Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትበአፍሪካ ቀንድ ጎህ ሊቀድ ነው ልበል?

በአፍሪካ ቀንድ ጎህ ሊቀድ ነው ልበል?

ቀን:

በታደሰ ሻንቆ

የታላላቅ አገሮች የንግድ ግብግብ ለንዝረቴ ተሰናዱ ይለናል

በዓለማችን ውስጥ ያልተጠበቁ አስገራሚ ድርጊቶች መከሰታቸው ዛሬም ቀጥሏል፡፡ የሰሜን ኮሪያና የአሜሪካ የፍጥጫ ቀረርቶ ወደ ሰላም ጎዳና (የኑክሌር ሙከራ ወደ ማቋረጥና ተቋማዊ አቅም ወደ መነቃቀል አቅጣጫ) ይጠመዘዛል ብሎ የገመተ አልነበረም፡፡ ይህንን መሳዩ ለግምት ያስቸገረ ነገር የሚከሰተው ግን ቅጥ አምባሩ በማይታወቅ የነገሮች አካሄድ ምክንያት አይደለም፡፡ ፕሬዚዳንት ትራምፕ እየተጠበበት ያለውን ከረር ረገብ፣ ራመድ ፈግፈግ የማለት፣ እንዲሁም በጋራ መድረክ አንድ ነገር በሰዋራና በተናጠል መንገድ ደግሞ ሌላ ነገር የማድረግ (አዲስ ያልሆነ) የጨዋታ ሥልት ለማስተዋል ከቻልን፣ ብዙ ነገሮች ፈትል እንዳላቸው እንረዳለን፡፡ ኪም ጆንግ ኡንና ዶናልድ ትራምፕ “ዋ!” ይባባሉ በነበሩበት ጊዜ ዴኒስ በሚባለው ዝነኛ አፍሪካ አሜሪካዊ የቅርጫት ኳስ ተጨዋች የሚመራ (የሰሜን ኮሪያን ቅርጫት ኳስ የመገንባት አደራ የተቀበለ) ቡድን በጎንዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ሥራ እያካሄደ ነበር፡፡ ትራምፕንና የሰሜን ኮሪያውን መሪ አግባብቶ ሲንጋፖር ላይ ለማገኛኘት የሰመረ ሚና በመጫወቱም፣ ይኸው ዝነኛ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ለመመሥገን በቅቷል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከሰሜን አሜሪካ፣ ከፓስፊክ እስያና ከአውሮፓ ታላላቅ ኢኮኖሚዎች ጋር አሜሪካ ያላትን ንግድ በተመለከተ፣ የንግድ ልውውጣችን ይመጣጠን አለበለዚያ የንግድ ጉድለቴን በታሪፍ ቅጠላ አጣጣለሁ የሚል አቋም ስትወስድ፣ ፍላጎቷን ለማሳካት ከቡድን ይበልጥ በተናጠል መሞከሯ አይዘነጋም፡፡ ፍላጎቷ አልሞላ ብሎ ወደ አሜሪካ በሚገባ የአሉሚኒየምና የብረታ ብረት ምርት ላይ ቀረጥ የመጣል ውሳኔን ካሳለፈች በኋላም ውሳኔው ያስከተለውን አፀፋና ሙቀት እየለካች ቆይታ፣ ጊዜው ሲደርስ የተወሰኑ ጎረቤቶችንና ነባር ባልንጀሮችን ለጊዜው ከታሪፍ ቅጣይ ውጪ አድርጋ ቻይና ላይ የማነጣጠር ዘዴ ተጠቅማለች፡፡ የብልጠት መነቃቃቱ ሌላውም ቤት ኖሮ፣ ወደ ትራምፕ አሜሪካ ፍላጎት የሚጠጋ ሲጠፋ የታሪፍ ቅጣዩ ለሁሉም ተደረገና “የንግድ ጦርነት! የታሪፍ ጥበቃ! ከዓለም ንግድ ድርጅት ስምምነት ውጪ!” የሚለው ጫጫታ ታላላቆቹን ሊያዳርስ በቃ፡፡

ሰኔ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. በካናዳ ተከፍቶ የነበረው የቡድን ሰባት ስብሰባም ቁልፍ መነጋገሪያ ይኸው የአሜሪካ ንግድ ጥበቃ ጉዳይ ነበር፡፡ ቡድን ሰባት ካናዳ ውስጥ አይሆኑ ሲሆን፣ ቻይና ውስጥ ደግሞ ቻይናና ሩሲያ በኒሻን ሽልማት በተኳለ የነባር ወዳጅነት መሞጋገስ የንግድ መስተጋብራቸውን የማሳደግ ስምምነት ያካሂዱ ነበር፡፡ ትራምፕ ይህንን እያየ ከቡድን ሰባት ሰብሰባ መዘግየቱ፣ በነባር አቋሙ ከመፅናትም ባለፈ ሩሲያ ተካትታ የቀድሞው ቡድን ስምንትነት እንዲመለስ ሐሳብ አቅራቢ መሆኑና ስድስቱን አገሮች ለብቻ ትቶ (ስብሰባ ሳይጠናቀቅ) ወደ ሲንጋፖር ማቅናቱ፣ የትራምፕ የጨዋታ ዘይቤ ሌላ መገለጫ ነው፣ ከፋፍሎ ወደሚፈልገው ስምምነት የሚጠጋ ውጤት የማግኘት፡፡ የማናውቃቸው ሥውር ሥራዎችም ይኖሩ ይሆናል፡፡ ፊት ለፊት እያየነው ባለው የአሜሪካ “ለብቻ መቅረት” እና ለጊዜው ወደ ስድስትነት ዝቅ ባሉት ታላላቆች ትይዩ የቻይናና የሩሲያ ሰሜን ኮሪያን ያልዘነጋና እስከ ላቲን አሜሪካ ክንዱን የዘረጋ ሠፈር የማበጀት አዝማሚያ ገና እየዋለለ ያለ (“መነጠል”፣ ቅልቅልና ሽግሽጉ ሁሉ ገና ያልጠራና ያልረጋ) ነው፡፡ ከቻይና ባለፈ የአውሮፓ ኅብረትንና እነ ህንድን አካሎ ከአሜሪካ ጋር እየተካሄደ ያለው የታሪፍ ሰቀላ ምልልስ ጉዞውና ውጤቱ መካረር ብቻ ላይሆን ይችላል፡፡ ብልጥ ለብልጥ ከተገማመቱ ወዲያ እንደገና ወደ መለሳለስና አማካይ ቦታ ላይ ወደ መገናኘት ሊመጡ ይችሉም ይሆናል፡፡ 

እንዲህ ባለ አኳኋን ውስጥ ያሉት ጌታ አገሮች በቀይ ባህርና በአፍሪካ ቀንድ ደጃችን አካባቢ ከሞላ ጎደል ጣቢያ አላቸው፣ እያበጁም ይገኛሉ፡፡ በየአገሮቻችን ውስጥም የየራሳቸው “የአጋርነት” ቋጠሮ አላቸው፡፡ በደፈናውም የዓለማችን ኢኮኖሚ ይሳሳባልና የግዙፎቹ ትንንቅ እኛንም መንዘሩ አይቀርም፡፡ የእርስ በርስ የንግድ ግንኙነታቸው ቀዝቅዞ እንደ አፍሪካ አገሮች ያሉ ደካማ አካባቢዎችን በማካካሻነት መሻማት ካመጡ፣ የመደራደርና ፍትሐዊ የንግድ ስምምነት ውስጥ የመግባት አቅማችን ይጨምር ይሆናል፡፡ የየጎራ ጭፍራ መሆንን የሚያስገድድ አጣብቂኝም ይመጣብን ይሆናል፡፡ የንግድ ግብግቡ ታላላቆቹን አገሮች በፋይናንስና በኢኮኖሚ ቀውስ እንዘጭ የሚያደርግ ጦስ ካስከተለ ደግሞ፣ አሁን እየታየ ካለው በራፍ ላይ በቆመና በሞትና ሕይወት መሀል ባለ ስደተኛ ላይ ከመጨከን (የገባውንም በተለያየ ሥልት መልሶ ከማብረር) የከፋና ደሃ አገሮችን የሚጎዳ ጣጣ የሚከተል መሆኑን አስቀድሞ መገመት ብልህነት ነው፡፡ ምክንያቱም በምዕራብ አገሮች ዘንድ የበረታው ስደተኛ ጠልነትና የቀኝ ፖለቲካ ገዥነት ከደሃ አገሮች የፍልሰት አፍላቂነት ማደግ ጋር በቅርብ የተገናኘ ስለሆነ፡፡ 

ለዚህም ነው ዛሬ ደሃ አገሮችን የሚያዋጣቸው የእርስ በርስ ትግግዝን መሠረት ባደረገ መፍጨርጨር ላይ መተማመን ነው የሚባለው፡፡ ትግግዛዊ መፍጨርጨሩ፣ ፀረ ድህነት ትግልን እያከበዱ ያሉ የሽብር፣ የትርምስ፣ የውጊያና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን የማቅለል ሥራዎችንና የየነጠላ አገርን አቅም ማነስ በኅብረት ማጣጣትን ሁሉ የተመለከተ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ምሥራቅ አፍሪካ/የአፍሪካ ቀንድ ትርምስ የሚወደውን ያህል ከፍተኛ የንግድ መንቀሳቀሻ የባህር መንገድ ያለበት እንደመሆኑ መሰናዶውና ፈተናው ልዩ ነው፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ አንዱ መሰናዶ የተያዘውን የመሰባሰብ አዝማሚያ ደረጃ በደረጃ በጋራ ገበያም ሆነ በኮንፌዴሬሽን አራምዶ፣ አገሮችን ለንትርክና ለጦርነት ሲዳርጋቸው የኖረውን የቅኝ ግዛት ድንበር እስከ መደምሰስ ማነጣጣር ነው፡፡ በቅኝ ገዥዎች የተቆራረሱ ብዙ አገሮች ከቅኝ ገዥዎች ጠንቅ ገና ነፃ እንዳልወጡ ሁሉ፣ የአፍሪካ ቀንድ አገሮችም ገና ነፃ አልወጡም፡፡ ነፃነታቸው የሚሟላው የቅኝ ግዛት ድንበሮቻቸውን ሰርዘው ኩታ ገጠም አምሳያ ሕዝቦቻቸውን በአንድ አገርነት ያገናኙ ጊዜ ነው፡፡ ይህ ትልም ከላይ የተንጠለጠለ የቀጣናው መንግሥታት አቋም ብቻ መሆን የማይበቃው፣ ከመንግሥታቱ አልፎ የፓርቲዎችና የኅብረተሰቦች እንቅስቃሴ እስከመሆን ስርፀትን የሚፈልግ ነው፡፡

የኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ በቀጣናው ዓይን

እስካሁን ለታዛቢም ለገላጋይም ግራ ሆኖ የቆየው የኢትዮ ኤርትራ ጠብ መፈታት ደግሞ የአፍሪካ ቀንድን አካባቢ የመሰባሰብ ዕድል ጉልህ ዕርምጃ ወደፊት የሚያስኬድ ነው፡፡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለኤርትራ ያቀረበው የአልጀርስን ስምምነት መሠረት ያደረገ፣ ሰላምን የመመለስና የሕዝብ ዝምድናን የማነፅ ሐሳብ ላይ ብዙ ቃላት ተወርውረዋል፡፡ የተወሰኑትን እያነሳን እንመዝናቸው፡፡

የድንበሩ ጉዳይ የሁለቱን አገሮች ተዋሳኝ ሕዝቦች መሠረት አድርጎ ነው መፈታት ያለበት አንዱ መቃወሚያ ነው፡፡ ከመጀመርያውም ከቅኝ ገዥዎች ውል ይልቅ ሕዝብ መሠረት ተደርጎ ቢሆን ኖሮ ስንት ውስብስቦሽ በተቃለለ ነበር፡፡ የሚሆን ቢሆን ዛሬም ከዚያ የተሻለ መልካም መንገድ የለም፡፡ ነገር ግን ካንደኛው ወገን በኩል ያለው አቋም፣ ከዚህ ቀደም በጋራ የተቋቋመው የድንበር ኮሚሽን የወሰነውን ይግባኝ የለሽ ውሳኔ ከመቀበል በቀር ሌላ ነገር መስማት የማይሻ እስከሆነ ድረስ ሕዝብ ላይ መሠረት ያደረገ ግልግል ላይ መድረቅ፣ የኤርትራ መንግሥት ያሁን አቋም ተቀይሮ ከእኛ ጋር እስኪገጣጠም ድረስ ጠቡ ይቆይ ብሎ እንደማለትም ነው፡፡ የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ላይ ሙጭጭ ያለ አቋም እስኪቀየር መጠበቅ ደግሞ የግድ ኢሳያስ አፈወርቂ እስኪቀየር ድረስ መጠበቅ ብቻ ላይሆን ይችላል፡፡ ኢሳያስንም የሚተካው መንግሥት ያንኑ አቋም ይዞ ሊቀጥል የሚችልበት ዕድል ዝግ አይደለምና፡፡ ቀን ባደረሰን ጊዜ ሰላም ይወርዳላ ከተባለ፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሰላምና ዝምድና ለሁለቱም አገሮችና ለቀጣው ያለው የህልውና ትርጉም አልተጨበጠንም ማለት ነው፡፡ ወይም ጠባችንንን ጊዜ ስሰኪፈታልን ስንጠብቅ ቀጣናችን አንድ ቀንድ አይደለም፡፡ አሥር ቀንድ ሊያበቅል እንደሚችል ዘንግተናል ማለት ነው፡፡ የአልጀርሱን ስምምነት የኤርትራ መንግሥት የተመድን ሰላም አስከባሪ ባስወጣና በኤርትራ ጀማሪነት ሁለቱም አገሮች መተነኳኮል ውስጥ በገቡ ጊዜ ተሽሯልና አሁን ጊዜው የአዲስ ስምምነት ነው ባይነትም፣ የፀብ ዘመንን አሳጥሮ ሰላምን በማስገኘት ረገድ እላይ ከተቸነው ሐሳብ አይሻልም፡፡ እንዲያውም ፀብን ለመፍታት የምር የሆነ ፍላጎትን ከሚያሳይ ይልቅ የአልጀርሱን ውሳኔ በዘዴ የማምለጥ ፍላጎትን የሚያሳይ መሳይ ነው፡፡ “የብዙ ሺዎች አጥንትና ደም የተገበረበትን መሬት መስጠት የኢትዮጵያውያንን መስዋዕትነት ከንቱ ማስቀረት ነው! ክህደት ነው!” ባዩ አቋም ከናካቴው ለሰላም ቦታ የሌለው፣ የአልጀርሱን ስምምነት ተመርኩዞ ሰላም ከኤርትራ ጋር መፍጠር ለቀጣናዊ (ትልቅ) አንድነት አንድ ውድ ማኮብኮቢያ መሆኑ ከአድማሱ ውጪ ነውና ሌላ የምለው የለኝም፡፡ ከአፄ ምኒልክ አንስቶ እስከ ኢሕአዴግ መንግሥት ድረስ ተሠሩ በሚባል ጥፋቶች ውስጥ ገብተው እየባዘኑ ሊያባዝኑን የሚሹት፣ የዛሬው ጊዜ ከደቀነው ርዕሰ ጉዳይ ውጭ ናቸውና ከእነሱም ጋር ጉዳይ የለኝም፡፡ 

በኢትዮጵያ መንግሥት የቀረበውን የእርቅ ሐሳብ ከሚደግፉ መሀልም፣ “ስለወደብና ስለአሰብ ነገር ማነሳሳት የለብንም፣ ወደብ ፈልገው እንጂ እኛን ፈልገው አይደለም እንዳይሉን መጠንቀቅ ስላለብን. . .” የሚል የእብለት “ንቃት”  ሊያስጨብጡን የሚሞክሩም አሉ፡፡ ወደብ የሚያሳስበን መሆኑ ገሃድ የወጣ እውነት ነው፡፡ ከ‹‹ባህር ምድር” ጋር ታሪክ ያላት አገር ለአጭር ጊዜ በቆየ የቅኝ ገዥዎች አፈና ምክንያት የወደብ መብት በማጣቷ መብከንከኗ ምን ያስገርማል? እንኳን ባለረዥም ታሪኩ የወደብ ጉዳይ ይቅርና የት ጋ እንዳለ እስከቅርብ ጊዜ የማይታወቀው ባድመ ከ1990ዎች ጦርነት ወዲህ የግብግብና የእርቅ ቁልፍ ለመሆን በቅቶስ አልነበር? አሁንም የኤርትራና የኢትዮጵያ ዝምድና ከተመለሰም በኋላ ነገር ዓለሙን በኤርትራ ወደብ አከራይነት፣ በኢትዮጵያ ወደብ ተከራይነት ላይ ለመደምመድ መሞከር ለብዙ የኢትዮጵያ ሰው የማይዋጥ መሆኑ አይቀርም፡፡ እንዲህ ያለው የአከራይና የተከራይ ግንኙነት በሌሎች ሁለገብ ተራክቦዎች ላይ ጥላ ሆኖ ማንገላታቱም የሚጠበቅ ነው፡፡ ይህ ሁሉ አያስገርምም፡፡ ለዚህ ነው ቅኝ ገዥነት የሰነቀረባቸውን የድንበር አጥር ማፍረስ ለሁለቱም ነፃነታቸው ነው የምንለው፡፡

በኢትዮጵያ በኩል ወደብ ብቻ የሚታየቸው፣ ከወዲያም በኩል ለኢትዮጵያ ብለው የሚያደርጉት የፅድቅ ሥራ ዓይነት የሚመስላቸው ካሉ ከእንቅልፋቸው ይንቁ፡፡ ሁለቱ አገሮች በፀብና በኩርፊያ የኖሩበት ጊዜ ያስገነዘበው ትልቁ እውነት፣ አንዳቸው ያለ ሌላቸው ህልውናቸው የተሟላ እንደማይሆንና በቀይ ባህር አካባባቢ ጥቅማቸውንና ታፋሪነታቸውን ሊያስከብሩ በማይችሉበት ደረጃ የሚኮሰምኑ መሆናቸውን ነው፡፡ 

የአልጀርሱን ስምምነት ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ በሁለቱም አገሮች በኩል የሚጎረብጥና ቅሬታ የሚፈጥር ነገር አያጣውም፡፡ ሁለቱም አገሮች በቀጣናዊ መሰባሰብ ዕይታ ውስጥ የኢትዮ ኤርትራ ሕዝቦች ዕጣ የማይነጣጠል መሆኑን የተረዱ እስከሆኑ ድረስ፣ የሚጎረብጡ ነገሮችን በድርድር ማለስለስ አያዳግትም፡፡ የድንበር ኮሚሸኑን የድንበር መስመርና የካሳ ጉዳይን ማክረር ለማይነጣጠል ዕጣቸው አስፈላጊ አይደለም፡፡ ከዚህ ዕይታ አኳያ ድንበር ማስመር ውስጥ ቢገባ እንኳ፣ ድንበርተኛ ሕዝብን በማያስከፋ አኳኋን እያካካሱ ለማረቅ አይከብዳቸውም፡፡ ሌላው ቢቀር የድንበር ኮሚሽኑን የድንበር መስመር ተቀብለው በሕዝብ ላይ ወዲህ ነህ ወዲያ ነህ የሚል መረበሽ ሳንፈጥር የምድር ላይ ሥራውን ለተወሰነ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ እናዘግየውና፣ የዝምዳችንን ጥንካሬ ዓይተን እንመለስበታለን የሚል ውሳኔ ላይ መግባባት ሞት የሚሆን አይመስለኝም፡፡ ዋናው ነገር፣ በሁለቱም በኩል የቶሎ ቶሎ ቤት ያልሆነና ዕጣቸውን በአፍሪካ ቀንድ ዓውድ ውስጥ የተመለከተ የጽኑ ሰላምና ዝምድና መሠረት መጣላቸው ነው፡፡

ይህ ብቻውን መቼ ሊበቃ? በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ጠንካራ የመረጋጋትና የልማት መልህቅ መሆንና የቀጣናዊ መሰባሰብ መሳኪያ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ራሱ እየተደጋገፉ የግራ ቀኝ ውዝግቦችን ማራገፍ፣ በዴሞክራሲ ሥርዓት፣ በፖሊሲዎችና በመንግሥታዊ ጠባይ ሁሉ መቀራረብንና ትምምን መፍጠርንን ከሁለት ሦስትነት ወደ አንድ አገርነት ማለፍን የግዝፈት መደምደሚያ አድርጎ ቅርብ አለማደርን ይጠይቃቸዋል፡፡

ለመሆኑ የኢትየጵያ ጓዳ ጎድጓዳ ለግዝፈት ዝግጁ ነው?

ለረዥም ዘመን ባዳቀቀን አፈና ላይ 27 ዓመታት የተሟሸንበት የተበጣጠሰ አተያይ ታክሎ ካፈራነው የጥላቻ፣ የግጭት፣ የግድያና አንዳችን ሌላችንን የማፈናቀል ሀብት ጋር ልፊያ እንደያዝን መሆናችንን ከአኅጉራችን የመሰባሰብ ድምፅ ጋር ስናስተያይ “ዘመን ጥሎን ለካ የትና የት ሄዷል?” ያስብላል፡፡ “ክልል” ወይም ልዩ አስተዳደር ልሁን ባይ ትንንሽ ድንኳን ተከላ ውስጥ የምንትረከረክም ቆም ብለን ዙሪያችንን እንይና “ወይ ጉዳችን! የት ጋ ነው ያለነው!” እንበል፡፡ ድንኳን ውስጥ የተወሸቅንም ከድንኳን ብቅ ብለን ቀጣናችን ውስጥ ምን እየተባለ እንደሆነ እናድምጥ! በብጥስጣሽ ብሔርተኝት እንደተቀሰፍን ያለን፣ ዝናብ ባለበት ሰፊ መስክ ውስጥ እዚያም እዚያም እርስ በርሳችን ውስጥ ጭንቅላት ቀብሮ ከመመሰግ ባልተለየ አኳኋን ውስጥ እንዳለን ይታየን!

የሁለት ወገን መስማማትን የሚያስገኝ የተሻለ የፀብ ማፍረሻ አማራጭ በሌለበት፣ በእጅ ያለውን የአልጀርስ ስምምነት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባነሳ ጊዜ “ክህደት ተፈጸመ!”፣ “ኢሳያስን ከውድቀት ለማዳን!” ብሎ በሠልፍም ሆነ በመግለጫ ለመኮነን የቸኮልን፣ የአልጀርስ ስምምነትን ይዞ ወደ ሰላም መምጣት ግብ ሳይሆን መንገድ መሆኑ ይገለጥልን! እውነቱ እየታወቃችሁ አጋጣሚውን ለድጋፍ ችግር መነገጃ ማድረግ የበለጠባችሁ ከነበራችሁም፣ ሕዝብ ከሰላምና ከዕርቅ በሚያገኘው ጥቅም ላይ ልቡ እንዲሸፍት በማድረግ የፖለቲካ ትርፍ ለማትረፍ መሞከር አይረቤ ንግድ እንደሆነ ይታያችሁ! በተፋጣጭ ጥጎች ውስጥ ሐሳቦችንና አድራጎቶችን እያስገቡ መሰደር ኋላ ቀርነት ነው፡፡ ሐሳቦችንና አድራጎቶችን የሚበጁ፣ የማይበጁ ብለን እንከራከርባቸው እንጂ የኢትዮጵያዊነት መመዘኛ (አገር የመካድና ያለመካድ ጉዳይ) አናድርገው!! ኢትዮጵያዊነትን የመለካት ፈራጅነትንስ ማን ሰጥቶን?! ሮጦ ፍርድና ኩነና ውስጥ መግባት ከሌላው መሻልን አያሳይም፡፡

ትልቅነት፣ ቅሬታቸውን ያለ ኩነና እንደገለጹት የኢሮብ ሠልፈኞች ሆኖ መገኘት ነው፡፡ ትልቅነት ኩነናን በኩነና ሳይከፍሉ ጨዋ ትችት መስጠት ነው፡፡ በሰላም ሐሳቡ ምክርና አወሳሰን ላይ አጋር ድርጅቶች ሳይገኙ በሚል “ተቆርቋሪነት” በኩል አሳብሮ ቅሬታ ቢጤ የመሰንቀርን አሮጌ ዘዴ መጠቀምም ለትዝብት ያጋልጣል እንጂ ሞገስ አያስገኝም፡፡ ለብሔረሰብ አሳቢ መስሎ ወጣቶችን ከጀርባ እየወሰወሱ ወደ ጥፋት መማገድ የትንሽነት ልኩ አዘቅት የወረደ ነው፡፡ በአጭሩ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ለኢትዮጵያም፣ ለቀጣናችንም፣ ለዘመናችም የሚመጥን አተያይ፣ ምግባርና የፖለቲካ ፓርቲ አደረጃጀት ይኑረን!!

ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በታየው ከዋና ከተማችንና ከተለያዩ አካባቢዎች የተሰባሰበ ብሔረ-ብዙ ኢትዮጵያን አንጣሎ በነበረው ትዕይንት መገባደጃ ላይ የተሰነዘረው የቦምብ ጥቃት፣ ዓላማው ጠንቋይ የሚያስፈልገው አልነበረም፡፡ ማንም ያድርገው ማን፣ ዓላማው አገር ምድር ሕዝብ (ያለብሔረሰብ ልዩነት) የተስፋ ብርሃን ባደረገው ጠቅላይ ሚኒስትር ላይ ጉዳት አድርሶ በዚያ ሥፍራ የነበረ ሥፍር ቁጥር የሌለው ሕዝብና የአዲስ አበባ ነዋሪ በደም ፍላት ቀውሶ፣ በአራቱም ማዕዘናት እንደ ቋያ የሚስፋፋ የመጨፋጨፍ ድብልቅልቅ እንዲከፍት ለማድረግ ነበር፡፡ ከዴሞክራሲ ጉዟችን ፋንታ በዚህ ዓይነቱ ሰቅጣጭ መጨፋጨፍ እንጠቀማለን የሚሉ እንዴት ያሉ ህሊና ቢሶች ይሆኑ?! የተቆጣ ሕዝብ ለማሰብ ጊዜ የለውምና ሮጦ ጥቃት የሚከፍተው በጠላው ላይ ይሆናል በሚል አስሊነት (የእነሱ እጅ በደም ሳይቆሽሽ) ቁርሾ ለማወራረድ የፈለጉ ወፈፌዎች? የእርስ በርስ መጨፋጨፍ ሲፋፋም አገር መቁረጥ/ማስቆራረጥ ይቀለናል ያሉ የአዕምሮ ድንኮች? ብዙ ደም በጎረፈበት ሰዓት ላይ፣ በነፃ ዕርምጃና በጦር ፍርድ ቤት የሚቀጣ “ጊዜያዊ” ወታደራዊ አገዛዝ ብናውጅ፣ ሕዝብ ከሰማይ ወረዳችሁልን ብሎና እግር ስሞ ይቀበለናል ብለው ያደቡ ፈላጭ ቆራጮችና ዘራፊዎች?

መስቀል አደባባይ የተያዙት ሰዎች የምርመራ ውጤት ከእነዚህ አቅጣጫዎች ውጪ ይሁንም አይሁንም፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እነዚህን የአደጋ መምጫዎች መቼውንም ሊዘናጋባቸው አይገባም፡፡ የጠጠር መጣያ ያልነበረው በሚባል ደረጃ አዲስ አበባ ላይ ያስገመገመው የሰኔ 16 ትዕይንት ላሳየው ለሸር ያለመበለጥ ብስለት፣ ጥቃት አድራሾችን የመያዝና ቁስለኞችን የመንከባከብ ቆራጥነት የማይረሳ ክብር ይድረሰው! መሰሪዎች የመበላላት ድግስ እየደገሱልን መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ሆኖ፣ በአዲስ አበባ የታየው ብስለትና ንቁነት የሁሉም አካባቢዎች ይሁን!! እንኳ ግጭትና መፈናቀል ኮሽታ የማይሰማበት የሕዝቦች እጅ ለእጅ መያያዝ የሞት ሽረት ጉዳይ መሆኑን አገር ልብ ይበል!!! ይህ አደጋ ከተከሰተ በኋላ የታጠቀውን የመንግሥት አውታር ለዴሞክራሲ አገዛዝ ታማኝ አድርጎ የማዘጋጀት ሥራ በቀላልና በአጭር ጊዜ እንደማይገባደድ፣ የመረጃና የደኅንነት አውታሩም የሕዝብንና የአገሪቱን ደኅንነት በመጠበቅ ረገድ ለአንድ ሰኮንድም ሳይዘናጋ ነቅቶ የመጠበቅ አቅሙ መጠናከር እንዳለበት አስተዋሽ የሚሻ አይመስለኝም፡፡

በመጨረሻም ጠሪም ተጠሪም የማይጠይቅ አንድ የርብርብ ድርሻ ላስታውስ፡፡ የዴሞክራሲ ግንባታ ጅምራችን ተስፋው ያማረና የሁሉን ርብርብ የሚሻ በመሆኑ ምክንያት፣ በትጥቅ ነክ ትግል ውስጥ የነበሩ ወደ ሰላማዊ መንገድ እየመጡ መሆኑን ለማየት በቅተናል፡፡ ኢንዱስትሪያዊ ኢኮኖሚ ለመገንባት የምትውተረተረው አገራችን ከዓለም ኢኮኖሚ ጋር ያላት ትስስር እየጨመረ እንደመሄዱ ከዓለም የፋይናንስና የካፒታል ገበያዎች/ኩባንያዎች ጋር የምትተሳሰርበት ጊዜ መጥቷል፡፡ በሌላ በኩል በአካባቢዋ ውስጥ ከጎረቤቶቿ ጋር ኢኮኖሚያዊ ውህደት ወደ ማድረግ እያመራችም ነው፡፡ እነዚህ ጉዞዎች እንዳይባርቁ፣ በተለይም እያረፈ ዓለምን በሚጎበኘው የፋይንስና የኢኮኖሚ ቀውስ መንኮትና መጨራመት የአገሪቷ ዕጣ እንዳይሆን፣ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ግንባታዋ በደንበር ገንተር እንዳይዋጥ፣ የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚንና ፋይናንስን ጉራንጉርና የጨዋታ ጥበቦችን በቅርብ የምውታቁ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ሊቆች፣ እንዲሁም ባለገንዘቦች፣ ቴክኖሎጂስቶችና ልዩ ልዩ ቴክኖሎጂዎችን ቀስሞ ወደ አገር የማሸጋገር (ወደ ሥራ የመቀየር) ዕድሉ ያላችሁ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ተወላጆች ሁሉ፣ ኢትዮጵያ ከምክር እስከ ቀጥተኛ ተሳትፎ ድረስ አስተዋጽኦዋችሁን ከመቼውም ጊዜ በላይ የምትሻበት ይህ ያሁኑ ወቅት ይመስለኛል፡፡ ድል ለዴሞክራሲና ለኢኮኖሚ ግስጋሴያችን!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...