከሰታል የተባለው የሕዝቦች መለያየትን፣ አንዳንዶች እንደሚገልጹት የቤተሰብና አልፎ ተርፎም የአንድ ጎጆን ለሁለት የመክፈል ክስተትን ማስወገድ ካስፈለገ፣ በአጠቃላይ ውሳኔውን መቃወም ሳይሆን የሚያስፈልገው፣ አሁን እንደተደረገው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተቀብሎ በሒደት ግን አፈጻጸሙ የሚለወጥበት አካሄድ ካለ መነጋገር ነበር፡፡ ምክንያቱም ይህ ውሳኔ የኢትዮጵያን መሬት ለኤርትራ የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን፣ ከኤርትራም ወደ ኢትዮጵያ ግዛት የሚያካልልባቸው ቦታዎች ስለሚኖሩ በዚያም ወገን ተመሳሳይ ሥጋት ሊኖር ይችላል ነው፡፡ ከመንግሥታት ይልቅ በጉዳዩ ቀጥታ ተጠቂ ናቸው የሚባሉት የኅብረተሰብ ክፍሎች ግልጽና ነፃ በሆነ ሕዝበ ውሳኔ እንዲመልሱትም መነጋገር ይቻላል፡፡

      እነዚህ የመፍትሔ ሐሳቦች የሁለቱንም አገር መንግሥታት ሊያስማሙ የማይችሉ ከሆኑና እስከነ አካቴውም በድንበሩ ጉዳይ ላይ ተቀምጠው ለመነጋገር ፈቃደኛ ባይሆኑ ግን (እንደሚባለው በኤርትራ መሪ ግትር አቋም ምክንያት)፣ ያለው አንድና ብቸኛ አማራጭ ውሳኔውን ተቀብሎ ቤተሰብንም ሆነ ትምህርት ቤት፣ ወይንም ጎጆ ቤትን ቆርሶ በሰላም መለያየት ይመስለኛል፡፡ የኢሮብና የሌሎች ኢትዮጵያውያን ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል ከተባለም፣ እያንዳንዱ ግለሰብ የግሉና ለግሉ በሚያደርገው ውሳኔ ላይ ተመሥርቶ የሚወሰን ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያዊ መሆን የሚፈልግ ካለ በኢትዮጵያ መንግሥት ሙሉ ፈቃድ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ገብቶ እንዲኖር ይደረጋል፡፡ የመኖሪያ ቦታዬን አለቅም የሚል ካለም አዲሱ ዜግነቱን ተቀብሎ ወደ ኤርትራ ይጠቃለል፡፡ በኤርትራም በኩል የሚኖሩት ሕዝቦችም ዕጣ ፈንታ በእዚህ መሠረት ውሳኔ ያገኛል ማለት ነው፡፡

      በእዚህ አጋጣሚ ማንም ሰው ቢሆን ይቀበለዋል ብዬ የምገምተው ቀላል ጉዳይ፣ የትኛውም በዓለም ላይ የተደረሰ የፍርድ ውሳኔ ሁለቱንም ተቃራኒ ወገኖች አስደስቶም ይሁን አስማምቶ አያውቅም፡፡ ቀድሞ ነገር ከሳሽና ተከሳሽ ለመስማማት ፈቃድ ቢኖራቸው እኮ ወደ ፍርድ ቤት መሄድም አያስፈልጋቸውም ነበር፡፡

ለጦርነቱ መነሻነት ድንበር እንደ ምክንያት ቀረበ እንጂ ባድመን ስለሰጠን ሰላም አናገኝም

      ሁለት ግምታዊ አስተሳሰቦች የተካተቱበት ምክንያት ስለሆነ ለመመለስ እጅግ በጣም አስቸጋሪ በመሆኑ፣ እንደ ጥያቄው ሁሉ መልሱ በመላምት ይሁን ከተባለ ባድመን ከሰጡ በኋላ የሚሆነውን ማየት ነው የሚለው በቂ ይሆናል፡፡ ለማንኛውም ውሳኔውን ከተቀበልን በኋላ የሚነሳ የኢኮኖሚም ይሁን የፖለቲካ ጥያቄ ካለም ‹እሰየው› ብሎ በእኛም በኩል መደራደሪያዎቻችንን ማቅረብ ይቻላል፡፡

      እንዲያው ለመሆኑ የትኛው ኢትዮጵያዊ ባድመን ይጠላል? አይደለም ባድመ አሰብ፣ ጂቡቲና በርበራ የኢትዮጵያ አካል ቢሆኑ ሁላችንንም ሊያስደስቱን ይችሉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በምን ዓይነት መንገድ ነው ኢትዮጵያዊ የምናደርጋቸው የሚለውን ጉዳይ በጥልቀት ልናስብበት ይገባል፡፡ ጉልበት ስላለን ብቻ የሌላውን መሬት ይዘን ‹ለትውልድ ምን ዓይነት ጠባሳ እናተርፍ ይሆን?› በማለት ማሰብ መቻል አለብን፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው ያለ ምክንያትና በመላምት የሚከራከሩ ሰዎችን ማሳመን ከባድ ይሆንብኛል እንጂ፣ ከመላው ኢትዮጵያ ጋር ሳወዳድራት ባድመ የበሬ ግንባር የምታህል ሥፍራ መሆኗንም መግለጽ ይቻላል፡፡

      አባቶቻችን የአገራቸውን አፈር እንኳ አሳልፎ ላለመስጠት ያደርጉ የነበረውን ጥረት ስላልሰማሁ አይደለም፡፡ ነገር ግን አባቶቻችን ሕግን የሚያከብሩና በዓለም አቀፍ ሕግ ላይ ያላቸው ዕምነትም ከፍተኛ የነበረ (አንዳንዴም የተጠቁበት) መሆኑን ስለማውቅም ጭምር ነው፡፡ ለነገሩ አሁንም ቢሆን እየተደረገ ያለው ወደ መደራደር መግባት ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በወሰደው አንድ የወደፊት ዕርምጃ፣ የኤርትራ መንግሥት ሁለት ዕርምጃ ወደፊት መጣ እንጂ (የኢትዮጵያን የሰላም ጥሪ ከመቀበልም አልፎ የልዑካን ቡድኑን ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ መወሰኑ)፣ እንደተባለው በቅድሚያ ባድመን ስጡኝ፣ ወይም የመከላከያ ኃይላችሁን ከግዛቴ አስወጡ የሚል ጥያቄ አልቀረበም፡፡ ወደ ድርድር ለመግባት ልዑካን ከመላክ በተጨማሪ ወደ ኢትዮጵያ መተው ለመነጋገር መፍቀዳቸውም ትልቅ ነገር ነውና ይኼንን አጋጣሚ ማበላሸት እንደማያስፈልግ ልንገነዘበው ይገባል፡፡

የሔጉ ውሳኔ ፍትሐዊ ስላልሆነ ልንቀበለው አይገባም

      የእዚህን መከራከሪያ አቅራቢዎች የምሞግታቸው ጉዳይ ቢኖር ጉዳዩን ገልብጠው ቢመለከቱት መልሳቸው ምን ሊሆን እንደሚችል በመጠየቅ ነው፡፡ ባድመ የተፈረደው ለኢትዮጵያ ቢሆንና ኤርትራ ይዛ አለቅም ብላ ቢሆን ምን ይፈጠር ነበር? ከምን በመነሳት ነው ውሳኔው እኛ በማንፈቅደው መንገድ ስለተሰጠ ፍትሐዊ አይደለም ብለን መከራከር የምንችለው? ሲጀመርስ ፍትሐዊ ያልሆነ ውሳኔስ እንዴት ነው የምንገልጸው? እኔ እስከሚገባኝ ድረስ አንድ ተከራካሪ የተሰጠኝ ፍርድ አግባብ አይደለም ብሎ ሲያስብ ማድረግ የሚችለው ጉዳይ፣ ይግባኝ በመጠየቅ መሄድ እስከሚቻልበት ርቀት በሕግ አግባብ መጓዝ ብቻ ነው፡፡

      ከዓረና ፓርቲ አቶ ገብሩ አሥራት አይጋ ፎረም ለተባለው ድረ ገጽ የሰጡትን ቃለ ምልልስ እንደሰማሁት፣ የዚህ ውሳኔ ፍትሐዊነት ተቀባይነት እንደሌለው ለመግለጽ የሰጡት ምክንያት ‹‹የሔጉ ኮሚሽን ውሳኔ አዲግራትን ወይም ማይጨውን ቆርሶ ቢሰጥ እንቀበለዋለን ወይ?›› የሚል መሆኑ ማንም ጤነኛ ሰው ሊረዳው ከሚችለው በላይ የማያሳምን ደግሞ ምክንያት (Lame Excuse) ሆኖብኛል፡፡ ዛሬ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል መሆናቸው በጀን እንጂ፣ የመንግሥትን ሥልጣን በያዙበት ወቅት ያቀረቡት ሐሳብ ቢሆን ኖሮ አገሪቱን ብዙ መዘዝ ውስጥ የሚጨምራት ንግግር ይሆን ነበር፡፡

      ታኅሳስ 4 ቀን 1994 ዓ.ም. በአልጀርስ ኢትዮጵያ በፈረመችው የሰላም ስምምነት መሠረት፣ የሔጉ የድንበር ግልግል ኮሚሽን የሚሰጠው የፍርድ ውሳኔ ይግባኝ እንደማይኖረው ተስማምተናል፣ ምናልባትም ውሳኔው እኛ እንደምንፈልገው ከተሰጠ ጉዳዩን በአጭር ለመቋጨት የዘየድነው መላ ሊሆን ይችላልና ክፋት አልነበረውም፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ግን ያሰብነው አልተሳካም፡፡ ከእዚህም ባለፈ እኛም ሆንን የኤርትራ መንግሥት ላለፉት 16 ዓመታት ምንም የተሻለ መፍትሔ አላመጣንም፣ ለወደፊቱም ቢሆን እንዲህ ቢሆን የሚባል የጦርነትም ሆነ የሰላም መፍትሔ የለንም፡፡ ታዲያ ችግሩ አለ ከተባለ እስከ መቼ አዝለነው ልንዞር ነው ያሰብነው?

ስህተትን በሌላ ስህተት ማረም አይቻልም

      እጅግ በጣም ትክክል የሆነ ግን ያለቦታው ተገልብጦ የቀረበ ሐሳብ ነው፡፡ የቀደመው ስህተት በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰደው ጦርነቱን የማስቆም ዕርምጃና እሱንም ተከትሎ የገባበት የሕግ አጣብቂኝ ነው ካልን፣ አሁን ስህተት የሚሆነው ደግሞ የተሰጠውን የፍርድ ውሳኔ አለመቀበሉ ይሆናል እንጂ ፍርዱን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መቀበሉማ ያለፈውን ስህተት ማስተካከል ነው የሚሆነው፡፡ ይልቁንስ የኤርትራ መንግሥት ይኼንን ዘዴ በሚገባ ተጠቅሞበታል ብዬ አስባለሁ፡፡ ምንም እንኳ ያላቅማቸው በጀመሩት ጦርነት ከፍተኛ ኪሳራ ቢያጋጥማቸውም፣ በአልጀርሱ ስምምነት መሠረት ያገኙትን ድል ላለማስነጠቅ በከፍተኛ ጥንቃቄ (የጦርነትም የሰላምም አየር በአካባቢው እንዳይነፍስ በማድረግ) ለ16 ዓመታት ሲጫወቱ ቆይተው፣ ዛሬ በትክክል የሚፈልጉትን ሁሉ ለማግኘት አጋጣሚው እንደ ተፈጠረላቸው ሲረዱ፣ ልዑካኖቻቸውን እስከመላክ የሚደርስ ዕርምጃ መውሰዳቸው፣ ስህተትን በሌላ ስህተት ላለማረም ያደረጉትን ጥረት የሚያሳይ ነው፡፡ በእዚህ መስመር መበለጣችንን መቀበል አለብን፡፡

      ለማጠቃለል ያህል ከእዚህ በላይ የተጠቀሱትንና ሌሎችንም በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተወሰነውን ውሳኔ ያለመቀበል አስተያየቶች እየሰማን ያለነው፣ በይበልጥ በትግራይ ክልል ውስጥ እየተንቀሳቀሱት ካሉት ሁለቱ ፓርቲዎች (ከሕወሓትና ከዓረና) በኩል መሆኑ፣ ምናልባትም ‹አንዱ በአንደኛው ላይ ግብ ለማስቆጠር እያደረጉት ያለ ጥረት ይሆን እንዴ?› ብዬ እንድጠይቅ አስገድዶኛል፡፡ በበኩሌ ያለኝ ቀና ምክር ግን ወቅቱ ለእንደዚህ ዓይነት የፖለቲካ ጨዋታ የተመቸ ባለመሆኑ ለአፍታ ቆም ብለው የክልላቸውንም ሆነ የአገሪቱን ዘላቂ ጥቅም በሚያስጠብቅ መንገድ ውሳኔውን ቢመለከቱት መልካም ነው የሚል ነው፡፡ ለኤርትራ ሕዝብ ከትግራይ ሕዝብ የበለጠ የሚቀርበው ወዳጅ ሊኖረው አይችልም፡፡ ይኼንንም ዝምድና በነፃነት ትግሉ ወቅት ዓለም በሙሉ የታዘበው ነው፡፡ ኤርትራንም ስናስብ ወደቦቿን፣ መሬቷንና ጥቅሞቿን ሳይሆን፣ ምስኪኑን ለዘመናት በሰላም አብሮ የኖረውንና የተጎሳቆለውን የኤርትራን ሕዝብ ታሳቢ እናድርግ፡፡ እሱ ቢቀር ሁለት በሰላም የሚኖሩ ጎረቤቶች እንዲፈጠሩ መጣር ምን ይከብዳል? የኤርትራን መንግሥትም ይሁን መሪውን እንደ ጠላት ከመቁጠር ታቅበን፣ እንደ አንድ የጎረቤት አገር መንግሥት በመመልከት አስፈላጊውን ቀናነት ማሳየት ከአንድ በድንበር ላይ ከሚገኝ ቦታም በላይ፣ የሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች ተዋህደው ራሳቸውን አንድ ለማድረግ የሚችሉበትን ዕድል ሊፈጥር ይችላልና ሰፋ አድርጎ ማሰብ ይሻላል፡፡ ያለፈውን ቂምና ቁርሾ እያሰቡ የትም ድረስ መዝለቅ አይቻልም፡፡ ዘላቂ ጥቅም እንጂ ዘላቂ ጠላት የለምና፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...