Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግብርናው ዘርፍ የቴክኖሎጂ ጅምሮች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሶፊያ የተሰኘችው ሰው መሰሏ ሮቦት በኢትዮጵያውያን የተጎበኘችበት የዘንድሮው የአይሲቲ ዓውደ ርዕይ ካስተናገዳቸው በርካታ ኩነቶች መካከል አንዱ የግብርናው ዘርፍ ላይ ሲካሄዱ የነበሩ አንዳንድ የቴክኖሎጂ ትግበራዎች የተቃኙበት መድረክ ይጠቀሳል፡፡

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ከግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ላለፉት አራት ዓመታት ሲተገብረው በቆየው የሞባይል አጭር መልክዕት አገልግሎት አማካይነት ሲሰጥ ስለቆየው አገልግሎት ያካሄደው ሥነ ሥርዓት በዓውደ ርዕዩ ከታካሄዱ ሲምፖዚየሞች መካከል አንዱ ነበር፡፡

ማክሰኞ፣ ሰኔ 26 ቀን 2010 ዓ.ም. በተካሄደውና ‹‹አይሲቲ ለግብርና ልማት›› በተሰኘው ሥነ ሥርዓት ወቅት እንደተጠቀሰው፣ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ከኢትዮ ቴሌኮም በተሰጠው የኔትወርክ አገልግሎት አማካይነት ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ከ30 ሚሊዮን በላይ ጥሪዎችን በ8028 ነፃ የስልክ መስመር በኩል ማስተናገዱንና ከ3.6 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎችን መመዝገቡን የኤጀንሲው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ካሊድ ቦምባ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

የገበሬዎችን የዕለት ተዕለት ጥያቄዎች ከማዕከል እየተቀበሉ የሚያስተናግዱ፣ የግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን በማሳተፍ በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች አገልግሎቱ ሲሰጥ መቆየቱን የጠቀሱት ሥራ አስፈጻሚው የማዳበሪያ አጠቃቀምን፣ የምርጥ ዘር፣ የፀረ ተባይና ፀረ አረም አጠቃቀምና መሰል ጥያቄዎች ያሏቸው በርካታ ገበሬዎች በሚልኩት የድምፅና የጽሑፍ ጥያቄ መሠረት ማብራሪያና ምክር ሲሰጥ መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡

ኤጀንሲው በአራቱ ክልሎች ለሚገኙ የግብርና አምራቾች አገልግሎት በሙከራ ደረጃ ባስጀመረበት ወቅት፣ ከድንች፣ ከሽንኩርትና ከካሮት አምራቾች ዘንድ በቀን 500 ጥሪዎችን መቀበል እንደጀመረ አስታውሶ፣ ይህ የጥሪ ብዛት ቀስ በቀስ ወደ 57,400 ጥሪ በማደጉ የሙከራውን ሥራ ወደ ሙሉ ትግበራ ለማስገባት የሚያስችል ውጤት ማግኘቱን አትቷል፡፡

እንደ ሥራ አስፈጻሚው ማብራሪያ የጥሪ ማዕከሉ የሚያስተናግደው የገበሬዎችን ጥያቄዎች ብቻም ሳይሆን የግብርና ልማት ወኪሎችን፣ የባለሙያዎችና የሌሎችንም ጥሪዎች ሲሆን፣ የግብርና ባለሙያዎችና የኤክስቴንሽን ሠራተኞች ዕውቀታቸውን ይበልጥ ለማስፋት የሚረዷቸው ማብራሪያዎችን ከጥሪ ማዕከሉ ስለሚያገኙ በየጊዜው ተጠቃሚ ከሆኑት ውስጥ እንደሚገኙበት ተጠቅሷል፡፡

የግብርናና የእንስሳት ሀብት ሚኒስትር ዴኤታው ኢያሱ አብርሃ (ዶ/ር) በበኩላቸው በአገሪቱ ግብርና ውስጥ የኢንፎርሜሽንና የኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎት ወሳኝ የሆነበት ጊዜ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ በአገሪቱ በየወቅቱ የሚከሰቱ የሰብል በሽታዎችን ቀድሞ ለመከላከል፣ ወረርሽኞች ሲከሰቱም የመስፋፋት አቅማቸውን ለማካደም አይሲቲ ወሳኝ እንደሆነ ያብራሩት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወረርሽኝ አደጋ እየጋረጠ የመጣውን የ‹‹መጤ ተምች›› ወይም አሜሪካን ፎል አርሚዋርም እየተባለ የሚጠራውን ነፍሳት በመጥቀስ ነበር፡፡

በኬንያና በሌሎችም አገሮች ውስጥ እስከ 30 በመቶ የበቆሎ ሰብል ያወደመው ይህ ተምች፣ ዓምና በኢትዮጵያ ያደረሰው ውድመት አምስት በመቶ ገደማ ነበር ያሉት ሚኒስትሩ፣ ይህ የሆነው በአይሲቲና ሌሎችም የቴክኖሎጂ ዕገዛዎች መረጃዎች ለገበሬው በስፋት ቀድመው እንዲደርሱና ጥንቃቄ ማድረግ በመቻሉ ነው ብለዋል፡፡

ይሁንና በአሁኑ ወቅት በናይጄሪያ ‹‹ሳውዝ አርሚዋርም›› የሚል መጠሪያ የተሰጠው ተምች ከበቆሎ ባሻገር ሁሉንም ዓይነት ሰብሎች እያጠፋ እንደሚገኝ የጠቀሱት ሚኒስትር ኢያሱ፣ ተምቹ በወረርሽኝ መልክ ወደ ኢትዮጵያ ሊመጣ የሚችልበት ዕድል ሰፊ በመሆኑ ከወዲሁ ተዘጋጅቶ ለመጠበቅ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ማካሄድ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በወረቀት ሰነድ በሚደረግ የግብይት ሥርዓት ላይ የተመሠረተው የቫውቸር አገልግሎት በርካታ የሙስናና የማጭበርበር ችግሮች የነበሩበት አገልግሎት ለገበሬዎች ሲቀርብ መቆየቱን ተጠቅሶ፣ በአሁኑ ወቅት ግን አምስት ሚሊዮን ገደማ አምራቾች ያለምንም የገንዘብ ንክኪ በስልካቸው አማካይነት የ7.6 ቢሊዮን ብር ግምት ያለው የሰባት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ግዥ መፈጸም የቻሉበት የቴክኖሎጂ ሥርዓት እየተተገበረ እንደሚገኝ ኤጀንሲው ይፋ አድርጓል፡፡

የኤሌክሮኒክ ቫውቸር (ኢቫውቸር) ሥርዓት ገበሬዎቹን ከአነስተኛ ፋይናንስ አቅራቢ ድርጅቶች ጋር በማገናኘት፣ ገበሬዎቹ የሚፈልጉትን የማዳሪያ ወይም የምርጥ ዘር መጠን ግዥ ሲፈጽሙ፣ ከማዕከል በሚደረግ ግንኙነት የፋይናንስ ግብይቱ በኤሌክትሮኒክ ዘዴ የሚካሄድበት ሥርዓት ነው፡፡ ገበሬው በብድር ጭምር ተጠቃሚ የሚሆንበት ይህ ሥርዓት፣ በአሁኑ ወቅት በአራቱም ክልሎች እየተስፋፋ ስለመምጣቱ ግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ 

ሚኒስቴሩ በኢትዮጵያ የአነስተኛ ሜካኒዜሽን ቴክሎጂዎችን ለማስፋፋት ስትራቴጂ መንደፉን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ በተለይ ዘር በመዝራትና ምርት በመውቃት ሒደት ወቅት የገበሬውን ልማት የሚቀንሱ መሣሪዎች በስፋት አገልግሎት መስጠት የሚጀምሩበት አካሄድ የሚኒስቴራቸው ዕቅድ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ይህም ሆኖ የአገሪቱ የግብርና ሥራ በአብዛኛው በሰው ጉልበት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ ገበሬዎችን ከሥራቸው በማያፈናቅሉ አካሄዶች እንደሚቃኝም ይናገራሉ፡፡ በዚህ ታሳቢነትም ሰፊ የሰው ገልበት የሚጠይቁ የአጨዳ ሥራዎች በሰው ጉልበት ታግዘው የሚካሄዱበት አሠራር የምርት ጥራት ላይ ካልሆነ በቀር በአብዛኛው በገበሬው ጉልበት እንደሚከናወኑ ገልጸዋል፡፡

የዝናብ ሥርጭት ሁኔታንና ሌሎችም የአየር ትንበያ መረጃዎችን ያካተቱ ልዩ ልዩ ወቅታዊ የግብርና መረጃዎች ለገበሬው እንደሚቀርቡ ቢገለጽም፣ አሁንም ድረስ አብዛኛው የአገሪቱ የግብርና አምራች ኃይል ዘር የሚዘራው በእጅ እየተበነ፣ በጥማድ በሬ እያረሰ ምርት ሲያበራይ በልማዳዊ መንገድ ለነፋስ እየተበነ ነው፡፡ ዘመኑ የደረሰበትንና ‹‹ፕሪሲሽን›› የሚባለውና ለፍፁምነት እጅጉን የቀረበውን የቴክኖሎጂ ደረጃ አብዛኛው አርሶ አደር የማግኘቱ ጉዳይ ብዙ የሚቀረው ነው፡፡

በርካታ አገሮች የሚጠቀሙት ዘር የሚፈልጋቸውን ግብዓቶች፣ የውኃ አጠቃቀም፣ የማዳበሪያ፣ የኬሚካልና መሰል ይዘቶች ቀድሞ በማስላት ምን ያህል ምርት በምን ያህል ቦታ ሊገኝ እንደሚችል ሁሉ ቀድመው የሚተነብዩበት የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ደርሰዋል፡፡ በአንፃሩ የኢትዮጵያ ግብርና አነስተኛ ሜካኒዜሽን ለመተግበር ጅምር ላይ ሲሆን፣ እስካሁንም የሚያቀርባቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶችና አጠቃቀማቸው ከላይ እንደታየው በአየር ትንበያ ወይም በዝናብ መጠንና ሥርጭት፣ አለያም በማዳበሪያ አጠቃቀምና መሰል ይዘቶች ላይ የተመሠረተ የመጀመሪያ ደረጃ መረጃዎችን ከማሠራጨት ባሻገር በመስኖ ሥራዎች፣ በድኅረ ምርት፣ በገበያና በሌሎችም የእሴት ሰንሰለቶች ውስጥ የሚታየው የቴክኖሎጂ አቅርቦትና ትግበራ ውስን ሆኖ ይገኛል፡፡ ትራክተር መጠቀም የጀመሩ አርሶ አደሮች የጥገናና የመለዋወጫ አቅርቦት በማጣት መቸገራቸውን ደጋግመው ሲገልጹ መቆየታቸው አይነዘጋም፡፡

ይህ ይባል እንጂ የአገሪቱን የቴሌኮም አገልግሎት የሚያቀርበው የኢትዮ ቴሌኮም ኩባንያ፣ በአሁኑ ወቅት ለግብርና ብቻም ሳይሆን ለትምህርትና ለጤናውም ዘርፍ ጭምር አገልግሎቶቹን በድጎማ ጭምር ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አንዷለም አድማሴ (ዶ/ር) ጠቅሰዋል፡፡ ወረዳኔት በተሰኘው የቴሌኮም የአገልግሎት መረብ አማካይነት ግብርና ዘርፍ በርካታ አካባቢዎችን ተጠቃሚ እንዳደረገ ገልጸዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች