Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉኢትዮጵያንንና ኤርትራን ወደ ሰላም የሚያደርስ ጥሩ ጥርጊያ አለ

ኢትዮጵያንንና ኤርትራን ወደ ሰላም የሚያደርስ ጥሩ ጥርጊያ አለ

ቀን:

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

ባለፉት ሁለት ሳምንታት በሁለቱ አገሮች ዕርቀ ሰላም ዕውን እንዳይሆን እንከን የሚሆኑ ተግዳሮቶች ምን እንደሆኑ አቅርቤ ነበር፡፡ እነዚያን ተግዳሮቶች መሠረት አድርገን ከተጓዝን ዕርቀ ሰላም እንዲፍን የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ደግሞ እንደሚከተለው ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡

ወደ ሕዝቦች አንድነት የሚወስደን ታሪካዊ አንድነታችን ነው

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እንደሚታወቀው ኤርትራን የምትጨምረዋ ኢትዮጵያ ከግብፅም ባሻገር እስከ ጥንታዊት ፐርሺያ ግዛቷን አስፋፍታ የነበረች አገር ናት፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ (በኦሪትና በወንጌል) እንዲሁም በቁርዓንና በልዩ ልዩ ኢስላማዊ መጻሕፍት ኤርትራን ስለምትጨምረው ስመ ገናናዋ ኢትዮጵያ በሰፊው ተጽፏልና አሁን ካለው ሁኔታ ጋር ሲያገናዝበው ሊጨንቀው ይችላል፡፡ ለአንዳንዱም ተረት ይመስለዋል፡፡ ከታሪክ ጋር ለተጣላ፣ ታሪክን ክዶ ልቦለድ ለሚናገር ደግሞ እውነቱ ሲነገር የቅናት ዛሩ ሊነሳበት ይችላል፡፡ ነገር ግን ኤርትራን የምትጨምረው ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በመላው ዓለም ስመ ገናና፣ እንዲሁም ሰፊ ግዛት የነበራት መሆኗን ጥንታውያኑ የግሪክ፣ የሮማ፣ የባይዛንታይን፣ የፊንቅ፣ የቻይናና የዓረብ ታሪክ ጸሐፊዎች በሰፊው ጽፈውላታል፡፡ በምሥራቅ አፍሪቃ የሥልጣኔ ጮራን የፈነጠቀች አገር መሆኗን አሁንም በኤርትራ (በተለይም በአክሱም፣ በአዱሊስ፣ በመጠራ፣ በቋሐይቶ፣ በይሓ፣ በእንደርታ፣ በውቅሮ፣ በላስታና በጎንደር ወዘተ.) ያሉ ቅርሶቿ ያረጋግጣሉ፡፡ ወደፊት ታላቅነቷን የሚመሰክሩ መረጃዎችም ሩቅ ባልሆነ ጊዜ ተቆፍረው እንደሚወጡ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር የአንዳቸው ታሪክ ያላንዳቸው የተሟላ ሊሆን አይችልም፡፡

ስለሆነም ነገርን ከሥሩ፣ ውኃን ከጥሩ እንዲሉ አቶ ተክለ ፃድቅ መኩሪያ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከኑብያ እስከ ዛጉዌ›› በተሰኘ መጽሐፋቸው እንዳቀረቡት የታሪክ አባት የሚባለው ስመ ጥሩው ሄሮዱተስ ወደ ግብፅ መጥቶ ዓባይንም ጉብኝቶ በጻፈው የታሪክ መጽሐፉ፣ እንደዚሁም ዲዮዶር የሚባለው የሮማ ጸሐፊ ከግብፅ በፊት ሥልጡንና ገናና የነበረችው ኤርትራን የምትጨምረው ኢትዮጵያ መሆኗን፣ እሷም በመጀመርያ ግብፅን ወርራ ቅኝ አገር አድርጋ መያዟን፣ ግብፅንም 18 የኢትዮጵያ ነገሥታት እንደገዟትና ራሷ ኢትዮጵያ ግን በማንም ተገዝታ የማታውቅ አገር መሆኗን፣ ነገሥታቱም ሕዝቡም ሥልጡን ደግሞ እንግዳ ተቀባይ፣ ሰላማዊ፣ በጦርነት ጊዜ ጀግናና ጎበዝ መሆናቸውን እያጋነኑ ጽፈዋል፡፡

አቶ ተክለ ፃድቅ መኩሪያ ከጠቀሱት በተጨማሪ ኤርትራን የምትጨምረው ኢትዮጵያ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከ40 ጊዜ በላይ ተጠቅሷል፡፡ በቁርዓን ውስጥ በሱራ አል-ሉቕማን እንደምንገነዘበው፣ ሉቕማን ከኢትዮጵያውያን ነብያት አንዱ ሲሆን በሌሎች መጻሕፍት ደግሞም ኤዞፕ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሱራ አል-ፊል አፄ ካሌብ በዓረቢያ ያደረሱትን ወረራ የሚመለከት ሲሆን፣ በሐዲሶችና በሌሎች ኢስላማዊ መጻሕፍት የኢትዮጵያ ስም በተደጋጋሚ ይወሳል፡፡ ኤርትራን የሚጨምረው የኢትዮጵያ ጉዳይ የአንድ ወገን ብቻ ባለመሆኑ፣ በዚህ አጋጣሚ ይህን ታሪክ እንደሚከተለው ሰፋ አድርገን እንመልከተው፡፡

በክርስቶስ ልደት አካባቢ ገኖ የነበረውና የኢትዮጵያ ጥንታዊ ሥልጣኔ   የሚያረጋግጡትና ዛሬ ‹‹ኤርትራ›› ተብሎ በሚታወቀው ግዛት ምሥራቃዊ ክፍል በድንጋይ ላይ ተቀርፀው የተገኙት የታሪክ ቅርሶች  በቂ መረጃዎች ናቸው፡፡ እነዚህንም የታሪክ መረጃዎች ተክለ ፃድቅ መኩሪያ የኢትዮጵያ ታሪክ ከኑብያ እስከ ዛጉዌ በተሰኘው መጽሐፋቸው፣ ዶ/ር ሥርገው ሀብለ ሥላሴ ‹‹ጥንታዊና መካከለኛው ዘመን እስከ 1270 የኢትዮጵያ ታሪክ›› በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ እ.ኤ.አ. በ1972 በታተመ መጽፋቸው ውስጥ ባሰፈሩት ካርታ ላይ ከሃምሳ በላይ የሚሆኑ የድንጋይ ላይ የታሪክ ማስረጃዎች የተገኙባቸውን ቦታዎች ያሳያሉ፡፡ ከእኝህ የታሪክ ምሁር በተጨማሪ፣ ሞንሮ ሄይ ስለአክሱም ጥንታዊ ሥልጣኔ እ.ኤ.አ. 1991 ባሳተሙት መጽሐፋቸው፣ ፕሮፈሰር ፓንክረስት ስለጥንታዊትና ዘመናዊት ኢትዮጵያ ባወሱባቸው ሥራዎች ሁሉ፣ ዶ/ር ላፒሶ ጌ. ደሌቦ ስለጥንታዊት፣ ማዕከላዊትና ዘመናዊት ኢትዮጵያ ባወሱባቸው ሥራዎቻቸው ሁሉ በሰፊው አትተዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያና የሥልጣኔ ምንጭ›› በሚል ርዕስ የምርምር ሥራቸውን በጆርናል ላይ ያሰፈሩት አሜሪካዊው ጆን ጂ ጃከሰን፣ ዶ/ር አኑ ማውሮ በጥንት ሜዲትራኒያን አካባቢ ስለነበሩ ጥቁር አፍሪካውያን በ2006 ዓ.ም. ለንባብ ባበቁት የምርምር ሥራቸው፣ ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል እንደነበረች ሳያወሱ አላለፉም፡፡

ሕዝብና ሕዝብን የሚያስተሳስሩ መሠረታዊ ነገሮች

የትግራይና የኤርትራ ሕዝብ በአመዛኙ አንድ ቋንቋ ማለትም ትግርኛ ተናጋሪ ሲሆን፣ ይህም አንድ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝብ በመላው ትግራይ፣ ሰራዬ፣ ሐማሴንና አከለጉዛይ በተሰኙ የኤርትራ ሦስት ታላላቅ አውራጃዎች ይገኛል፡፡ የዚህ አካባቢ ሕዝብ የሚከተላቸው እምነቶች ክርስትናና እስልምና ሲሆኑ፣ ክርስቲያኑም በእጅጉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታይ ነው፡፡ ሙስሊሙም ሙሉ በሙሉ ሱኒ ሲሆን የጀበርቲ ዝርያ እንደሆነ ያምናል፡፡ ጀበርቲዎች ደግሞ ከሱማሌ እስከ ኤርትራ፣ ከጅቡቲ እስከ ዳህላክ (በስተሰሜን)፣ ከጅቡቲ በዓፋር፣ በወሎ እስከ ጎንደርና ጎጃም (በስተምዕራብ) ይዘረጋል፡፡ ሕዝቡ በአብዛኛው በግብርና የሚተዳደር ከመሆኑም በላይ፣ በማንነቱና በነፃነቱ ኮርቶ የሚኖር ሕዝብ ነው፡፡ በቋንቋ፣ በሃይማኖትና በሥነ ባህሪያዊ አመለካከቱ አንድ በመሆኑም ጠላቶች በመካከል ገብተው ሊከፋፍሉት ቢሞክሩም የማይለያይ ሕዝብ መሆኑን አስመስክሮ ኖሯል፡፡

የትግራይና የኤርትራ ሕዝብ በአመዛኙ አንድ ቋንቋ ማለትም ትግርኛ ተናጋሪ ሲሆን፣ የሁለቱ አካባቢ ሰዎች ወገኖቻቸውን ለማዋሀድ ታጥቀው በተነሱበት ጊዜ ‹‹ትግራይ ትግርኝ›› የሚል መፈክር ይዘው መንቀሳቀስ እንደጀመሩ ይታወሳል፡፡ ትግራይ ትግርኝ ስንልም በኤርትራ ክፍለ አገርና በትግራይ ክፍለ አገር የሚገኘውን የአካላ ጉዛይና የሐማሴን፣ የሰራዬ አውራጃዎችን ጨምሮ ማለታችን ነው፡፡ ትግራይ ትግርኝ ማለት ታላቋ ወይም ታናሿ ትግራይ ማለት ሳይሆን ሙሉዋ ትግራይና ኤርትራ ማለት ነው፡፡ ትግራይ ትግርኝ የሚባለው ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው በትግራይና በኤርትራ ክፍለ አገር ውስጥ ትግርኛ የሚናገረውን ሕዝብ የሚያጠቃልል ሲሆን፣  በኤርትራ ደግሞ በምዕራብ ኤርትራ ደጋማ ሥፍራ በአስመራና በአካባቢዋ የሚገኙትን ትግርኛ ተናጋሪዎችና የሚያጠቃልል ነው፡፡ ይህንንም ሕዝብ በእነርሱ አገላለጽ ኸበሳ ይሉታል፡፡ ለእኛ የሚገባን ደግሞ የሰራዬ፣ የአከለ ጉዛይ፣ የሐማሴን ሕዝብ ማለት ሲሆን ይህም ትግርኛ ተናጋሪውን አፋር፣ ሳሆ፣ ኩናማ፣ ናራ፣ ቢለንና ባሪያን፣ ወዘተ. ይጨምራል፡፡ በጥቅሉ ከኤርትራም ከትግራይም የተለያየ ብሔር ብሔረሰብ ቢኖርም በትግራይና በኤርትራ ይዋጥና ትግራይ ትግርኝ ይሆናል፡፡ ከዚህ በመለስ እንደ አፋር፣ ትግረና የመሳሰሉት እኛም ነፃነት እንሻለን ብለው ቢጠይቁ አይሆንም፡፡ ለምን? ያለ አፋር ማለትም ያለ አዶሊስ፣ ያለ ራሒታ፣ ያለ ቆሐይቶ፣ ያለ ሰነዓፈ ኤርትራ የማይታሰብ በመሆኑና ረዥሙ የባህር ድንበርም በትግርኛ ተናጋሪ ተያዘ አልተያዘ የኤርትራ ግዛት ሆኖ በኢጣሊያ በመያዙ የሚሆን አይደለም፡፡

 

ወደ ሰላም የሚወስደን ጎዳና

የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ የሽምግልና ጉዳይ በመሆኑ፣ ከሁሉ አስቀድሞ ኤርትራውያን ሲባል ከኢጣሊያ ቅኝ አገዛዝ ወዲህ በተለይም 1943 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ጋር ከተዋሀደች በኋላ በፌዴሬሽኑና በውህደቱ ባለመስማማት የጦር መሣሪያ ትግል አድርገው 1985 ዓ.ም. ሁለተኛ ሬፈረንደም ተካሂዶ ኤርትራ ራሷን የቻለች፣ የአፍሪካና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ከሆነች በኋላ ራሳቸውን የኤርትራ ዜጎች ያደረገችውን ኤርትራ ማለት ነው፡፡

የኤርትራ ታሪክ 1,000 ኪሎ ሜትር ያህል ርዝመት ካለው የባህር ዳርቻ ላይ የተመሠረተ ሲሆንብዙ ሳይንቲስቶችም የሰው ልጅ መገኛ ይህ አካባቢ እንደሆነና ወደ ተለያዩ ክፍለ ዓለማት የሄደው ከዚህ ተፈጥሮ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ በዚህ የባህር ዳርቻ ሰዎች ተፈጥረው ወደ ሌሎቹ ክፍለ ዓለማት መሄድ ብቻ ሳይሆን፣ ከሌሎች ክፍላተ ዓለማትም በርካታ ወራሪዎችና ቅኝ ገዥዎችም መጥተዋል፡፡ ከነዚህም መካከል ከደቡብ ዓረቢያ ማለትም ከዛሬይቱ የመን፣ ኦቶማን ቱርኮች፣ ፖርቱጋሎች፣ ግብፆች፣ እንግሊዞችና ኢጣሊያዊያን 19ኛው ክፍለ ዘመን መጥተዋል፡፡ ከክፍለ ዘመን በላይ በሆነ ጊዜም በአጎራባች አገሮች ማለትምግብፅናሱዳን፣ በምዕራብና በሰሜንና በደቡብ ኢትዮጵያ መጥተዋል፡፡ 

ወደ ሰላም የሚወስድ ጎዳና ባህልና ቋንቋ

እንደሚታወቀው በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የፈለገው መንግሥት በቦታው ቢቀመጥ፣ የፈለገው የፖለቲካ ሁኔታ ቢፈጠር ምንም ሊደረጉና ሊበጠሱ የማይችሉ ነገሮች አሉ፡፡ በእሰላሙም በክርስቲያኑም አካባቢ ለዘመናት የቆየ ግንኙነት ካለ መሠረታዊ የሆነ ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት አለ፡፡ ያንን የፖለቲካ ፍፃሜ ሊቀይረው አይችልም፡፡ በሕዝቦች መካከል ለዘመናት የቆየ የቋንቋ፣ የባህልና ሌሎችም ግንኙነቶች ካሉ እነዚህ ግንኙነቶች ምንም ዓይነት አጥር ቢሠራ ሊታጠፉ የሚችሉ አይደሉም፡፡ የደም ደመና ሊሸፍን ቢችል እንኳ ያ ደመና ሲያልፍ ሊገለጥ ይችላል፡፡ አሁን ያለው እውነት በደም ደመና ተሸፍኖ የነበረው ነገር እየተገለጠ መሆኑ የሚያመለክት ነው፡፡ እናም ከዚህ ከደመናው ባሻገር አንድ ነገር እንዳለ ይገባናል፡፡ ተራው ሕዝብ ከዚያ በላይ የሚሄድ ነገር እንዳለ ይረዳል፡፡ ተራው ሕዝብ ሪፈሪንደሙ የታሪክ መጀመርያ ወይም መጨረሻ እንዳልሆነ ይገባዋል፡፡ ስለሆነም ስለሚቀጥለው ያስባል፡፡ ካነጋገሩ ለሚቀጥለው በሚሆን በሚያመችና በሚጠቀም መልኩ የሚያስብ ይመስለናል፡፡ እናም ስለሕግና ስለፖለቲካ መከራከር ያው ሥራችን ነው፡፡ ይህንን በምናደርግበት ጊዜ አንዳንዴ እንደ ሕዝብ ከእነዚህ ባሻገር ነገር እንዳለም እያስተዋልን ቢሆን ሊጠቅም ይችላል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በኤርትራ ላይ ያለው ግልጽ አቋም

የኤርትራ ሪፈረንደም በነፃነት ሲጠናቀቅ የኢትየጵያ መንግሥት አቋም የሚያወላዳ አልነበረም፡፡ ዛሬም ያ አቋም ስለመቀየሩ የሚያመለክት ፍንጭ የለም፡፡ በሪፈረንደሙ ክብረ በዓል የኢትዮጵያ ልዑክ ያሰሙት ንግግር እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

‹‹ለ17 ዓመታት በደርግ ፍፁም ምሕረት የለሽ በትር ስትደበደቡ የነበራችሁ የኤርትራ ሕዝች ሆይ! የኢትዮጵያ ሕዝብ እናንተ በመሬታችሁ፣ በቀያችሁ፣ በአየራችሁና በተፈጥሮ ሀብታችሁ በነፃ የመንቀሳቀስ መብት ተነፍጋችሁ በዘመናዊ ጦር መሣሪያ የእሳት ላንቃ ስትለበለቡ፣ በመላው ኢትዮጵያ ያሉ ዜጎች ከእናንተ ጋር መጋየታቸው፣ የጫጉላ ቀናቸውን ሳይጨርሱ፣ ወለዱትን ልጅ ሳይስሙና የከፈቱትን በር ሳይዘጉ እንደወጡ የቀሩ እንዳሉ ደግሞ የታወቀ ነው፡፡ ይህም በሚያውቀውና በማያምንበት ነገር ግን በግዴታው የዘመተና በኤርትራ በረሃ የቀረ ዜጋ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ልጆችን ያለ አባት፣ የብዙ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ያለ ባል፣ የብዙ ኢትዮጵያውያን ወላጆችን ያለ ጧሪ እንዳስቀረ በአንድ በኩል እያሳየ በሌላ በኩል ደግሞ ለ17 ዓመታት የተደረገው ጦርነት ሁለቱንም ወንድማማች ጭቁን ሕዝቦች የመከራ ገፈት ቀማሽ እንዳደረገው ያመለክታል፡፡

‹‹ዛሬ የድላችሁን አንደኛ ዓመት በታላቅ ክብር የምታከብሩ የኤርትራ ሕዝቦች ሆይ! በዚህ የታሪክ አጋጣሚ አንድ እውነት እንድነግራችሁ ፍቀዱልኝ፡፡ ይኸውም እውነት የኤርትራ ሕዝብ መጨፍጨፍ፣ ማለቅ፣ በማንኛውም መልኩ ሊሳካ በማይችል የጥፋት መሣሪያ ከምድረ ገጽ ቢደመሰስ ደስ የሚላቸው ጥቂት ፋሽስቶችን፣ የሥርዓቱ ቀንደኛ አራማጅና አቀንቃኞች ቢኖሩም የእናንተ ጥፋት ጥፋታቸው፣ የእናንተ አበሳ አበሳቸው፣ የእናንተ ምሬት ምሬታቸው ሆኖ በሁሉም አቅጣጫ የእናንተ ድል እንዲሳካ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ ሕዝቦች እንዳሉ ደግሞ ምንጊዜም መዘንጋት የለበትም፡፡ የትግራይ ሕዝብ የኤርትራ ሕዝብ ሲነድ አብሮ መንደዱ፣ የጎንደር ሕዝብ የኤርትራ ሕዝብ ሲጨፈጨፍ አብሮ መጨፍጨፉ፣ የአፋር ሕዝብ የኤርትራ ሕዝብ በደም ጎርፍ ሲዋኝ አብሮ መዋኘቱ፣ እንደ ቅርብ ምሳሌ የሚጠቀስ ሲሆን በተቀረው የኢትዮጵያ ምድር ያለውም ሕዝብ ቢያንስ ቢያንስ በማኅበራዊ ኑሮና በኢኮኖሚ በመጎሳቆሉ የኤርትራ ሕዝብን መራራ ፅዋ ሲጎነጭ እንደነበረ አሌ አይባልም፡፡ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ የኤርትራ ተወላጆችን ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጥሎ ለመምታት ጥረት ሲደረግ ስኬታማ ውጤት ያልተገኘውም ለዚሁ ነው፡፡ በኤርትራ መሬት ውስጥ በግድ የዘመቱ ወታደሮች ተጋብተውና ተዋልደው መገኘታቸውም ቢሆን ሕዝቦች ምን ያህል ሰላማዊ ሕይወትንና ፍቅርን እንደሚሹ ይጠቁማል የሚል ግንዛቤ አለኝ፡፡

‹‹እውነታው ይኽው ሆኖ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ሰላምን፣ ወንድማማችነትን፣ ፍትሕንና ዴሞክራሲን ቢፈልጉም ገዥ መደቦች ግን ‹‹ነጣጥለህ ግዛ›› በሚለው መርኋቸው ሕዝብን በሕዝቡ ላይ አነሳሱት፡፡ በተለይም በነቃው፣ በልዩ ልዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደራጅቶ በነበረው የኤርትራ ሕዝብ ላይ በመጀመርያ በኮንፌዴሬሽን፣ ከዚያም በፌዴሬሽን ቀጥሎም በአንድነት ስም ገብተው ነገሩ ‹‹ወርቅ ላበደረ ጠጠር›› እንደሚባለው ሆነና ነፃነት ለሚፈልገው የባርነት፣ ዴሞክራሲ ለሚፈልገው ሕዝብ አምባገነንነት፣ ፍትሕ ለሚፈልገው ሕዝብ የግፍ ካባ አጎናፀፉት፡፡ ቅኝ ገዥዎች የሰጡትን መብት ሳይቀር ነጠቁት፡፡ ሰብዕናውን ረገጡት፡፡ በአገር አንድነት ስም ሕፃናት በቦምብ ጋዩ፣ ነፍሰ ጡሮች በሚሰቀጥጥ ሁኔታ ተገደሉ፡፡ አዛውንቶች ተንገላቱ፡፡ ሀብትና ንብረት ወደመ፡፡ በተለይ፣ በተለይ፣ በኤርትራ ሕዝቦች ጥያቄ ላይ ብቻ ሳይሆን የደረሰባቸውን ግፍ በመረዳት በኩል አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባዕድ ነው፡፡ እንኳንስ በኤርትራ ሕዝብ ላይ የደረሰው በደል በሐውዜንና በመርሳ የተፈጸመውን ያውቅ የነበረው ጥቂት ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ የደርግ ፋሽስታዊ መንግሥት በአዲስ አበባ፣ በጎንደር፣ በባህር ዳር፣ በደብረ ዘይትና በሌሎችም ሥፍራዎች በልዩ ልዩ ሰበቦች የፈጀውን ሕዝብ አንዴት እንደፈጀው በውል ለመረዳት የቻለው እንኳን ከስምንትና ከዘጠኝ ወራት አይበልጥም፡፡ ይልቁንም ያናፍሰው በነበረው ኃይለኛ የፕሮፓጋንዳ ሞገድ ንፁኃንን እንደ ወንጀለኞች አድርጎ ያቀርብ ስለነበረ እውነታው እንደ ደበዘዘ እንዲቆይ አድርጎታል፡፡ እውነቱ ይኸው ነበር፡፡ በኤርትራ ሕዝቦች ላይ የደረሰው አስመራሪና አንገፍጋፊ ግፍ የምናስበውና የምናየው ከዚህ አኳያ ነው፡፡

‹‹በመጨረሻም በኤርትራ የፈነጠቀው የድል ጮራ በመላው ኢትዮጵያ እያበራ የሚገኝ፣ ዕድገታችሁ ዕድገታችን በመሆኑ እስካሁን ድረስ ባስመዘገባችኋው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ውጤቶች እንደምንኮራ፣ በምንም መንገድ ቢሆን ያሉንን ባህላዊ፣ ታሪካዊ፣ ሥነ ባህሪያዊ ልዶች እያጠናከርን እንጂ እያላላን እንደማንሄድ የማምን መሆኔን እየገለጽኩ የሽግግር መንግሥቱ ፅኑ አቋሙም የሕዝቦች አንድነት በመፈቃቀድና በመፈቃቀር ላይ የተመሠረተ ነውና የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች እጅግ በተሻለና እውነተኛ በሆነ መንገድ ወንድማማችነታቸውን እንዲያጠነክሩ ጥረት እንደሚደረግ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡ ድላችሁ ለዘላቂውም ሰላም፣ ለፍትሐዊ ሥርዓት፣ ለዲሞክራሲያዊ ዕድገትና ለወንድማማችነታችን መጠናከር እንዲያበቃችሁ እመኛለሁ፤›› የሚል ነበር የተወካዩ ንግግር፡፡ ይህን መልዕክት ዛሬም ቢሆን አለና ለሰላም መሠረት እንደሆነ አያጠያይቅም፡፡

የኤርትራና የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የፖለቲካ ውህደት

ሁለተኛው የኢትዮ ኤርትራ የሚኒስትሮች የጋራ ስብሰባ መጋቢት 27 ቀን 1987  ዓ.ም. አስመራ ውስጥ ሲካሄድ በወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ታምራት ላይኔ (ከመስከረም 1984 እስከ ነሐሴ 14 ቀን 1987 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሽግግር መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ከነሐሴ 18 ቀን 1987 እስከ ጥቅምት 13 ቀን 1989 ዓ.ም. የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ሲሠሩ ነበር፡፡ በአቶ ታምራት የሚመራ የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን የጉባዔው ነጥቦች በስፋት እንደሚዳሰሱና የወደፊት የድርጊት መርሐ ግብሮች እንደሚነደፉ፣ መጋቢት 25 ቀን 1987 ዓ.ም. የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ በመጀመርያ ገጹ አስፍሮት ነበር፡፡

ጋዜጣው በመጋቢት 28 ቀን ዕትሙ ‹‹የኢትዮ ኤርትራ የጋራ ስምምነት ተፈረመ›› በሚል ርዕስ ባቀረበው ዜና እንደገለጸው፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ በመካከላቸው ጠንካራ የኢኮኖሚ ትብብር ለመፍጠርና ወደፊት ለሚፈለገው ምጣኔ ሀብታዊ ውህደት መሠረት የሚያስችል የነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ተፈረመ ሲል በመጀመርያው አንቀጹ አስፍሯል፡፡ ጋዜጣው እንደገለጠው ሁለቱ አገሮች የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶቻቸውና የንግድ አገልግሎታቸው ከታሪፍ ነፃ በሆነ መንገድ መለዋወጥ የተስማሙበትን ይህንኑ ውል በኢትዮጵያ በኩል የፈረሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ ናቸው፡፡ በኤርትራ ወገን የፈረሙት ደግሞ አቶ ሙሐመድ አህመድ ሸሪፎ የኤርትራ የአገር ግዛት ሚኒስትር ናቸው፡፡ ስምምነቱ መጋቢት 27 ቀን 1987 ዓ.ም. የተመፈረመ ሲሆን፣ ይኸው የነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት የአገር ውስጥ ምርቶችን ከታሪፎችና ከታሪፍ ጋር ከተያያዙ ክፍያዎች ሁሉ በሙሉ ነፃ የሚያደርግ ነው፡፡ ይኸው የሁለቱ አገሮች የነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ውሉ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ደረጃ በደረጃ ተግባራዊ እንደሚሆን፣ ይህንንም ክንውን የሚከታተል ጽሕፈት ቤት እንዲቋቋም መወሰኑ በሰነዱ ተመልክቷል ሲል አዲስ ዘመን ዘግቧል፡፡

የኢኮኖሚና የትራንስፖርት አገልግሎትን በተመለከተም በሁለቱ አገሮች ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል የመግባቢያ ሰነዶች ተፈርመዋል፡፡ በቀጣዮቹ ጊዚያትም የጉምሩክ አንድነት በማምት ወደ አጠቃላዩ የምጣኔ ውህደት ለመድረስ በሁለቱም ወገን አስፈላጊው ጥረት እንደሚደረግ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ሁለቱም አገሮች በውጭ ግንኙነት ረገድም በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው አማካይነት ፈርመዋል፡፡ ይኸው ጋዜጣ በመጋቢት 30 ቀን 1987 ዓ.ም. ዕትሙ የመጀመርያ ገጽ ላይ ‹‹የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት በአርዓያነት እንደሚጠቀስ ተገለጸ›› በሚል ርዕስ ባወጣው ግንባር ቀደም ዜናው፣ ‹‹ሕዝቦቻችንን ለከፍተኛ ዕልቂት የዳረገው ጦርነት ካበቃ በኋላ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የወንድማማችነት ስሜት፣ ፍላጎትና ጥረት በዓለም ላይ በከፍተኛ አርዓያነት የሚጠቀስ መሆኑን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አስታወቁ፤›› ሲል አስፍሯል፡፡

የኤርትራ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ አስመራ ውስጥ በሰጡት መግለጫ አስከፊ ጦርነት ካጋጠማቸው ከሌሎች አገሮች ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ሲነፃፀር መንግሥታቱ ለጋራ ዕድገት፣ ሰላምና መረጋጋት በየጊዜው ከሚቀይሷቸው መርሐ ግብሮችና ስምምነቶች ባሻገር በሕዝቦቻቸው መካከል የሚታየው መተጋገዝ፣ አብሮ የመኖርና የመተሳሰብ ፍላጎት የይስሙላ ወይም ‹‹አርቲፊሻል›› ያልሆነ ግንኙነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ግንኙነቱ በጋራ ጥቅምና መተሳሰብ፣ በዘላቂና መሠረታዊ የኢኮኖሚ ጠቀሜታዎች ላይ ያተኮረና በየጊዜውም በውጤቶች እየታጀበ የሚጓዝ በመሆኑ ዓለም አቀፍ አድናቆትን እያተረፈ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ በተለይ በወቅቱ የሁለቱ አገሮች የነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ላይ መድረሳቸው ለወደፊቱ ለኢኮኖሚ አንድነት የሚያበቃ ምልክት መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ፣ ‹‹በዚህ በጎ መንፈስ እስከቀጠልን ድረስ ዛሬ የሚታዩ ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችን ለማስወገድ በጋራ ጥረታችን ለአኅጉራችን ጭንር ብዙ አስተዋጽኦ ለማበርከት ያስችለናል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የተፈለገውን አንድነትና ብልፅግና የማምጣቱ ተግባር በሕዝቦች ካልታገዘ ወይም ካልተደገፈ በመንግሥታቱ ብቻ ውጤት አያመጣም፤›› ያሉት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የመንግሥታት ጥረት የሕዝቦች ፍላጎትና የዘለቄታ ጥቅማቸው መሆን ስላለበት፣ የሁለቱ አገሮች መንግሥታት የጋራ ዓላማና እንቅስቃሴ ከዚህ ውጪ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ በዚያው ሰሞን አስመራ በተካሄደው የኢትዮጵያና የኤርትራ የሚኒስትሮች ከፍተኛ የጋራ ኮሚሽን ሊቀመንበር ጭምር የሆኑትና ዋናውን ስምምነት በኢትዮጵያ በኩል የፈረሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ በሰጡት መግለጫ፣ የጋራ ስብሰባው ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ወገን ብቻ ወጥተውና ግልጽ ሆነው የነበሩ ፖሊሲዎችና የስትራቴጂ ጥያቄዎች፣ በኤርትራም በኩል በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ በሚገኙበት ወቅት በመካሄዱ ለረዥሙ ዓላማ መነሻ ሊሆን የሚችል መሠረት እንደተጣለ አስረድተዋል፡፡ በተለይም በኢኮኖሚው የንግድ ዘርፍ የሁለቱም አገሮች ሕዝቦች በመካከላቸው ሊያደርጉት ለሚገባው እንቅስቃሴ የነፃ ንግድ ቀጣናው መፈረም እንደሁም በውጭ ግንኙነት በሌሎችም የማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ቀደም ሲል የተፈረሙ ስምምነቶች በመገምገም ጭምር፣ ለበለጠ ውጤት መዘጋጀት ከፍተኛ ተግባር እንደሆነ አስረድታዋል፡፡

ሰኔ 16 ቀን 1988 ዓ.ም. የታተመው ዕለተ ሰንበት አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ‹‹የኢትዮጵያና የኤርትራ ድንበሮች ትርጉም ወደ ሌለበት ደረጃ እንደሚያድጉ ተገለጸ›› በሚል ርዕስ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን በመጥቀስ በመጀመርያው ገጽ ላይ ማስፈሩ የሚታወስ ነው፡፡ በዚህ ዕለት የታተመው ጋዜጣ እንዳብራራው የኤርትራ ፕሬዚዳንት በቀጣዩ ሒደት የኢትዮጵያና የኤርትራ ድንበሮች ትርጉም ወደ ማይኖራቸው ደረጃ እየተለወጡ እንደሚሄዱ፣ የሁለቱም አገሮች የተናጠል ጥቅምም ከጋራ ጥቅም በታች እየዋለ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

አዲስ ዘመን፣ አዲስ አበባ ውስጥ በትግርኛ እየታተመ የሚወጣውን ‹‹ኣሰር›› ለተባለ የትግርኛ መጽሔትን ጠቅሶ እንደገለጸው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ግንኙነት ይበልጥ እየተጠናከረ እንደሚሄድ እምነታቸው ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ከኢትዮጵያ ጋር በኮንፌደሬሽን መዋሀድ እንደሚቻል ገልጸው ነበር (ይህን በሚመለከት የሚሰጡት አስተያየት አለን?›› የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው፣ ‹‹ጉዳዩ የስያሜ ካልሆነ በስተቀር አሁንም በሚመለከቱን የጋራ ጉዳዮች ላይ ተዋህደን እየሠራን ነው፤›› በማለት ያለፈው የአምስት ዓመት (ከ1983 እስከ 1985) ሒደት የጠንካራ ግንኙነት አብነት መሆኑን አመልክተዋል ሲል ዘግቦ ነበር፡፡

አስመራ ተገኝቶ ጥያቄ ያቀረበላቸው የመጽሔቱ ሪፖርተር እንዳሰፈረው፣ የኤርትራ ፕሬዚዳንት እንደገለጹት ሰፊ የሆነ አኅጉራዊና አካባቢያዊ መደጋገፍ እንዲኖር፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለው ጠንካራ ግንኙነት እንደ አንድ አብነት መወሰድ አለበት ማለታቸውን ዘግቧል፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ የኮንፌደሬሽንን ትርጉም ለኣሰር ሲያብራሩ፣ ‹‹ኮንፌደሬሽን የሚለውን ቃል ስያሜውን ብቻ በመውሰድ አላስፈላጊ ትርጉም ከመስጠት፣ ፖለቲካዊና የሥነ አዕምሯዊ ግንኙነታችንን በይዘቱ መረዳት ይገባል፤›› ያሉት አቶ ኢሳያስ ‹‹የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ስያሜው የፈለገው ይሁን የቅርብና የሩቅ የጋራ ጥቅሞች ያሉት ስትራቴጂካዊ ጥያቄ በመሆኑ መስፋት ያለበት ነገር ነው፡፡ ኮንፌዴሬሽን ማለት ሰፊ ዝምድና መመሥረት ማለት እንጂ በነፃነት ዋጋ ወይም ሉዓላዊነት ላይ መደራደር ማለት አይደለም፡፡ ግንኙነታችን እየተጠናከረና እያደገ በሄደ ቁጥር ራሱ የሚፈጥረው ሥርዓት ነው፤›› ብለው ነበር፡፡

ማጠቃለያ

እውነታው ይኸው ነው፡፡ የኢትዮጵያንና የኤርትራን ወንድማማች ሕዝብን ወደ ነበረበት ለመመለስ ማለትም ዕርቀ ሰላም ለማስፈን የሚያስችሉት ተጨባጭ ሁኔታዎች በርካታ ናቸው፡፡ ይኼም ሆኖ አንዱ ብሔር ወይም ከሌላው እበልጣሁ ወይም አንዱ የበላይ ሌላው የበታች አድርጎ ማየትን ማስወገድ ይገባል፡፡ ሕዝብ አንድነቱ ፋይዳ ሊኖረው የሚችለውም በእኩልነት ላይ የተመሠረተና ተጨባጭ የሆነ ድርድር የተካሄደ እንደሆነ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ የሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች ግንኙነት የማያስደስታቸው የውስጥና የውጭ ኃይሎች ልዩ ልዩ መሰናክሎችን ሊደቅኑ እንደሚችሉ የታወቀ ነው፡፡ ለምሳሌ የምሥራቅ ጀርመን ሕዝብ ከወገኖቹ ከምዕራብ ጀርመኖች ጋር ለመቀላቀል ቢሻም፣ አንዳንድ አገሮች ውህደቱ እንዳይካሄድ ማሰናከል ሆነው ቆይተዋል፡፡ የወንድማችነት ስሜት እንዲጠናከር ማገዝ ሲገባቸው የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ነዝተዋል፡፡ ሕዝቦች አንድ መሆናቸውን ከግምት ውስጥ ባለማስገባት አንዱን ኃያል ሌላን ደካማ፣ አንዱን ሀብተታም ሌላን ደሃ፣ አንዱን እርኩስ ሌላን ቅዱስ አድርገው ለማቅረብ ሞክረዋል፡፡ በሁለቱም በኩል ችግር የሚፈጥሩ የውስጥ ኃይሎች እንዲሰማሩ በማድረግ ሥርዓት አልባኝነት እንዲከሰት ያልተቆጠበ ጥረት አድርገዋል፡፡

ሰላማዊ ግንኙነቱን የማይፈልጉ ኃይሎች በፕሮፓጋዳናቅስቀሳ ዘርፍም ከአነስተኛዲዮ ጣቢያ፣ ከሚበተኑ ወረቀቶችና በስብሰባ ሊሠራጩ ከሚችሉ ሐሳቦች ጀምሮ እስከ ትልልቅ ሬዲዩ ጣቢያዎች፣ ጋዜጦች፣ መጽሔፍቶችና ሌሎች የፕሬስ ውጤቶችን በመጠቀም ለማጥላላት ጥረት ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ በፕሬስ ውጤቶች የሚካሄደው የጥላቻ ዘመቻ ከሰላማዊ ትግል የሚለየው እሳት እሳት፣ ጥይት ጥይት ስለሚሸት መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ጥላቻ እንደ አሜባ የመስፋፋትና የማደግ ባህሪ ስላው ኅብተረሰቡን ወደ ግጭትና ትርምስ ያደርሳል፡፡ ጦርነት ደግሞ በቅድሚያ የሚበላው ወጣቱን ክፍል ሰለሆነ የመሻሻልና የማደግ ዕድል አብሮ ያከትማል፡፡ በአንድ በኩል ወጣቱ ትኩስ ኃይልአጥፊ መሣሪያ በግጭት አውድማ ላይ ስለሚገናኝ ኅብረተሰብን ገደብ ለሌለው ጥፋት ይደርጋል፡፡ ልዩነቶችን በጦር ሜዳ ለመፍታት መሞከር ለሚቀጥለው ግጭት መሠረት መጣል እንጂ ችግሩን ከመሠረቱ ማስወገድ አይደለም፡፡ የጦርነት ሎጂክ ሌላ የጦርነት ሎጂክ እየወለደ የአምራችነት ሳይሆን የጦርኛነት ባህል ተስፋፍቶ ኅብረተሰብን ጉዳት ላይ ይጥላል፡፡ በሰዎችና በሰዎች፣ በብሔረሰቦችና በብሔረሰቦች መካከል ጥላቻ በሚስፋፋበት ሁኔታ ጉዳት የሚደርሰው በሰዎች ላይ ብቻ አይደለም፡፡ ዕፅዋት፣ አዝርዕት፣ እንስሳት ከባቢ አየርና ሌሎችም የሰው ሕይወት የተመሠረተባቸው ነገሮች ሁሉ ጉዳት ላይ ይወድቃሉ፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያ መሬት የተፈጥሮ ፀጋውን የተገፈፈው አካባቢው ለብዙ ምዕተ ዓመታት የጦርነት አውድማ በመደረጉ ምክንያት ጭምር መሆኑ ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለበትም፡፡ የውጭ ወራሪ ኃይሎች በሰሜን ኢትዮጵያ ለተደረጉ ጦርነቶች ምንጮች እንደነበሩ ግልጽ ነው፡፡

ስለዚህ ወደ ሕዝቦች አንድነት ለመጓዝ አስቀድመን የጥላቻን መርዝ ከመዝራት እንቆጠብ፡፡ ከዚያም ሕዝቦች እርስ በርስ እንዲገናኙ ነፃ እናድርጋቸው፡፡ ሕዝቦች በነፃ እየተገናኙ መነጋገር፣ መነገድና ሌሎች ማኅበራዊ ግንኙነቶችን ለመመሥረት በሚበቁበት ወቅት በመጀመርያ ሕዝባዊ ውህደት፣ ቀጥሎም ኢኮኖሚያዊ ውህደት፣ በመጨረሻም ፖለቲካዊ አንድነት መምጣቱ የማይቀር ይሆናል፡፡ ይህን እያደረግን የሕዝቦችን የውህደት ግንብ መገንባት እንጀምር፡፡ ይሳካልናል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...