Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የኢኮኖሚ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያስፈልገናል››

አቶ መስፍን ነመራ፣ የፋይናንስ ባለሙያ

አቶ መስፍን ነመራ ከ17 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ውስጥ በልዩ ልዩ ኃላነት መስክ ያገለገሉ የፋይናንስ ባለሙያ ናቸው፡፡ እኚህ የቀድሞ የባንኩ ባለሙያ ከ1997 ዓ.ም. ወዲህም በፖለቲካው መስክ ተሳትፎ በማድረግ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በመሆን ማገልገላቸውም ይታወቃል፡፡ ምንም እንኳ ከብሔራዊ ባንክ ከተለዩ 20 ዓመታትን ቢያሳልፉም፣ አሁንም ድረስ በግላቸው በፋይናንስና በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ በማማከርና በምርምር ሥራዎች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ላለፉት አሥር ዓመታት ከፋይናንሱም ከፖለቲካውም ርቀው ቢቆዩም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ እየታዩ ያሉት የኢኮኖሚና የፋይናንስ ችግሮች ካሉበት ብቅ እንዲሉ እንዳስገደዷቸው ይገልጻሉ፡፡ በብሔራዊ ባንክ ውስጥ ስለሚታዩ የአሠራር ችግሮች፣ መንግሥት በቅርቡ ወደ ግል እንደሚዛወሩ ስላሳወቃቸው ተቋማት፣ ስለውጭ ምንዛሪ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስለሚኖራቸው አስተዋጽኦና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ብርሃኑ ፈቃደ ከአቶ መስፍን ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡-እንደ መነሻ ከምንዛሪ ለውጡ እንነሳ፡፡ የምንዛሪ ለውጡ የተባለውን ውጤት ሲያመጣ አልታየም፡፡ የወጪ ንግድን ያሻሽላል ቢባልም አልሆነም፡፡ ከዚህ ይልቅ ሌሎች አማራጭ ዕርምጃዎችን መውሰድ አይቻልም ነበር?

አቶ መስፍን፡- የብር የመግዛት አቅም እንዲቀንስ መደረጉ ላይ አሁን እየተነጋገርን ባለንበት ወቅት ሌላ ተጨማሪ የምንዛሪ ለውጥ ሊያስፍልግ የሚችልበት አካሄድ እየታየኝ ነው፡፡ የብር አቅም ከሚገባው በላይ ዋጋ የተሰጠው ይመስላል፡፡ በመደበኛው የባንክ የምንዛሪ ተመንና በጥቁር ገበያው መካከል ያለው የዋጋ ልዩነት ወደ አሥር ብር ገደማ እየተጠጋ ነው፡፡ ያለው የምንዛሪ ለውጥ በወቅቱ አስፈላጊ ነበር ወይስ አልነበረም ወደሚለው መግባት አልፈልግም፡፡ በመሠረቱ ግን የምንዛሪ ለውጥ የምታደርገው እንዲሁ ዝም ብለህ ሳይሆን፣ የማዕከላዊ ባንኩ ሊያከናውናቸው ሲገባው ያልሠራቸው በርካታ ሥራዎች በመኖራቸው ነው ችግሮች የሰፉት፡፡ በአጭሩ ብሔራዊ ባንክ ዋና ሥራው ገንዘብ አሳትሞ ወደ ገበያው እንዲሠራጭ ማስገባት፣ ባንኮችንና ሌሎችንም የፋይናንስ ድርጅቶች መቆጣጠር፣ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ማስተዳደር ነው፡፡ ይህ በጠቅላላው የአገሪቱን የገንዘብ ፖሊሲ የሚመለከት ተግባር ነው፡፡ ሆኖም ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ የትኛውም የብሔራዊ ባንክ ባለሥልጣን ስለገንዘብ ፖሊሲው፣ ስለምንዛሪ ተመኑ፣ ስለዋጋ ግሽበቱ፣ ወዘተ. በተገቢው መንገድ ሲያብራራ ሰምቼ አላውቅም፡፡ ዋናው ሥራው ይህ መሆን ሲገባው ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ማተሚያ ቤት ሆኖ ነው የኖረው፡፡ የግል ባንኮችን መቆጣጠር ሥራው ነው ሲባል ተንከባብኮ ማሰደግ እንጂ እየቀጣና እየገረፈ መምራት አይደለም፡፡ ባንኮቹ ሲቀጡና ሲገረፉ ነው የኖሩት፡፡ የምንዛሪ ለውጡን ብሔራዊ ባንክ ራሱ አጥንቶ ለመንግሥት አስፈቅዶ ይሁን ወይም አድርግ ተብሎ ታዞ ስመሆኑ አናውቅም፡፡ ከዕርምጃው ወዲህ ከምንዛሪ ለውጥ መገኘት የነበረበትን ጥቅም አግኝተናል ወይ? በምንዛሪ ለውጡ ሳቢያ የወጪ ንግዱ ተነቃቅቶ ገቢው ጨምሯል ወይ የሚሉትን ለመመለስ ከዘርፉ ራቅ ብዬ ስለቆየሁ ዝርዝር አኃዙ ባይኖረኝም የምንዛሪ ለውጡ ከጥቅም ይልቅ ጉዳት ስለማምጣቱ ግን የሚያሳዩ ሁኔታዎች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ዕርምጃውን የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የዋጋ ግሽበትን ያባብሳል በማለት ከጅምሩ ሲቃወሙት ቆይተዋል፡፡ ብሔራዊ ባንክ የወጪ ንግዱን ለማቀላጠፍ በማሰብ የወሰደው ዕርምጃ ስለመሆኑ ቢያስታውቅም የወጪ ንግዱ ቁልቁል ከመጓዝ አልተገታም፡፡ ለወጪ ንግድ መዳበር አንደኛው መሣሪያ ቢሆንም ለዚህ ሲባል ግን ምንዛሪ እንዲለወጥ መደረጉን እንዴት ገመገሙት?

አቶ መስፍን፡- በንድፈ ሐሳብ ደረጃ የወጪ ንግድን ለማበረታታት አንዱ ሥልት ቢሆንም፣ ለምንዛሪ ለውጡ በአፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ የወጪ ንግድ ዘርፍ ግን የለንም፡፡ አብዛኛው የወጪ ንግድ ሸቀጦቻችን የግብርና ምርቶች ናቸው፡፡ ሌሎች ዘርፎች ከመንግሥት ይዞታ ነፃ የሚደረጉበት አካሄድ በሚገባ ሳይፈጠር፣ ለወጪ ንግድ ማበረታቻ ብቻ በሚል ምክንያት የምንዛሪ ለውጥ ማድረጉ እንዳልሠራ ታይቷል፡፡ የወጪ ንግዱ አፈጻጸም ባለበት ከመቆም ባሻገር ወደ መቀነሱ እየመጣ ይመስላል፡፡ ይህ በሆነበት ወቅት የምንዛሪ ተመን ማስተካከያ ማድረጉ አስፈላጊ አልነበረም ማለት ነው፡፡ ያመጣው ጥቅምም የለም፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ 16 የግል ባንኮች አሉ፡፡ አቅማቸው ግን በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ኢኮኖሚው የሚፈልገውን ገንዘብ እያንቀሳቀሱ ነው? ኢኮኖሚው የሚፈልገውን የፋይናንስ አቅርቦት በማስፋፋት አኳያ የሚጠበቅባቸውን እየተወጡ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ መስፍን፡- ኢትዮጵያ ውስጥ 16 የግል ባንኮች ቢኖሩም በኬንያ ወደ 50 ገደማ የግል ባንኮች አሉ፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ ባንኮች የመስፋፋት ዕድል አላገኙም፡፡ ይባስ ብሎም ቁጥራቸው የበዛ ይመስል በግድ ተዋህዳችሁ ጥቂት አቅም ያላቸውን ባንኮች ውለዱ እየተባሉ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሌሎች የግል ባንኮች ላይ የተጣለው የ27 በመቶ የብሔራዊ ባንክ ቦንድ አይመለከተውም፡፡ የግሎቹን ግን እየጎዳቸው ነው፡፡ ይህንን ችለው እየተንቀሳቀሱ ባሉበት ወቅት ካለፈው ዓመት ጀምሮ የብድር አሰጣጣቸው ላይ ጣሪያ ተቀምጦባቸዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ካበዱሩት ገንዘብ ላይ በዚህ ዓመት ከ16.5 በመቶ በላይ እንዳያበድሩ ታዘዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የባንኮች የቅርንጫፍ ማስፋፋት ሥራ ቆሟል፡፡ ብሔራዊ ባንክ በሌሎች ወሳኝ ሥራዎቹ ላይ እንደ መጨነቅ የግል ባንኮችን መቀጥቀጡ ላይ ነው የተጠመደው፡፡ የማውቃቸው የግል ባንኮች ኃላፊዎች ስብሰባ በተጠሩ ቁጥር ተሸማቀው እንደሚሄዱ ነው የሚናገሩት፡፡ ስድብና ዘለፋ ሁሉ እንደሚቀምሱ እንሰማለን፡፡ እርግጥ ነው የግል ባንኮችም በርካታ ድክመቶች አሉባቸው፡፡ ነገር ግን እስከነድክመታቸውም ቢሆን ለኢኮኖሚው ማበርከት የጀመሩትን የፋይናንስ ጥልቀት ወይም ፋይናንሺያለ ዲፕኒንግ አገልግሎት እንዳይሄዱበት እየገታቸው ነው፡፡ ግራ ተጋብተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት እየታየ ባለው ለውጥ ምን ይመጣ ይሆን ብለው እየጠበቁ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የፋይናንስ ፖሊሲ እንደሚከተል ይናገራል፡፡ በአንፃሩ መንግሥት ሰፋፊ ፕሮጀክቶችን ይተገብራል፡፡ አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች የሚጠይቁት ፋይናንስ ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አቅም በላይ ነው፡፡ መንግሥት በሚከተለው የኢንቨስትመንት ፖሊሲና ብሔራዊ ባንክ በሚከተለው የገንዘብ ፖሊሲ መካከል መግባባት አለ ማለት ይቻላል?

አቶ መስፍን፡- የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ምንድነው የሚለውን አላውቀውም፡፡ የማታውቀው ለምንድነው ብትለኝ ሹማምንቱ አውጥተው የነገሩን ነገር የለም፡፡ ጥብቅና አቅርቦትን የመቀነስ ፖሊሲ ይከተላል ለሚለው ለእኔ ግን እንደዚያ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም አንድን የግል ባንክ ካለፈው ዓመት ብድርህ አኳያ ከ16.5 በመቶ በላይ እንዳታበድር እያልከው፣ንግድ ባንክና ልማት ባንክ ግን ያለ ገደብ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ወደ ሥርጭት ሲያስገቡ የሚናገራቸው ያለ አይመስልም፡፡ ብሔራዊ ባንኩ ወደ ገንዘብ ማተሚያ ቤትነት የተለወጠ ይመስለኛል፡፡ ቁጥሮች በእጄ የሉኝም እንጂ በሚገባ ቢታይ ብዙ ችግሮች ይወጣሉ፡፡ የገንዘብ አቅርቦት በምን አግባብ እንደሚመራ ግልጽ አይደለም፡፡ እኔ ብሔራዊ ባንክ ውስጥ ሥሠራ በነበረበት ወቅት መንግሥት ምን ያህል ገንዘብ መደበር እንዳለበት ጥብቅ በሆነ አሠራር ይመራ ነበር፡፡ መንግሥት ባለፈው ዓመት 100 ሚሊዮን ብር ገቢ አግኝቶ ከሆነ ዘንድሮ መበደር የሚችለው በቀጥታ አድቫንስ መልክ ይህንን ያህል በመቶ፣ ከግምጃ ቤት ሰነዶች ይህንን ያህል በመቶ ተብሎ ይቀመጥና ተደማምሮ እንዲበደር የሚፈቀድለት መጠን፣ ካለፈው ዓመት ገቢው እንዳይበልጥ ሁሉ ይደረግ ነበር፡፡ ይህ አሁን የለም፡፡ መንግሥት የሚፈልገውን ነገር ሁሉ የሚያገኝበት ወቅት ላይ ነው የምንገኘው፡፡ በሌሎች አገሮች ውስጥ የማዕከላዊ ባንክ ገዥዎች በሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ አባላት አይደሉም፡፡ ገለልተኛ ሆነው ነው የሚሠሩት፡፡ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመስመር የወጣ ነገር ሲጠይቁት አይሆንም ማለት መቻል አለበት፡፡ የማይሆነው ከሙያው አኳያ በምክንያት ነው፡፡ ይህ ካላስማማው ሥልጣኑን ይለቃል፡፡ በእኛ አገር ግን የብሔራዊ ባንክ ገዥ በመሆን ለዓመታት በኃላፊነት መቀመጥ የቻሉት ከሚያውቁ ይልቅ ለመንግሥት ኃላፊዎች የተመቹ በመሆናቸው ነው ብዬ አስባለሁ፡፡  

ሪፖርተር፡- የገንዘብና የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፀደቀላቸው የመጪው ዓመት በጀት ዕቅድ ውስጥ መንግሥት ከአገር ውስጥ የሚበደረው ገንዘብ ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ተናግረው፣ ይህ ገንዘብ ከጠቅላላው በጀት ውስጥ ከሦስት በመቶ በታች በመሆኑ የዋጋ ግሽበት አያስከትልም ብለው ነበር፡፡ ይህንን እንዴት ያዩታል?

አቶ መስፍን፡- መንግሥት ለበጀት ጉዳይ ምን ያህል ገንዘብ እንደሚበደር አናውቅም፡፡ የተጠቀሰው አኃዝ ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ የተፈለገ መጠን ሊሆን ይችላል፡፡ ማረጋገጥ አንችልም እንጂ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከንግድ ባንክ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ስለመበደረቻው እንሰማለን፡፡ እንዲህ ያለው ገንዘብ በበጀት ውስጥ ተካቷል ወይ ከተባለ በእኔ ግምት ከበጀት ውጭ ይመስለኛል፡፡ ትንሽ ፋይንሱን እናውቃለን የምንልና የአገር ጉዳይ የሚያሳስበን ሰዎች መረጃውን በሚገባው መጠን አናገኝም፡፡ ነፃ ፕሬስም እንደሚገባው ስሌለ፣ ያለውም ቢሆን በቅጡ ስለማይንቀሳቀስ እንዲህ ያሉ ግዙፍ የመንግሥት ብድሮች ሚስጥር ሆነው ይገኛሉ፡፡ የምርት አለመጨመር እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የዋጋ ግሽበቱ ዋናው ምክንያት የገንዘብ አቅርቦት ከፍተኛ መሆኑ ይመስለኛል፡፡ ሰሞኑን ከገበያ እንደምንሰማው የዋጋ ግሽበቱ በየዕለቱ እየጨመረ ነው፡፡ ብዙ ማወቅ ሲገባን የማናውቃቸው እንድናውቃቸው የማይደረጉ ነገሮች በርካታ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ከሰሞኑ ንግድ ባንክ እስከ 400 ቢሊዮን ብር ሊመለሱ የማይችሉ ብድሮችን ስለመስጠቱ እንሰማለን፡፡ ንግድ ባንክ ስለዚህ ጉዳይ ማስተባበያ ሊሰጥበት ይገባዋል፡፡

ሪፖርተር፡– አገሪቱ ከባድ የብድር ችግር ውስጥ ገብታለች፡፡ የብድር ክምችቷ አሳሳቢ ወደሚባለው ደረጃ በማደጉ ከፍተኛ የብድር ዕዳ ወዳለባቸው አገሮች ተርታ የመግባቷ ጉዳይ እየታየ ነው፡፡ የአገሪቱ የክፍያ ሚዛን ጉድለትም ብሶበታል፡፡ የወጪ ንግዱም እያሽቆለቀለ በመሆኑ እነዚህ ጉዳዮች ላይ ምን ዓይነት አፋጣኝ መፍትሔ ማምጣት ይቻላል? ምን ዓይነት ለውጦች ሊመጡ ይችላሉ? ምን ዓይነት የገንዘብ ፖሊሲስ ችግሩን ሊያስተካክለው ይችላል?

አቶ መስፍን፡- ተለዋዋጭ የማክሮ ኢኮኖሚ ይዘቶች የተያያዙ ናቸው፡፡ የአገር ውስጥ ብድር፣ የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲ፣ የመንግሥት ገቢና ወጪን የሚመለከተው የፊስካል ፖሊሲና ሌሎችም በማዕከላዊ ባንኩ ባለሙያዎች ተተንትኖ ልኬቱ ምን ያህል መሆን እንደሚገባው መቀመጥ አለበት፡፡ ከዚህ በላይ መሆን የለብትም፣ መብለጥ የለበትም ተብሎ በባለሙያዎች መቅረብ መቻል ነበረበት፡፡ የዕዳ ክፍያ ጫናቸው በዝቶ በአሁኑ ወቅት በዓመት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ መክፈል እንደተጀመረ ሰምነተናል፡፡ ይህ ጫና ሊጨምር ይችላል፡፡ የአገሪቱ የወጪ ንግድ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር ማለፍ አልቻለም፡፡ ለወደብ ኪራይ በዓመት ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ እየወጣ፣ 1.2 ቢሊዮን ዶላር የብድር ዕዳ በሚከፈልበት ወቅት ከወጪ ንግድ የሚገኘውን ገቢ እነዚህ ሁለቱ ጉዳዮች ብቻ የሚወስዱት ከሆነ፣ የሌሎች እንደ መድኃኒት፣ ነዳጅ ግዥ፣ ወዘተ. ያሉት ወጪዎች ሲታከሉበት ወዴት ልናመራ እንደምንችል ግልጽ ነው፡፡ አኃዛዊ መረጃው ያላቸው ሰዎች ይህንን ተንትነው ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ 

ሪፖርተር፡- ብሔራዊ ባንክ ለባንኮች የሚከፍለው የተቀማጭ ወለድ ገንዘብ አለ፡፡ ለአብነት ለ27 በመቶ የባንኩ ሰነድ ግዥ የግል ባንኮች የሚከፈላቸው ወለድ ከአራት በመቶ አይበልጥም፡፡ በአንፃሩ የግል ባንኮቹ ከብሔራዊ ባንኩ ሲበደሩ ከ16 በመቶ በላይ ወለድ ያስከፍላቸዋል፡፡ ይህ በመሆኑም ባንኮች ለአጭርና መከላከለኛ ጊዜ ተበዳሪዎቻቸው ገንዘብ ሲያቀርቡ ከ20 በመቶ በላይ ወለድ የሚጠይቁበት አሠራር እየታየ ነው፡፡  ጫናው ዞሮ ዞሮ ሕዝቡ ላይ እያረፈና የባንክ አስቀማጮችም በገዛ ገንዘባቸው ተጎጂ እየሆኑ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ጉዳይ እርስዎ የብሔራዊ ባንክ ባልደረባ በነበሩ ጊዜ እንዴት ነበር የሚቃኘው? 

አቶ መስፍን፡- እንደ አጋጣሚ እኔ ብሔራዊ ባንክ በነበርኩ ጊዜ የግል ባንኮች ገና በመቋቋም ላይ ነበሩ፡፡ የግክ ባንኮች ከብሔራዊ ባንክ ስለመበደራቸው ብዙም አላውቅም፡፡ ከሆነም በአሁኑ ወቅት አስፈላጊ አይመስለኝም፡፡ ለምን ቢባል ማበደር ስላልቻሉ ከሚገባው በላይ ገንዘብ በእጃቸው ይዘው ቁጭ ስላሉ ነው፡፡ ነገር ግን ለ27 በመቶ የቦንድ ሰነድ አራት በመቶ ብቻ እየተከፈለም የህዳሴው ግድብ በዚህ አካሄድ መታገዙ ባልከፋ ነበር፡፡ ሌሎች የፋይናንስ ማፈላለጊያ ዘዴዎች መታየት ነበረባቸው፡፡ ትልቁን ዝሆን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከዚህ አሠራር ነፃ አድርጎ የግል ባንኮች ብቻ መጫን ተገቢ አይደለም፡፡ ይህንንም ችለው እየሠሩ ባሉበት ወቅት የብድር አሰጣጣቸው ላይ የተጣለው ገደብ፣ የብሔራዊ ባንክን አሠራር የሚያስኮንነው ነው፡፡ የግል ባንኮችን እንደ ጠላት የመንግሥት ባንኮችን እንደ ወዳጅ የሚያይበት አሠራር ቀርቶ ሁሉን ማዕከል ያደረገ አካሄድ መከተል ይኖርበታል፡፡ ቆም ብለን ማየት ያለብን ጊዜ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የግል ባንኮች በብሔራዊ ባንክ የሚወቀሱባቸው ጉዳዮችም በርካታ ናቸው፡፡ ባንኮቹ ከሚገባው በላይ የተከማቸ ገንዘብ አላቸው፡፡ የ27 በመቶ የቦንድ ግዥ እንዲፈጽሙ ታዘውም ከፍተኛ ትርፍ ማግኘታቸው አልቀነሰም በማለት ባንኩ የሚወስደው ዕርምጃ ባንኮቹን እንዳልጎዳ የባንኩ ገዥ ደጋግመው ሲናገሩ እንሰማ ነበር፡፡ ይህንን እንዴት ያዩታል?

አቶ መስፍን፡- ይህ እንግዲህ ከዓመት በፊት የነበረ መከራከሪያ ነው፡፡ ትርፋማነታቸው ላይ የሚነሳው እውነት ነው፡፡ ሌሎች አገሮች ውስጥ የማይታይ ዓይነት ትርፋማት ይታይባቸዋል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው በእኔ እምነት የውድድር ችግር የፈጠረው ነው፡፡ አዳዲስ ባንኮች እንዳይገቡ ከፍተኛ የካፒታል መጠን ተቀምጦባቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ይመስለኛል አዳዲስ ባንኮች ሲፈጠሩ ማየት ያልቻልነው፡፡ ኢትዮጵያ ግን አሁንም በርካታ ባንኮች ያስፈልጓታል፡፡ ውድድሩ ነፃና ገበያ ተኮር እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በየትኛውም አገር ለአስቀማጩ ሰባት በመቶ ወለድ ከፍሎ አበዳሪውን ከ20 በመቶ በላይ ወለድ የሚጠይቅ ከፍተኛ የወለድ ህዳግ አይቼ አላውቅም፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ጋር ሊያያዝ ከቻለ በዋጋ ግሽበት ሳቢያ ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝነው ስለዚሁ አነስተኛ ወለድም እናንሳ፡፡ የዋጋ ግሽበቱ ወደ 20 በመቶ እየተጠጋ ነው፡፡ የባንክ ተቀማጭ ወለድ ግን ሰባት በመቶ ነው፡፡ ይህ በመሆኑ ባንክ ገንዘብ የሚያስቀምጥ ሰው የገንዘቡ የመግዛት አቅም እየቀነሰበት እንደሚመጣ ግልጽ ነው፡፡ 

አቶ መስፍን፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ገንዘብ ባንክ ማስቀመጥ ለደህንነቱ እንጂ ከወለድ ትርፉ ለመጠቀም እንዳልሆነ የታወቀ ነው፡፡ ምክንያቱም የዋጋ ግሽበቱ ስለሚባለው ነው፡፡ የባንኮች ተቀማጭ በከፍተኛ ደረጃ ሊጭምር የቻለበት ዋናው ምክንያት የሚመስለኝ ግን በከፍተኛ ደረጃ ገንዘብ ስለሚታተም ነው፡፡ እንደ ደንቡ የአንድ አገር ማዕከላዊ ባንክ ገንዘብ አትሞ ወደ ኢኮኖሚው የሚያስገባው ያረጁ የገንዘብ ኖቶችን ለመተካት፣ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያስፈልገውን የገንዘብ አቅርቦት በማስላት ለማቅረብና ኢኮኖሚው መደበኛ በሆነው የንግድና መሰል እንቅስቃሴ ሳቢያ ገንዘብ በብዛት ሲያስፈልገው፣ እነዚህን ምክንያቶች ጠቅሰህ ገንዘብ አሳትመህ ማስገባትህን ታስታውቃለህ፡፡ እንደምናየው ግን መንግሥት የውጭ ምንዛሪ እንጂ ብር ሲቸግረው ሰምተን አናውቅም፡፡ ከእኛ የተሻለ የኢኮኖሚ ደረጃ ያላቸው አገሮች እኮ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ በመከተላቸው ሳቢያ የሠራተኛ ደመወዝ መክፈል ሲቸገሩ እያየን ነው፡፡ ሚናውን የሚወጣ የማዕከላዊ ባንክ ስላላቸው ገንዘብ እንደ ልብ አይለቀቅም፡፡ እኛ አገር ውስጥ ግን የብር አቅርቦት ችግር የለብንም፡፡ መንግሥት ገንዘብ የማይቸግረው ምን ቢኖር ነው የሚለውን ማየት ይገባል፡፡ በየጊዜው ምን ያህል ገንዘብ ታትሞ ወደ ኢኮኖሚው እንደሚገባ ግልጽ አይደለም፡፡ ይህንን ሚስጥር አለማድረግ የአገር ደኅንነትን አይነካም፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምን ያህል ነው ብድር የሰጠው? 400 ቢሊዮን ብር ስለማበደሩ እንሰማለንና እነማን እንደተበደሩት በዝርዝር ሊገለጽን ይገባል፡፡ በዚህ ዓመት ባንኩ ሒሳቡን ሲዘጋና ሪፖርት ሲያደርግ ማስደመጥ ያለበት መሠረታዊ የሚባሉ እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን ናቸው፡፡ የማይከፈሉ ሒሳቦች በግልጽ ምን ያህል እንደሆኑ መታወቅ አለባቸው፡፡ አለበለዚያ በምንሰማቸው ከፍተኛ የብድር ገንዘቦች መነሻነት ባንኩ ሊዘጋ የሚችልበት ሥጋት እአተፈጠረ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ተቀማጩና ካፒታሉ ምን ያህል እንደሆነ ባላውቅም፣ የሰማነውን 400 ቢሊዮን ብር ብድር መከፈል ካልቻለ ባንኩ አደጋ ውስጥ መግባቱ ነው፡፡ በሌሎች አገሮች ውስጥ እንዲህ ዓይነት ነገር ሲከሰት አስቀማጮች ገንዘባቸውን ለማውጣት ይጣደፋሉ፡፡ አንድ ባንክ እንዲህ ያለ ደረጃ ላይ ሲደርስ ብቻውን አይደለም የሚወድቀው ሌሎችንም ይዞ ነው የሚጠፋው፡፡ እንዲህ ያለው ጉዳይ በኢትዮጵያ እንዳይከሰት የባንኮችን የብድር መጠን፣ የተቀማጭ ሐሳብ ደረጃና ሌላውንም በየቀኑ ይከታተላል፡፡ ብሔራዊ ባንክ በዚህ ደረጃ ንግድ ባንክን ይቆጣጠራል ወይ የሚለውን መናገር ይቸግረኛል፡፡ እኔ ይህንን የሚነግረኝ ሰው ባገኝ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ንግድ ባንክ ምን ያህል ገንዘብ ለእነ ማን እንዳበደረ ማወቅ እፈልጋለሁ፡፡ ትንሽም ብትሆን በባንኩ ተቀማጭ ካለችኝ የባንኩን የብድር አሰጣጥ ሁኔታ የማወቅ መብት አለኝ፡፡ ምን ያህሉ የተበላሸና መደበኛ ወይም ተከፋይ ብድር እንደሆነ ማወቅ እፈልጋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ባንኮቹ ግን ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው የአምስት በመቶ የተበላሸ ብድር እርከን በታች እያስመዘገቡ ስለመሆናቸው ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡

አቶ መስፍን፡- ብሔራዊ ባንክ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እኮ ለሦስት ወራት የሚበቃ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እንዳለው ሲገልጽ ነበር እኮ፡፡ አሁን ግን ይህ እንዳልሆነ እየታየ ነው፡፡ ሪፖርት እንደ አቅራቢውና እንደሚቀርብለት አካል ሁኔታ ሊዘጋጅ የሚችል ነገር ነው፡፡ በርካታ መንገዶች አሉ፡፡ እኔ ለአለቃዬ የተለያየ ዓይነት ሪፖርት ላቀርብ እችላለሁ፡፡ በመሆኑም አሁን ካለው የለውጥ አየር አኳያ ነገሮች ግልጽ መውጣት አለባቸው፡፡ ፕሬሱም እነዚህን ጉዳዮች በመከታተል ይፋ ማውጣት አለበት፡፡ በሽታን በመደበቅ መድኃኒት ማግኘት አይቻልም፡፡

ሪፖርተር፡- የፋይናንስ ዘርፉ እርስዎ ከነበሩበት ጊዜና አሁን ካለው አኳያ ምን ያህል ለውጥ አለው? ዘርፉ ማድረግ ሲገባው ያላደረጋቸው ነገሮች ምንድን ናቸው ይላሉ?

አቶ መስፍን፡- እኔ ብሔራዊ ባንክን ከለቀቅሁ 20 ዓመታት ሊሞላኝ ነው፡፡ የግል ባንኮች ያን ጊዜ ገና ምሥረታ ላይ ነበሩ፡፡ አሁን በርካታ ለውጦች አሉ፡፡ ያን ጊዜ የነበረውን የብሔራዊ ባንክ የቁጥጥር ችሎታ ከአሁኑ ጋር ማወዳደሩም ፍትሐዊ አይደለም፡፡ ብሔራዊ ባንክ በአሁኑ ወቅት በጣም ጠንካራ የቁጥጥር ባንክ መሆን ሲገባው ይህን የሚያመላክቱ ነገሮች እያየን አይደለም፡፡ የግል ባንኮች እየመጡ አይደለም፡፡ አሁንማ ያሉትም ቢሆኑ የቅርንጫፍ መስፋፋት እንቅስቃሴያቸውን እያቆሙ ነው፡፡ ተቀማጭ ሰብስቦ በዚያ ገንዘብ ኢንቨስት ማድረግ አዋጭ እየሆነ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- አገሪቱ የብድር ጫና ውስጥ በመግባቷ ኢኮኖሚው የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማንቀሳቀስ ወይም ወደ ኢኮኖሚው እንዳታስገባ የሚገድቡ አስገዳጅ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ነው፡፡ ለፕሮጀክቶች ኢንቨስት ከማድረግ ይልቅ ለዕዳ ክፍያና መሰል ተግባራት ቅድሚያ እንድትሰጥ እየተገደደች በመሆኑ፣ አገሪቱ በዚህ አኳኋን ከቀጠለች በመጪዎቹ ሁለትና ሦስት ዓመታት ውስጥ ምን ሊከሰት ይችላል ብለው ይገምታሉ?

አቶ መስፍን፡- የአገር ውስጥ ብድር ሁኔታውን በተመለከተ መረጃው የለኝም፡፡ መረጃውን ማግኛ መንገድም የለም፡፡ ይሁንና የገንዘብ ፖሊሰ ስንል የገንዘብ መጠኑን፣ የውጭ ምንዛሪ ፖለሲውንና ሌላውንም የገንዘብ ጉዳይ ያያይዛል፡፡ የአገር ውስጥ ብድር ከውጭ ምንዛሪ ተመን ጋር የሚታይ ቢሆንም በዚህ ረገድ ስለሚሠራው ሥራ ሲገለጽ አልሰማም፡፡ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት መከሰቱ ይፋ ወጥቷል፡፡ የምናውቃቸው ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ከአምስት አመታት ቀደም ብለውም ሲያስጠነቅቁት የቆዩት ጉዳይ ቢሆንም ሰሚ ጠፍቶ ችግሩ ግፍቶ መጥቷል፡፡ የአገሪቱ የወጪ ንግድ፣ አየር መንገዱ፣ መርከብ ድርጅትና የቱሪዝም ዘርፉ የሚያመጡት ገቢ ተደማምሮ የሚገኘው ገንዘብ ከስድስት ቢሊዮን ዶላር አይበልጥም፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ ሐዋላ ገቢውስ?

አቶ መስፍን፡- በሐዋላ ገቢ ላይ የሚቀርበው የተምታታ አኃዝ ነው፡፡ ገቢው አራት ቢሊዮን ዶላር ደርሷል የሚባለው በእነ ዓለም ባንክ መረጃ መሠረት ሐሰት ነው፡፡ ትክክለኛውና በባንክ በኩል የሚላከው ሐዋላ መጠን ከ700 ሚሊዮን ዶላር አይበልጥም፡፡ እርግጥ ነው ኢትዮጵያ በውጭ ካሏት ዜጎች አኳያ ብዙ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ቢኖርባትም ይህም እየቀነሰ ነው፡፡ በወጪ ንግድ ላይ መሥራት ቶሎ ለችግር አይደርስም፡፡ የእርሻ ውጤቶች ጊዜ ይወስዳሉ፡፡ ከቱሪዝም፣ ከሐዋላ፣ ከውጭ ብድርና ዕርዳታ የሚገኘው ገንዘብ ነው በፍጥነት ለችግር የሚደርሰው፡፡ አሁን ባለው የዋጋ ግሽበትና የምንዛሪ እጥረት ችግር እንኳንና ሦስት ወይም አምስት ዓመት ቀርቶ ለሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ውስጥ ችግር ውስጥ እንደምንድቅ እያሰጋኝ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአገሪቱ የምንዛሪ እጥረት መንግሥት በእጁ አይነኬ የነበሩ ተቋማትን ወደ ግል እንዲዛወሩ እስከመወሰን አድርሶታል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላሉ?

አቶ መስፍን፡- በነገራችን ላይ ፕሬይቬታይዜሽን የሊበራላይዜሽን ክፍል በመሆኑ የሚጠላ ነገር አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ዘው ተብሎ የሚገባበት ሳይሆን በጥናትና በዝግጅት የሚገባበት ተግባር ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ሒደት የሚደግፉ መዋቅሮች ያስፈልጋሉ፡፡ የካፒታል ገበያ ያስፈልጋል፡፡ ተጀምረው የነበሩ የቆዩ የካፒታል ገበያ ጥናቶች የት እንደቆሙ አይታወቅም፡፡ ብሔራዊ ባንክ የራሱን ጥናት አጥንቶ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትም ጥናት አስጠንቶ ነበር፡፡ የካፒታል ገበያው በዚህ ሒደት እንደሚከፈት ሲጠበቅ ድንገት ቀርቷል ተባለ፡፡ ለምን እንደሆነ አላውቅም፡፡ ይህንን የሚያውቅ ሊነግረን ይገባል፡፡ የካፒታል ወይም የስቶክ ገበያውን የሚመራ ራሱን የቻለ ተቋም መመሥረት ያስፈልገናል፡፡ ኬንያ ይህንን ገበያ የሚቆጣጠር የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የሚባል ተቋም አላት፡፡ አሜሪካም ሴኩሪቲ ኤንድ ኤክስቼንጅ ኮሚሽን የሚባል ተቋም አላት፡፡ እነዚህ ሁሉ ለካፒታል ገበያው መቋቋም የሚያስፈልጉ ስለሆኑ እኛም በቶሎ ልንፈጥራቸው ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የውጭ ምንዛሪ እያገኘ ያለና ውጤታማ ድርጅት በመሆኑ ነገውኑ ወደ ግል እናዛውረው ማለት የወርቅ እንቁላል የምትጥለውን ዝይ እንደማረድ እንዳይሆን ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ሽያጩስ እንዴት ሊከናወን እንደታሰበ መገለጽና በዝርዝር መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ አስፈሪ የሚባሉ ልምዶች አሉ፡፡ ሩሲያና ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የተካሄደውን የፕራይቬታይዜሽን ሒደት ካየን አስፈሪ ጎኖች ነበሯቸው፡፡ እነዚህ ድርጅቶች የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀብት ናቸው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ችግሩን ለመቅረፍ አያስችል ይሆናል እንጂ፣ እንደ እኔ ከሆነ የሚሸጠውን ድርሻ ኢትዮጵያውያን ቢገዙ እርመጣለሁ፡፡ አሊያም በውጭ ያለው የዳያስፖራው ማኅበረሰብ ቢገዛቸው እመርጣለሁ፡፡ የውጭ ኩባንያዎችና ድርጅቶች ትራፋቸውን ወደ አገራቸው መውሰድ ይፈልጋሉ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለውጭ ድርጅቶች ቢሸጥ በዶላር ትርፍ የመክፈል ጉዳይ ችግር ላይሆንበት ይችላል፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም ግን እንዴት ነው የሚሆነው? ባቡሩና ሌላውም በብር ነው አገልግሎት የሚሰጡት፡፡ ይህም ሊታይ ይገባዋል፡፡ ቀድሞ ነገር የተጣራ ሀብታቸው ምን ያህል እንደሆነ ማን ነው የሚያውቀው፡፡ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የወጣበት ወጪ፣ ምን ያህል እያስገባ እንደሆነና እንሽጠው ብንልስ ምን ያህል ያስገኛል የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ ነገሮች ይጠኑ፡፡

ሪፖርተር፡- ብሔራዊ ባንክ ከተነቀፈባቸው የቅርብ ጊዜ ዕርምጃዎቹ መካከል በትውልደ ኢትዮጵያውያን የተያዙ የባንክ አክሲዮኖችን በተመለከተ የተወሰደው እርምጃ ይጠቀሳል፡፡ ዕርምጃው አግባብ እንዳልነበር በስፋት ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላሉ?

አቶ መስፍን፡- ዳያስፖራው ጠላት አይደለም፡፡ በውጭ የሚኖሩና ለአገር መትፍሔ መሆን የሚችሉ በርካታ ጭንቅላቶች አሉ፡፡ ይሁንና ባንኩ የወሰደው ዕርምጃ ተገቢ አይደለም፡፡ ለምሳሌ አዋሽ ባንክ ውስጥ 17 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ በዳያስፖራው ማኅበረሰብ የተያዘ የአክሲዮን ድርሻ ነበር፡፡ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የባንክ አክሲዮን ድርሻ እንዳይገዛ መከልከሉ ብዙ ጉዳቶች አሉት፡፡ አዋሽ ባንክ ከተቋቋመ 21 ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ በራሳቸው ምክንያት የውጭ ዜግነት ያገኙ ሰዎች የትርፍ ክፍፍል ድርሻቸውን ሊወስዱ በሚመጡበት ወቅት መታወቂያ አምጡ፣ ዜግነታችሁ ይታይ እየተባሉ ተዘረፍዋል ማለት ይቻላል፡፡ የባንኩ ባለአክሲዮን ከሆኑ በኋላ ነው ዜግነታቸውን የቀየሩት፡፡ በመሆኑም ድርሻቸው ይሸጥ በመባሉ የአንድ ሺሕ ብር ዋጋ የነበረው አንድ አክሲዮን 20 ሺሕ ብር ድረስ ተሸጧል፡፡ ትልውደ ኢትዮጵያዊው በሆነ ምክንያት የባንክ ባለድርሻ መሆን አለመቻሉ ከታወቀ፣ ወይ በራሳችሁ መንገድ ሸጣችሁ ውጡ አሊያም ለሌላ ኢትዮጵያዊ ዘመዳችሁ አስተላልፉ ማለት ይቻል ነበር፡፡ ቀናነት ስሌለ ወንጀለኛ የሆኑ ይመስል በእኩለ ቀን የተፈጸመ ዘረፋ ሊባል በሚችል ሁኔታ በ20 ሺሕ ብር የተሸጠው ድርሻቸው እያለ ለእነሱ ግን በአንድ ሺሕ ብር ተሰልቶ ነው የተሰጣቸው፡፡ በዚህ ሒደት ልዩነቱን የወሰደው ብሔራዊ ባንክ ነው፡፡ የግል ባንኮቹ በአክሲዮን ድርሻ ሽያጩ ተጎጂ ነበሩ፡፡ ቢያንስ ለአክሲዮን ድርሻ ማሳተሚያ፣ ለሰው ኃይልና ለሌላውም ያወጡት ወጪ አልታየላቸውም፡፡ ወንጀል ተፈጽሟል ማለት ይቻላል፡፡ አሁን ግን ከዳያስፖራው ጋር ሰላም ማውረድ የሚያስፈልግበት ጊዜ በመሆኑ፣ መንግሥት የተፈጸመውን ስህተት በማስተካከል የአክሲዮን ድርሻቸውን እንዲስተካክልላቸው ማድረግ አለበት፡፡ የእኔን ትርፍ መንግሥት የሚወርስበት ምክንያት አይታየኝም፡፡ የዳያስፖራው ማኅበሰረብ ወደ ኢትዮጵያ ቢመጣ እጃችንን ዘርግተን እንቀበላለን በሚባልበት ወቅት፣ እንዲህ ያሉት ነገሮች ላይ ይቅርታ ጠይቆ ገንዘባቸውን መመለስ ይገባል፡፡ እንዲያውም ወደ ግል ይዛወራሉ የተባሉት ድርጅቶችን ትርፋችንን ወደ ውጭ እንውሰድ የማይሉ፣ ዕውቀቱና ገንዘቡ ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያንና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንዲሳተፉባቸው ቢደረግ መልካም ነው፡፡ የግል ባንኮች መሥራች ባለድርሻዎቻቸው በስመ ዳያስፖራ ወይም ትውልደ ኢትዮጵያዊነት ሰበብ ሲዘረፉ ምንም ነገር አለማለታቸው፣ ከገዥው ባንክ ጋር ያላቸውን የግንኙነት ችግር አመላካች ነው፡፡ ባንኮቹ በርካታ ቅሬታዎች እንዳሏቸው አውቃለሁ፡፡ ይሁንና በግልጽ አውጥተው መነጋገርና ለችግሮቻቸው መፍትሔ የሚያገኙበት መድረክ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ዳያስፖራው የፕራይቬታይዜሽን ጉዳዮች ሲመጡ ሥጋቶች አሉት፡፡ ወይ እንደ ሌላው የውጭ ዜጋ የለየለት የኢንቨስትመንት ከለላና ዋስትና አግኝቶ አይገባም፡፡ ወይም ደግሞ እንደ ተወላጅነቱ የሚሰጡት መብቶች በተፈለገ ጊዜ የሚነሱ ከሆነና ከዚህ ቀደም በብሔራዊ ባንክ የተፈጸመው ጉዳይ ባልሻረበት ወቅት፣ መንግሥት ባቀረባቸው የፕራይቬታይዜሽን ጥሪ የመሳተፉ ነገር ከፋይናንስ ባሻገር የፖለቲካ ዋስትናው እንዴት ሊታይ ይችላል? ከዚህ ቀደም የዳያስፖራ ቦንድ ሽያጭ በሕግ ተወስኖ እንዲሠራበት ሲመክርም ስለነበር ይህንን ጉዳይም በማካተት ነገሩን ቢያስረዱን?

አቶ መስፍን፡- ከዳያስፖራው ጋር ብሔራዊ ዕርቅ አለያም ሌላ ስያሜ የሚሰጠው የመልካም ግንኙነት ሥራ ማከናወን ያስፈልጋል፡፡ ከዳያስፖራው ጋር በጠላትነት የመተያየት አካሄድ መሻሻል አለበት፡፡ በአሁኑ ወቅት በዳያስፖራው አካባቢ የአገሪቱን ወቅታዊ ለውጥ ለመደገፍ ፍላጎት እንዳለ እያየን ነው፡፡ በእኔ አስተሳሰብ የኖርማላይዜሽን ወይም ሌላም ስያሜ እንስጠው ብቻ በመንግሥትና ውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መካከል ጥሩ ግንኙነት በመፍጠር እንደ ፊሊፒንስ፣ ህንድና ሌሎችም አገሮች የሚጠቀሙትን ያህል ኢትዮጵያም መጠቀም እንድትችል ማድረግ ይገባል፡፡ ይህን ለማድረግ አንደኛው መንገድ የተወሰደባቸውን የባንክ የአክሲዮን ድርሻ እንመልስላቸው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የሐዋላ ገንዘብ አትላኩ፣ መንግሥትን በዚህ ዕርምጃ እንቆንጥጠው የሚል አቋም የሚያራምዱ ዳያስፖራዎች አሉ፡፡ ይህንን መከራከር ያስፈልጋል፡፡ ነገሩ የገባን ሰዎች ይህንን ጉዳይ ማስረዳት አለብን፡፡ የሐዋላ ገንዘብ በባንክ አትላኩ በሚለው ተቃውሞ መንግሥት የሚቆነጠጥ የሚመስላቸው ሰዎች በተወሰነ ደረጃ ተሳስተዋል፡፡

በደርግ መንግሥት ወቅትም ተመሳሳይ ክርክር ተነስቶ ነበር፡፡ ደርግ እርዳታ እንዳያገኝ፣ ስንዴ ቢላክለትም ወታደሮቹን ስለሚያበላበት እርዳታ እንዳይደረግለት የሚል ክርክር ነበር፡፡ ነገር ግን የእህል እርዳታው ለደርግ ተሰጠውም አልተሰጠው በእርሻ ሰብል ድርጅት በኩል ከገበሬው በግዳጅ እየገዛ ወታደሩን ይቀልባል እንጂ፣ ወታደሩን አያስርበውምና ይህ አቋም ትክክል አይደለም ብለው የሚሟገቱም ነበሩ፡፡ አሁንም መንግሥት በእኔው ዶላር ሕዝብ የሚጎዳ ሥራ ይሠራል ብለህ ካመንክ ያንተ ዶላር መጣም ቀረም የሚሠራውን መሥራቱ አይቀርም፡፡ በአሁኑ ወቅት መንግሥት ለመጨቆኛ ወይም ለማፈኛ ሥራ ቢፈልግ እንኳ በውጭ ከሚኖሩ ዜጎች የሚመጣው ዶላር ብዙም አያስፈልገውም፡፡ ብር እንደ ልብ አለው፡፡ መቶ ዶላር በባንክ በኩል የሚልክ ሰው አስተዋጽኦው ቀላል አይደለም፡፡ ብሔራዊ ባንክ በውጭ ከሚኖሩ ዜጎች በባንክ ከሚላከው ዶላር ውስጥ 30 በመቶውን ራሱ ያስቀራል፡፡ ምን ላይ እንደሚውለው ባናውቅም 70 በመቶውን ለመድኃኒት አስመጪዎችና ለሌሎችም አስፈላጊ ነገሮች መግዣነት ሲውል፣ ተጠቃሚው ገንዘቡ የሚላክለት ሰውም ጭምር እንደሆነ መገንዘብ ይገባል፡፡ እርግጥ ከፖለቲካው ባሻገር በመደበኛው የባንክ ምንዛሪና በጥቁር ገበያው መካከል ያለው የዋጋ ልዩነትም ዶላር በባንክ እንዳይላክ አንዱ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል መዘንጋት የለበትም፡፡ ዳያስፖራው በባንክ የሚላከው ገንዘብ በተዘዋዋሪ መንገድ ለአገርና ለወገን ይጠቅማል ብሎ ካሰበ ገንዘቡን በሕጋዊ መንገድ መላኩን ማቋረጥ የለበትም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰሜን አሜሪካ በሚካሄደው ዓመታዊ የስፖርት ፌስቲቫል ላይ ለመገኘት ጥሪ ማቅረባቸውንና አዘጋጆቹ ሳይቀበሉት እንደቀሩ የሰማነው እውነት ከሆነ ተገቢ አይሆንም፡፡ የማረጋጋቱን ሥራ እንደጨረሱ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን እየሄዱ ቢያነጋግሩ መልካም ነው፡፡ በርካታ ፋብሪካዎች ሥራ እያቆሙ ባሉበት ወቅት እንዲህ ያሉ እርምጃዎች ያስፈልጋሉ፡፡ መድኃኒት ፋብሪካዎች እየተዘጉ እኮ ነው፡፡ ከዚህ ችግር ለመውጣት ብሔራዊ ባንኩን በጥሩ ደረጃ ሊመሩ የሚችሉ፣ ጥሩ የብድር ፖሊሲ በማውጣት የአገሪቱን የገንዘብ ቀውስ ሊያረጋጉ የሚችሉ ሹማምንት ቢመጡ፣ ዕዳ የማሰረዝ፣ የማራዘም ሥራ ለመሥራት የሚያግዙ ጥሩ ብቃትና ጭንቅላት ያላቸውን ባለሙያዎች በመያዝ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡ ሌላው መፍትሔ በውጭ የሚኖሩ ዜጎች ለመንግሥት ይቅርታ አድርገውለት በባንኮች የነበራቸውን የአክሲዮን ድርሻ መልሰው በውጭ ገንዘብ መግዛት እንዲችሉ ቢደረግ ይበጃል፡፡ ዳያስፖራዎች ባንክ እንዲያቋቁሙ ቢፈቀድላቸው ጉዳቱ ምንድነው? አቅሙ አላቸው፡፡ በሙሉ ወይም በከፍተኛ የአክሲዮን ባለድርሻነት በውጭ ምንዛሪ በሚገዛ አክሲዮን ባንክ ቢያቋቁሙ፣ ገንዘብ በመላክ ብቻም ሳይሆን መጥተውም እንዲያስተዳደሩት ቢደረግ ትልቅ መፍትሔ እንደሚገኝ አስባለሁ፡፡

በመጪዎቹ ጥቂት ወራት ውስጥ ቢሊዮን ዶላሮችን በአስቸኳይ ማግኘት ካልቻልን አደጋ ውስጥ መሆናችን የታወቀ ነው፡፡ ባለሙያዎች መሥራት ከሚችሉበት ቦታ እየተገፉ፣ ቦታው በማይገባቸው የፓርቲ አባላት እየተያዘ አገሪቱም ሕዝቧም ዋጋ ሲከፍሉ ኖረዋል፡፡ አገሪቱ አሁን ከገባችበት የባሰ ገደል ውስጥ አለመግባቷም የሚገርም ነው፡፡  ደርግ ወደ ውድቀቱ ሰሞን እንዳደረገው ሁሉ ለአገር እስከጠቀመ ድረስ የፓርቲ አባል ሆነም አልሆነ ማንኛውም ሰው በለውጥ እንዲሳተፍና አስተዋጽኦ እንዲያበርክት ማድረግ ይገባል፡፡ እስካሁን ባለው የሹመት አሰጣጥ ከፓርቲ አባልነት ውጪ ያለ ሰው እንዲሳተፍ ሲደረግ አልታየም፡፡ ይህ መሰበር አለበት፡፡ ከፓርቲ ሳጥን ውጭ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ከፓርቲ አባልነት ውጪ የሆኑ ሰዎች በተለይም በዳያስፖራው አካባቢ በነፃ ጭምር ማገልገል የሚፈልጉ በርካታ ባለሙያዎች ስላሉ እነሱን ማካተት ይገባል፡፡ አለበለዚያ በምንገኝበት ችግር የተነሳ የኢኮኖሚ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ የሚያስፈልገን ይመስለኛል፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማስተላልፈው መልዕክት የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ያለበቂ ምክክርና ውይይት እንዳይፀድቅ ነው›› አቶ ፊሊጶስ ዓይናለም፣  የሕግ ባለሙያ

አቶ ፊሊጶስ ዓይናለም በዳኝነትና በጥብቅና ሙያ ለረዥም ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ከአምስተርዳም ዩኒቨርሲቲ በሕገ መንግሥትና አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ  ጠበቆች ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ...

‹‹ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው?›› ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት...

ዘንድሮ ጀርመን በኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ግእዝና አማርኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክና መልክዓ ምድር ጠንቅቆ የተማረው የታላቁን ምሁር ሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ የልደት በዓልን እያከበረች ትገኛለች፡፡ በ1616 ዓ.ም....

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...