Wednesday, May 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮ ቴሌኮምን አጠቃላይ የሀብት መጠን ለመለካት አራት የውጭ ኩባንያዎች ይወዳደራሉ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት ሙሉ በሙሉና በከፊል ወደ ግል እንደሚያዛውራቸው ይፋ ካደረጋቸው የልማት ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው ኢትዮ ቴሌኮም፣ በአሁኑ ወቅት ያሉት ቁሳዊና ሌሎችም ሀብቶቹ ተጠቃለው እንዲተመኑና አጠቃላይ ሀብቱ ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ አራት የውጭ አማካሪ ኩባንያዎችን ለማነጋገር መዘጋጀቱ ታወቀ፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ አንዷለም አድማሴ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔን ተከትሎ የኩባንያውን መልካም ስምና ገጽታ፣ የዘረጋቸውን መሠረተ ልማቶችና ሌሎችም ንብረቶች ያካተተ አጠቃላይ የዋጋ ትመና ለመሥራት ኬፒኤምጂ፣ ኧርነስት ኤንድ ያንግ፣ ድሎይት እንዲሁም ፕራይስ ዋተር ሐውስ ኩፐርስ (ፒደብሊውሲ) የተባሉትን ኩባንያዎች በማነጋገር ከአራቱ አንዳቸውን ለሥራው እንደሚቀጥር ይጠበቃል፡፡ 

በከፊል ወደ ግል ይዛወራሉ ከተባሉት የልማት ድርጅቶች ውስጥ የተመደበው ኢትዮ ቴሌኮም፣ ምን ያህል ሊያወጣ እንደሚችል የሚደረገው ጥናት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠቃሎ እንደሚያልቅ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል፡፡ የኩባንያውን የዋጋ ትመና ከአራቱ ኩባንያዎች ውስጥ አንዱ እንዲያከናውነው የተፈለገበትና በጨረታ ሌሎች የማይሳተፉበት ምክንያትም፣ አቅሙ የሌላቸው ኩባንያዎች በጨረታ አሸንፈው ነገር ግን ወደ ግል የማዛወር ሒደቱን ሊያጓትቱት ይችላሉ ከሚል ሥጋት በትልልቆቹ ላይ ማተኮር እንዳስፈለገም ተብራርቷል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም የሀብት መጠን ምን ያህል ነው የሚለውን ለመለካት ቅድሚያ የቋሚ ሀብት ምዘና ሥራዎችን ማካሄድ እንደተጀመረ፣ ሆኖም አጠቃላይ የኩባንያውን ጠቅላላ ሀብትና ንብረት በዋጋ ተመን ወደ ግል ለማዛወር በሚደረገው ሒደት የመጀመርያው ሥራ ሲሆን፣ ኩባንያውን በአክሲዮን ድርሻ በከፊል ወደ ግል የማዛወሩ ሒደትም ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሊካሄድ የሚችልበት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ከዋና ሥራ አስፈጻሚው ለመረዳት ተችሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮ ቴሌኮም ወደ ሁለት ተቋምነት ሊከፈል ይችላል የሚሉ መረጃዎች እየተሠራጩ በመሆናቸው ስለዚሁ ጉዳይ ተጠይቀው ያብራሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አንዷለም (ዶ/ር)፣ ኩባንያው ለሁለት በመከፈሉም ሆነ በሌሎች መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚሰጡት ዝርዝር መመርያ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በሚደረገው ውይይት መሠረት የኩባንያው የወደፊት አካሄድ እንደሚታወቅ ከመግለጽ በቀር፣ አሁን ይህ ነው የሚባል የተጨበጠ መግለጫ መስጠት እንደሚቸግር አስረድተዋል፡፡  

ይሁንና በአሁኑ ወቅት ሌሎች ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት መስጠት የሚችሉበት ሰፊ ዕድል ስለመኖሩ ፍንጮች ያመላክታሉ፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንደጠቆሙት፣ ከመንግሥት የቴሌኮም ፈቃድ ለማግኘትና አገልግሎቱን ለመስጠት ፍላጎት ያላቸው ኩባንያዎች ለፈቃድ ብቻ እስከ 600 ሚሊዮን ዶላር ሊከፍሉ የሚችሉበት የቴሌኮም ዘርፍ በአገሪቱ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡

 ኢትዮ ቴሌኮም በትንሹ ሁለት ጊዜ ባካሄዳቸው የቴሌኮም መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ሥራዎች ብቻ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡ በመጀመርያው የቴሌኮም መሠረተ ልማት ዝርጋታ ለተሳተፈው ኖኪያ ኩባንያና በኋላ በቻይናው ዜድቲኢ አማካይነት ለተገነባው የመሠረተ ልማት 1.5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት የተረደገ ሲሆን፣ ከሦስት ዓመት በፊት ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀውና በአሁኑ ወቅት ከ21 ሺሕ ኪሎ ሜትር በላይ ለሚሸፍነው የፋይበር መስመርና ሌሎችም የቴሌኮም መሠረተ ልማቶች የ1.6 ቢሊዮን ዶላር ወጪ መደረጉ ይታወሳል፡፡ በዚህ ሥራ ሁዋዌ በዋናነት እንዲሁም ዜድቲኢና የስዊድን ኤሪክሰን ኩባንያ መሳተፋቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች