Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናከ50 ዓመታት በላይ ያገለገለው የንግድ ሕግ በሦስት ዓመታት ጥናት ሊሻሻል ነው

ከ50 ዓመታት በላይ ያገለገለው የንግድ ሕግ በሦስት ዓመታት ጥናት ሊሻሻል ነው

ቀን:

አምስት መጻሕፍትን አካቶ የያዘውና ከ50 ዓመታት በላይ ለ58 ዓመታት ሲሠራበት የቆየው የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ፣ በሦስት ዓመታት ጥናት ተሻሽሎ ሊቀርብ ነው፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የመጨረሻ ግብዓት ከባለድርሻ አካላት ለመውሰድ ማክሰኞ ሰኔ 26 ቀን 2010 ዓ.ም. በኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል ለሁለት ቀናት ያዘጋጀው ጥናታዊ መድረክ ላይ እንደተነገረው፣ የንግድ ሕጉ ከ2006 ዓ.ም. መጨረሻ ጀምሮ ከሸማቾች፣ ከሕግ ጥናትና ምርምር፣ ከቀድሞው ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ከኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ ከብሔራዊና ንግድ ባንኮች፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ በትምህርቱ የላቀ ዕውቀት ካላቸውና ከሌሎችም ተቋማት የተውጣጡ ምሁራን፣ ለስድስት ወራት በቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) ጥናት ተደርጎበታል፡፡

የሕግ ማርቀቅና ማፅደቅ ዳይሬክተር አቶ በላይ ሁንዴ እንደገለጹት፣ ከ50 ዓመታት በላይ በማገልገል ላይ የሚገኘው የንግድ ሕግ ከዓለም አቀፍ የንግድ ሕግ ጋር ያለውን አንድነት፣ ጉድለትና ሊስተካከሉ የሚገቡ ነገሮች፣ በንግድ ሕጉ ውስጥ መካተት ሲኖርባቸው ያልተካተቱ፣ ተካተው ለመተግበር አስቸጋሪ የሆኑ ሳይታዩ የቆዩ ድንጋጌዎችና ሌሎች ጉድለቶችን በዝርዝር በማጥናት፣ በአሁኑ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በወቅቱ የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ በነበሩት አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ለሚመራው ቋሚ ኮሚቴ ማስረከባቸውን አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

ስለነጋዴዎችና የንግድ መደብሮች፣ ስለኅብረት ሽርክና ማኅበር፣ ስለባንክና ኢንሹራንስ፣ ስለኪሳራና ሌሎች የንግድ እንቅስቃሴዎች የሚደነግጉ አምስት መጻሕፍትን በዝርዝር በማጥናት የጎደሉትን የማሟላት፣ የማይጠቅሙትን በማውጣት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው የንግድ ሕግ ለማወጅ የመጨረሻ ግብዓት ማስፈለጉንም አክለዋል፡፡ በእያንዳንዱ መጽሐፍ ላይ ጠለቅ ያለ ዕውቀት ያላቸው ምሁራን መሳተፋቸውንም ስም በመጥራት ጠቁመዋል፡፡

ረቂቅ ሕጉ ለሚኒስትሮች ምክር ቤትና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ከመፅደቁ በፊት፣ ለአንድ ዓመት ዓውደ ጥናት በማዘጋጀት ከተለያዩ ምሁራንና ልምድ ካላቸው የተለያዩ ተቋማት መሪዎች ጋር ውይይት መደረጉንም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

የተሻሻለው የንግድ ሕግ ረቂቅ ለሚቀጥሉት 50 እና ከዚያ በላይ ዓመታት እንዲያገለግል ሆኖ መጠናቱንና በርካታ ምሁራን የተሳተፉበት መሆኑን የገለጹት ደግሞ፣ ለጥናቱ የፋይናንስ ድጋፍ ማድረጉ የተገለጸው የፍትሕ ለሁሉም ፕሬዚዳንት ፓስተር ዳንኤል ገብረ ሥላሴ ናቸው፡፡

የሲንጋፖር፣ የደቡብ ኮሪያ፣ የጋና፣ የታንዛኒያና የደቡብ አፍሪካን ጨምሮ ከሌሎች አገሮች ልምድ በመነሳት፣ ረቂቁ ላይ በሚገባ እንደተሠራና ከዓለም አቀፍ የንግድ ሕግ ድንጋጌዎች ጋር ተወዳዳሪ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ ሕጉ ዘመኑን የተከተለ እንዲሆን ተደርጎ የተሠራ መሆኑንም አክለዋል፡፡

በአሁኑ ዘመናዊ ዓለም ውስጥ የአንድ አገር ኢኮኖሚ ዕድገት በተፈለገው ደረጃ ማደግ እንዲችል ከሚያስፈልጉ ሕጎች አንዱና ዋነኛው፣ ሁሉን አቀፍ የሆነና ዘመኑ የሚጠይቀውን መሥፈርት የሚያሟላ የንግድ ሕግ መኖር መሆኑን የገለጹት ደግሞ የፌዴራል ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ገለታ ሥዩም ናቸው፡፡ የነበረው የንግድ ሕግ ከአምስት አሠርት ዓመታት በፊት የቆየ በመሆኑ፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ማስተናገድ ያልቻለ፣ ድንጋጌዎቹን ተግባራዊ ለማድግ ሲሞከር ከወቅቱ ሁኔታ ጋር አብሮ መሄድ የማይቻል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አንዳንድ ድንጋጌዎችም በሥራ ያልተፈተሹ በመሆናቸው ተግባራዊ አለመደረጋቸውን አክለዋል፡፡

በመሆኑም ከዘመኑ ጋር ለማጣጣም የንግድ ሕጉን እንዲሻሻል መደረጉን አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ድርድር ላይ በመሆንዋ፣ ይኼንን ግምት ውስጥ ያስገባ፣ የአገሪቱን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በአግባቡ ለማስፈጸም ከአኅጉራዊና ከዓለም አቀፍ የንግድ ሕጎችና አሠራሮች አንፃር የተጣጣመ ሕግ ለማርቀቅ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ የውይይት መድረኩ እስከ ረቡዕ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ ለሁለት ቀናት ሲቆይ የሕግ ባለሙያዎቹን ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ፣ አቶ ታምሩ ወንድማገኘሁ፣ ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ፣ አቶ ዮሴፍ አዕምሮን ጨምሮ በርካታ ምሁራን ተሳትፈውበታል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...