Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርሰላማዊውን ድባብ ለማደፍረስ የሚያነሳሳ ከዲያብሎስ የቅርብ ወዳጅ በስተቀር ማን ሊሆን ይችላል?

ሰላማዊውን ድባብ ለማደፍረስ የሚያነሳሳ ከዲያብሎስ የቅርብ ወዳጅ በስተቀር ማን ሊሆን ይችላል?

ቀን:

በመርሐፅድቅ መኮንን ዓባይነህ

ኢትዮጵያውያን ወደ አደባባይ በመውጣት ራሳቸውን በሰላማዊ ሠልፍና በሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባዎች የመግለጽና ሐሳባቸውን በተደራጀ መንገድ የማሰማት መብት አላቸው፡፡ ይህ ዴሞክራሲያዊ መብት በተወካዮቻቸው አማካይነት ባፀደቁትና የእኛ ነው ብለው በሚተማመኑበት ሕገ መንግሥት አንቀጽ 30 ንዑስ አንቀጽ 1 ሥር የተረጋገጠ ነው፡፡

      ይሁን እንጂ እንዳለመታደል ሆኖ በጣት ከሚቆጠሩ ጥቂት አጋጣሚዎች በስተቀር ይኼንን ሕገ መንግሥታዊ ትሩፋት በፍላጎታቸው ሥልት ተጠቅመውበት አያውቁም ለማለት ያስደፍራል፡፡ እንዲያውም ይህ ጸሐፊ የሚያስታውሰው በሦስተኛው ዙር ብሔራዊ ምርጫ ዋዜማ የቀድሞው ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ሚያዚያ 30 ቀን 1997 ዓ.ም. ጠርቶት በነበረው፣ ከአንድ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ በተገኘበት ታላቅ ሠልፍ ላይ የታየውንና እስካሁን ድረስ ከብዙ ወገኖች ህሊና የማይጠፋውን ፍፁም ሰላማዊ የመብት አጠቃቀም ድባብ ብቻ ነው፡፡ ከእዚያ ውጪ የሚደረጉ ሕዝባዊ ሠልፎች ወይም ስብሰባዎች ቢኖሩ አንድም በመንግሥት አነሳሽነት የተጠሩ ወይም ሕዝባዊ በዓላትን ለማክበር የሚካሄዱ መሆን አለባቸው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

      ቅዳሜ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ በመስቀል አደባባይ የተካሄደውና ሚሊዮኖች በነቂስ ወጥተው የተሳተፉበት አስደማሚ ሰላማዊ ሠልፍ ግን፣ በመንግሥት ወይም በየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት አነሳሽነትና ቅስቀሳ የተጠራ አልነበረም፡፡ እንዲያውም በእዚህ ረገድ በአገሪቱ ታሪክ ሰፊው ሕዝብ በራሱ ፈቃድና ያለማንም አስገዳጅነት ወደ አደባባይ የወጣበትና ከውስጡ በተመለመሉ አስተባባሪዎች ጋሻ ጃግሬነት እየተመራ ያካሄደው የመጀመሪያው ግዙፍ ሰላማዊ ሠልፍ ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ የሰላማዊ ሠልፉ ዓላማም ቢሆን ግልጽና የማያሻማ ግብ ያለው ሆኖ ሥልጣን ባለው የመንግሥት አካል ዕውቅና የተሰጠው ነበር፡፡ ይኸውም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አሊ በአገሪቱ የጀመሯቸውን የለውጥ ዕርምጃዎች መደገፍና ሦስት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ያስመዘገቧቸውን ውጤቶች በማወደስ፣ ለሥራ አፈጻጸማቸው ተገቢውን ዕውቅና መስጠትና በጥረታቸው እንዲገፉበት ከልብ በመነጨ ምሥጋና ማበረታታት ነው፡፡

      ከሁሉም የመዲናዋ ማዕዘናት ተጠራርቶና በመንፈስ ብቻ ተግባብቶ የተንቀሳቀሰው የሠልፉ ሱናሜ ፍፁም ሰላማዊ እንደ ነበር በጊዜው የተካፈሉ ሁሉ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ባሸበረቁ ካነቴራዎችና ባንዲራዎች አጊጠው የለውጡን ዕርምጃ ከሚያስተጋቡ ልዩ ልዩ መፈክሮች በስተቀር፣ የሕዝባዊ ስብሰባና የሰላማዊ ሠልፎች ሥነ ሥርዓት አዋጁ በሚከለክለው መሠረት የጦር መሣሪያ የያዘ ሰው አልታየባቸውም፡፡ በአዲስ አበባ ሰማይ ሥር ስለኢትዮጵያ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እየዘመሩና እየጨፈሩ ወደ መስቀል አደባባይ መትመማቸው፣ እዚያ እንደደረሱ ቁጥራቸውን ለመገመት በሚያዳግት ሁኔታ ተጨናንቀው መታደማቸው ብቻ እውነት ነበር፡፡

      ሠልፈኞቹ እንዲያ የሚናፍቋቸውና አብዝተው የሚሳሱላቸው አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ በመስቀል አደባባይ የተገኙት፣ እንደ አብዛኞቹ ዳተኛ መሪዎች ምልዓተ ሕዝቡን ብዙ ሳያስጠብቁና ሳያጉላሉ ነበር፡፡ ይባስ ብለው ለሠልፈኛው የፍቅርና የአክብሮት ሰላምታ ከሰጡ በኋላ ወደ ተዘጋጀላቸው መድረክ በመውጣት ለተሰበሰበው ሕዝብ ያሰሙት ንግግር እንደ ተለመደው ብቻ ሳይሆን፣ ከወትሮውም በላቀ ሁኔታ ወሰን የሌለው ትህትና የታየበትና ሁሉን አካታች ይቅርታ የተንፀባረቀበት ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

      የዶክተሩ ሰውኛ አንደበት ፊት ለፊት የምንመለከተውን ገጻቸውን ብቻ ሳይሆን፣ በህቡዕ የተያዘውን ውሳኔ ልባቸውን ጭምር የማሳየት ኃይል አለው፡፡ ‹‹ይህች አገር ሁለት ወር ሠርቶ የሚታበይና ይህንኑ ሰበብ አድርጎ ለውዳሴ ከንቱ የሚቻኮል ሳይሆን፣ ለዘመናት አስሮና ተብትቦ የያዛትን አደገኛ ሰንኮፍ ከስሩ ነቃቅሎ የሚጥልላትና እስከ ወዲያኛው ነፃ የሚያወጣት መሪ ነው የሚያስፈልጋት፤›› ሲሉ ያስደመጡትና ወደር የሌለው ትህትናን የተላበሰው አነጋገራቸው፣ በእርግጥም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ብሩህ አዕምሮ፣ ቅን ልብና አርቆ አስተዋይነት ያሳያል፡፡

      ነገር ግን በጥባጭ ሳለ ጥሩ አይጠጣምና በማያባራ ጭብጨባ ታጅቦ ለ18 ደቂቃዎች ያህል የዘለቀውን ያንን ማራኪ ንግግራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ አትሮኖሱን ተሰናብተው ወደ ክብር መቀመጫቸው እንደተመለሱ ብዙ ሳይቆዩ ነበር፣ እርሳቸውና ባልደረቦቻቸው ከተቀመጡበት ከቀኝ አቅጣጫ በኩል በእዚያ ሥፍራ ይሆናል ተብሎ ያልተጠበቀ የቦምብ ፍንዳታ የተሰማው፡፡ በሚገባ ታቅዶ፣ በቂ መሰናዶ ተደርጎበትና ተቀነባብሮ የተፈጸመ ቢመስልም  ፍንዳታውን ማን እንዳደረሰው እስካሁን ድረስ በውል አይታወቅም፡፡

      የጥቃቱ ሰለባዎች ወዲያውኑ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል አምቡላንሶች ወደ መዲናይቱ የተለያዩ ሆስፒታሎች ተወስደዋል፡፡

ዕድለኝነታቸውን በሚጠቁም ሁኔታ በእዚህ አስደንጋጭና አሸማቃቂ ክስተት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደረሰባቸው አካላዊ ጉዳት ባይኖርም፣ በፍንዳታው የወደቁ ወገኖቻቸውን መመልከቱ ብቻ የፈጠረባቸውን ሲቃ በከባድ ሐዘን ተጨማደው በቴሌቪዥን ከሰጡት መግለጫ በቀላሉ ለመረዳት ይቻላል፡፡

       እንዲያም ሆኖ እንኳ አገሪቱ በልበ ሰፊነት ለሁሉም የዘረጋቻቸው የፍቅርና የይቅርታ እጆች አሁንም ገና እንዳልታጠፉ ገልጸው፣ የሽብር ጥቃቱን ለፈጸሙት ወገኖች የንስሐ በሩ እንዳልተዘጋባቸው ጨምረው ያሰሙት መልዕክት ተለሰላሽነታቸውን ሳይሆን ኢተበቃይነታቸውን ከወዲሁ አመላካች ነው፡፡ ለሰላሙና ለአንድነቱ ፍፁም ቀናዒ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይኼንን አፀያፊ የሽብርተኝነት ድርጊት በጠቅላይ ሚኒስትሩና እርሳቸውን ለማመስገን አደባባይ በወጣው ሠልፈኛ ላይ በእዚህ ደረጃ የፈጸሙትንና ያቀነባበሩትን እኩይ ህሊና የተጠናወታቸው አካላት ማንነት ፖሊስ አጣርቶ ለፍርድ እንዲያቀርባቸው በከፍተኛ ጉጉት እየተጠበቀ ነው፡፡ ያም ሆኖ የሽብር ጥቃቱ የተፈጸመው ከመድረኩ እምብዛም ባራቀ ሥፍራ ላይ መሆኑ ሲታይ ዋናው ዒላማ ምናልባትም ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይሆኑ እንዳልቀሩ ከወዲሁ ለመገመት አያዳግትም፡፡

      ከእዚያ የጥፋት በትር ለጥቂት ያመለጡት ቆፍጣና መሪ ግን ድንገቱ የፈጠረባቸውን ብስጭት ለጊዜው ዋጥ አድርገው፣ የሁከት ፈጣሪዎቹን ታናሽነትና ወራዳነት ካስታወሱ በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅና ጨዋ ሕዝብ በመሆኑ ፍቅር የተራቡ ናቸው ያሏቸውን ንፁኃን ወገኖቻችንን ደም በከንቱ የማፍሰስ ሱስ ካለባቸው፣ ከእነዚህ የአዕምሮ ምንዱባን ጋር አብሮ ማነስ አይገባውም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ አክለውም ያንን የመሰለ ሰላማዊ ድባብ ለመረበሽ በተሰነዘረው የቀቢፀ ተስፋ ትንኮሳ የጥቂት ወገኖቻችን ሕይወት መቀጠፉና በርካታ ወንድም እህቶቻችን በአካል መጎዳታቸው ክፉኛ ቢያሳዝነንም፣ የጀመርነውን የለውጥ ዕርምጃ ለመቀልበስ ትናንት ሞክረው እንዳልተሳካላቸው ሁሉ ዛሬም ሆነ ነገ ሊሳካላቸው ከቶ አይችልም ሲሉ በቁርጠኝነት ተናግረዋል፡፡

      በመሠረቱ ተገቢው ጥበቃ ይደረግለታል እንጂ የጦር መሣሪያ ባልታጠቀና ሥልጣን ላለው የመንግሥት አካል አሳውቆ ሐሳቡን በሰላማዊ ትዕይንት ብቻ ለመግለጽ ባዶ እጁን ወደ አደባባይ በወጣ ሕዝብ ላይ ይኼንን ዓይነቱን ጥቃት መፈጸም፣ ወይም መቃጣት ከአስነዋሪነት አልፎ በአገሪቱ ሕግ መሠረት በከባድ ወንጀል የሚያስጠይቅ የሽብርተኝነት ድርጊት ነው፡፡ እነሆ በጥቃቱ ሳቢያ የደረሰውን ጉዳትና ያንኑ ጥቃት በቀጥታ ያደረሱትን ወገኖች ብቻ ሳይሆን፣ ከጥቃቱ በስተጀርባ የማን እጅ እንዳለበት ወይም ሊኖርበት እንደሚችል ጭምር በገለልተኛ ምርመራ ማረጋገጡ የሚጠቅመው ለእዚህ ነው፡፡

      ‹‹አልቦ ነገር ዘይስአኖ ለእግዚአብሔር›› ነውና በፈጣሪ ሽፋን ውጤቱ ከተገመተው በታች ቢሆንም፣ ይኼንን የመሰለ አስከፊ ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ማንነታቸው በማያሻማ ሁኔታ ከተረጋገጠ በኋላ አንገት ከሚያስደፋ ውግዘት ባለፈ ተይዘው በሕግ የመጠየቃቸውና የመቀጣታቸው ፋይዳ በድርጊቱ የተሳተፉትን ወገኖች በግል ከመበቀል የዘለለ እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡ በመርህ ደረጃ የትኛውም የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት የሚደነግገው ቅጣት ከተበቃይነቱ ይልቅ አራሚነቱ፣ አስተማሪነቱና ሌሎች ሰዎች ተመሳሳይ ድርጊት ለመፈጸም ከመነሳሳታቸው በፊት ሁለት ጊዜ እንዲያስቡ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ሰጪ ሆኖ ማገልገሉ እንደሚያመዝን እዚህ ላይ በአንክሮ ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡

      ይኼንን በውል ለመረዳት በኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 1 ሥር የሰፈሩትን ወርቃማ ድንጋጌዎች በዋቢነት ይመለከታል፡፡ ከእዚህ እንደሚከተለው ይነበባሉ፡፡ የወንጀል ሕግ መሠረታዊ ዓላማ ለጠቅላላው ጥቅም ሲባል የአገሪቱን መንግሥት፣ የሕዝቦቿንና የነዋሪዎቿን ሰላም፣ ደኅንነት፣ ሥርዓት፣ መብትና ጥቅም መጠበቅና ማረጋገጥ ነው፡፡

      የወንጀል ሕግ ዓይነተኛ ግብ ደግሞ ወንጀል እንዳይፈጸም መከላከል ሲሆን፣ ይኼንን የሚያሳካው ስለወንጀሎችና ስለቅጣታቸው የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ነው፡፡ ማስጠንቀቂያው በቂ ባልሆነበት ጊዜ ወንጀል አድራጊዎቹ ተቀጥተው ሌላ ወንጀል ከመፈጸም እንዲቆጠቡና ለሌሎች ማስተማሪያ እንዲሆኑ፣ ወይም እንዲታረሙ ወይም ራሳቸውም ቢሆኑ ተጨማሪ ወንጀሎችን እንዳይፈጽሙ ዕርምጃዎች እንዲወሰዱባቸው በማድረግ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...