የፖሊስ ኮሚሽነሩንና የፀጥታ ቢሮ ኃላፊውን ጨምሮ አራት ሹማምንት ታገዱ
በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በአሶሳ ከተማና ዙሪያው በሚገኙ ከተሞች ሰኔ 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ተጠርጥረው ከታሰሩት 54 ተጠርጣሪዎች መካከል፣ 11 የክልሉ ፖሊስ አባላት መሆናቸው ተገለጸ፡፡
የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አሻድሊ ሐሰን እንደገለጹት፣ ለሦስት ቀናት በቆየው ግጭት የ14 ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ ተረጋግጧል፡፡ አብረው እየሠሩ ከመኖርና ከመከባበር ውጪ ሌላ ነገር በማያውቁት በክልሉ ነዋሪዎች መካከል ብጥብጥ እንዲነሳና የሰው ሕይወት እንዲያልፍ መደረጉ እንዳሳዘናቸው ገልጸው፣ ድርጊቱ በጣም አሳዛኝ ስለሆነ ከዚህ በኋላ መቼም ይሁን መቼ አይደገምም ብለዋል፡፡
የመከላከያ ሠራዊትና የክልሉ የፀጥታ ሠራተኞች በጋራ ባደረጉት ጥረት የከፋ ችግር ሳይደርስ ግጭቱን መቆጣጠር መቻሉን አስታውሰው፣ ለግጭቱ መነሳትና መባባስ በዋናነት ተሳታፊ ነበሩ ተብለው የተጠረጠሩ 54 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የኅብረተሰቡን ፀጥታ ማስከበርና የተፈጠረውን ግጭት ማስቆም የሚገባቸው 11 የፖሊስ አባላት ተሳታፊ ሆነው ተገኝተዋል ተብለው፣ በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ አክለዋል፡፡
የክልሉን የፀጥታ ሁኔታ በመከታተል አስፈላጊውን ዕርምጃ በመውሰድ ኃላፊነታቸውን መወጣት ባለመቻላቸው ለሕይወት መጥፋት፣ ለንብረት መውደምና ለዘረፋ ዳርገዋል ተብለው የተገመገሙ አራት ኃላፊዎች ከሥራና ኃላፊነታቸው መነሳታቸውንም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡
ከኃላፊነት የተነሱት የክልሉ የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዲንሳ በየነ፣ የፖሊስ ኮሚሽነሩ አብደላ ሻህዲ፣ የፀረ ሽምቅና ዓድማ ብተና ፖሊስ መምርያ ኃላፊና ምክትላቸው መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ በአሁኑ ጊዜ ሙሉ ሰላም ሰፍኖ ኅብረተሰቡ የዕለት ተዕለት ሥራውን እያከናወነ መሆኑንና በአሶሳ፣ በዞን ከተሞችና በወረዳዎች ከኅብረተሰቡ ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል፡፡
በግጭቱ ለሞቱ ሰዎች ቤተሰቦችና ንብረት ለወደመባቸው ዕርዳታ ለማድረግ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጥናት እየተደረገ መሆኑም ተገልጿል፡፡