Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየስኳር ኮርፖሬሽን ቦርድ ሜቴክ እጅ የቀሩ ሦስት የስኳር ፕሮጀክቶች ኮንትራት እንዲቋረጥ ወሰነ

የስኳር ኮርፖሬሽን ቦርድ ሜቴክ እጅ የቀሩ ሦስት የስኳር ፕሮጀክቶች ኮንትራት እንዲቋረጥ ወሰነ

ቀን:

ውሳኔውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማፅደቅ አለባቸው

ኮርፖሬሽኑ ዕርምጃው ቀደም ብሎ እንዳይወሰድ ‹‹ማስፈራሪያ ይደርሰኝ›› ነበር አለ

የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ለዓመታት ሊያጠናቅቃቸው ያልቻላቸው ሦስት ግዙፍ የስኳር ፕሮጀክቶች የግንባታ ውሎች እንዲቋረጡ መወሰኑን፣ የፕሮጀክቶቹ ባለቤት የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን አስታወቀ ይኼንኑ ውሳኔም ኮርፖሬሽኑን የሚመራው ቦርድ እንዳፀደቀውገልጿል፡፡

የፓርላማው የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኮርፖሬሽኑን ሥራ አፈጻጸም ሰኞ ሰኔ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ሲገመግም፣ የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድአወቅ አብቴ ሜቴክ እጁ ላይ የቀሩትን ሦስት ፕሮጀክቶች ለመፈጸም የስድስት ወራት ማራዘሚያ ቢሰጠው እንደሚጨርስ ቢገልጽም፣ ኮርፖሬሽኑ ግን በሜቴክ ላይ እምነት እንደሌለው ገልጸዋል።

የስኳር ፕሮጀክቶቹን በአንድ ዓመት ከስድስት ወራት አጠናቆ ለማስረከብ ታሳቢ ተደርገው የተጀመሩ ቢሆንም፣ በሰባት ዓመታት ጊዜ ውስጥ አንድም ፋብሪካ አለመጠናቀቁን ያስታወሱት አቶ ወንድአወቅ፣ የማጠናቀቂያ ጊዜው 20 ጊዜ በላይ ተራዝሞለትም ሜቴክ የፈጠረው ነገር እንዳልነበር በመግለጽ የተጠየቀውን ተጨማሪ ጊዜ መፍቀድ ተገቢ ሆኖ እንዳላገኙት ተናግረዋል። በመሆኑም የበለስ አንድና ሁለት የስኳር ፋብሪካዎች፣ እንዲሁም የኦሞ ኩራዝ አንድ የስኳር ፋብሪካ ግንባታ ውል እንዲቋረጥ የስኳር ኮርፖሬሽን ማኔጅመንት ወስኖ ለቦርድ እንዳሳወቀና ቦርዱም ውሉ እንዲቋረጥ መወሰኑን አቶ ወንድአወቅ ለቋሚ ኮሚቴው አስታውቀዋል።

ሜቴክ ከጀመራቸው አሥር ግዙፍ የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክቶች አንዳቸውንም ማጠናቀቅ ሳይችል የተነጠቀ ሲሆን፣ ከሜቴክ ተነጥቆ ለቻይና ኩባንያ የተሰጠው ኦሞ ኩራዝ ሁለት ተጠናቆ ወደ ምርት ሒደት መግባቱ ይታወቃል። የወልቃይት ስኳር ፋብሪካም እንደዚሁ ተነጥቆ ለሌላ የቻይና ኩባንያ መሰጠቱይዘነጋም። እንደ መንግሥት የመጀመርያ ዕቅድ ቢሆን ኖሮ ለሜቴክ የተሰጡት ፕሮጀክቶች በሙሉ እስከ 2007 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ መጠናቀቅ የነበረባቸው ሲሆን፣ በዚህ ዓመት የአገሪቱን የስኳር ፍላጎት ሙሉ በሙሉማርካትና ቀሪውን የተትረፈረፈ ምርት ለውጭ ገበያ ኤክስፖርት በማድረግ፣ 2007 ዓ.ም. መጨረሻ ጀምሮ በየዓመቱ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ነበረበት።

የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ ለዕቅዱ አለመሳካት ዋነኛው ምክንያት የአሥሩም ፋብሪካዎች የግንባታ ኮንትራት በዘርፉ ምንም ልምድም ሆነ አቅም ለሌለው የአገር ውስጥ ኩባንያ ሜቴክ መሰጠቱ መሆኑን፣ ከሦስት ዓመት በላይ በዚሁ ጉዳይ ላይ ባደረገው ተደጋጋሚ ግምገማ መገንዘቡን ሲዘገብ መቆየቱ ይታወሳል። ከዚህም አልፎ ግንባታውን ለሚፈጽመው ሜቴክ አመራሮች ‹‹ከሕግ በላይ አይደላችሁም›› በማለት ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ እንደነበር፣ የቀድሞው የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ለማንኛውም ነገር ለመጠየቅ ዝግጁ መሆናቸውንና ከፋብሪካዎቹ ግንባታ ጋር በተገናኘ የሠሩት የሚፀፅታቸው ነገር እንደሌለ ለኮሚቴው መግለጻቸውን በተመለከተ መዘገባችን ይታወሳል።

ኮሚቴው የስኳር ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎችን በመጥራት ባካሄደው የሥራ አፈጻጸም ግምገማ በድጋሚ የስኳር ፕሮጀክቶቹ አለመጠናቀቅን በማንሳት የኮርፖሬሽኑን አመራሮች ከፕሮጀክት አስተዳደር ጋር በተገናኘ ወቀሳ ሰንዝሮባቸዋል። በዚህ የኮሚቴው ወቀሳ አግባብነት ያልተደሰቱት የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድአወቅ ጠንከር ባለ ምላሽ ቋሚ ኮሚቴውን ተችተዋል። ሜቴክ በዘርፋ ምንም ልምድ እንደሌለው እየታወቀ አሥር ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እንዲገነባ ሲሰጠው ሁሉም የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ያለተቃሮኖ እንደተቀበሉት ያስታወሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ይኼንን ሒደትም የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ ያውቅ እንደነበር ገልጸዋል። ስኳር ኮርፖሬሽን በሜቴክ የግንባታ አፈጻጸም ላይ ለዚሁ ቋሚ ኮሚቴ ያለውን የመረረ ቅሬታ ካቀረበ በኃላ፣ በ2008 ዓ.ም. ይኸው ቋሚ ኮሚቴ የስኳር ፕሮጀክቶቹን በአካል ተዘዋውሮ በመጎብኘት ኮርፖሬሽኑን ማገዝ ሲገባው ሜቴክን ማድነቁን አስታውሰው ትችት አዘል ቅሬታ አቅርበዋል።

‹‹ሁሉም በየፊናው አጨብጭቦ ካደነቀ በኃላ እኛን በየመድረኩ በመገምገም ማስጨነቁ ተገቢ አይደለም፡፡ ኃላፊነት እንወስዳለን፡፡ ነገር ግን ከአቅማችን በላይ ከሆነ ምንም ማድረግ አንችልም፤›› ብለዋል። ከዚህ ቀደም ባሉት ዓመታት መቋረጥ አለባቸው ተብለው በኮርፖሬሽኑ የተገመገሙ የስኳር ፕሮጀክቶችን ውል በማቋረጥ ዕርምጃ ለመውሰድ የተደረገ ሙከራ ቢኖርም፣ በኮርፖሬሽኑ አመራሮች ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ዛቻ በመሰንዘራቸው ዕርምጃ መውሰድ እንዳልተቻለም አቶ ወንድአወቅ ገልጸዋል። ‹‹ዕርምጃ ልንወስድ ስንል ይህማ ከግንብ ጋር መጋጨት ነው፡፡ እስኪ ሞክሯትና ወዮላችሁ፤›› እንደተባሉም አጋልጠዋል። ዛቻውን የሰነዘሩ ባለሥልጣናትን ማንነት ባይገልጹም፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸውና ከጉዳዩ ወጪ የሆኑ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ኮርፖሬሽኑም ሆነ ቦርዱ በሜቴክ እጅ የቀሩ ሦስት ፕሮጀክቶች ውል እንዲቋረጥ ቢወስኑም በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ መስጠት የሚችሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል። ይኼንን የተረዳ የሚመስለው ቋሚ ኮሚቴው የቀሩት ስኳር ፋብሪካዎች እስከ 2011 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ እንዲጠናቀቁ ኮርፖሬሽኑ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስቧል። ይኸው ቋሚ ኮሚቴ ግንቦት 29 ቀን 2010 ዓ.ም. የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የሥራ አፈጻጸምን እንደገመገመ፣ በወቅቱም ሜቴክ ከፍተኛ የሀብት ብክነትና የውጤታማነት ችግር እንዳለበት ማመኑን መዘገባችን ይታወሳል። የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር ሆነው በቅርቡ የተሾሙት ቀድሞው የንግድ ሚኒስትር በቀለ ቡላዶ (/) ለኮሚቴው በሰጡት አስተያየት፣ በሜቴክ ውስጥ የመንግሥትን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለመደገፍ የሚያስችል ትልቅ አቅም መኖሩን፣ ይሁን እንጂ ኮርፖሬሽኑ የያዛቸው ግዙፍ የመንግሥት ልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እየተከናወኑ አለመሆናቸውን፣ የውጤታማነትና የሀብት ብክነት ችግሮች እንዳሉ አረጋግጠው ነበር።

ቋሚ ኮሚቴው ባደረገው ግምገማ ኮርፖሬሽኑ የመንግሥት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ተረክቦ ለመፈጸም አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን፣ በራሱ የጀመራቸውን ሥራዎችንም በተመለከተ ከፍተኛ የሀብት ብክነት የታየበት መሆኑን አረጋግጧል። በአጠቃላይ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት ማባከኑን ቋሚ ኮሚቴው አስታወቋል። ኮርፖሬሽኑ ምንም ዓይነት የገበያ ጥናት ሳያደርግ የተለያዩ ማሽኖች፣መለዋወጫ ዕቃዎችና መሣሪያዎችን በማምረት አከማችቶ እንዲቀመጡ ማድረጉን ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል። በጥቅሉ ዘጠኝ ቢሊዮን በላይ ብር የሚገመቱ ንብረቶች ያለ ጥናት ተመርተው ገበያ በማጣታቸው ለበርካታ ዓመታት በመጋዘን ተከማችተው እንደሚገኙ ጠቁሟል። የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለመደገፍ በጥናት ላይ ተመሥርቶ ባለመሥራቱ 4.4 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የእርሻ ትራክተሮች፣ መሣሪያዎችና የመለዋወጫ ዕቃዎች በአዳማ የእርሻ መሣሪያዎች ኢንዱስትሪ ክምችት ውስጥ እንዲቀመጡ ማድረጉን ጠቁመዋል።

ከአሥር ሺሕ በላይ የእርሻ ትራክተሮችና መለዋወጫዎች ተመርተው በገበያ ዕጦት በመጋዘን እንዲከማቹ ያደረገው ሜቴክ ለአርሶ አደሮች በረዥም ጊዜ የዱቤ ሽያጭ ለማከፋፈል ዕቅድ ቢኖረውም፣ ዕቅዱን በተመለከተ ከክልል መንግሥታት ስምምነት አላገኘም። በቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ክምችት ክፍል ደግሞ 4.6 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ የተለያዩ መለዋወጫዎች ያለሥራ በመቀመጣቸው ለብክነት እየተዳረጉ መሆኑ ተጠቅሷል። ድርጅቱ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ሊደግፍ በሚችል ሁኔታ በጥናት ላይ ተመሥርቶ እየሠራ አለመሆኑን የቋሚ ኮሚቴው አባላት በግምገማው ላይ አንስተዋል። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ገብረ እግዚአብሔር አርዓያ እንደገለጹት፣ ኮርፖሬሽኑ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በውሉ መሠረት ማጠናቀቅ አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን፣ በውል ከተፈቀደው የጊዜ ገደብ በእጅጉ የተራዘመ ጊዜ ውስጥም ማጠናቀቅ አለመቻሉን ተናግረው ነበር።

ተቋሙ በየጊዜው ለምክር ቤቱ የሚያቀርባቸው ሪፖርቶች ወጥነት የጎደላቸውና እርስ በእርስ የሚጣረሱ መሆናቸውን፣ ለአብነትም የያዩ ማዳበሪያ ፕሮጀክት አፈጻጸም ሪፖርት ተዓማኒነቱ ጥያቄ ውስጥ እንደሆነ ገልጸው ነበር። በተጨማሪም የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ የበለስ ቁጥር አንድ ስኳር ፋብሪካዎች ግንባታቸው 90 በመቶ በላይ እንደተጠናቀቀ ከአንድ ዓመት በፊት የተገለጸ ቢሆንም፣ አዲሱ ዋና ዳይሬክተር በቀለ ቡላዶ (ዶ/ር) ያቀረቡት ሪፖርት ግን ከአምናው ያነሰ መሆኑን የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ጠቁመዋል።

ያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ 11 ቢሊዮን ብር ይጠናቀቃል ተብሎ የተገመተ ቢሆንም፣ በሁለት ዓመት እንደሚጠናቀቅ የታቀደው ይህ ፋብሪካ ከስምንት ዓመት በኋላም አፈጻጸሙ 50 በመቶ በታች ነው፡፡ ፋብሪካውን ለማጠናቀቅም የሚያስፈልገው ወጪም 22 ቢሊዮን ብር መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ። በሜቴክ ውስጥ በሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና አነስተኛ ክፍያ ምክንያት ከፍተኛ የሠራተኛ ፍልሰት እየገጠመ መሆኑ ታውቋል። አዲሱ የተቋሙ አመራር ኮርፖሬሽኑ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለመደገፍ በጥናት ላይ ተመሥርቶ እንዲሠራ የማስተካከያ ዕርምጃ እንዲወስድም ቋሚ ኮሚቴው ማሳሰቡን መዘገባችን ይታወሳል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...