Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅጥቁሩና ነጩ መሀል ግራጫ አለ!

ጥቁሩና ነጩ መሀል ግራጫ አለ!

ቀን:

‹‹መርካቶ! መርካቶ!›› እያለ ይጣራል ወያላው፡፡ ‹እምዬ መርካቶ ያለው ሸምቶ ያጣው ቀምቶ› የተባለላት ናት፡፡ ጥቂት ሰዎች ታክሲው ውስጥ ታድመናል፡፡ ጥቂቶችን እየጠበቅን ነው፡፡ መሙላት አንፃራዊ ቢሆንም ሲሞላ ጉዟችን ይጀመራል፡፡ መገናኛ መነሻችን ነው፡፡ የታክሲውን መሙላት ከሚጠባበቁት መሀል በዓለም ዋንጫው ውጤት አንጀቱ ቁስል ያለ ቢጤ፣ ‹‹መቼ ይሆን ግን በዓለም ዋንጫው የአፍሪካዊ ቡድኖች እስከ መጨረሻው የሚዘልቁት?›› በማለት ላነሳው ጥያቄ መልስ የሚሰጠው አላገኘም፡፡ ተሳፋሪዎች ‹‹መቼም . . . ›› የሚሉ ይመስላሉ፡፡

ትንሽ ቆየት ብሎ፣ ‹‹ምነው እንደ አትሌቲክስ ሁሉ በመጀመርያ ዙር አውሮፓውያንና አሜሪካውያኑ ተሸኝተው፣ ፍፃሜው ላይ አፍሪካውያን የሚፎካከሩበትን ዘመን እግዜሩ ባመጣልኝ፤›› በማለት ጠየቀ፡፡ ይኼን ጊዜ ታክሲያችን እየሞላ ነበር፡፡ መሙላቱም ሳያንስ አንድ ሰው ጨዋታውን ተቀላቀለ፡፡ ‹‹መቼም እግዜሩ ይህንን ፀሎትን ሲያነበው፣ ዘንድሮ ሰው ምን ነክቶታል በማለት እንደሚያልፈው ምንም ጥርጥር የለኝም፤›› ብሎ መለሰለት፡፡

ይህን ጊዜ ሌላ ሰው፣ ‹‹አፍሪካችን እኮ እስካሁን በዓለም ዋንጫው ተወክላ ትገኛለች፤›› በማለት አሻሚ ሐሳብ አነሳ፡፡ ሁሉም ተሳፋሪዎች በግርምት ዞር ብለው ተመለከቱት፡፡ በዚህ ዘመን ግራ የሚያጋባ ሰው አይጠፋም፡፡ እርሱ ብቻም አይደለም፡፡ በሁሉም ነገር ላይ ‹መረጃ አለኝ! አውቃለሁ! ብዬ ነበር!› የሚል ሰው በዝቷል፡፡ አንዳንዱማ ልክ እንደ ጣቃ እየተተረተረ ከአገር ውስጥ ትንሿ ጉዳይ እስከ ትልልቁ ዓለም አቀፍ ውስብስብ ነገር ድረስ ሲቀደድ አጀብ ያሰኛል፡፡ ሰሞኑን እየሆነ እንዳለው ማለት ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የቅድሙ ሰውዬ ፈገግ እያለ፣  ‹‹እንዴ የፈረንሣይን ቡድን አላያችሁትም ማለት ነው?›› ብሎ አስፈገገን፡፡ ይኼኔ የሰውዬው ሐሳብ ያልተዋጣለት መሳይ፣ ‹‹እንዲህ ያለ ጭፍን አስተሳሰብ ያለፈበት ነው፤›› ብሎ የሰውየውን ምልከታ አንቋሸሸ፡፡ እኛም ሐሳቡን በውል ስላልተረዳን ለማወቅ አሰፈሰፍን፡፡ ሰውየውም፣ ‹‹አሁንስ ሁሉም ነገር የእኛ ነው የሚለው ሰው ብዛቱ? በዚህ ሒሳብ ከሄድንማ ሁሉም ቡድኖች ኢትጵያዊያን ናቸው፡፡ ያሸነፉትም የተሸነፉትም . . . ›› እያለ ወደ ጥንት ዘመን ሊወስደን ሞከረ፡፡ ይኼን ጊዜ ነበር አንድ ሰው፣ ‹‹ኧረ በፈጠረህ በሶፊያ ዘመን ወደ ሉሲ አትጎትተን?›› ብሎ የቀለደበት፡፡

አንድ ጎልማሳ ደግሞ ሰሞነኛው ብርድ እያንዘፈዘፈው፣ ‹‹የሰሞኑን ብርድ ሶፊያን ያሳቅፋል፤›› በማለት ፈገግ አሰኘን፡፡ ይኼን ጊዜ ጨዋታው ወደ ማቀፍና መተቃቀፍ ተለወጠ፡፡ ‹‹በተለይ በሰኔ አሥራ ስድስቱ ሠልፍ ላይ ተቃቀፉ ሲባል አቅፌሽ ዞር ስል ያጣሁሸ ጉብል፣ እባክሽን ደግመን . . . ›› ሲል በሰውየው ሁኔታ የተገረመ ወጣት፣ ‹‹በነገራችን ላይ ሶፊያ አግብታ መውለድ ትፈልጋለች . . . ›› እያለ ብቻውን ሳቀ፡፡ ታክሲያችን ጉዞውን ጀምሯል፡፡ ከወጣቱ አፍ የቀለበው የእሱ ቢጤ፣ ‹‹እንግዲህ ሶፊያ ኢትዮጵያዊ ፈጣሪና ኢትዮጵያዊ ልጅ ይኖራታል ማለት ነው፤›› እያለ ሳቀ፡፡  ‹‹በዚህ ዘመን የሚያስፈልገን ብርድ ልብስ ፋብሪካ እንጂ ሌላው ዘበት ነው፡፡ እስቲ በመጀመርያ በልተን እንደር፣ ለብሰን እንደር ሌላው በጊዜው ይደርሳል፤›› በማለት የግል አስተያየቱን የሰጠው ዝምተኛ መሳይ ሰው ነው፡፡

ወያላው ለመጀመርያ ጊዜ አስተያየቱን መስጠት ጀመረ፡፡ ‹‹ኧረ እዚህ ታክሲ ውስጥ ጎታች መንፈስ አለ፡፡ ሶፊ ሲሉት ሉሲ፣ እርቅ ሲሉት ፀብ የሚል . . . ›› እያለ አዲስ ነገር ሲጎነጉን ሾፌሩም ተደርቦ፣ ‹‹በእናታችሁ አትጎትቱን ወደፊት እንፈንጠርበት፤›› ሲል ትንሽ ትኩረት ተሰጠው፡፡ ቀጥሎም፣ ‹‹እኔ እንዲያውም በትውልዴ ሶማሌ ነኝ፡፡ ያለችኝ ፂም ላይ ሒዩውማን ሔርም ቢሆን ቀጥዬባትና ሂና ተቀብቼ ወደ ይገባኛል ጥያቄ የማመራበትን መንገድ መቅረፅ እፈልጋለሁ፤›› ሲል ወያላው ሳቀበት፡፡ ቀጥሎም፣ ‹‹አንተ ግን ምንድነው እንደዚህ የሚገለባብጥህ? ባለፈው ደቡብ ክልል ወርቅ ተገኘ ስትባል የአባቴ ቅድመ አያት ከደቡብ ነው አልከን፣ እሺ አልን፡፡ መቼ ለታ ደግሞ አማራ ክልል ላይ የሆነ ልማት ታየ ስትባል የእናቴ የዘር ሐረግ የሚመዘዘው ከአማራ ነው ብለህ ለምነህ አሳመንከን፡፡ እሺ ብለን አመንን፡፡ ይባስ ብለህ አሁን ደግሞ ሶማሌ ገብተህ አረፍከው?›› በማለት ወሳኝ ጥያቄ ሰነዘረለት፡፡ ይኼን  ጊዜ አንድ ሰው፣ ‹‹እንዲያው በአግባቡ ቢጣራና የዚህ ሰው የዘር ሐረግ ውስጥ ብትፈልግ ሶፊያም አትጠፋም፤›› በማለት ፈገግ አሰኘን፡፡

አንድ ተሳፋሪ ለሶፊያ ኢትዮጵያዊ ስም አውጣላት ቢባል፣ ‹‹ሉሲ እንዳትሰማ፤›› በማለት ቀለደ፡፡ ቀጥሎም፣ ‹‹አይ እኛ ሉሲንም የእኛ አልን፡፡ ሶፊያንም የእኛ አልን፡፡ ቀጣዩ እንግዲህ በዓለም ዋንጫ ውስጥም ፈረንሣይ የእኛ እያላችሁ ራሳችሁን አፅናኑ፤›› እያለ የእኛ የሆነ ምንም ነገር የለም የሚመስል አስተያየት ሰጠ፡፡ ይኼን ጊዜ አንድ ጥጉን ይዞ የነበረ ሰው ማወራት ጀመረ፡፡ ሁሉም ሰው ጥግ ላይ ነው ያለው፡፡ ‹‹ኧረ ወገን እንቀራረብ . . . ›› ሲል ሰውየው እንዲያብራራ ምልክት አሳየነው፡፡ እርሱም እንዲህ በማለት ቀጠለ፣ ‹‹ግማሹ ሁሉን ነገር የእኛ፣ አፍሪካ ሳትቀር የእኛ፣ ሉሲ የእኛ፣ ሶፊያ የእኛ፣ . . . እያለ ይናውዛል፡፡ ሌላው ደግሞ የእኛ የሆነ ምንም የለም፣ ምኑም ውስጥ የለንበትም እያለ ይፈላሰፋል፡፡ ሁለቱም ጥግ ጥጋቸውን ይዘዋል፡፡ ኧረ ጎበዝ እንቀራረብ . . . ›› ብሎ ፈገግ አሰኘን፡፡ ወያላው በተራው፣ ‹‹አራምባም ያሉት ቆቦም ያሉት ይምጡና እዚህ መሀል ኢትዮጵያ ላይ እንወያይ፤›› አለ፡፡ እንግዲህ ሁሉም እያወራ አድማጭ እንዳይጠፋ፡፡

በመብራት ኃይል የተበሳጨ አንድ ሰው፣ ‹‹የዘንደሮው መብራት ልክ ዝናብ ጠብ ሲል ዘልሎ የሆነ ስርቻ ውስጥ የሚደበቅ እየመሰለኝ ነው፤›› ሲል፣ ‹‹ዘንድሮም መብራት ይጠፋል ልትለኝ እንዳይሆን?›› በማለት ሌላው ጠየቀው፡፡ ሰውየውን፣ ‹‹መቼም የዓለም ዋንጫውን ሩሲያ ሄደህ ነው እየተከታተልክ ነው ያለኸው ለማለት አልደፍርም፤›› ሲለው ሰውዬውም በምላሹ፣ ‹‹ይገርምሃል እዚሁ አገሬ ቁጭ ብዬ ነው የምከታተለው፡፡ ዳሩ ግን መብራት ጠፋም መጣም ማልቀሴን ስላቆምኩ ነው፡፡ ወዳጄ አታልቅስ፡፡ እስቲ ማመሥገንን ተለማመድ፡፡ ያለህን ነገር ማክበርና ማድነቅ ተለማመድ፡፡ አፍሪካ ለምን በዓለም ዋንጫው እስከ መጨረሻው አልደረሰችም ብለህ አታጉረምርም፡፡ ዳሩ ግን አፍሪካም ኢትዮጵያም ያፈራቻቸው ታላላቅ አትሌቶች አስበህ ተፅናና፡፡ እነዚህን አትሌቶች ፈረንሣይም፣ ፖርቹጋልም፣ ብራዚልም ብትሄድ አታገኛቸውም፡፡ ስለዚህ ስለሌለህ ነገር ማልቀሱን ተውና ስላለህና አለ ስለተባለው ነዳጅ ብትቦርቅ ይሻልሃል፤›› በማለት ረዥም አስተያየት ሰጠ፡፡

ሌላ ደግሞ፣ ‹‹እኔ ግን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላልተወሰነ ጊዜ መቋረጥ አለበት ባይ ነኝ፤›› ሲል ወያላው፣ ‹‹እውነትህን ነው እስቲ ስቴዲዮሙን ለአንድ ሁለት ዓመት ጤፍ ዘርተን እንየውና ከዚያ ምናልባት ወደፊት እንመለስበት ይሆናል፤›› ሲል የመጀመርያው ሰው፣ ‹‹አንድ አርቴፊሻል ሳር መግዛት አቅቶን ነው ወይስ ለሳር መግዣ የተሰበሰበውን ገንዘብ የግቢያቸውን ሳር አርቲፊሻል እያስደረጉበት ነው?›› በማለት ጥያቄ አቀረበ፡፡ ‹‹ኳስ ጨዋታ የአስማት ያህል በከበደባት አገር ውስጥ ሜዳን ለጤፍ መዝሪያነት የሚመኝ ትውልድ ከተፈጠረ፣ ሳሩን እያጋዘ ቤቱ ለመውሰድ የሚያሰፈስፍ ከበዛ አልቆልናል በሉኛ . . . ›› የሚሉ ጥግ ላይ የተቀመጡ አዛውንት ናቸው፡፡

‹‹እኔ ግን ነዳጅ፣ ወርቅ፣ የከበረ ድንጋይ፣ . . . ተገኘ ቢባል እንኳን አንድ የዓለም ዋንጫ ላይ የሚሳተፍ ብሔራዊ ቡድን አገኘን ካልተባለ በስተቀር በምንም አልደሰትም፡፡ የእግር ኳስን ደስታ ምንም ሊተካልኝ አይችልም፤›› በማለት አንዱ አለቃቀሰ፡፡ ይኼን ጊዜ ወያላው፣ ‹‹ብራዘር አትጎትተን፡፡ እኛ የዓለም ዋንጫውን እናዘጋጃለን ብለን እናምናለን፡፡ ዋናው ነዳጁ በቧንቧ ወደ የቤታችን መምጣቱ ነው፡፡ ከዚያ ሁሉም ቅርፅ ይይዛል . . . ›› ሲል ሾፌሩ ተደርቦ፣ ‹‹ያን ጊዜ በዓለም ዋንጫ መወዳደር ብቻ ሳይሆን የማዘጋጀት መብቱን እንጠይቃለን፡፡ ምንም የሚያሠጋን ነገር የለም፤›› እያለ ቀለደ፡፡ እኛም እምዬ መርካቶ በሯን ከፍታ እየጠበቀችን ነበርና መጨረሻችን ላይ ወረድን፡፡ በየፊናችንም ተበታተንን፡፡ ምኞት ሁሌም ያለ ነውና መመኘታችን ይቀጥላል፡፡ ከነጩና ከጥቁሩ መህል ግራጫውን አንዘንጋ፡፡ መልካም ጉዞ!  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...