በአደጋ የተጎዱን፣ በቁርጠት የተዋከቡን፣ በከባድ ደዌ የተንገላቱትን፣ በሞትና በሕይወት መካከል ሆነው የሚያጣጥሩትን በወሳንሳ አጋድሞ፣ በአምቡላንስ አጣድፎ፣ ሐኪም ቤት ማድረስ አማራጭ የሌለውና የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡ ስቃይን የማስታገስና ከሕመም የመፈወስ ፀጋ የተሰጣቸው ሐኪሞች በሥራቸው ሊመሰገኑ ሲገባ ወቀሳ እንደሚበዛባቸው፣ የኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር ፕሬዚዳንት ዶ/ር ገመቺስ ማሞ ይናገራሉ፡፡ ሐኪሞች በሠሩትና ባደረጉት ነገር ምሥጋና ሊቸራቸው ይገባል፡፡ ይህ መሆኑ ቀርቶ ግን ኅብረተሰቡን ይበድላሉ ከማለት ውጪ ምሥጋና ተችሯቸው እንደማያውቅ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ደግሞ ሐኪሞችን ቅር ከማሰኘት አልፎ በእጅጉ ማሳዘኑ አይቀርም፡፡
የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅና የኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር በጋራ ያዘጋጁትና የመጀመርያው ‹የኢትዮጵያ የሐኪሞች ቀን› ሰኔ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አዳራሽ በተከበረበት ሥነ ሥርዓት ላይ ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹እንዲረዳንና እንዲያመሰግነን የምንፈልገው ኅብረተሰቡ ነው፡፡፡ እኛን ያመሰገነ ሰው ሁሉ እንደወደደን ነው የምንቆጥረው፤›› ብለዋል፡፡
ሐኪሞች በሥራ ውጤታቸው በተመሰገኑ ቁጥር አገልግሎታቸውን በጥራትና በብቃት እንዲያከናውኑ የሚያደርጋቸው ሲሆን፣ ለበለጠ ሥራም ያነሳሳቸዋል፡፡ ከዚህ አኳያ የሕክምና አገልግሎት በጥሩ ሁኔታ ያገኘ ሰው የረዳውን ሐኪም ቢያመሰግን ሞራል ይሰጠዋል፡፡ በአንፃሩም ሐኪሙም ሲመሰገን በሥራው መከበሩ ከእኔ በላይ የለም የሚል መታበይ እንዳይፈጠርበት መጠንቀቅ እንዳለበት ዶክተሩ ተናግረዋል፡፡
እስካሁን ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባልደረቦቻቸው የቸሯቸው ምሥጋና ካልሆነ በስተቀር በመንግሥት ደረጃ አንድም ዕውቅና ተችሯቸው እንደማያውቅ ዶ/ር ገመቺስ ጠቁመው፣ በአሁኑ ጊዜ ግን በአደባባይ በፓርላማ ምሥጋና ለመጀመርያ ጊዜ እንደተቸራቸውና ይህም ሁኔታ ለሐኪሞች ስንቅ እንደሆናቸው አስረድተዋል፡፡
‹‹የሐኪሞች ቀን›› ሳይማር ያስተማራቸውን፣ ሳይበላ ያበላቸውን፣ ደክሞ፣ ወጥቶ፣ ወርዶና ለፍቶ፣ ሐኪሞቹ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ያደረሳቸውን ኅብረተሰብ የሚያስቡበትና በሙያቸውና እግዚአብሔር በሰጣቸው ፀጋ ብቻ ማንንም ከማንም ሳይለዩ በንፁህ ልቦና እንዲያገለግሉ በድጋሚ ቃል የሚገቡበት ዕለት መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ይህ ቀን ‹‹የሐኪሞችን ቀን›› የሚከበርበት ዕለት እንዲሆን የተደረገበት ዋናው ምክንያት የመጀመርያዎቹ ኢትዮጵያውያን ሐኪሞች በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሜዲካል ፋኩልቲ (የጤና ሳይንስ ኮሌጅ) ትምህርታቸውን ጨርሰው የተመረቁበት ቀን መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን ከዶ/ር ገመቺስ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡
የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ ፕሮቮስት ዶ/ር ወንድምአገኝ ገዛኸኝ ‹‹የሐኪሞችን ቀን በየዓመቱ እንደ ባህል አድርገን የምናከብረው ለኮሌጁ መቋቋምና ጥንካሬ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሕክምና ባለሙያዎች ዕውቅና በመስጠት ነው፡፡ ዕውቅናውም አንድ አዋርድ በስማቸው መሰየም ነው፤›› ብለዋል፡፡
ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ የተከበረውን የሐኪሞች ቀን ምክንያት በማድረግ ለሕክምና ኮሌጁ በቀዶ ሕክምና ሙያ፣ በዲፓርትመንት ኃላፊነትና በሜዲካል ዳይሬክተርነት ለረዥም ዓመታት ያገለገሉ፣ ከኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር መሥራቾች መካከል አንዱ የሆኑና በአሁኑ ጊዜ በሕይወት የሌሉት ፕሮፌሰር ታዬ መኩሪያ ዕውቅና እንዲቸራቸውና ለዚህም አንድ ጎላ ብሎ የሚታይ ትልቅ አዋርድ በስማቸው እንዲሰየም የኮሌጁ ማኔጅመንት እንደወሰነ ፕሮቮስቱ ተናግረዋል፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር አሚር አማን የኢትዮጵያ የሐኪሞች ቀን በየዓመቱ ሰኔ 25 ቀን እንዲከበር የኢትዮጵያ ሐኪሞች ማኅበር ያሳለፈውን ውሳኔ በሚኒስቴሩ ዘንድ ቅቡል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሕክምና ሥራ ላይ ጥፋት ሲከሰት ጣትን በጤና ባለሙያው ላይ ከመቀሰር ወይም የዕውቀትና ክህሎት ችግር አለበት ብሎ ከመደምደም፣ ብሎም ወደ ክስ ከመሄድ በፊት ብቁ ነህ ብሎ ዲግሪ የሰጠው አካል መጠየቅ እንዳለበትም አስረድተዋል፡፡ ሐኪሞች ጥፋት ስለፈጸሙ ጤና ተቋም ድረስ ሄዶ እንደ ወንጀለኛ አስሮ መውሰዱ መቆም እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡
ሐኪሞች በሠሩት ስህተት መጠየቅ ያለባቸውም ሐኪሞችና ሌሎችም ባለሙያዎች ያሉበት የሕክምና (ሜዲካል) ጉባዔ ዘንድ ጉዳያቸው በመጀመርያ ቀርቦ ከታየና ከተጣራ በኋላ መሆን እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡
‹‹የጤና ባለሙያዎች ጥቅማ ጥቅምና የሚገባቸውንም የደመወዝ ደረጃ ማስከበር ሌላው ችላ የማይባል ጉዳይ ነው፤›› ያሉት ዶ/ር አሚር ይህም ጉዳይ የአገሪቱ አቅም በፈቀደ መጠን በመተግበር ላይ እንደሆነና ትግበራውም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል፡፡
በሕክምና ኮሌጁ ሥር የሚገኘው ብሔራዊ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና ማዕከል ባልደረባ የሆኑት ሲስተር ሃና ሀብተማርያም፣ ከግል ኪሳቸው ገንዘባቸውን እያወጡ ችግረኛ ለሆኑ የኩላሊት ታካሚዎች የሁለትና የሦስት ቀናት የዳያሊሲስ አገልግሎት ወጪያቸውን በመሸፈንና የመድኃኒት መግዣ በመስጠት የረዱትን የኩላሊት ሐኪሞችን በዕለቱ አመስግነዋል፡፡
ሌላዋ አመስጋኝ ደግሞ ወ/ሮ በላይነሽ ዱካቶ ይባላሉ፡፡ ወ/ሮ በላይነሽ በሰጡት የምሥጋና ቃል በ2008 ዓ.ም. በሥራ ላይ እንዳሉ ግራ እግራቸው ከባድ ጉዳት እንደደረሰበት፣ ወዲያውኑ የግል ሕክምና ተቋም ተወስደው ለአገልግሎት ከ85 ሺሕ ብር በላይ እንደተጠየቁና፣ ይህንንም ለመክፈል ባለመቻላቸው በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ ሥር ወደሚገኘው አቤት ሆስፒታል ተወሰደው የተጎዳው እግር ተቆርጦ በምትኩ ሰው ሠራሽ እግር እንደተገጠመላቸው ይናገራሉ፡፡ አሁን በጥሩ ሁኔታና እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኙ የገለጹ ሲሆን፣ ለዚህ ላበቋቸውና ለረዱዋቸው ሐኪም የ‹‹ማቱሳላን ዕድሜ›› ተመኝተውላቸዋል፡፡
‹‹የሥነ ልቦና ሕክምና፣ መልካም ቃልና ተስፋ የሕክምናው ግማሽ ይመስለኛል፡፡ ማንኛውም ታካሚ ወደ ሆስፒታል ሲሄድ የሐኪሙን ፊት ወይም ፈገግታ ያያል፡፡ ፈገግታ ለአንድ ሐኪም የሕክምናው ቁልፉና መግቢያው ነው፡፡ በዚህም መሠረት ሐኪሞች ፈገግታ አይለያችሁ፤›› ያሉት ዕውቁ ደራሲ አቶ ኃይለ መለከት መዋዕል፣ ጥር 17 ቀን 2009 ዓ.ም. መስቀል አደባባይ መንገድ በመሻገር ላይ እንዳሉ መብራት ጥሶ በሚበርር አንድ ሞተር ሳይክል አደጋ ደርሶባቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በደረሰባቸው አደጋ ወደ ጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል ተወስደው ያልተቋረጠ እንክብካቤና ሕክምና እንዳገኙና በዚህም እንደዳኑ ተናግረዋል፡፡ የጀመሩትንም ልቦለድና የሌሎችም ወጣት ደራስያን አርትኦት ለመሥራት እንደቻሉም ገልጸው፣ ለዚህም ያበቋቸውን የሕክምና ባለሙያዎች ከልብ አመስግነዋል፡፡