Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ በሥልጣናቸው አይቀጥሉም

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ በሥልጣናቸው አይቀጥሉም

ቀን:

የአዲስ አበባ ምክር ቤት ጉባዔ ለማካሄድ የፓርላማ ውሳኔ እየተጠበቀ ነው

በአገሪቱ አጋጥሞ በነበረው ከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት ምርጫ ባለመካሄዱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የሥልጣን አካል ዕድሜው እንደሚራዘም ቢጠበቅም፣ ከንቲባ ድሪባ ኩማ መቀጠል እንደማይፈልጉ ማስታወቃቸውን ምንጮች  ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከጀመሩት የለውጥ ሒደት ጋር መራመድ አይችሉም በተባሉ የካቢኔ አባላት ሹምሽር እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡

አቶ ድሪባ በ2005 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በተካሄደ ምርጫ፣ ከትራንስፖርት ሚኒስትርነት ወደ ከንቲባነት መሸጋገራቸው ይታወሳል፡፡ ላለፉት አምስት ዓመታት አዲስ አበባን በከንቲባነት ሲመሩ ቢቆዩም፣ በዚህ ኃላፊነት በሌላ ምርጫ ለመቆየት ፍላጎት እንዳልነበራቸው ታውቋል፡፡ እሳቸው የሚመሩት ካቢኔ በተደጋጋሚ ሹምሽርና ሽግሽግ ቢደረግበትም፣ አሁን ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ ሹምሽር እንደሚደረግበት ይጠበቃል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታቦር ገብረ መድኅን (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የምክር ቤት ስብሰባ ለማካሄድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ እየተጠበቀ ነው፡፡

‹‹የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ የሹምሽር አጀንዳ እስካሁን ለምክር ቤቱ አላቀረበም፡፡ ምናልባት ሊያቀርብልንና በስብሰባችን ልንመለከተው እንችላለን፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የአዲስ አበባን ቻርተር የማውጣት ሥልጣን ያለው ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው ብለው፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ስብሰባ ለማካሄድ የፓርላማ ውሳኔ እየጠበቀ  መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ምናልባት ፓርላማው በቻርተሩ ላይ ማሻሻያ ካደረገ ሐምሌ 2 ቀን 2010 ዓ.ም. የምክር ቤቱ ጉባዔ ሊካሄድ ይችላል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤትና በከንቲባ ድሪባ የሚመራው ካቢኔ ሥልጣን ከያዘ ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. አምስት ዓመት የሚሞላው በመሆኑ፣ ምርጫ ተካሂዶ በሌላ መተካት ነበረበት፡፡ ነገር ግን ባለፉት ሦስት ዓመታት አገሪቱ በከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ በማሳለፏ በዚህ ዓመት ምርጫ ሳይካሄድ ቀርቷል፡፡

በዚህ መሠረት የከተማው አስተዳደር ማቋቋሚያ ቻርተር 361/1995 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እንዲሻሻል ውይይት እየተካሄደበት ነው፡፡ በቻርተሩ መሠረት፣ ‹‹የአዲስ አበባ ምክር ቤት የሥራ ዘመን አምስት ዓመት ይሆናል፡፡ ነገር ግን ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ገጥሞ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ምርጫ ማካሄድ ያልተቻለ እንደሆነ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የምርጫ ጊዜው ሊራዘም ይችላል፤›› የሚል የማሻሻያ አንቀጽ ለመጨመር ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡

በምክር ቤቱ ይህ አንቀጽ ተጨምሮ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ዕድሜ ከተራዘመ፣ የከንቲባ ድሪባ የመልቀቅ ፍላጎት እንዳለ ሆኖ በአስተዳደሩ ካቢኔ ከፍተኛ ሹምሽር እንደሚኖር ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር የሚገኙ ቢሮዎች የካቢኔ አባላት ናቸው፡፡ እነዚህ ቢሮዎች በአጠቃላይ 34 ሲሆኑ፣ በካቢኔ ውስጥ በኃላፊዎቻቸው ይወከላሉ፡፡

ከእነዚህ የቢሮ ኃላፊዎች ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከጀመሩት የለውጥ ሒደት ጋር መጓዝ አይችሉም የተባሉ ተነስተው፣ በአዳዲስ ኃላፊዎች እንደሚተኩ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...