Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልሰኔ 26 ከፀደይ ወደ ክረምት

ሰኔ 26 ከፀደይ ወደ ክረምት

ቀን:

‹‹… ሰኔ ደግሞ መጣ ክረምት አስከትሎ

ገበሬው ተነሣ ማረሻውን ስሎ፡፡

ሐምሌም ተከተለ ገባ ዝናብ ጭኖ

ቀንና ሌሊቱን በዝናብ ጨፍኖ፡፡

ነሐሴ ተተካ ኃይለኛው ክረምት

ያወርደው ጀመረ የዝናብ መዓት፡፡…››

አንድ ገጣሚ ‹‹የዓመቱ ወራት›› ብሎ ከመስከረም እስከ ጳጉሜን ያሉትን የኢትዮጵያ 13 ወራትን ገጽታና ባህሪያት የገለፀበት ነበር፡፡ ዘንድሮ ከወርኃ ግንቦት ጀምሮ በተለይ የበልጉ (የፀደዩ) ዝናብ በርትቶ የታየበትና ወደ ክረምቱ መሸጋገሩ እየታየ ነው፡፡

ዘመን ከሚሞሸርባት፣ ዓመት ከሚቀመርባት ከወርኃ መስከረም የሚነሣው የኢትዮጵያ ዓመት ቁጥር በአራት ወቅቶች የተመደበ ነው፡፡ አራቱ ወቅቶች (ዘመኖች) ክረምትና በጋ፣ መፀውና ፀደይ ናቸው፡፡

ክረምት ዝናም፣ የዝናም ወራት ማለት ነው፡፡ ከሰኔ 26 ጀምሮ የሚገባ ያመት ክፍል ነው፡፡ ሰኔ መገባደጃውን ተክትሎ ስለሚመጣው ክረምት ታላቁ ቅዱስ ያሬድ ‹‹የዝናብ ኮቴ ተሰማ በዘነበ ጊዜም ነዳያን ይደሰታሉ፣ የተራቡም ይጠግባሉ፤›በማለት በስድስተኛው ምዕት ዓመት ጽፏል፡፡

ቅዱስ ያሬድ በአራቱ ወቅቶች ተመሥርቶ ባዘጋጀው በታላቁ መጽሐፈ ድጓው በሁለት ዓመቶች ውስጥ የሚውለውንክረምት ወቅትን በሰባት ክፍሎች እንደሚከተለው መድቦታል፡፡

ከሰኔ 26 እስከ ሐምሌ 18 ደመና፣ ዘር፤ ከሐምሌ 19 እስከ ነሐሴ 9 መብረቅ፣ ነጐድጓድ፣ ባሕር፣ አፍላጋት (ወንዞች) ጠል፤ ከነሐሴ 10 እስከ 27 ደሴቶች፣ የቁራ ጫጩት፣ የፍጥረታት ዓይን ሁሉ፤ ከነሐሴ 28 እስከ ጳጉሜን 5 (6) ጎሕ፣ ነግህ፣ ጽባሕ፣ ብርሃንና መዓልት ይባላሉ፡፡

በአዲሱ ዓመት ውስጥ የሚውሉም ከመስከረም 1 እስከ 7 ዘመነ ዮሐንስ፤ መስከረም 8 ዘካርያስ፤ ከመስከረም 9 እስከ 15 ዘመነ ፍሬ፤ መስከረም 16 ሕንጸት፤ ከመስከረም 17- 25 ዘመነ መስቀል ናቸው ናቸው፡፡

ገበሬው በዘመነ ክረምት እኩሌቶቹን ዘሮች በሰኔ፣ ገሚሶቹን በሐምሌ፣ እንዲሁም ሌሎቹን ዘሮች በነሐሴና በመስከረም ይዘራል፡፡ አትክልቱንም ይተክላል፡፡ የክረምቱ ወራት የሚያበቃው አዲሱ ዓመት በገባ በመስከረም 25ኛው ቀን ላይ እንደሚሆን የባሕረ ሐሳብ መምህራን ይገልጹታል፡፡  

በጋ እንደተፈጸመ የሚከተለው ወቅት ፀደይ ነው፡፡ ከመጋቢት 26 ቀን እስከ ሰኔ 25 ቀን ድረስ ይዘልቃል፡፡ የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ጸደይን፣ አጨዳ፣ የአጨዳ ወራት ዘመነ በልግ ይለዋል፡፡ በወዲያ መከር፣ በወዲህ በልግ የሚደርስበት የሚታጨድበት፣ ወዲያውም የሚዘራበት የዘር ወር ሲልም ያክልበታል፡፡

በመጋቢት፣ በሚያዝያና በግንቦት የሚዘንበው ዝናብ የበልግ ዝናብ፣ በመባልም ይጠራል፡፡ አፈ ሊቅ አክሊሉ ገብረኪሮስ ፀደይን እንዲህ አመስጥረውታል፡፡ ‹‹ሐጋይ (በጋ) ወርኃ እሳት ሆኖ እንደቆየ፣ ፀደይም ወርኃ መሬት ሆኖ ይቆያል፡፡ መምህራን ይህንን ሲያስረዱ እንዲህ ይላሉ፡፡ የመሬት ወራት ከመሆኑ የተነሳ ወደ ሜዳ ሄዶ ደንጊያ ቢፈነቅሉ የሳር፣ የእንጨት ልምላሜ ያለአንዳች ዝናብ ለምልሞ ይገኛል፡፡

‹‹ወደ ጓዳ ገብቶ ጋን ቢያነሱ፣ እንዲሁ የሳር ልምላሜ ለምልሞ ይገኛል፡፡ ገበሬም በልግ ከመከር ስጠኝ ብሎ ለፈጣሪው ዕጥፍ ድርብ ምስጋና የሚያቀርበው በዚህ ወራት ነው፡፡

ግጥም ገጣሚም፣ ፀደይ የበልግ አዝመራ የሚገኝበት ወራት መሆኑን ሲያመለክት እንዲህ ብሏል፡፡

ሁሉም ያምረኛል በየምግባሩ፣

እነ አለቃ እንደብተራ ቅኔ ሲመሩ

ገበሬዎችም ሚያዝያን ሲያዘምሩ

ወታደሮችም ጥይት ሲዘሩ፡፡

ገበሬዎቹ በመጋቢት በሚያዝያ በግንቦት የሚዘንበውን ዝናብ የበልግ ዝናብ ይሉታል፡፡ በለገልን በልግ ሰጠን እያሉ የበልግ ወራት እርሻውን ያከናውናሉ፡፡

‹‹ፀደይ በመስከረም? ወይስ በመጋቢት? በፈረንጅ ወይስ በሀበሻ?›› በሚል ርዕስ ሐተታ የጻፉት አፈ ሊቅ አክሊሉ እንደገለጹት፣ ዛሬ ግን አንዳንድ ሰዎች በአውሮፓ ክፍለ ዘመን እየተመሩ ፀደይ ‹‹በመስከረም 26 ቀን የሚገባው›› ክፍለ ዘመን ስም ነው እያሉ ያቀርባሉ፡፡ መምህራን ፀደይ በጥቅምት በኅዳር ነው አይሉም፤ የአቡሻህርና የመርሐ ዕዉር ቁጥር መምህራን፣ ድጓ ነጋሪዎች ሳይቀሩ የኢትዮጵያ ፀደይ በመስከረም መጨረሻ ይገባል አይሉም፡፡ አይከራከሩበትም አይለያዩበትም፡፡

ፀደይ የሚገባው በመጋቢት 26 ቀን ነው ማለትን አይክዱም፣ አያስተባብሉም ክፍለ ዘመናችንም ከፈረንጆች ክፍለ ዘመን መለየቱን ገልጠው ያስረዳሉ፡፡ እኛ መፀው ስንል ፈረንጆች ፀደይ ገባ ይላሉ እያሉ የክፍለ ዘመናችንን ልዩነት ሐተታ ያብራራሉ፡፡ መጻሕፍቱም ይህንኑ ይመሰክራሉ፡፡

ታዲያ አንዳንድ ሰዎች ክፍለ ዘመናችንን ለምን ያዘዋውሩታል? ሲሉ አፈ ሊቅ ይጠቅሳሉ፡፡ ፀደይ ማለት በልግ ማለት እንደሆነ እየታወቀ፣ የበልግ ዝናብ ዘንቦ ገብስ ዘንጋዳ ማሽላ በቆሎ የሚዘራበት ወራት ከፊታችን ቁሞ ነገሩን ቀምሞ እየመሰከረ አደናጋሪ ነገር መምጣት ምን ይጠቅመናል? ይልቅስ ‹‹ወረጎ መሬት›› ማለት መሬት የሚሰባበት የሚወፈርበት የሚዳብርበት ወራት መሆኑን መገንዘብ መረዳት ያስፈልጋል ሲሉ አስረግጠው ያሳስባሉ፡፡

አንድ በብዙኃን በሚታወቀው ብሂል ‹‹ለሞኝ ሰኔ በጋው መስከረም ክረምቱ›› ላይ አንዱ በነጠቃ ‹‹ለሞኝ መስከረም ፀደዩ መጋቢት መፀዉ›› ብሎታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...