Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የህንዱ ‹‹ኢትዮጵያን ስቲል›› አልሚኒየም ቅብ የቆርቆሮ ክዳን ለገበያ አቀረበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የገበያውን አሥር በመቶ ድርሻ ይዟል

በዓመት ከ16 ሺሕ ቶን በላይ የቤት ክዳን ቆርቆሮ፣ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ቆርቆሮና ሌሎችም የብረታ ብረት ምርቶችን ለገበያ እያቀረበ የሚገኘው ኢትዮጵያን ስቲል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ፣ በአሁኑ ወቅት ለገበያ እያቀረባቸው ከሚገኙ ምርቶች ባሻገር ‹‹ዱሙዛዝ›› የሚል መጠሪያ የሰጠውን አዲስ የአልሚኒም ቅብ የቆርቆሮ ክዳን ምርት ለገበያ ማቅረብ እንደጀመረ አስታውቋል፡፡

ኩባንያው ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ አዲሱ የቆርቆሮ ምርት እስካሁን ለገበያ ከሚያቀርባቸው ምርቶች ይልቅ ሁለት ዕጥፍ ዚንክ የተቀባና ጋልቫናይዝድ የሆነ ሲሆን፣ ዕድሜ ልክ እንዳይዝግ በሚያስችል ቴክኖሎጂ እየታገዘ የሚመረት ነው፡፡

የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ ፓንገች ጉፕታ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ በአሁኑ ወቅት ከ20 ሚሊዮን ብር ካፒታል በማስመዝገብ እየተንሳቀሰ የሚገኘውና እ.ኤ.አ. በ1997 በኢትዮጵያ የመጀርያውን ፋብሪካ በመክፈት ሥራ የጀመረው ኢትዮጵያን ስቲል በሚል ስያሜ የተመሠረተውን ማምረቻ መነሻ በማድረግ ነበር፡፡ ኩባንያው በአፍሪካ 12 አገሮች ውስጥ ፋብሪካዎችን የተከለ ሲሆን፣ በኢትዮጵያም አዲስ አበባን ጨምሮ፣ በጎንደር፣ በቀመሌና በሐዋሳ ፋብሪካዎችን ተክሏል፡፡ የምርት ማሳያዎችም እንዲሁ በአዲስ አበባ አምስት ሲኖሩት በክልል ከተሞችም ተጨማሪ አምስት ማሳያዎችን እንደከፈተ ሥራ አስኪያጁ ጠቅሰዋል፡፡

በአፍሪካ ከ50 ዓመታት በላይ በዘለቀው የሳፋል ግሩፕ ሥር ከሚተዳደሩት ኩባንያዎች አንዱ የሆነው ኢትዮጵያን ስቲል በአሁኑ ወቅት ለገበያ ካቀረባቸው የቤት ክዳን ቆርቆሮ ምርቶች ውስጥ ‹‹ዱሙዛዝ›› የሚል መጠሪያ የሰጠው ምርት፣ የዚንክ ቅቡ ሁለት ዕጥፍ የሆነና ዕድሜ ልክ እንዳይዝግ ተደርጎ የተፈበረከ ስለመሆኑም አስታውቋል፡፡ የቤት ክዳን ቆርቆሮው ዝገትን ከመከላከል ባሻገር ሙቀትን የመቋቋም ደረጃው በቴክኖሎጂ ተሻሽሎ ቢመረትም፣ በዋጋ ረገድ ከነባር ምርቶቹ ብዙም ልዩነት እንደሌለው ሥራ አስኪያጁ ጉፕታ ይናገራሉ፡፡

የመኖሪያ ቤት ክዳን ቆርቆሮን ጨምሮ፣ ለፋብሪካ ግንባታ ሥራ የሚውሉ አሉሚኒየም ፕሮፋይሎችን በማምረትም በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ እስከ 10 በመቶ ድርሻ መያዝ የሚያስችለውን ምርት እያቀረበ እንደሚገኝ ኩባንያው ጠቅሷል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዓመት 16 ሺሕ ቶን የቤት ክዳን ቆርቆሮና አሉሚኒየም ፕሮፋይሎችን የሚያመርተው ኢትዮጵያን ስቲል፣ በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥም አሁን ያለውን ገበያ ድርሻ ይበልጥ ለማስፋፋት የሚችልባቸውን የምርት ማስፋፊያ ሥራዎች እንደሚያከናውን አስታውቋል፡፡

ከ200 በላይ ሠራተኞችን የሚያስተዳድረው ፋብሪካው፣ በአዲስ አበባ አቃቂ አካባቢ በ30 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ፋብሪካ አለው፡፡ በለቡ፣ መገናኛና ሌሎችም የአዲስ አበባ ክፍሎች የማሳያና የአገልግሎት መስጫ ማዕከላትን በማንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡

በአፍሪካ የመጀመርያውን ፋብሪካ በኬንያ፣ ሞምባሳ ከተማ እ.ኤ.አ. በ1962 የተከለው ሳፋል ግሩፕ፣ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ጨምሮ በአንጎላ፣ በብሩንዲ፣ በማላዊ፣ በሞዛምቢክ፣ በናሚቢያ፣ በሩዋንዳ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በታንዛንያ፣ በኡጋንዳና በዛምቢያ ፋብሪካዎቹን አንሰራፍቷል፡፡ የአልሚኒየም ቅብ የቤት ክዳን ቆሮቆሮ በማምረት ፈር ቀዳጅ ስለመሆኑ የኩባንያው ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች