በሳምንቱ መጀመርያ ‹‹የግሉ ዘርፍና ወቅታዊ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፈተናዎቹና ዕደሎቹ›› በሚል ርዕስ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ አንጋፋ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችም ይህንኑ ሐሳብ በመንተራስ ሙያዊ ዕይታቸውን ለታዳሚው አካፍለዋል፡፡ አገሪቱ የምትገኝበትን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ የተነተኑ ሲሆን፣ የኢኮኖሚ ባለሙያዎቹ ለረጅም ጊዜ ከሕዝብ ጆሮ ርቀው የቆዩ ነገር ግን ለመንግሥት የሚበጁ ሙያዊ ትችቶችንና ምልከታቸውን ሲያቀርቡ ተደምጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ 11 በመቶ በአማካይ ሲያድግ መቆየቱ ቢታወቅም፣ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ያጋጠሟት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች፣ አጣብቂኝ ውስጥ እንድትገባ ስለማድረጋቸው በባለሙያዎች ሲብራሩና ሲተነተኑ ቆይተዋል፡፡ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ቀውስ መነሻ ዋና ዋና ነጥቦች ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት፣ የብድር ዕዳ ጫና፣ ከፍተኛ የንግድ ሚዛን ጉድለት፣ ከፍተኛ የሥራ አጥነት፣ የገንዘብ አቅርቦት ችግርና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሚዛኑን ይደፋሉ፡፡
‹‹ኢትዮጵያ አደገች ተመነደገች እየተባለች በቆየችበት ወቅት እነዚህ ችግሮች እንዴት ተከሰቱ? ችግሮቹ ከመከሰታቸውስ በፊት ሊከሰቱ እንደሚችሉ እንዴት ማወቅ አልተቻለም?›› የሚለውን ጥያቄ በማንሳት የችግሮቹን ምንጮች በተለያየ አቅጣጫ ያብራሩት የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው ኢዮብ ተስፋዬ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
በማብራሪያቸው ካነሷቸው ጉዳዮች አንዱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ነው፡፡ የአምስት ዓመቱ ዕቅድ ሲወጣ ተስፋ ያደረጋቸው በርካታ ጉዳዮች ነበሩ ያሉት ማክሮ ኢኮኖሚስቱ ኢዮብ፣ የተለጠጠው ዕቅድ በመጀመርያው ዓመት ትግበራው ሁለት ቢሊዮን ዶላር የነበረውን የወጪ ንግድ ገቢ በአምስተኛ ዓመቱ ላይ አሥር ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ያልም ነበር ብለዋል፡፡ ዕቅዱ የተሰላው ‹‹ዘኢስት ኤሺያን ታይገርስ›› እንደሚባሉት እንደ ደቡብ ኮሪያ፣ ሲንጋፖርና ማሌዥያ ሁሉ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚም የምሥራቅ አፍሪካ ነብር ኢኮኖሚ እንዲሆን ተብሎ በማሰብ ነበር፡፡ እንደ ነብር ፈጣንና ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመፍጠር ተፈልጎ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህንን ዕቅድ ያወጡት ሰዎች ከመነሻው መሠረታዊ ነገር መርሳታቸውን የኢኮኖሚ ባለሙያው ይተነትናሉ፡፡ ተረስቷል ብለው የጠቀሱት መሠረታዊ ጉዳይም የፋይናንስ ሀብት ነው፡፡ ዕቅዱን ፋይናንስ ለማድረግ የታሰበው በአንድ መንገድ ብቻ መሆኑ መሠረታዊ ክፍተት እንደፈጠረ ያምናሉ፡፡ ዋናውና መሠረታዊው ችግር በብድር ላይ የተመሠረተ ዕቅድ መሆኑ ነበር፡፡
‹‹ፕሮጀክቶች የሚሠሩት በብድር መሆኑ፣ ኢኮኖሚ ውስጥ ለብር መብዛት ምክንያት ሆኗል፤›› በማለት የአገር ውስጥ አጠቃላይ የገንዘብ አቅርቦቱን ከፍ አድርጎታል፡፡ ብሔራዊ ባንክ ሲከተል የቆየው የገንዘብ ፖሊሲም ‹‹ልቅ›› ወይም ተስፋፊ (ኤክስፓንሽናሪ ሞንታሪ ፖሊሲ) እንደነበር በመግለጽ፣ ‹‹ብሔራዊ ባንክ ማዕከላዊ ባንክ ከመሆን ይልቅ የገንዘብ ማተሚያ ቤት ነበር ማለቱ ይቀላል፤›› በማለት ተችተዋል፡፡ ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም ከውጭ የሚገባው ዕቃ እንዲጨምር በማድረግ፣ ወደ ውጭ ከሚላከው ይልቅ የሚገባው ከፍተኛ እንዲሆን በማድረግ የንግድ ሚዛን ጉድለትን ማስፋቱ፣ ዕቅዱ ለማስፈጸም የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማግኘት የሚጠየቀው ብድር በየጊዜው እንዲጨምር ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ይህ መሆኑ ሳያንስ ፕሮጀክቱ ‹‹ከመሬት ሳይነሱ ብድሩን የመክፈያ ጊዜ ደርሷል፤›› በማለት ዕቅዱ ምን ያህል ጫና እንዳስከተለ አብራርተዋል፡፡
የገንዘብ አቅርቦት የንግድ ሚዛን ጉድለትና የውጭ ብድር ዕዳ ጫና ተደማምረው ከፍተኛ ጫና እንዳስከተሉ ያብራሩት እኚሁ የኢኮኖሚ ባለሙያ፣ ጫናው ከመጣ በኋላ እንደመፍትሔ የተወሰደው ዕርምጃ ግን ሌላ ችግር ይዞ ስለመምጣቱም አብራርተዋል፡፡ የምንዛሪ ተመን ማስተካከያ ማድረግ ነበር መፍትሔው፡፡ ‹‹ዲቫሉዌሽን በእርግጥ ኤክስፖርትን ለማበረታታት የሚሉ ሽፋኖች ይሰጡት እንጂ መሠረታዊ ችግሮቹ ግን መንግሥት ሲከተለው የነበረው የገንዘብ ፖሊሲ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ይህ የተሳሳተ ፖሊሲ የዋጋ ግሽበትን በማባበስ የኅብረተሰብ ኑሮ ላይ የውጭ ዕዳ ጫና ፈጥሯል ያሉት ኢዮብ (ዶ/ር)፣ የንግድ ሚዛን ጉድለቱንም እያባባሰው መምጣቱን አብራርተዋል፡፡
በእርግጥ እነዚህ ነገሮች አይከሰቱ ማለት እንደማይቻልና እሳቸውም እንዲህ ማለታቸው እንዳልሆነ የጠቀሱት ኢዮብ (ዶ/ር)፣ ነገር ግን ፕሮጀክቶቹ ፋይናንስ የሚደረጉበት ሌሎች ሞዴሎች ቢኖሩ ኖሮ የተፈጠረው ኢኮኖሚያዊ ችግር አሁን በደረሰበት ደረጃ ላይከሰት ይችል እንደነበር ያምናሉ፡፡ አማራጭ ካሏቸው ሞዴሎች ውስጥም ፕሮጀክቶችን በእሽሙር ወይም በሽርክና ከውጭ ባለሀብቶች ጋር እንዲገነቡ ቢደረግ ቀውሱን ማስቀረት ይቻል እንደነበር ተናግረዋል፡፡
‹‹አሁን ተከሰቱ የተባሉት ችግሮች ሊመጡ እንደሚችሉ ጥቂቶች ቀደም ብለን ተናግረን ነበር፤›› ያሉት ኢዮብ (ዶ/ር)፣ ሰሚ ግን አልተገኘም በማለት ነበር ቁጭታቸውን የገለጹት፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረት የተከሰተው አንድም በብሔራዊ ባንክ ድክመትና አመራሩ ለመንግሥት በሰጠው የተሳሳተ ምክር እንደሆነም ኢኮኖሚስቱ ያምናሉ፡፡ መንግሥትን ሊያማክሩ የተቀመጡ የብሔራዊ ባንክ ገዥዎች የውጭ ምንዛሪ እጥረትና ችግር አይመጣም ስላሉት መንግሥት ተደፋፍሮ አንዳንዴም በጀብደኝነት ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ወደ መገንባቱ ሥራ የገባው በማለት የገዥውን ባንክ ኃላፊዎች ኮንነዋቸዋል፡፡ ‹‹አሁን የምንዛሪ ለውጡ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎቱን ይቀንሳል ተብሎ ነበር፡፡ [እንደታሰበው] ይህ መፍትሔ ሳይሆን ሲቀር ግን ወደ ፕራይቬታይዜሽን ተገባ፤›› ብለዋል፡፡ አገሪቱ ብርቅዬ የምትላቸውን ኩባንያዎቿን ለሽያጭ ያቀረበችበት ዋነኛው ምክንያትም ይኸው የተሳሳተው አካሄድ ስለመሆኑ ተብራርቷል፡፡
የኢዮብ (ዶ/ር) ማብራሪያ አጠቃላዩን የፋይናንስ ዘርፉን ሁኔታም የዳሰሰ ነበር፡፡ የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ለውጦች ማሳየቱን፣ በዚህ ጊዜ ውስጥም የግል ባንኮች፣ ማይክሮ ፋይናንሶችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች መቋቋማቸው ተወስቷል፡፡ የእነዚህ ተቋማት ካፒታልና የሚሰጡት ብድር መጠን ስለማደጉ ተወስቷል፡፡ ሆኖም የተገነባው የፋይናንስ ዘርፍ ‹‹የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ቁመናና ወርድ የሚመጥን አይደለም፤›› ብለውታል፡፡ ይህንን አባባላቸውን ለማፍታታት በምሳሌነት ከጠቀሷቸው ውስጥ የሚሰጧቸው አገልግሎቶች ብድር፣ ሌተር ኦፍ ክሬዲትና ሐዋላ ላይ ብቻ የተመሠረቱ መሆናቸው ይገኙበታል፡፡ ‹‹የተስፋፋ የፋይናንስ አገልግሎት አሰጣጦች የሉም፡፡ ዓለም የሚሠራባቸው የፋይናንስ አገልግሎቶችም የሉም፡፡ ከዚህም ባሻገር አሠራራቸው ያረጀ ያፈጀ መሆኑም ተጠቃሽ ችግር ነው፤›› ብለዋል፡፡
በብር ማስያዣ ንብረት ዋስትና ላይ ተመሥርተው የሚሠሩ ናቸው በማለት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን እንደ ማሟሻ አንስተውታል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደ መኪና ሞተር በትናችሁ ብታዩት ‹ሜዲን ተፈራ ደግፌ› ነው የሚለው፤›› በማለት ባንኩን ከመሠረቱት ቀደምት ጉምቱ ሰዎች ከተከሉት አሠራር ብዙም ለውጥ ያላሳየ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡ የፋይናንስ ዘርፉ በአብዛኛው በንግድና በኢንሹራንስ ላይ ብቻ የተንጠለጠ መሆኑም ሌላኛው ችግር እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
‹‹የኢንቨስትመንት ባንክ፣ ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ፣ ኢስላሚክ ባንክ፣ ሞርጌጅ ባንክ ኢትዮጵያ ውስጥ የሉም፡፡ ጭራሹኑ ኅብረተሰቡ በቤት ዕጦት እየተቸገረ በአንድ በኩል ደግሞ ቁጠባ ያስፈልጋል እየተባለ ኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክን ዘግቶ ንግድ ባንክ፣ ውስጥ ማስግባቱ ትክክል አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የልማት ባንክ፣ ንግድ ባንክ አለያም የቤቶች ባንክ ስለመሆኑ ሚናው በግልጽ አይታወቅም በማለት ውህደቱና አካሄዱ ትክክል እንዳልነበር ተችተዋል፡፡
ዓለም ወደ ሞርጌጅ ባንክ እየሄደ እንደሆነ በማመላከትም እዚህ አገር ሰው ካልሰረቀ በቀር ቤት መሥራት የማይገፋው አቀበት እየሆነበት በመሆኑ ይህንን ሊያቃልል የሚችል የሞርጌጅ ባንክ ሊኖር ይገባ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ቤት ማግኘት ዓለም አቀፋዊና የተባበሩት መንግሥታት የደነገገው መብት በመሆኑ ኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ በቤቶች ዘርፍ ፋይናንስ እንዲያቀርብ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት እንዲሠራ ቢደረግ የቤቶች ችግርን ለማቃለል ትልቅ ሚና ይኖረው እንደነበር አስረድተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በከፍተኛ የተበላሸ ብድር ውስጥ መዘፈቁና ሌሎችም በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ አሉ የተባሉ ችግሮችን በማንሳት ሰፊ ሙያዊ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡
ሌላው የኢኮኖሚ ባለሙያና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር ባልደረባ ሰይድ ኑሩም (ዶ/ር) ሙያዊ ሐሳባቸውን ለታዳሚው ካቀረቡት መካከል ይገኙበታል፡፡ በኢኮኖሚው ውስጥ ለተፈጠሩ ችግሮች እንደ መንስዔ የጠቀሷቸው ነጥቦች፣ ከኢዮብ (ዶ/ር) ጋር ተቀራራቢ ነበሩ፡፡ ባለፉት 12 ዓመታት ውስጥ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በአሥር በመቶ ሲያድግ መቆየቱን የመንግሥት መረጃዎችን በማጣቀስ፣ ዕድገቱም ትልቅ ሊባል የሚችል ስለመሆኑ ያመለክታሉ፡፡ ነገር ግን የዜጎች አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢ የኢኮኖሚውን ያህል ስላለማደጉ፣ ከፍተኛ የኑሮ ውድነትና የሥራ አጥነት ስለመፈጠሩ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ስለመከሰቱ፣ የንግድና የክፍያ ሚዛን ጉድለት ስለመስፋቱ፣ አገራዊ የብድር ዕዳ ጫና ፈታኝ ስለመሆኑ አውስተዋል፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚው አለመረጋጋት የልማት ጥረቶችን እየፈታተነ እንደመጣም ገልጸዋል፡፡
አገሪቱ የምትገኝበት ሁኔታ ባለበት ከቀጠለ ግን ፈጣን ዕድገት ማስዝገብ ቀርቶ በቀንድ አውጣ ጉዞም መራመድ ሊሳነው እንደሚችል ሥጋታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ፈጣኑ የኢኮኖሚ ዕድገት ጥራት የመብራት፣ የውኃ፣ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት ማምጣት፣ በቂ የሥራ ዕድል መፍጠርና አብዛኛው ዜጋ ሊቃመሰው የሚችል የኑሮ ደረጃ መፍጠር፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ማሳፈን፣ አስተማማኝ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘትና የብድር ዕዳ ጫና ያላጎበጠው አስተማማኝ አገራዊ አቅም መፍጠር ለምን ተሳነው? ለሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ከምላሻቸው ውስጥ የመጀመርያው የዕድገት ጥራትን የተመለከተው ነበር፡ መሠረታዊ ችግር ነው ብለው ያስቀመጡት፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፖሊሲና ከመዋቅራዊ ለውጥ ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ በማብራራት ነበር፡፡ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ውስጥ በግልጽ እንደተቀመጠው ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መሻገር ይጠበቅ ነበር፡፡ ዘመናዊ ግብርናም ቦታ ተሰጥቶታል፡፡ ‹‹ዕቅዱን ስናየው ነቅሰን የምናወጣቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ችግሮች በጣም ውስን ናቸው፤›› ያሉት ሰይድ (ዶ/ር) ‹‹ክፋቱ ግን እነዚህን ለመፈጸም አለመቻል ችግሮች አስከትሏል፤›› ይላሉ፡፡
በኢትዮጵያ መንግሥት ፍላጎት መሠረት ቀጣይነት ያለው ዕድገት ማምጣትና ፍላጎቱን በአገር ውስጥ ምርቶች መሸፈን ወይም ከውጭ ሊገቡ የሚችሉ ምርቶችን በዘላቂነት ሊተካ የሚችል፣ ብሎም የውጭ ምንዛሪ የሚያመነጭ ኢኮኖሚ መፈጠር መቻሉ መሠረታዊ ከሚባሉ የመፍትሔ መንገዶች ዋናዎቹ ስለመሆናቸው አብራርተዋል፡፡
በዕለቱ ሌላው ተናጋሪ የነበሩት ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር አለማየሁ ባቀረቡት ጽሑፍ ውስጥ በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ ሶሺዮ ኢኮኖሚክ ችግሮች በማለት አምስት ነጥቦችን አስቀምጠዋል፡፡ የመጀመርያው ወጥነት የጎደለው የኢኮኖሚ ዕድገት ሲሆን፣ የሥራ አጥ ቁጥር መብዛትና ድህነት ሁለተኛው ችግር ነው፡፡ ፍትሐዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍልና ግጭቶች ሦስተኛው የማክሮ ኢኮኖሚው ብልሹ አስተዳደር ሆኗል፡፡ አራተኛው ሙስናና ፖለቲካዊ ግጭቶች ሲሆኑ፣ አምስተኛው የትምህርት ጥራት ጉድለት፣ የአስፈጻሚው አቅም ማነስና የብቁ ባለሙያዎች እጥረትን የተካተቱበት የሶሺዮ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መገለጫዎች ናቸው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የመንግሥት ዋነኛ የፋይናንስ ፖሊሲ የዋጋ ግሽበትን መከላከል ላይ ያተኮረ እንዲሆን የተገደደው፣ በአገሪቱ ጤና የጎደለው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ስለመኖሩ አመላካች ነው ያሉት ፕሮፌሰር ዓለማየሁ፣ ይህም በመንግሥት ፖሊሲ ላይ ተግዳሮት ለመሆን እንዳበቃው አብራርተዋል፡፡
በአገሪቱ ለተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ ቁልፍ ችግሮች ናቸው ብለው ያስቀመጡትም፣ ሙስና የሰፈነበት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፣ ግልብና አቅምን ያላገናዘቡ ዕቅዶች፣ ለፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውለው ጤናማ ያልሆነ ብድር ዋናዎቹ ተጠቃሽ መንስዔዎች ሲሆኑ፣ ማክሮ ኢኮኖሚው በብልሹ አስተዳደር ሳቢያ የገጠመው የውጭ ምንዛሪና የዋጋ ግሽበት የተበላሸ አስተዳደር ለኢኮኖሚው ጎደሎ መሆን ተወቃሽ ተደርገዋል፡፡
ከፊሲካል ፖሊሲ ጋር በተያያዘ ፕሮፌሰሩ የጠቀሱት ከፍተኛ የታክስ ምጣኔ፣ የተሳሳተ ዳሰሳና ፖለቲካዊ የታክስ ፖሊሲ ናቸው በማለት የገለጿቸው ችግሮችም ለኢኮኖሚው መታመም አስተዋጽኦ ነበራቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መንግሥት ያወጣቸው የኢኮኖሚ ዕቅዶች በዋነኝነት ግብርናና የፍጆታ ምርቶች ላይ ትኩረት አለማድረጋቸውም ለችግሩ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው ገልጸዋል፡፡ ከሁሉም በላይ የመንግሥት ደካማ የፕሮጀክት አስተዳደር ሜጋ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ውስጥ እንዳይጠናቀቁ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡
ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ከሌሎቹ የሙያ አጋሮቻቸው ለየት ያሉበት ነጥብ፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ዕድገት የተመለከተው ሐሳባቸው ነበር፡፡ እንደ እሳቸው እምነት፣ አገሪቱ የደረሰችበት የዕድገት ደረጃ የሚባለውን ያህል አይደለም፡፡
ላለፉት አሥር ወይም 12 ዓመታት መንግሥት ኢኮኖሚው ከ11 በመቶ በላይ ማደጉን ቢገልጽም፣ እሳቸው በሠሩት የኢኮኖሚ ሥሌት ግን ኢትዮጵያ በዚህን ያህል መጠን አላደገችም፡፡ የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ)፣ የዓለም ባንክና የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያወጧቸው ትንበያዎች የተለያዩ ስለመሆናቸው አስታውሰው፣ ‹‹እኔ የኢኮኖሚክ ሞዴል ተጠቅሜ ስሠራው 11 በመቶው ከየት እንደመጣ ግር ይለኛል፤›› ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ በእሳቸው ሥሌት ኢኮኖሚው ሲያድግ የነበረው በግማሽ ቀንሶ ወይም አምስትና ስድስት በመቶ ገደማ እንደነበር የሚያሳይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በመንግሥት ኢኮኖሚያዊ አኃዝ አልስማማም ብለው የጠቀሱት ሌላው ነጥብ፣ በአገሪቱ ደሃ የሚባለው የሕዝብ ቁጥር መጠን ነው፡፡ መንግሥት የደሃው ብዛት ከ100 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ 23 ሚሊዮን ብቻ ነው እንደሚል የጠቀሱት ፕሮፌሰር ዓለማየሁ፣ ይህ አኃዝ የተሰላው አንድ ሰው በወር 600 ብር ካገኘ ሁሉንም ወጪዎች ይሸፍንበታል፤ ይበቃዋል ከሚል መነሻ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
23 ሚሊዮን ሕዝብ ደሃ ነው የተባለውን መረጃ በመያዝ በዓለም አቀፍ መለኪያ መሠረት በድህነት ወለል የሚገኘው ሕዝብ በቀን የ1.25 ዶላር ገቢ ያገኛል በሚለው መስፈርት መሠረት ሲሰላ፣ ከ60 እስከ 70 በመቶው ሕዝብ ደሃ መሆኑን ያሳያል ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ ዕድገቱ ሁሉንም ሕዝብ አካታችና ተጠቃሚ እንዳላደረገ ያሳያል ይላሉ፡፡
የወጣቶች ሥራ አጥነት መረጃም በተመሳሳይ የሚታይ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ያለው የሥራ አጦች ቁጥር ከሚገለጸውም በላይ ከፍተኛ ስለመሆኑ ሞግተዋል፡፡ በቅርቡ የሠሩትን ጥናት በመጣቀስ እንዳብራሩት፣ በአሁኑ ወቅት ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆኑት የመንግሥትና የግል ሠራተኞች በዓለም አቀፍ የድህነት መለኪያ መስፈርት መሠረት ሲወሰድ አብዛኞቹ ከድህነት በታች እንደሚኖሩ ያሳያል ካሉ በኋላ ሁኔታውን ‹‹አስፈሪ›› ሲሉ ገልጸውታል፡፡
ሥራ ያለውም ሥራ የሌለውም በድህነት ውስጥ መገኘቱ ወደ ግጭት ሊወስድ እንሚችል የጠቀሱት ፕሮፌሰሩ፣ መንግሥት እንዳጋነነው ከፍተኛ ባይሆንም የኢኮኖሚው ዕድገት ግን ጥሩ ደረጃ ላይ የሚቀመጥና በአፍሪካ ደረጃ ትልቅ የሚባል ስለመሆኑ አልሸሸጉም፡፡ ‹‹የአፍሪካ ዕድገት አማካዩ አምስት በመቶ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ስድስትና ሰባት ሊሆን ስለሚችል፣ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ዕድገቱ ሁሉንም ኅብረተሰብ ተጠቃሚ አላደረገም፤›› ብለዋል፡፡ ይህም አሁን ላለው ችግር መባባስ ምክንያት ስለመሆኑንም የተለያዩ አኃዞችን በማጣቀስ አስረድተዋል፡፡
ታዋቂው የንግድ ሰው አቶ ክቡር ገና በበኩላቸው፣ የግሉን ዘርፍ ስለሚመለከቱ ማነቆዎች አብራርተዋል፡፡ ማነቆ ብለው ከጠቀሷቸው ውስጥ አንዱ የፋይናንስ ችግር ነው፡፡ የመሬት አቅርቦት ችግርንም አንስተዋል፡፡ መሬት ቢገኝ እንኳ እንደ ኤሌክትሪክ ኃይል ያሉ መሠረተ ልማቶችን ለማግኘት ያለው ውጣ ውረድ ምን ያህል አድካሚ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ሲገኝም የአቅቦቱ መቆራረጡ ምርታማነትን እንደሚቀንስ ጠቅሰዋል፡፡ የንግዱ ኅብረተሰብ ችግር ብለው ያነሱት ሌላው ነጥብ የታክስ ጉዳይ ነው፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት የተፈጠረውን አስቸጋሪ ሁኔታ በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡ የተፈጠሩት ችግሮች ወደ ረብሻ ጭምር ሲያመሩ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ አንድን ችግር ለመፍታት ሲባል ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ደንቦችን መውጣት በንግድ ኅብረተሰቡ ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖም መጠቀስ እንደሚገባው አቶ ክቡር አመልክተዋል፡፡
የአገሪቱን ወቅታዊ የኢኮኖሚ ሁኔታዎች የተመለከቱ ማብራሪያዎችንና ትንታኔዎችን የሰጡት እነዚህ ባለሙያዎች፣ ችግሮቹ ሊስተካከሉባቸው የሚችሉባቸው አሠራሮች እንዲፈጠሩ፣ የችግር መንስዔ ፖሊሲዎች እንዲቀየሩና መዋቅራዊ ለውጥ እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡
የፋይናንስ ዘርፉን መቀየር እንደሚያስፈልግ ያመለከቱት ኢዮብ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚመጥን ማዕከላዊ ባንክ መፈጠር እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ ‹‹አትም ሲባል የሚያትም የባንክ ገዥ መኖር የለበትም፡፡ ኢኮኖሚያዊ እውነታውን እያየ የሚመራ መሆን አለበት፤›› ካሉ በኋላ፣ ብሔራዊ ባንክ ሪፎርም መደረግ እንዳለበት ፖሊሲዎቹም መቀየር እንደሚገባቸው፣ የፋይናንስ ዘርፉም እንደገና መዋቀር እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል፡፡
ፕሮፌሰር ዓለማየሁ በበኩላቸው የአገሪቱን ኢኮኖሚ በዘላቂ ዕድገት መርህ ማስኬድ እንዲቻል ፈርጀ ብዙ ተግባራት መከናወን እንደላባቸው ጠቅሰው፣ የመንግሥት የማስፈጸም ብቃትን በማሳደግ በኢኮኖሚው ውስጥ የተቆጣጣሪነት ሚናውን በአግባቡ እንዲወጣ የሚያስችሉትን መዋቅራዊ ማሻሻያዎች ወደ መሬት ማውረድ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡