ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አሕመድ ወደ ኃላፊነታቸው ከመጡ ወዲህ ለፈጸሟቸው መልካምና ተስፋ ሰጪ ተግባራት ባልተለመደ መልኩ ምሥጋና ለማቅረብ መስቀል አደባባይ በነቂስ የወጣው ሕዝብ ላይ የደረሰው የቦምብ አደጋ አስደንጋጭ ነበር፡፡ ለሰላምና ለፍቅር የታደሙ ኢትዮጵያውያንን ስሜት የነካ እኩይ ድርጊት ተፈጽሟል፡፡ ሰላምና ፍቅር በሚሰበክበት አደባባይ እንዲህ ያለው ተግባር መፈጸሙ በእጅጉ ሊኮነን ይገባል፡፡
በዚህ አሳዛኝ ድርጊት ማግሥት የሰማነው ዜና፣ ሐዘንና ቁስልን የሚያሽር ሳይሆን አይቀርም፡፡ ኢትዮጵያ ነዳጅ አወጣች የሚለው ዜና እሰይ ሌላም የምሥራች ደራርቦ ያሰማን፤ የኢትዮጵያን መቅናትና መነሳት የምንሰማበት ዘመን ያድርግልን የሚያሰኝ ብሩህ ጅማሬ እየታየ ነው፡፡
ነዳጁ መውጣት መጀመሩ ነገር ነው፡፡ ዜናው አገራችን ከዚህም የበለጠ ዕምቅ ሀብቶቿን ተጠቅማ ራሷን ለማበልጸግ የምትችልበትን ምልክት ማሳየት እንደጀመረች ያመላክታል፡፡ ያሉን ሀብቶች ወደፊት ብዙ ዶላር የምንመነዝርበትን ዕድል የሚፈጥሩ መሆናቸው ብቻም ሳይሆን፣ ከልብ ከተሠራባቸው የሚገድ ምንም ነገር እንደሌለም የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ራሷን ለመቻል አቅምና ችሎታ እንዳላትም ይጠቁማሉ፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የተገኘውን ነዳጅ በጥንቃቄ ካላስተዳደርነው የሥጋትና የግጭት ምንጭ ሊሆን እንደሚችል ማሰቡ ተገቢ ነው፡፡ ከወዲሁ አኩራፊ እንዳለ፣ በነዳጁ መውጣት የተበሳጨ አካል እንዳለ ታይቷል፡፡ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) ቀንደኛው የዚህ ፕሮጀክት ተቃዋሚ መሆኑን በይፋ አውጇል፡፡ የነዳጅ ማውጣቱ ሥራ እንዲደናቀፍ ፍላጎት እንዳለውም በይፋ አስታውቋል፡፡
እንዲህ ላለው አደጋ መዘጋጀት ብቻም ሳይሆን፣ ቅሬታ ያደረበትን የትኛውም የአገሪቱ ዜጋ፣ ድርጅትም ሆነ ተቃዋሚ አካል ያደረበትን ቅሬታ ለመፍታት የሚያስችል የአካታችነትና የተደማጭነት ዕድል እንዲያገኝ ማድረግ ተገቢ ይሆናል፡፡ አዲሱ አስተዳደር ለፖለቲካዊ ቅራኔዎች መፈታት ሆደ ሰፊ ተነሳሽነት እንዳለው፣ ለይቅርታ ምሕረት የተረጉ እጆች እንዳሉት እየገለጸ ነው፡፡ በድርጊትም አሳይቷል፡፡ የኤርትራን መንግሥት ከጦርነት ሥጋት ወደ ፍቅር ማዕድ ጋብዟል፡፡ ተሳክቶለታልም፡፡ ሌሎችም ትጥቅ ያነገቡ፣ ጫካ የገቡ ተቃዋሚዎችን ወደ አብሮነት ባመጣበትና እጁ ኦብነግና መሰል ቡድኖችንም ማቀፉን፣ ማካተቱን ይበርታበት፡፡
ይህ ሲደረግና አንድነት ሲጠነክር ኢኮኖሚውን ሊደግፉ የሚችሉ ተግባራት ላይ ትኩረት ማድረግም ይመጣል፡፡ ኢኮኖሚው እንደሚገባው እንዳይራመድ ከገቱት በርካታ ችግሮች ውስጥ አንዱ የውጭ ምንዛሪ ድርቅ ነው፡፡ ለዚህ ሕመማችን የፈውስ መንገድ በመሆን ነዳጅ መጠነኛ ዕገዛ ያደርጋል እንጂ፣ ዘላቂ መፍትሔ እንደማይሆን ግልጽ ነው፡፡ የወጪ ንግድ ምርቶችን በብዛትና በጥራት አምርቶ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን ማሳደግ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆን አለበት፡፡
የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ፣ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀሙና ለአጠቃቀሙ እየተካሄደበት ያለው መንገድ ተደማምሮ ለሸማቾች የሚቀርበውን ምርት ከገበያ እያራቀ የአቅርቦት እጥረትና የዋጋ ንረትን በመፍጠር የኑሮ ውድነቱን እያባባሰው ነው፡፡
ዘወትር እጥረት ሲከሰት ያለ ልፋታቸው የሚከብሩ ሌቦች እንዲስፋፉ በር ይከፍታል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ ያተኮረና ትክክለኛውን ችግር መነሻ ያደረገ ፖሊሲ ለነገ ሳይባል መተግበር እንደሚያስፈልግ ባለሙያዎች እያሳሰቡ ነው፡፡ መንግሥት እስካሁን የተመራባቸው የፋይናንስ ፖሊሲዎች ሀብት አመንጪ ከመሆን፣ ችግር ፈቺ ከመሆን ይልቅ የሚተበትቡ ሆነዋልና ይስተካከሉ እየተባለ ነው፡፡
አገሪቱ ለወጪ ንግድ የሚበቁ በርካታ ጥሬ ሀብቶች ቢኖሯትም፣ በአግባቡ ልትጠቀምበት ካልቻለችባቸው ምክንያቶች አንዱ እንዲህ ያለውን ሀብት ተጠቅሞ ለአገሪቱና ለሕዝቧ ተገቢው ለውጥ እንዳይመጣ ያደረጉ ፖሊሲዎች በየጊዜው እየታረሙና እየተስካከሉ አለመምጣታቸ ነው፡፡ የወጪ ንግዱን ለማበረታት ያስችላሉ የተባሉ ዕርምጃዎች ስለመወሰዳቸው ቢነገረንም ያመጡት ለውጥ የለም፡፡
የዚህ ዘርፍ ዋና ዋና ችግሮች ከዚህ ቀደም በተከታታይ ለውይይት ሲቀርቡ የቆዩና በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ የሚታወቁ በመሆናቸው፣ ይኼንን በሚገባ ተመልክቶ አዲስ አሠራር መቅረጽ ያስፈልጋል፡፡ በወጪ ንግድ መስክ የተሰማሩ የንግድ ኅብረተሰብ አባላት ከእስከዛሬው አሠራራቸው ተላቀው ለራስ ብቻ ሳይሆን፣ ለአገርና ለሕዝብም ጥቅም እንዲተጉ፣ ስማቸው በመልካም በድርጊታቸው እየተወሳ እንዲኖሩ የሚያደርጋቸውን ተግባር መፈጸም ይጠበቅባቸዋል፡፡
የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ምርቶች እንደ አገሪቱ አቅም አኳያ ወደ ውጭ ሊላኩ ያልቻሉት በመንግሥት ፖሊሲ ችግር ብቻ እንዳልሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ የላኪዎችም ድርሻ አለበት፡፡ የወጪ ንግድ አሠራር ይሻሻል ሲባል ላኪዎቻችን ያለባቸውን ድክመት መቅረፍ ጭምር በመሆኑ፣ የወጪ ንግድ ገቢያችንን ማሳደግ ካስፈለገ፣ በሁሉም በኩል ሥር ነቀል ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ የጉምሩክ አሠራሮች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ቅልጥፍና በአጠቃላይ የሎጂስቲክስ ዘርፉን ያረጀና የተንዛዛ አሠራር መለወጥ ይጠይቃል፡፡
የገበያ መዳረሻ አገሮችንም ማስፋት የሚያስችል አሠራር በመዘርጋት ኤምባሲዎች ዋነኛ ሥራቸው ለአገር ምርት ገበያ በማፈላለግ መጠመድ፣ የውጭ ባለሀብት ማምጣትና የአገሪቱን ተወዳዳሪነትና ተፈላጊነት በሚያጎለብቱ በዚህ ተግባራት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ማድረግ ይገባል፡፡
በጥቅሉ የውጪ ምንዛሪ እጥረቱን ለመቅረፍ የወጪ ንግድ ዕድገት አንዱና ዋነኛው ተግባር ከመሆኑ አንፃር በዚህ ዙሪያ የሚሠራውን ሥራ ከፖለቲካ ጥገኝነት ማላቀቅና በባለሙያዎች የሚመራ ማድረግም ተገቢ ይሆናል፡፡ በዚህ ረገድ የሚደረገው ለውጥ በውጭ ምንዛሪ እጥረት የሚፈጠረውን ችግር ለማቃለል የሚረዳ ሲሆን፣ በውጭ ምንዛሪ ዕጦት እየተሳበበ በኅብረተሰቡ ላይ የሚቆለለውን ዋጋ ለመቆጣጠርም ይረዳል፡፡ ለዚህም ነው ቢያንስ ያለውን እያብቃቁ በመጠቀም የዶላር ለማኝ ከመሆን የሚገላግለን የወጪ ንግድ ፖሊሲ የለውጡ አካል እንደሆን የሚጠየቀው፡፡
ከዚሁ ጎን መነሳት ያለበት ጉዳይ የአገሪቱን የወጪ ንግድ እንደሚታደጉ ይነገርላቸው የነበሩ ተቋማት ለወጪ ንግድ የሚውል ምርት እናመርታለን በሚል ለጥሬ ዕቃና ለሌላውም ግብዓት መግዣ ወዘተ. እያሉ ወደ ውጭ የሚያወጡት ገንዘብ በአግባቡ መፈተሽ አለበት፡፡ ነገርን ነገር ያነሳዋልና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ባለበት አገር ውስጥ፣ ሕዝብ በሚያለቅስበት፣ መድኃኒትና ሌላውም አሳሳቢ ሸቀጥ ስለመጥፋቱ በሚነገርበት አገር ውስጥ በየመንገዱ ዳር ተቸምችመው፣ የመሸጫ ቤት አጣበው የሚታዩ የቅንጦት ተሽካርካሪዎችን ስናይ፣ ዕውን የዶላር እጥረቱ የሚባለውን ያህል አለ ወይስ ነገሩ ሌላ ነው ያሰኛል፡፡ በሚሊዮኖች ዋጋ የሚያወጡ መኪኖች ከየት እየመጡ ነው ዶላር ከከተማው የጠፋው? ቢባል የሚናናቅ ምልከታ አይመስለኝም፡፡
ስለዚህ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀማችን እንዴት መሆን ይገባዋል የሚለውንም ጥያቄ የሚመልስ አሠራር መዘርጋት አለበት፡፡ በለውጥ ጎዳና የምንጓዝ ከሆነ ለውጡ የእስከዛሬውን አሠራራችንና ፖሊሲዎቻችን በመፈተሽ የሚሻሻለውን በመጠገን፣ እንደነበረ መቀጠል ያለበትን በጊዜው ፍላጎት መሠረት ቃኝቶ መጓዝ ይገባል፡፡
ወደ ውጭ ከሚላኩ ምርቶች ባሻገር ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ዓይነተኛ የሆኑ የኢኮኖሚ ዘርፎችም ተገቢው ቅኝት ያሻቸዋል፡፡ የቱሪዝም ዘርፉ ዘመኑን የሚመጥን፣ የቱሪስቱን ፍላጎትን የሚሞላ አገልግሎትና አቅርቦት ኖሮት ቢሠራበት፣ አቅምና ችሎታው ያላቸው ተዋናዮች እንዲሳተፉበት ቢደረግ፣ በመንግሥት ሹመኞች ዘርፉ እንዲታሽ ከማድረግ ባሻገር ያሉ አማራጮች እየታዩ፣ በውጭ ድርጅቶችም ሆኑ በሌሎች አቅሙ ባላቸው አካላት እንዲተዳደር ቢደረግ ለውጭ ምንዛሪ በአፋጣኝ መፍትሔ ከሚያስገኙ መድኃኒቶች አንዱ ነውና ይታሰብበት እንላለን፡፡ እንደ ቱሪዝም ዘርፉ ሁሉ የሐዋላ ገቢና ሌሎችም ትኩረት የሚሹ የአጭር ጊዜ መፍትሔዎች ስላሉ መንግሥት ጥሩ መካሪዎቹን ጆሮ ይስጣቸው እንላለን፡፡