Tuesday, April 23, 2024

በውጭ ያሉ ተቃዋሚዎችን ወደ አገር ውስጥ እያስገባ ያለው የሰላም ጥሪ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኢትዮጵያ ላለፉት ሦስት ዓመታት በከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞና አመፅ ስትታመስ ቆይታ አንፃራዊ የሚባል ሰላምና መረጋጋት የታየበት ወቅት ላይ ትገኛለች፡፡ ምንም እንኳን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ግጭቶች እየተከሰቱና የሰዎች ሕይወት እያለፈ፣ አካል እየጎደለና ንብረት እየወደመ ቢሆንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ጊዜ በኋላ አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት በአገሪቱ ታይቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩን ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በአገሪቱ ለውጥ እየተመዘገበ ነው ብለው የሚያምኑ በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የትጥቅ ትግል እያደረጉ ያሉትን ጨምሮ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉትን ጥሪ ተከትለው ወደ አገር ውስጥ እየገቡና ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ከመንግሥት ጋር እየተወያዩ ይገኛሉ፡፡

መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በፓርላማ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን የተሰየሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ‹‹በአንድ አገር ውስጥ የሐሳብ ልዩነቶች ይኖራሉ። የሐሳብ ልዩነት እርግማን አይደለም። ልዩነቱ እንዳለ ሆኖ መደማመጥና በመርህ ላይ ተመሥርተን መግባባት ስንችል የሐሳብ ልዩነት በረከት ይዞልን ይመጣል። በሐሳብ ፍጭት ውስጥ መፍትሔ ይገኛል። በመተባበር ውስጥ ኃይል አለ። ስንደመር እንጠነክራለን። አንድነት የማይፈታው ችግር አይኖርም፣ አገር ይገነባል። የእኔ ሐሳብ ካላሸነፈ ሞቼ እገኛለሁ ማለት ግን እንኳን አገርን ሊያቆም ቤተሰብን ያፈርሳል። ያለችን ኢትዮጵያ ነች፡፡ ከየትኛውም የፖለቲካ አመለካከት በላይ አገራዊ አንድነት ይበልጣል። አንድነት ማለት ግን አንድ ዓይነትነት ማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል። አንድነታችን ልዩነቶቻችንን ያቀፈ ብዝኃነታችንን በኅብረ ብሔራዊነት ያደመደቀ መሆን አለበት፤›› ብለው የሐሳብ ብዝኃነት እንደሚያስፈልግ፣ ለአገር ብልፅግናም ከፍተኛ ሚና መጫወት እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፣ ‹‹ከኢሕአዴግ ውጪ ያሉ ፓርቲዎችን የምናይበት መነጽር እንደ ተቃዋሚ ሳይሆን እንደ ተፎካካሪ፣ እንደ ጠላት ሳይሆን እንደ ወንድም፣ አማራጭ ሐሳብ አለኝ ብሎ እንደመጣ አገሩን እንደሚወድ የዜጋ ስብስብ ነው፡፡ ስለዚህ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ የተመቻቸና ፍትሐዊ የመወዳደሪያ ሜዳ እንዲኖር በመንግሥት በኩል ፅኑ ፍላጎት ያለ በመሆኑ፣ ስለሰላምና ፍትሕ በልዩ ልዩ መንገድ የምትታገሉ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች አብሮነታችንንና ሰላማችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ፣ ብሔራዊ ጥቅሞቻችንንም አሳልፈው የሚሰጡ የአስተሳሰብ መስመሮችን በአርቆ አስተዋይነትና አገራዊ ፍቅር፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ የተሻለ የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር የምናደርገው ጥረት እንድታግዙ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፤›› ሲሉም በውጭ የሚኖሩ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ወደ አገር ውስጥ ገብተው በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ንግግራቸው፣ ‹‹ዴሞክራሲ ለእኛ ባዕድ ሐሳብ አይደለም። በዓለም ውስጥ በብዙ ማኅበረሰቦችና አገሮች ዴሞክራሲ በማይታወቅበት ዘመን በገዳ ሥርዓታችን ተዳድረን ለዓለም ተምሳሌት ሆነን ኖረናል። አሁንም ዴሞክራሲን ማስፈን ከየትኛውም አገር በላይ ለእኛ የህልውና ጉዳይ እንደሆነ እናምናለን። ዴሞክራሲ ያለ ነፃነት አይታሰብም። ነፃነት ከመንግሥት ለሕዝብ የሚበረከት ስጦታ አይደለም። ከሰብዓዊ ክብር የሚመነጭ የእያንዳንሱ ሰው የተፈጥሮ ፀጋ እንጂ። ነፃነትን በዚህ መልኩ ተረድቶ ዕውቅና የሰጠውን ሕገ መንግሥታችንን በአግባቡ መተግበር፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተለይም ሐሳብን የመግለጽ፣ የመሰብሰብና የመደራጀት መብቶች በሕገ መንግሥታችን መሠረት ሊከበሩ ይገባል። የዜጎች በአገራቸው የአስተዳደር መዋቅር በዴሞክራሲያዊ አግባብ በየደረጃው የመሳተፍ መብትም ሙሉ በሙሉ ዕውን መሆን አለበት፤›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ በመከተል ለመጀመርያ ጊዜ ወደ አገር ውስጥ የገቡት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ራሳቸውን በመገንጠል የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) ፓርቲን በማቋቋም በሊቀመንበርነትና በምክትል ሊቀመንበርነት እየመሩ ባሉት አቶ ሌንጮ ለታና ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) የተመራው አምስት አባላት ያለው የልዑካን ቡድን ነበር፡፡

ፓርቲው ቀደም ብሎ ግንቦት 3 እና 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ከኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ጋር ባደረገው ውይይት መግባባት ላይ በመድረሱ ወደ አገር ውስጥ እንደሚገባ ባስታወቀው መሠረት፣ ወደ አገር ውስጥ በመግባት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን ጨምሮ ከሌሎች የኢሕአዴግና የኦሕዴድ አመራሮች ጋር አብረው ለመሥራት ውይይት አድርገዋል፡፡ የኦዴግ አመራሮች የግንቦት 20 በዓል በሸራተን ሲከበር በእንግድነት ተገኝተው ነበር፡፡ በወቅቱ በሰጡት መግለጫ ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጥምረት ለመሥራት እንደሚያስቡም አስታውቀዋል፡፡

አቶ ሌንጮ ‹‹አገሪቱ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚ በፍጥነት እየተለወጠች በመሆኑና እኛ ደግሞ ከአገሪቱ ከወጣን ረዥም ጊዜ ስለሆነን፣ ያንን ካጠናን በኋላ ነው ተሳትፏችን በምን ዓይነት ሁኔታ ይሁን የሚለውን የምንወስነው፤›› በማለት፣ ዓላማቸው አሁን ያለው ፌዴሬሽን ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ተናግረው ነበር፡፡

ከኦዴግ ልዑካን በኋላም በአገሪቱ ለውጥ አለ ብለው በማመን ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ወደ አገር ውስጥ እየገቡ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ፡፡

ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የትጥቅ ትግሉን በመተው ወደ አገር ውስጥ የገባው የኦሮሞ አንድነትና ነፃነት ግንባር (ኦአነግ) ሲሆን፣ በብርጋዴር ጄኔራል ከማል ገልቹ ሲመራ የነበረ ነው፡፡ ዘጠኝ አባላት ያሉት አዲስ አበባ የገባው የልዑካን ቡድን በአቶ ተማም ባቲ የተመራ ሲሆን፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን ጥሪ ተቀብለው እንደመጡና ፓርቲ አቋቁመው ለመንቀሳቀስ እንደሚያስቡ ተናግረዋል፡፡ የልዑካን ቡድኑ አባላት በአሜሪካ፣ በአውሮፓና በካናዳ ሲንቀሳቀሱ ነበሩ፡፡

ሌላው ተመሳሳይ ምክንያት በመስጠት ወደ አገር ውስጥ የገባው በብርጋዴር ጄኔራል ኃይሉ ጎንፋና አባ ነጋ ጃራ የሚመራው የተባበረው ኦሮሞ ነፃነት ግንባር አባላት ልዑክ ነው፡፡ የግንባሩ ምክትል ሊቀመንበርና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሉ ጎንፋ መንግሥት ባቀረበው ሰላማዊ ጥሪ መሠረት፣ የትጥቅ ትግል በማቆም ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ወደ አገር መግባታቸውን አስታውቀዋል፡፡ ከሕዝብ ጋር ለመሥራትና በአገሪቱ እየታዩ ያሉ ለውጦች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ከመንግሥት ጎን እንደሚቆሙ አስታውቀዋል፡፡

በተመሳሳይ ሞረሽ ለወገኔ የሚባል ድርጅት በአሜሪካ በመመሥረት እቅስቃሴ ላይ የነበሩት አቶ ተክሌ የሻው ናቸው፡፡

አቶ የሻውን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው ያነጋገሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንን፣ ‹‹አገሪቱ የጀመረችውን የለውጥ ጉዞ ለመቀላቀል በርካቶች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን አድንቀዋል። በተመሳሳይ ሌሎች ኢትዮጵያውያንም ይኼንን ጥሪ ተቀብለው በቀጣይ ወደ እናት አገራቸው እንደሚመለሱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል፤›› ሲል የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በፌስቡክ ገጹ አስነብቧል፡፡

የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁንም፣ ይኼንን በማስመልከት በፌስቡክ ገጻቸው ላይ፣ ‹‹በዛሬው ዕለት ኑሯቸውን በአሜሪካ ያደረጉትና ሰሞኑን ወደ አገራቸው የመጡትን አምባሳደር ካሳ ከበደን (ዶ/ር) እና አቶ ተክሌ የሻውን ተቀብለናቸዋል:: ለአማራ ሕዝብ ይጠቅማል በምንላቸው የጋራ ጉዳዮቻችን ላይ ለመሥራት ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ተረድተናል፤›› ብለዋል፡፡

ምንም እንኳን በርካታ የተቃዋሚ ፖለቲካ ኃይሎች ወደ አገር ውስጥ እየገቡ ቢሆንም፣ መንግሥት አሁንም ድረስ ተመሳሳይ ጥሪዎችን እያቀረበ ነው፡፡

እሑድ ሰኔ 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በባህር ዳር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን ለመደገፍ በተደረገ ሕዝባዊ ሠልፍ ላይ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተመሳሳይ ጥሪዎችን አስተላልፈዋል፡፡

አቶ ደመቀ በንግግራቸው፣ ‹‹በፖለቲካ አስተሳሰባችን እዚህ ወይም እዚያ ልንቆም እንችላለን፡፡ የአንደኛው ወይም የሌላኛው አስተሳሰብ አራማጅ ልንሆን አንችላለን፡፡ የእኔ ሐሳብ የተሻለ ነው፣ የበለጠ ይጠቅማል ብለን ልንፎካከርም እንችላለን፡፡ መሠረታዊው ጉዳይ ሁላችንም ለዚህች አገር ጥቅምና የተሻለ ነገር ፍለጋ የተሰማራን መሆናችን ነው፡፡ እርግጠኝነትና ልባዊነት የሚያስፈልገው እዚህ ላይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በዚህ አጋጣሚ ብአዴን በአማራው ስም በውጭ አገር የተደራጁና ለእሱ የሚታገሉ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የተለያዩ ማኅበራዊ የሚዲያ ተቋማት በሰላም ለመንቀሳቀስ እስከወሰኑ ድረስ ወደ ክልላችን መጥተው እንዲቀሳቀሱ ጥሪ እያስተላለፈ፣ እኛም ግማሽ መንገድ ድረስ ተጉዘን ለሕዝባችን ጥቅም መከበር አብሮ ለመሥራት ዝግጁ መሆናችንን አረጋግጣለሁ፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱም፣ ‹‹በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ የአማራን ሕዝብ በልማትና በዴሞክራሲ ተጠቃሚ እናደርጋለን የሚል ሐሳብ ይዛችሁ የምትሠሩ ተፎካካሪ ፖርቲዎች እንዳላችሁ እናውቃለን፡፡ ዓላማችሁና ፍላጐታችሁ የአማራን ሕዝብ መጥቀም እስከሆነ ድረስ በፍቅር ዓይን እንመለከታችኋለን። ከፊታችን ያሉ ትልልቅ ችግሮችን ተራርቀን በመቆም ልናሽንፋቸው እንደማንችል ተገንዝባችሁ ከአገር ውጭ ያላችሁ ተመልሳችሁ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያላችሁም ተቀራርበን አንድ በሚያደርጉን ነገሮች ላይ ተመሥርተን አብረን እንሥራ። ‹‹አንድ የሚያደርጉን ነገሮች ሁልቆ መሳፍርት የላቸውምና በሚያለያዩን ጥቃቅን ነገሮች ጊዜ ሳንጨርስ በጊዜ ወደ ቤታችን እንሰብሰብ፤›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከኅብረተሰቡ ጋር ሲያደርጓቸው በነበሩ ውይይቶችም ተመሳሳይ ጥሪዎችን አድርገዋል፡፡ በቅርቡም በፓርላማ የመጀመርያ ሪፖርታቸውን ባቀረቡበት ወቅት ትጥቅ ትግልና ሰውን በመግደል ሥልጣን መያዝ ኋላ ቀር እንደሆነ፣ የትጥቅ ትግል ላይ ያሉ ሰዎች በሰላማዊ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ገብተው እንዲታገሉ ጥሪ አስተላልፈው ነበር፡፡

ይኼንንም ጥሪ በማድነቅ በተለይ አርበኞች ግንቦት ሰባት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሉትን ሁሉ ተግባራዊ የሚያደርጉና የሕዝቦች ደኅንነት የተጠበቀ ከሆነ፣ የትጥቅ ትግሉን በመተው ወደ አገር ውስጥ ለመግባት ዝግጁ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

በተለያዩ የመንግሥት አካላት እየተደረጉ ያሉ ጥሪዎችን በመቀበል ወደ አገር ውስጥ እየገቡ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሉ ቢሆንም፣ በትጥቅ ትግል ተሰማርተው የሚገኙ ኃይሎች አሉን የሚሏቸውን ታጣቂዎች በምን ሁኔታ ወደ አገር ውስጥ አስገብተው ይንቀሳቀሳሉ የሚለው ጥያቄ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው፡፡ ሲቪል በመሆን በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ይቀጥላሉ ወይስ በአገሪቱ መከላከያ ውስጥ ይጠቃለላሉ የሚሉ መላምቶችም እንዴት ተግባራዊ ሊደረጉ እንደሚችሉ ግልጽ መግለጫ ከፓርቲዎቹ አልተሰጠም፡፡

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በፓርላማ በአሸባሪነት የተፈረጁት ግንቦት ሰባት፣ ኦነግና ኦብነግ እንዲሰረዝላቸው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወስኖ ለፓርላማው እንዲያፀድቀው መላኩ ይታወሳል፡፡ በተጨማሪም በወንጀል የሚፈለጉ ድርጅቶችና ግለሰቦች ምሕረት እንዲደረግላቸው ለፓርላማ እንደሚቀርብ መሰማቱም አይዘነጋም፡፡ እንዲህ ዓይነት ዕርምጃዎች የሰላም ጥሪውን የበለጠ ውጤታማ እንደሚያደርጉ ብዙዎችን እያስማማ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -