Tuesday, July 16, 2024

ከሰላምና ከዴሞክራሲ የሚቀድም የለም!

የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ በቅጡ የሚከታተል ማንም ሰው መልካም አጋጣሚዎች መፈጠራቸውን በቀላሉ ይረዳል፡፡ እነዚህ መልካም አጋጣሚዎች አስተማማኝ እንዲሆኑ ግን የፖለቲካ ጨዋታውን ማሳመር ተገቢ ነው፡፡ ከውጤት በፊት ሒደቱን በመግራት በተፈጠሩት መልካም አጋጣሚዎች ምን መደረግ እንዳለበት ጠንቅቆ መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡ አገር የለውጥ ባህር ውስጥ ስትገባ ዓላማው መታወቅ አለበት፡፡ እንደ አገር ከየት ወዴት መሸጋገር እንደሚያስፈልግ፣ በየመንገዱ ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ተግዳሮችችና ተስፋዎች፣ በተጨማሪም ዓላማን ለማሳካት ሲባል ሊኖሩ ስለሚችሉ የተለያዩ አማራጮች መጠበብ የግድ ይሆናል፡፡ ከምንም ነገር በላይ የአገር ህልውናን ማስቀደም የዓላማ መነሻ መሆን አለበት፡፡ ከኢትዮጵያ በፊት ምንም ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ የለም ማለት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ይቅደሙ ማለት ነው፡፡ የሚፈለገው ለውጥ ሁሉን አሳታፊ፣ በመርህ የሚመራና ከውዥንብር የፀዳ እንዲሆን ለሰላምና ለዴሞክራሲ ልዩ ሥፍራ ሊኖር ይገባል፡፡ ሰላምና ዴሞክራሲ መኖራቸው የሚረጋገጠው ደግሞ የተለያዩ ሐሳቦች በነፃነት ሲናኙ ነው፡፡

መጪው ጊዜ ብሩህ እንዲሆን መመኘት መልካም ቢሆንም፣ በጣም አስቸጋሪና ፈታኝ ነገሮች ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ከወዲሁ መዘጋጀት ይገባል፡፡ በቀላሉ ሊከናወኑ ይችላሉ ተብለው የሚጠበቁ ጉዳዮች ከሚታሰበው በላይ ሊከብዱ ይችላሉ፡፡ በፖለቲካዊ መስክ እየተሰሙ ያሉ ዝብርቅርቅ ነገሮች፣ የቢሮክራሲው ውጥንቅጥ፣ በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ እየታየ ያለው ክፍፍል፣ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ሊኖር የሚችለው ውዝግብና ድርድር፣ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚያገረሹ ግጭቶች፣ አሁንም ለሐሳብ ነፃነት የሚሰጠው እዚህ ግባ የማይባል ግምት፣ ወዘተ መጠነኛ ማሳያ ናቸው፡፡ በኢኮኖሚ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ እጥረት የፈጠረው ያልተረጋጋ ገበያ፣ የሕዝቡ የመግዛት አቅም መዳከም፣ አገሪቱ ላይ የተቆለለው የዕዳ ጫና፣ የምርትና የምርታማነት መቀዛቀዝና የመሳሰሉት የተጋረጡ ፈተናዎች ናቸው፡፡ በእነዚህ ችግሮች ላይ የገዘፈ ድህነት፣ እንደ ሰደድ እሳት የሚጋረፍ የኑሮ ውድነት፣ የመኖሪያ ቤት ችግርና ሌሎችም ፋታ የማይሰጡ ጉዳዮች አሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግሮች ባሉበት አገር መልካም አጋጣሚዎችን ማበላሸት ቀውስ መፍጠር እንጂ ለማንም አይጠቅምም፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ መስኮች መሠረታዊ ለውጥ እንዲያስመዘግቡ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና አስተዳደራቸው ከፊታቸው ትልቅ ኃላፊነት ይጠብቃቸዋል፡፡ ኢትዮጵያን ካለችበት አዘቅት ውስጥ ለማውጣት በሚደረገው ጥረት ግንባር ቀደም ኃላፊነት ቢኖርባቸውም፣ በሰከነ መንገድ ድጋፍ ሊያደርግላቸው የሚገባው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኃላፊነትም ከበድ ያለ ነው፡፡ ይኼንን እንደ ተራራ የገዘፈ ኃላፊነት በቅን ልቦና፣ እንዲሁም በከፍተኛ ትጋት መወጣት አለመቻል ሰላምን ያደፈርሳል፡፡ ዴሞክራሲ እንዳይሰፍን መሰናክል ይሆናል፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ ተዓምር መጠበቅ ራሱን የቻለ ፈተና ነው፡፡ ይኼንን የሽግግር ወቅት በብልኃት ለማለፍ የሚቻለው፣ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ሆነው ለመፍትሔ ሲረባረቡ ነው፡፡ እየተጀመረ ላለው ለውጥ ሁሉንም ነገር በአንድ ግለሰብ ትከሻ ላይ ከምሮ ውጤት መጠበቅ አይቻልም፡፡ ለውጡን ከሕዝብ ሁለንተናዊ ተሳትፎ አለያይቶ ሁሉንም ነገር ግለሰቦች ላይ መጫን አገሪቱን የማትወጣው ችግር ውስጥ ይከታል፡፡ ግለሰቦች ውጤታማ መሆን የሚችሉት ለተቋማት ጥንካሬ ልዩ ትኩረት ሲሰጥ ነው፡፡ ለሕግ የበላይነት ከበሬታ ሲቸር ነው፡፡ ሰላምና ዴሞክራሲም ዕውን የሚሆኑት በዚህ መንገድ ነው፡፡

በምክንያታዊነት የሚመራ ለውጥ ለስሜታዊነትና ለግብታዊነት ክፍተት አይሰጥም፡፡ ይልቁንም ሕዝብን ማዕከል በማድረግ ተሳትፎውን አካታች ይሆናል፡፡ የሕዝብ  ተሳትፎ ሲባል በቀጥታ በየተሰማራባቸው የሥራ መስኮች፣ በተዘዋዋሪ ደግሞ ይወክሉታል ተብለው በሚታሰቡ አደረጃጀቶች ነው፡፡ መልካም አጋጣሚዎች የበለጠ እየጎመሩ የሚሄዱትም እያንዳንዱ ዜጋ ለአገሩ ምን ማበርከት እንዳለበት መብቱንና ግዴታውን ሲረዳ ነው፡፡ የለውጡ ዓላማ ጥርት ብሎ ይገባው ዘንድ ደግሞ የሐሳብ  ድጋፍ ያስፈልገዋል፡፡ አመራሩም ዓላማውን ግልጽ ከማድረግ ጀምሮ የእያንዳንዱ ዜጋ ተሳትፎ ምን መምሰል እንዳለበት የማስረዳት ኃላፊነት አለበት፡፡ ሕዝብን ለማስደሰት ወይም ፍቅሩን ለማግኘት ሲባል ብቻ ሳይሆን፣ በድርጊት ሊገለጽ የሚችል ዓላማና ግብን ማመልከት ተገቢ ነው፡፡ ሰላምና ዴሞክራሲ የሚሰርፁት በዚህ መንገድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሰላም አየር እየነፈሰባት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ የሰላም አየር አስተማማኝ ሆኖ እንዲቀጥል ሲፈለግ፣ የሚያደናቅፉ ችግሮች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ መዘንጋት አይገባም፡፡ ሰሞኑን እያጋጠሙ ያሉ ብልጭ ድርግም የሚሉ ግጭቶችና የሚሰሙ ሥጋቶች ይኼንን እሳቤ ያጠናክራሉ፡፡ ሰላም ከሌለ ዴሞክራሲ ስለማይኖር ልብ ማለት ተገቢ ነው፡፡

በሌላ በኩል አቅጣጫቸውን የሳቱ አስተያየቶች በስፋት ይደመጣሉ፡፡ አንዳንድ ወገኖች መደመር ምን ማለት ነው በማለት ይጠይቃሉ፡፡ ለዚህ ጥያቄ ግን የሚሰጠው ምላሽ የተለያየ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ሲሰየሙ ባደረጉት ንግግር ለዚህ ጽንሰ ሐሳብ አቻ የሚሆን ማብራሪያ ሰጥተው ነበር፡፡ ‹‹አንድነት ማለት አንድ ዓይነትነት ማለት አይደለም፤›› ሲሉ፣ የመደመር ጉዳይም የለውጡ ተዋናይ በመሆን የራስን አቋም ማራመድ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በፓርላማ በአሸባሪነት የተፈረጁ ድርጅቶች እንዲሰረዝላቸው ለፓርላማ ማቅረብ፣ ብረት ያነሱ ኃይሎች ወደ ሰላማዊ ትግል እንዲመለሱ ጥሪ ማድረግ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ያኮረፉ ግለሰቦች ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ መፍቀድና የመሳሰሉት በልዩነት ውስጥ ሆኖ ለአገር የመሥራትን ህብር የሚያሳይ ነው፡፡ አንዳንዶች እንደሚሉት ሁሉም በተቀደደለት ቦይ አንድ ላይ መፍሰስ አለበት ማለትም አይደለም፡፡ ነገር ግን ለውጡ የሁሉም ተሳትፎ ታክሎበት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ አገር እንድትፈጠር ድርሻን መወጣት ነው፡፡ በሐሳብ መለያየት ቢኖርም፣ በአገር የጋራ ጉዳይ ግን ተቀራራቢ ዕይታ መኖር እንዳለበት መረዳት ይገባል፡፡ ገዥው ፓርቲና ሊቀመንበሩ የራሳቸው አጀንዳ እንዳላቸው ሁሉ፣ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎችና ግለሰቦችም የራሳቸው ይኖራቸዋል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ መደመር አንድ ላይ መጨፍለቅ ሳይሆን፣ በጋራ ጉዳዮች ላይ ተባብሮ መሥራት እንደሆነ ግንዛቤ ይያዝ፡፡ ሰላምና ዴሞክራሲ የሚገለጹት በዚህ መንገድ ነው፡፡

በፖለቲካና በማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፎች የተሰማሩ ምሁራን፣ በዚህ ወቅት ሕዝቡንም ሆነ የለውጡን ተዋንያን አቅጣጫ የማስያዝ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ አገር በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ስትዳክር ምክንያታዊ እሳቤዎች እንዲጎለብቱና ስሜታዊነት እንዲቀዛቀዝ፣ የምሁራኑ አበርክቶ ተፈላጊ ይሆናል፡፡ ከተጨባጭ ሁኔታዎች በመነሳት ጥንካሬዎችን የበለጠ ማፈርጠም፣ ደካማ ድርጊቶችን ደግሞ በሰላ ሒስ መተቸት ይገባል፡፡ የለውጡ ባቡር ላይ የተሳፈረ ሁሉ መነሻውን እንጂ መድረሻውን ካለወቀው ልፋቱ ሁሉ ገደል ይገባል፡፡ ለውጥ በተዓምር ሳይሆን በድርጊት ነው የሚገኘው፡፡ ድርጊት ደግሞ በመርህ መመራት አለበት፡፡ ከግለሰቦች ይልቅ ተቋማት ላይ ማተኮር፣ የተጎሳቆሉ ተቋማት ነፍስ እንዲዘሩ መትጋት፣ ለሕግ የበላይነት ክብር መስጠት፣ ለውጡ በስኬት እንዲጓዝ ስህተቶችን መቀነስ፣ የድል አጥቢያ አርበኞችን መገሰፅ፣ ሥልጣን  ማገልገያ እንጂ መባለጊያ እንዳይሆን መቆጣጠርና ልጓም ማበጀት፣ ወዘተ የግድ ይሆናል፡፡ በተለይ የተለየ ሐሳብ ያላቸው በተለየ ሁኔታ እንዲመጡ ዕድሉን ማመቻቸት ይገባል፡፡ ትናንት ለዚህ ነፃነት ሲጮሁ የነበሩ ዛሬ አፍ ለማዘጋት ሲሯሯጡ ይታያሉና ልዩ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ቦልቴር የሚባለው የጥንት ዘመን ፈላስፋ፣ ‹‹የምትናገረው ሁሉ ባይጥመኝም ሐሳብህን እንድትገልጽ ግን እስከ ዕለተ ሞቴ ጠበቃ እሆንሃለሁ፤›› እንዳለው ሁሉ፣ በሐሳብ መለያየት ሞት ስላልሆነ ለሐሳብ ነፃነት ልዕልና በጋራ መቆም ያስፈልጋል፡፡ ሰላምና ዴሞክራሲ መቅደም ያለባቸውም ለዚህ ነው፡፡

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...

በነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ሳቢያ አጠቃላይ ገበያው እንዳይታመም ትኩረት ይደረግ!

መንግሥት ነዳጅን ከመደጎም ቀስ በቀስ እየወጣ ነው፡፡ ለነዳጅ የሚያደርገውን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...

ከሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ተፃራሪ ላለመሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ድብልቅልቅ ስሜት የሚፈጥሩ በርካታ ሁነቶች ማጋጠማቸው አዲስ ነገር ባይሆንም፣ በዚህ ወቅት ከተለያዩ ፍላጎቶችና ዓላማዎች ጋር የተሸራረቡ ሥጋት ፈጣሪ ችግሮች በብዛት እየተስተዋሉ ነው፡፡...

መንግሥት ቃሉና ተግባሩ ይመጣጠን!

‹‹ሁሉንም ሰው በአንዴ ለማስደሰት ከፈለግህ አይስክሬም ነጋዴ ሁን›› የሚል የተለምዶ አባባል ይታወቃል፡፡ በፖለቲካው መስክ በተለይ ሥልጣነ መንበሩን የጨበጠ ኃይል ለሚያስተዳድረው ሕዝብ ባለበት ኃላፊነት፣ በተቻለ...