Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹አሠራራችን በጣም ኋላ ቀርና ዘመናዊነትን የማይከተል በመሆኑ አሁንም ቱሪዝም አያድግም››

አቶ ቁምነገር ተከተል፣ የኦዚ ቢዝነስና ሆስፒታሊቲ ግሩፕ ማኔጂንግ ዳይሬክተርና የኢትዮጵያ ቱሪዝምና ባህል ሥርፀት ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ

አቶ ቁምነገር ተከተል የኦዚ ቢዝነስና ሆስፒታሊቲ ግሩፕ ማኔጂንግ ዳይሬክተርና መሥራች ናቸው፡፡ እንዲሁም በቅርቡ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ቱሪዝምና ባህል ሥርፀት ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ ናቸው፡፡ ኦዚ በሆቴልና ቱሪዝም ላይ ያተኮረ የኢንቨስትመንት ዓውደ ርዕይ ላለፉት ስድስት ዓመታት አካሂዷል፡፡ ድርጅቱ በዋናነት የሚሠራው ዓለም አቀፍ የሆቴልና የሪዞርት ፕሮጀክቶችን ማማከር ነው፡፡ ልዩ ልዩ ጥናቶችን ከማድረግ ጀምሮ ዓለም አቀፍ ሆቴሎችን ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት፣ ፕሮጀክቶች በምን ደረጃ መሄድ እንዳለባቸው፣ የሥነ ሕንፃ ዲዛይን ጽንሰ ሐሳቦችን የማፍለቅ፣ ከግዢ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን እንዲሁም ሆቴሉ እስኪከፈት ድረስ ያሉት አጠቃላይ ሥራዎችን ሁሉ ይሠራል፡፡ ከሆቴልና ቱሪዝም የኢንቨስትመንት ዓውደ ርዕይ ጎን ለጎንም የማይስ ኢንዱስትሪ ከማይስ ኢስት አፍሪካ የተሰኘ የቢዝነስ ትራቭል ኤክስፖ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት አካሂደዋል፡፡ የማይስ ቱሪዝም የኮንፍረንስና ኤግዚቢሽን ቢዝነስና የኢንሴንቲቭ ትራቭል ቢዝነስን ወደ ኢትዮጵያ የሚያመጣ ኤክስፖ ነው፡፡ በሆቴል ኢንቨስትመንትና በቱሪዝም ዘርፉ ስላሉ ተግዳሮቶችና መሻሻሎች ዙርያ ሻሂዳ ሁሴን አቶ ቁምነገርን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- በመስተንግዶ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ዋና ዋና ችግሮች ምንድናቸው?

አቶ ቁምነገር፡- ትልቁ ችግር በመንግሥት በኩል ያለው ለመስተንግዶ ኢንዱስትሪ የሚሰጠው ትኩረት በጣም ዝቅተኛ መሆን ነው፡፡ ስለ ኢንዱስትሪው ማወቅ ግንዛቤ ማዳበር ያስፈልጋል ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽኖች ሲዘጋጁ በመንግሥት በኩል ትኩረት ካልተሰጠው ዓለም አቀፉ ልምድ ማግኘት ከባድ ይሆናል፡፡ በዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽኖች ላይ የሚሳተፉ ከውጭ አገሮች የሚመጡ ኢንቨስተሮች አብዛኞቹ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መሰማራት የሚችሉ ናቸው፡፡ እነሱን አግኝቶ ማናገርና በአገር ውስጥ መሥራት እንዲችሉ ማሳመን ይፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ኦዚ ምን ያህል ሆቴሎችን ያማክራል?

አቶ ቁምነገር፡- በአሁኑ ወቅት 45 ሆቴሎችን እናማክራለን፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 22ቱ ዓለም አቀፍ ብራንዶች ናቸው፡፡ ከ12 በላይ የሚሆኑን ለማማከርም ተፈራርመናል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ጎልደን ቱሊፕ፣ ራዲሰን ብሉ፣ ዱሲታኒ፣ ኢንተርኮንቲኔንታል፣ ቱሊፕ ኢን፣ ቦን ሆቴል፣ ፓርኪንግ ባይራዲሰን የመሳሰሉ አዳዲስ የሆቴል ፕሮጀክቶችን የምናማክረው እኛ ነን፡፡ የታይላንድ ዓለም አቀፍ ብራንድ የሆነው ዱስታኒ በኢትዮጵያ ውስጥ 400 ሺሕ ካሬ ላይ የሚያርፍ ትልቁ ሪዞርት ነው፡፡ ለገዳዲ ላይ የሚሠራ ሲሆን፣ ከ450 ክፍሎች በላይ ይኖሩታል፡፡ ይህ በምሥራቅ አፍሪካ ትልቁ ሪዞርት ነው፡፡ የኮንፈረንስ፣ የጤናና የስፖርት ማዘውተሪያ (ዌልነስ) መዳረሻ እንዲሆን ታስቦ የሚገነባ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ አዲግራት፣ ቢሾፍቱ፣ ሐዋሳ፣ ባህር ዳር፣ አዳማም ሌሎች ትልልቅ ፕሮጀክቶች አሉን፡፡ ካሉን 45 የሆቴል ፕሮጀክቶች መካከል ከ20 በላይ የሚሆኑት ባለ አምስት ኮከቦች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ሌሎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ሒደት ላይ ያሉ ምን ያህል ዓለም አቀፍ ሆቴሎች አሉ?

አቶ ቁምነገር፡- በሒደት ላይ ያሉ 18 ፕሮጀክቶች አሉን፡፡ በይፋ የሚገለጸው ፊርማ ሲካሄድ ነው፡፡ ምናልባት በሚቀጥለው ወር ሦስት የሚሆኑትን ልትሰሙ ትችላላችሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የቱሪዝም መዳረሻዎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ቢሆንም፣ ሆቴሎችና መሰል የመስተንግዶ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት የሚገነቡት በብዛት በአዲስ አበባና በጥቂት ከተሞች ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ዋናው ምክንያት ምንድነው? ይህም በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ ምን ያህል አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል?

አቶ ቁምነገር፡- አዲስ አበባ ላይም ይሁን የክልል ከተሞች ላይ ለሚሠሩ ኢንቨስተሮች የሚሰጠው ድጋፍ ተመሳሳይ ነው፡፡ ስለዚህም ሰዎች ቢዝነሱ በስፋት ወደሚገኝበት ቦታ እየሄዱ ዋና ከተማ ላይ ይሠራሉ፡፡ ትልቁ የእኛ አገር ችግር ለኢንቨስተሮች የሚሰጠው ድጋፍ (ፕሪቪሌጅ) ላይ ነው፡፡ በቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ላይ ለሚሠሩ የልማት ሥራዎች የተለየ ድጋፍ ወይም ፕሪቪሌጅ ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት ዘርፉ የሚጠይቀውን ፕሪቪሌጅ ማሟላት እስካልቻለ ድረስ እነዚህ የመዳረሻ ሥፍራዎችን ማልማት አይቻልም፡፡ ከመሬት ዝግጅት ጀምሮ፣ የሚከፈሉ የተለያዩ ክፍያዎች ታክስ ሆሊዴይ የመሳሰሉትን ልዩ ድጋፎች መስጠት ቢቻል ሆቴሉ እስኪለምድልኝ እከስራለሁ ብለው ሳይሰጉ መሥራት ይችላሉ፡፡ ከዚህ ባለፈ መንግሥት የትኛውን ቦታ ማልማት እንደሚያስፈልግ ጥናት ማድረግም ይኖርበታል፡፡

ሪፖርተር፡- ለምተዋል በተባሉ አካባቢዎችም ለምሳሌ በአዲስ አበባ የመስተንግዶ ኢንዱስትሪው አሁንም ገና ነው፡፡ በእዚህ ላይ ምን ይላሉ?

አቶ ቁምነገር፡- የአገልግሎት ጥራት ውድድር ከፅዳት ይጀምራል፡፡ የፀጥታና የጥበቃ እንዲሁም ሌሎች የአገልግሎት ጉዳዮች አሉ፡፡ አሉ የሚባሉት ችግሮች የሚቀረፉት በውድድር ነው፡፡ ውድድሩ እያደገ በመጣ መጠን የአገልግሎት ጥራት ውድድርም ይመጣል፡፡ ያሉትን የመስተንግዶ ችግሮች በተወሰነ መልኩ ለመቅረፍ አቅም ያላቸው ትምህርት ቤቶች እየተከፈቱ ነው፡፡ ነገር ግን ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው የሆስፒታሊቲ ትምህርት ቤቶች ያስፈልጋሉ፡፡ እነዚህ ሲሟሉ ያሉትን የመስተንግዶ ችግሮች ወደፊት ይቀርፋሉ፡፡ ባለው ሁኔታም ቢሆን ውድድሩ በራሱ ደረጃውን እያሻሻለ መጥቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ላይ ሆቴል እንደፈለግን ማግኘት ችለናል፡፡ እንደበፊቱ ከባድ አይደለም፡፡ የስብሰባ አዳራሾችን ለማግኘትም እንደበፊቱ አንቸገርም፡፡ የሚከፈቱ ሆቴሎች ቁጥር በበዛ መጠን በሚኖረው ውድድር በተለይ በዓለም አቀፍ ሆቴሎች መካከል የሚኖረው ውድድር ስለሚጨምር አገልግሎቱን በቀላሉ ማሳደግ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- አሉ የሚባሉ ሆቴሎች የውጭ ገበያን መሠረት አድርገው የሚከፈቱ የአገሬውን ተጠቃሚ በቁጥር የሚያጠግቡ ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ ምን ይላሉ?

አቶ ቁምነገር፡- አሁንም በውድድር የሚፈታ ነገር ነው፡፡ ውድድሩ በተጠናከረ መጠን ነዋሪው መጠቀም የሚችልበትን አቅም ይፈጥርለታል፡፡ ውድድርን ለማሳደግ ግን የግድ ዋጋ ማውረድ አያስፈልግም፡፡ ከተማው ውድ እስከሆነ ድረስ ውድ ዋጋ ይቀጥላል፡፡ በነገራችን ላይ የዓለም አቀፍ ሆቴሎችና ሌሎች ትልልቅ ሆቴሎች የዋጋ ውድድር እየጨመረ ሲመጣ ግን ዋጋ እየቀነሰ መጥቷል ውድ አይደለም፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት ዋጋቸው እየቀነሰ ነው የመጣው፡፡ ለምሳሌ በአፍሪካ ኅብረት ስብሰባዎች ሆቴሎች ይሞሉ ነበር፡፡ አሁን ግን በአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ የከተማው ሆቴሎች በ60 እና 70 በመቶ ብቻ ነው የሚሞሉት፡፡ አንዳንድ ሆቴሎች እንዲያውም 20 እና 30 ሰዎች ብቻ ይሆናል የሚያስተናግዱት፡፡ ስለዚህ ዋጋቸውን ቀንሰው ወደ ገበያ መቀላቀል አለባቸው ማለት ነው፡፡ ለአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ የሆቴል እጥረት ይከሰታል የሚለው ታሪክ ሆኗል፡፡ አሁን የምንጠብቀው በአንዴ 5 ሺሕ እና 10 ሺሕ ሰዎች ማስተናገድ የሚችሉ ሆቴሎች መፍጠር ነው፡፡ በአንዴ በሺዎች የሚቆጠሩ እንግዶችን የማስተናገድ አቅም ያላቸው ሆቴሎች ባለመኖራቸው ነው ትልልቅ ስብሰባዎች ወደ እኛ አገር የማይመጡት፡፡

ሪፖርተር፡-  ምክንያታዊ ዋጋ  የሚባለው ከምን አንፃር የተሰላ ነው?

አቶ ቁምነገር፡- አንዱ የምንወዳደረው ከጎረቤት አገሮች ጋር ነው፡፡ ለምሳሌ ለስብሰባ ናይሮቢ ነው አዲስ አበባ ነው የሚመቸው የሚለውን አዘጋጁ ሲወስን ዋጋውን ያወዳድራል፡፡ በዚህ ረገድ ያለብን ትልቅ ችግር አለ፡፡ ኢትዮጵያ ዋጋዎችን አደራጅታ መላክ አትችልም፡፡ ይኼንንም ለማድረግ ‹ኢትዮጵያን ናሽናል ኮንቬንሽን ኤንድ ቪስተር ቢሮ›  የሚባል መሥሪያ ቤት ያስፈልጋታል፡፡ ነገር ግን እስካሁን ድረስ የላትም፡፡ ላለፉት አራት ዓመታት እንደ ኦዚ ስንጨቃጨቅ የነበረውና አሁንም ቢሆን እንዲቋቋም ግፊት የምናደርግበት ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ናሽናል ኮንቬንሽን ቢሮ የሚባለው መሥሪያ ቤት ሲቋቋም በሆቴሎች ዋጋ ላይ ሚዛናዊነትን መፍጠር የሚችል ቢሮ ይቋቋማል፡፡ የዚህ ቢሮ መቋቋም ኢትዮጵያ ዓለም ላይ ያሉ ስብሰባዎችን መሳብ እንድትችል ያደርጋታል፡፡ ይህ መሥሪያ ቤት ባለመኖሩ ኢትዮጵያ የዋጋ ውድድሩን ሚዛናዊ ማድረግ እንዳትችል አድርጓት ቆይቷል፡፡ በተመሳሳይ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሆቴሎች 300 ዶላር ያስከፍላሉ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ 40 ዶላር ያስከፍላሉ፡፡ አራት ኮከብ የተሰጣቸው ሆቴሎች አንዳንዶቹ 150 ዶላር ያስከፍላሉ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ 60 ዶላር ያስከፍላሉ፡፡ ይህ የሆነው ሁለቱን የሚያመዛዝን የማርኬቲንግ ስትራቴጂ በአገር አቀፍ ደረጃ ባለመዘርጋቱ ነው፡፡ ይህን ለመሥራትም ናሽናል ኮንቬንሽን ቢሮ የግድ መኖር አለበት፡፡  ስለዚህም መንግሥት ናሽናል ኮንቬንሽንና ቪስተር ቢሮ መክፈት ይኖርበታል፡፡ 

ሪፖርተር፡- በኮንፈረንስ ቱሪዝም ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የውጭና የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን የተለያዩ ቦታዎችን እንዲጎበኙ የማድረግ ነገርም ብዙ አልተለመደም፡፡ ይህም አገሪቱ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንዳታገኝ አድርጓታል፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምን ይመስላል?

አቶ ቁምነገር፡- አሁንም መልሱ አንድና አንድ ነው ናሽናል ኮንቬንሽን ቢሮ አለመኖሩ የተፈጠረ ክፍተት ነው፡፡ የቢሮው ጥቅም ስብሰባዎች በሚመጡ ጊዜ ከቱር ኦፕሬተሮች፣ ከአየር መንገዶች ጋር ተነጋግሮ ቀድሞ ፕሮግራም ያዘጋጃል፡፡ 10 ሺሕ ሰዎች የሚመጡ ከሆነ ይኼንን ያህል ሰው ይመጣል ፍላጎቱ ያላችሁ ተጠቀሙበት ብሎ ለቱር ኦፕሬተሮች የማስተዋወቅ ሥራ ይሠራል፡፡ ከዚያም ዋጋዎችን ያወጣል፣ ከአየር መንገዶች ጋር ይደራደራል፡፡ ነገር ግን እዚህ ይኼንን የሚያሳልጥ ቢሮ የለም፡፡ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ሥራው ይኼ አይደለም፡፡ ዋና ሥራው አገሪቱን ማስተዋወቅ ነው፡፡ የናሽናል ኮንቬንሽን ቢሮ የማይስ ኢንዱስትሪ ነው የሚባለው፡፡ የኮንፈረንስ ኢንዱስትሪ ከማይስ ሥራ አንዱ ነው፡፡ በአህፅሮት ማይስ የሚባለው ኤግዚቢሽን፣ ስብሰባዎችና ኢንሴንቲቭ ትራቭል የተመሠረተ ሰፊ ጥቅም የሚያስገኝ የቱሪዝም ዘርፍ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የስብሰባ ኢንዱስትሪ መር ቱሪዝም ለመገንባት አገሮች ማይስ ቱሪዝም ላይ እየሠሩ ነው፡፡ ምክንያቱም የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን በቀላሉ ማስጎብኘት ያስችላቸዋል፡፡ በቀላል ምሳሌ ላስረዳሽ በሌዠር ቱሪዝምና በማይስ ኢንዱስትሪ የሚመጡ ቱሪስቶች ገንዘብ የማውጣት አቅማቸው በጣም የተለያየ ነው፡፡ በሌዠር ቱሪዝም አንድ ሰው 100 ዶላር ቢያጠፋ፣ በማይስ የመጣው በትንሹ 500 ዶላር ያጠፋል፡፡ ለዚህ ነው አገሮች ወደ ማይስ ፊታቸውን ያዞሩት፡፡ በማይስ የሚመጡ ጎብኚዎች ገንዘብ ከኪሳቸው ስለማያወጡ ብዙ ገንዘብ ያጠፋሉ፡፡ ወጪያቸውን የሚሸፍኑት ስፖንሰር የሚያደርጓቸው ተቋማት ስለሆኑ አይቆጥቡም፡፡ ለዚህ ነው ማይስ ኢንዱስትሪ ላይ ትኩረት አድርገን የምንሠራው፣ ናሽናል ኮንቬንሽን ቢሮ እንዲቋቋም ግፊት የምናደርገው፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ቱሪስቶች ለማረፍ የሚመርጧቸው ሆቴሎች ዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸውን በስም እየፈለጉ ነው ወይስ በኮከብ ደረጃ እየመረጡ ነው?

አቶ ቁምነገር፡- በዓለም አቀፍ ተጓዦች ዘንድ ስታር ሬቲንግ ብዙ ጊዜ ቦታ አይሰጠውም፡፡ ትኩረት የሚሰጡት ለአገልግሎት ጥራት ነው፡፡ አንዳንዶቹ ሆቴሎች ባለሁለት ኮከብ ሆነው ዓለም አቀፍ ደረጃ ይኖራቸዋል፡፡ እንግዶች ወደ እነዚህን ሆቴሎች የሚመጡት በእነሱ ከሌላው የተሻለ እምነት ስላላቸው ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ለእነዚህ ሆቴሎች ያላቸው ዓለም አቀፍ ኔትወርክም በራሱ ገበያ ይሰጣቸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን አገር በቀል ሆቴሎች ሆነው ዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያሟሉ አሉ፡፡ እነዚህም ሆቴሎች በበቂ ሁኔታ ጎብኚ ያስተናግዳሉ፡፡ እንግዶቹ የሚያገኙት የአገልግሎት ብቃትና የኮሙዩኒኬሽን ደረጃ ነው ለውጦችን ማምጣት የሚችለው፡፡ ማንኛውም ሆቴል አዲስ አበባ ላይም ይከፈት ሌላ ቦታ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን ካስተናገደ ዓለም አቀፍ ሊሆን ይችላል፡፡ ዓለም አቀፍ ትስስር (ቼይን ሆቴሎች) ያላቸው ሆቴሎች ግን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ብራንድ ያላቸው፣ ተመሳሳይ አልግሎት መስጠት የሚችሉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ እዚህ ያለውን ራዲሰን በተመሳሳይ ጥራትና የአገልግሎት ደረጃ ናይሮቢ ላይ ታገኚዋለሽ፡፡ ኢንተርናሽናል ቼይን ሆቴሎች ማለት ተከታታይነት ያላቸውና በተለያዩ አገሮች በተመሳሳይ የአገልግሎትና የጥራት ደረጃ የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ ከዚህ ውጪ ያሉ ሆቴሎች ራሳቸውን ዓለም አቀፍ ብለው የሚጠሩት የውጭ እንግዶች ስለሚያስተናግዱ ወይም ደግሞ ገጽታቸውን ከፍ ያደረጉ ስለሚመስላቸው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ማውጣት ያለፈበት ነገር ነው፡፡ አሁን ዘመኑ የቼይን ሆቴሎች ነው የሚሉ አስተያየቶች ከየአቅጣቸው ይሰነዘራሉ፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው? በእርግጥ የኮከብ ደረጃ ማውጣት ያለፈበትና የሚቀር ነገር ነው?

አቶ ቁምነገር፡- ለሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ማውጣት መቅረት የለበትም፣ አልቀረምም፡፡ ዓለም አቀፍ ትስስር (ቼይን) ሆቴሎች ራሳቸውን ባለ አራት ኮከብ፣ ባለ አምስት ኮከብ አይሉም፡፡ ነገር ግን የተለያየ ደረጃና ኮከብ አላቸው፡፡ የመጀመሪያው መካከለኛ ደረጃ የሚባለው ሲሆን፣ በጀትድ የሆኑ ከተገልጋዮች የመክፈል አቅም አንፃር አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው፡፡ የላይኛው መካከለኛ ደረጃ የሚባሉ ባለሦስትና አራት ኮከብ ሆቴሎች አሉ፡፡ አፕስኬል የሚባሉም አሉ፡፡ ከዚያም አፕስኬል አፕር ሆቴል የሚባሉ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች ይመጣሉ፡፡ ቀጥሎ ከአምስት በላይ ኮከብ ያላቸው ሌግዥሪ የሚባሉ ናቸው፡፡ የኮከብ ደረጃ የሚሰጣቸው በዚህ አግባብ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሆቴሎች ሲገነቡ እንደ እናንተ ያሉ አማካሪ ድርጅቶች የግድ ያስፈልጉናል ብሎ አምኖ እናንተን በሥራ የማሳተፉ ባህል ምን ያህል የዳበረ ነው?

አቶ ቁምነገር፡- እኛ የትኛው ፕሮግራም፣ የትኛው አሠራር ይጠቅማል የሚለውን ሐሳብ ነው ዲዛይን የምናደርገው፡፡ ለምሳሌ የለገዳዲውን ሪዞርት ላንሳልሽ ለገዳዲ ትልቅ ሪዞርት ነው፡፡ ነገር ግን ሪዞርት ስለተሠራ ሰው ይሄዳል ወይ? መኝታ ፈልጎ ይሄዳል ወይ? አይሄድም፡፡ ስለዚህም ሪዞርቱ ሁለት ነገር እንዲያካትት አድርገናል፡፡ አንደኛው የዌልነስ (የጤና) መዳረሻ እንዲሆን መደረጉ ነው፡፡ ሰዎች ሜዲቴት የሚያደርጉበት (የሚመሰጡበት)፣ ሐኪሞች የሚኖሩበት፣ የኒውትሪሽን (የሥነ ምግብ) ባለሙያዎች የሚገኙበት ቦታ ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የኮንፈረንስ መዳረሻም ነው፡፡ ኮንፈረንስ ካልተካሄደበት ሆቴሉ አይሞላም፡፡ አካባቢውም አይለማም፡፡ ስለዚህ ሆቴሉ ኮንፈረንሶች የሚካሄዱበት የስብሰባ አዳራሾች እንዲኖረው ተደረገ፡፡ ስሙም ዱሲታኒ ዌልነስ ኤንድ ኮንፈረንስ ዴስትኔሽን ሆቴል ነው የሚባለው፡፡ በተጨማሪም ቢሾፍቱን እንውሰድ፣ ቢሾፍቱ ላይ ሪዞርቶች እየተከፈቱ ነው፡፡ ቢሾፍቱ ለመዝናናት ብቻ ሳይሆን ለኮንፈረንስ መኬድም አለበት፡፡ ስለዚህ የቢሾፍቱ ራዲሰን ብሉ የኮንፈረንስና የዌልነስ መዳረሻ እንዲሆን ተደርጎ ነው የተሠራው፡፡ ከ1,200 ካሬ ሜትር በላይ በሆነ ቦታ ያረፈ የስፓ ማዕከሎች አሉት፡፡ ሐኪሞች የሚገኙበት፣ የጤና ክትትል የሚደረግበት፣ ለጤና ጠቃሚ የሆኑ የተመረጡ አትክልት የሚሸጡበት ቦታም አለው፡፡ በዚህ ደረጃ ኢንዱስትሪው እየተቀየረ ነው፡፡ ከተማ ውስጥ የሚከፈቱ ሆቴሎች የመኝታ አገልግሎት ብቻ የሚሰጡ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አልጋና ቁርስ ብቻ የሚፈለግባቸው ቦታዎች ላይ ባለ አራት ኮከብ ሆቴል ተገንብቶ አልጋና ቁርስ ብቻ የሚያቀርብ ሊሆን ይችላል፡፡ እኛ እንደዚህ ዓይነት ደረጃዎችን ነው የምንፈጥረው፡፡ አዎ አማካሪዎችን ማሳተፍ ተለምዷል፡፡ እንዲያውም አስገዳጅ ሆኗል፡፡ እንደበፊቱ ሰዎች ዝም ብለው አይገቡም፡፡

ሪፖርተር፡- ቀደም ብለው የተገነቡ ሆቴሎች ከግንባታ ጀምሮ የተለያዩ ቋሚ ችግሮች እንዳሉባቸው ይታወቃል፡፡ የእነዚህ ሆቴሎች የወደፊት ዕጣ ፈንታ በእርሶ አስተያየት ምን ሊሆን ይችላል?

አቶ ቁምነገር፡- በአጋጣሚ በጥሩ ሁኔታ የተሠሩም አሉ፡፡ ከዚህ ባሻገር ያሉት ብዙ ችግር ይገጥማቸዋል፡፡ ትልቅ የስታንዳርድ ችግር ይገጥማቸዋል፡፡ የሚፈርሱ ይኖራሉ፡፡ ብዙ ችግር የሚገጥማቸው በትክክል አሉ፡፡ በስታንዳርድ ጉዳይ ከገበያ የሚወጡም ይኖራሉ፡፡ ምናልባትም ከሆቴል በተሻለ ለትምህርት ቤትነት፣ ለክሊኒክ የሚመቹ ይኖራሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ አሉ ከሚባሉ ችግሮች መካከል የአስጎብኚዎች አሠራር ፈጠራ የታከለበት አለመሆኑ ይነሳል፡፡ አስጎብኚዎች ከተለመደው አሠራር ወጥተው መሥራት አለመቻላቸው አሳታፊ የሆኑ ባህላዊ ጨዋታዎችና ሥራዎችን እየፈጠሩ ወደ ጎብኚው አያደርሱም፡፡ እዚህ ላይ ምን ይላሉ?

አቶ ቁምነገር፡- እኔ የፈጠራ ችግር አለ ብዬ አላምንም፡፡ ኢትዮጵያ መች ገና ለዓለም ተዋወቀች? የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎች ገና መቸ ተዋወቁ? አንቺ እያነሳሽ ካለው አሠራር ርቀን ሄደን የተሻለ እናምጣ ነው፤ ይኼ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ያለውንም መቼ በአግባቡ ተጠቀምን? ያሉትን የቱሪዝም መዳረሻዎች በአግባቡ የሚያስተዋውቅ የለም፡፡ በመዳረሻ ሥፍራዎች ላይ ልማቶች የሉም፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ግብርና ሁሉ ቱሪዝም ትልቁ የኢኮኖሚ ምሰሶ መሆን አለበት፡፡  ቱሪዝም ዋጋ ያልተሰጠው ኢንዱስትሪ ነው፡፡ ፈጠራ ያልታከለበት አሠራር የሚከተሉትም በቂ ትኩረት ስላልተሰጠው ነው፡፡ መንግሥት ትኩረት ቢያደርግበት ከዚህ ዘርፍ ብዙ ፈጣሪዎችን ማውጣት ይቻላል፡፡ ብዙ ዓለም አቀፍ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎችም ይመጡ ነበር፡፡ በዩኔስኮ የቅርስ መዝገብ ከአፍሪካ ውስጥ እንደኛ የተመዘገበለት የለም፡፡ ግን እንዴት እናስተዋውቃቸው የሚለውን ቴክኒኩን፣ ብልሀቱንና ዘዴውን ማወቅ ይፈልጋል፡፡ እኔ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው የአፍሪካ አጨብጫቢ እንደ ሆንን ነው የሚሰማኝ፡፡ አሠራራችን በጣም ኋላ ቀርና ዘመናዊነትን የማይከተል በመሆኑ አሁንም ቱሪዝም አያድግም፡፡  በቅርቡ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ቱሪዝምና ባህል ሥርፀት ማኅበርም አንዱ ተግባሩ በዚህ ኢንዱስትሪ ላይ የሚታዩ ችግሮችን፣ ሕገወጥ አሠራሮችን መታገል ነው፡፡ መዋጋት ያለበት መንግሥት ነው፤ ግን እኛም የበኩላችንን እንጥራለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...

የልጅነት ሕልም ዕውን ሲሆን

‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚል በብዙዎች ዘንድ የሚዘወተር አባባል አለ፡፡ አባባሉ የተጎዳን ሰው ለመርዳት፣ የወደቁትን ለማንሳት፣ ያዘኑትን ለማፅናናት፣ ከገንዘብ ባሻገር ቅንነት፣ ፈቃደኝነት፣...