በልማት ምክንያት ከአዲስ አበባ ከተማ የተፈናቀሉ አርሶ አደሮችን በድጋሚ ለማቋቋም የታቀዱ ፕሮጀክቶችን ዕውን ለማድረግ፣ ሰኞ ሰኔ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. የመሠረት ድንጋይ ተጣለ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ አምስት ሺሕ የሚሆኑ አባወራዎችን ተጠቃሚ ለሚያደርጉ ፕሮጀክቶች የመሠረት ድንጋይ በጋራ ጥለዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ የከብትና የዶሮ ዕርባታ፣ ከብት ማደለብ፣ የወተት ሀብት ማቀነባበሪያ፣ አነስተኛ ንግድና የኪራይ ሕንፃ ግንባታዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ግንባታዎች በቦሌ፣ በአቃቂ፣ በየካ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶና በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍላተ ከተሞች የሚከናወኑ ናቸው ተብሏል፡፡
ፕሮጀክቱ በሚካሄዱባቸው አካባቢዎች ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ የመሠረት ልማት ግንባታዎች በተለይም የውኃ፣ የመንገድና፣ የኤሌክትሪክ ዝርጋታዎች እንደሚከናወኑ ታውቋል፡፡ ከእዚህ ባለፈም የሠርቶ ማሳያዎችና የመኖሪያ ቤት ግንባታዎችም ተካተዋል፡፡ ፕሮጀክቶቹን ለማካሄድ የመሠረት ድንጋይ ከመጣል በተጨማሪ፣ ግንባታዎቹን ለማካሄድ የሚያስችል የጨረታ ዝግጅት በመገባደድ ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚመድበው በጀት ለሚከናወኑት ግንባታዎች እስካሁን 200 ሚሊዮን ብር የወጣ ሲሆን፣ በሚቀጥሉት ወራት ደግሞ ተጨማሪ 500 ሚሊዮን ብር ይመደብላቸዋል ተብሏል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ በወቅቱ እንደተናገሩት፣ ከቦታቸው በተነሱ አርሶ አደሮች ላይ የደረሰውን ችግር ለመቅረፍ በአገር አቀፍና በከተማ ደረጃ ቀሪና ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ከፊት ይጠብቃሉ፡፡ ‹‹ከዚህ አንፃር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጀመራቸው ሥራዎች አድናቆት የሚቸራቸውና ሌሎች ከተሞችም ልምድ የሚቀስሙበት ነው፤›› ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ በበኩላቸው፣ ባለፉት አምስት ዓመታት የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን ለመደገፍ የተለያዩ ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል፡፡ ከዚህ በኋላም አርሶ አደሮች ለዘላቄታው እንዲቋቋሙ ለማድረግ ይሠራል ሲሉም አክለዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ በሚካሄዱ መጠነ ሰፊ ፕሮጀክቶች ምክንያት፣ በማስፋፊያ ቦታዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች ሲፈናቀሉ ቆይተዋል፡፡
ለተፈናቃዮቹ የሚሰጠው ካሳና ተለዋጭ ቦታ አነስተኛ በመሆኑ፣ አርሶ አደሮቹ በከፍተኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሲዳረጉ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ አስተዳደሩ ዘግይቶም ቢሆን ተፈናቃዮችን ለማቋቋም ረዥም ርቀት የሄደ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ የባሰ ችግር ውስጥ ለገቡ 2‚087 አርሶ አደሮች የዕለት ምግብ የሚያገኙበትንና ተያያዥ ችግሮችን ለማስወገድ 52 ሚሊዮን ብር በጀት ይዞ ሲሠራ መቆየቱም ተገልጿል፡፡