Thursday, July 25, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

በኢትዮ ኤርትራ የሰላም ድርድር በኢትዮጵያ በኩል ለዘላቂ ሰላምና ግንኙነት ሊቀርቡ የሚገባቸው አጀንዳዎች

በዓለሙ ጂማ

በቅድሚያ የከበረ ሰላምታዬን እየገለጽኩኝ ‹‹ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ አዲስ ምዕራፍ›› በሚል ርዕስ ሰኔ 17 ቀን 2010 ዓ.ም. በወጣው ዕትም ላይ ያቀረባችሁትን ትንታኔ አንብቤዋለሁ:: እኔም የኢትዮጵያ ባህር በር ጥያቄ አጅግ በጣም ከሚቆረቁራቸው ዜጎች ውስጥ አንዱ ነኝ:: በእዚህ አጋጣሚ ዕውቁን የኢትዮጵያ ልጅ ያዕቆብ ኃይለ ማርያምን (ዶ/ር) ሳላመሰግን አላልፍም:: በእዚህ ጉዳይ ላይ ጥቂት ማለት የምፍለግገው ነጥቦችን እንደ ሚከተለው ለማቅረብ እፈልጋለሁ:: 

በእዚህ ታሪካዊ ወቅት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጫፍ አስከ ጫፍ ለዴሞክራሲ፣ እኩልነት፣ ፍትሕና ነፃነት እንዲሁም ዜጎች የአገራቸውን ባለቤትነትን ለማረጋገጥ ያላቸውን ቁርጠኝነትና ድጋፍ በግልጽ ያሳወቁበትና ከፍተኛ ተስፋ በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አስተዳደርና ወደፊት ለሚገነቡት ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ሥር ነቀል ለውጦች ሰፊው ሕዝብ አጋርነቱን የገለጸበትና ተስፋ የሰነቀበት ወቅት ላይ እንገኛለን:: በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለረጅም ጊዜ ሳይፈታ የቆየውን የድንበር ውዝግብና ሌሎችም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ የድርድር ጥሪ ለኤርትራ መንግሥት ባቀረቡት መሠረት የኢትዮጵያና የኤርትራ መፃዒ ዕድልና ተስፋ አብሮ የተጣመረና የማይለያይ በመሆኑ ተስፋ ሰጪ ውይይቶች ተጀምረዋል:: ይህም ውይይት ፍሬ ያፈራል ብሎ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ አድርጓአል:: 

የሁለቱ አገሮች የመንግሥት ተወካዮች እስካሁን ድረስ የሰላም ድርድር እንዳያደርጉ ያገዳቸው የአልጀርስ ስምምነት አለመተግበሩ ነው ብሎ ለማመን የሚከብድ ነው:: የሁለቱ አገሮች መሪዎች እስካአሁን ድረስ የባድመ ጦርነትን መቆም ተከትሎ ‹‹ሰላም የለም ጦርነት የለም›› የሚለውን ትርጉም የለሽ የፉክክር ጉዞ ሲሄዱበት የነበረው መንገድ አንዱ ሌላውን ለማጥፋትና ለማክሰር የሚደረግ እሽቅድድም እንጂ ለሁለቱም አገሮች ከፍተኛ የኢኮኖሚና ሞራላዊ ኪሳራ እንዳሳረፈ ለማንም ግልጽ ነው:: 

የአልጀርስን ስምምነትም ሆነ ሌሎች በርከት ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በአዲሱ የሰላም ድርድር ላይ ቁልፍ ሆኖ መነሻና መድረሻው መሆን አለበት ብዬ  አምናለሁ:: መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በኤርትራ ነፃነትና ሉዓላዊነት ምንም ዓይነት ጥያቄና ተቃውሞ የለውም:: ሊኖረውም አይችልም:: ዋናው ቁም ነገር ኤርትራ እንደ አገር ራሷን ችላ ስትገነጠል የኢትዮጵያ አገራዊ ጥቅምና ፍላጎት ሕግና መርሕን ተከትሎ ተፈጽሟል ወይ የሚለው ትልቅ ጉዳይ በድርድር እስካልተፈታ ድረስ ዘላቂ ሰላም በሁለቱ አገሮች መካከል ይኖራል ብሎ ማሰብ አይቻልም:: 

ከእዚህ ጋር በተያያዘ በሚከተሉት አጀንዳዎች ዙሪያ ሰፊ ውይይት እንዲደረግና ኢትዮጵያ በድርድሩ ላይ መያዝ ያለባትን አቋምና የመፍትሔ ሐሳብ በግልጽ ቢቀመጥ መልካም ነው ብዬ አምናለሁ::

  1. ኢትዮጵያ ወደብ አልባ የሆነቸው በፖለቲካ መሪዎች ኢፍትሐዊ ውሳኔና ትብብር እንጂ በእውነተኛ ታሪክና ዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት አይደለም::

1.1 ትራ ስትገነጠል በኢትዮጵያና የኤርትራ ቅኝ ገዢ በነበረችው ጣሊያን መካከል ከ120 ዓመት በፊት በተደረጉ የድንበር ውል ስምምነቶች መሠረት ነው:: እነዚህ ውሎች በተደጋጋሚ የተሻሩና የሞቱ ውሎች ናቸው::

1.2 የአልጀርሱ ስምምነት ከመፈረሙ በፊት በድንበር ይገባኛል በክርክሩ ወቅት የኢትዮ ኢጣልያ የድንበር ውሎችን የሚሽሩና ውድቅ የሚያደርጉ ሌሎች ገዥ ውሎች፣ ስምምነቶችና ዓለም አቀፍ ሕጎች እያሉ በማስረጃነት እንዳይቀርቡ የተደረገና የኮሚሽኑ ውሳኔም ቀድሞ የአገርን ጥቅምና ደኅንነት አሳልፎ የሚሰጥ ውሳኔ እንደሚሆን የተወሰነበት አካሄድ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው::   

1.3 ኢትዮጵያ ወደብ አልባ እንድትሆን ታሪካዊ ኢፍትሐዊ በደል (Historical Injustice) የአገርን ጥቅም አሳልፈው በሚሰጡ የፖለቲካ መሪዎች ትብብር ስለተጫነባት በአገሪቱን ኢኮኖሚ ከፍተኛ ኪሳራ አሳርፏል:: አገሪቱ በዓመት ከምታገኘው አጠቃላይ የውጭ ንግድ ገቢ (ሦስት ቢሊዮን ዶላር አካባቢ) ውስጥ ከሁለት ሦስተኛው በላይ (ሁለት ቢሊዮን ያህል) ለጂቡቲ ወደብ አገልግሎት ወጪ ይሆናል:: ይሄ አሃዝ በየዓመቱ አገር ውስጥ ያለው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እያደገ ሲሄድ እየጨመረ እንደሚሄድ ግልጽ ነው:: እንዲሁም የአገሪቱ ብሔራዊ ደኅንነት በአፍሪካ ቀንድ አጠገብ ያሉ የተለያዩ ዓረብ አገሮች በአካባቢው የሚያደርጉትን ፉክክርና የቡድን ሩጫ ተከትሎ አደጋ ላይ እንዲወድቅ አድርጎታል::

1.4. የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ የአልጀርሱን ስምምነት ውሳኔዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተቀብየዋለሁ ከማለቱ በፊት ኤርትራ ስምምነቱን የሚጥሱ ተግባራትን ፈጽማለች:: የሰላም አስከባሪውን ኃይል ከ25 ኪሎ ሜትር ነፃ ቀጣና (Buffer Zone) ውስጥ አባራለች:: የድንበር ኮሚሽኑም በወረቀት ላይ የተሰመረውን ድንበር (Delineation) መሬት ላይ አውርዶ መሬት ላይ ባለው እውነታ ላይ ተመርኩዞ ቋሚ የወሰን ማካለል ምልክቶች (Physical Demarcation) አላደረገም:: እነዚህ ሁለት ቅድመ ሁኔታዎች ባልተሟሉበት ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግሥት ሙሉ ለሙሉ ስምምነቱን ውድቅ አድርጎ አዲስና የአገሪቱን ጥቅም አሳልፎ በማይሰጥበት መንገድ፣ የታሪክ የሕግና ዓለም አቀፍ ስምምነት ሰነዶችና ማስረጃዎች በሙሉ ቀርበው፣ በኢትዮጵያ በኩል ብቃት ያላቸው ምሁራን የሕግና ታሪክ አዋቂዎች ተወክለው በአዲስ ምዕራፍ መደራደር የሚቻልበት አማራጭ መንገድ እያለ ነው የኢትዮ ኤርትራ አዲስ የሰላም ስምምነት ሊካሄድ የታቀደው::

1.5. ከእዚህ በፊት በሌላ የአገር መሪ ስህተት ወይም ሆነ ተብሎ በተቀነባበረ

ሴራ የተላለፉ የአገርን ጥቅም አሳልፈው የሚሰጡ ውሳኔዎች ዘለዓለም የግድ ተፈጻመሆን አለባቸው የሚል እውነት በእዚህ ዓለም ላይ የለም::

      ለምሳሌ በላቲን አሜሪካ ቺሊና ቦሊቪያ፣ ከብዙ ዓመት በፊት በድንበር ይገባኛል ጥያቄ ጦርነት ውስጥ ገብተው ቺሊ ጦርነቱን አሸንፋ ቦሊቪያ የነበራትን የባህር በር ብታጣም እስካሁን ድረስ በተለያዩ ጊዜያት በሕዝብ ምርጫ የሚመረጡት የቦልቪያ መሪዎችና መንግሥት ጉዳዩን ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ድረስ በመውሰድ የባህር በር ጥያቄያቸውን በማቅረብ እየተከራከሩ ይገኛሉ::

1.6. ኢትዮጵያ የባህር በር እንዳይኖራት የተደረገው በጠመንጃ ኃይል ሥልጣን በያዘ ኃይል ተባባሪነት መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው:: አዲስ በሕዝብ የተመረጠና ውክልና ያለው መንግሥት ከእዚህ በፊት በኢትዮጵያ ሕዝብ ያልተመረጠና ሕጋዊ ተወካይነት (Legitimacy) የሌለው አምባገነን መንግሥት ያሳለፈውን ኢፍትሐዊ  ውሳኔ ተቀብሎ የማስፈጸምና የማስቀጠል ግዴታ የለበትም::

1.7 የአፋር ሕዝብ የቀይ ባህር ቆላማው አካባቢ ነባር ነዋሪዎች (Indigenous People) የሆኑና ከ70 በላይ የሚሆነው በኢትዮጵያ መሬት ላይ የሚገኙት ውሳኔ ሕዝብ ሳይከበርላቸው ወደ ኤርትራ በግድ እንዲካለሉ ተደርገዋል::  

2. አዲሱ የኢትዮ ኤርትራ የሰላም ድርድር ምን ዓይነት አቅጣጫና ስምምነቶች ሊኖረው ይገባል?

2.1. የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በአዲሱ የሰላም ድርድር ላይ መነሻና መድረሻ ሆኖ መቅረብ አለበት ብዬ  አምናለሁ::  ከጎረቤት አገሮች ጋር የኢኮኖሚ ትስስር (Economic Integration) ማድረግ የዓለም ወቅታዊ ሁኔታ የሚፈቅደውና የሚደገፍ ነው:: የኢኮኖሚ ትስስር ማድረግ ብዙ ጥቅሞች እንዳለው ሁሉ የራሱ የሆነ ችግሮችም አሉበት:: ይሄ ስምምነት በማንኛውም ጊዜና አጋጣሚ በአንዱ ወይም በሌላው ወገን በአግባቡ ባለመፈጸምና ተጠያቂነትን በማጉደል እንዲሁም ዴሞክራሲያው አሠራር በደንብ ባልጎለበተበት የአፍሪካ አገሮች ውስጥ በሌላ ሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ተፅዕኖ ሥር ወድቆ ፍትሐዊነት ሳይኖረው በአንዱ ወይም በሌላው አገር ምክንያት ሊቋረጥ የሚችልበት አጋጣሚ እንዳለ መረሳት የለበትም::

2.2. ሁለቱም አገሮች ለአገራቸው ዘላቂ ሰላምና ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ትስስርን ለመፍጠር በሚያመች መልኩ ኢትዮጵያ በትክክለኛ መረጃና ሕጎች ላይ መሠረት አድርጋ እንዳትከራከር አሻጥር ተሠርቶበት የተፈረመውን የአልጀርሱን ስምምነት ወደጎን ትተው በመሬት ላይ ባለው እውነታና የቀድሞ ትክክለኛ ታሪክና ማስረጃዎች ላይ ተመስርተው መስማማት አለባቸው::

2.3. ኢትዮጵያ የባህር በር እንዳይኖራት የተደረገበት ውሳኔ ፈጽሞ ኢፍትሐዊና ከሕግና ከዓለም አቀፍ ስምምነቶች አንፃር ተገቢ እንዳልሆነ የሁለቱንም አገር ተወካዮች ያውቁታል:: መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የአገሪቱ የባህር በር ጥያቄ ታላቅ አገራዊ አጀንዳ መሆኑን የሚያውቁና ፍትሐዊ መልስ እስከሚያገኝ ድረስ አጥብቀው የሚታገሉለት ጉዳይ መሆኑን የኤርትራ መንግሥት ሊያውቀው ይገባል:: በእዚህም ጉዳይ ላይ ቅንነት ካለ የጋራ መግባባትና ፍትሐዊ የሆነ ውሳኔ ላይ መድረስ ይቻላል::

2.4. ኢትዮጵያን የሚያክል ከ100 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ያለው ትልቅ አገር  ከቀይ ባህር በቅርብ ርቀት (ከ60 ኪሎ ሜትር በታች) ላይ ሆን ተብሎ እንዲዘጋ የተደረገበትን ኢፍትሐዊ ውሳኔ ተሸክሞ የሚሄድ አዲስ ትውልድ ይኖራል ብሎ መቀበል ይከብዳል:: በአካባቢው ባሉ ትንንሽ አገሮች ላይ ጥገኛ ሆኖ ጂኦ ፖለቲካና ደኅንነትን ሥጋት፣ ላይ የሚጥል በመሆኑ ይህ ችግር ዘላቂ መፍትሔ እስካላገኘ ድረስ የተዳፈነ እሳት ሆኖ የሚቆይና በማንኛውም ወቅት የሚነሳና በሁለቱ አገሮች መካከል የሚታሰበውን የሰላም ግንኙነት የሚያደበዝዝ ሆኖ ይቆያል:: ለአፍሪካ ቀንድ አለመረጋጋትም ትልቅ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል:: ዘላቂ መፍትሔ መስጠት ወቅቱ የሚፈልገው ጉዳይ መሆኑን የሁለቱም አገር መሪዎች ሊያውቁት ያስፈልጋል::

2.5. የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄን አንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍታት የሁለቱ አገሮች ታሪካዊ ግዴታ ነው:: ሁለቱም አገሮች በግልና በጋራ የራሳቸው ወደቦችን ማስፋፋትና ማሳደግ ይችላሉ፣ የኢኮኖሚ ትስስር በመፍጠር ድንበሮቻቸውን ነፃ ማድረግ ይችላሉ፣ ነፃ የንግድ ቀጠና መክፈት ይችላሉ፡፡ ነፃ ድንበር ከፍተው የሁለቱንም አገሮች ዜጎች በፈለጉበት ቦታ መሥራትና መኖር ይችላሉ:: ሌላው ደግሞ በሒደት ትስስሩን ወደ ኮንፌዴሬሽን በመውሰድ በመርሐ ሕግ ላይ በተመሠረተ መንገድ አብሮ መኖርና ማደግ ይቻላል:::  

2.6. የተለያዩ ተቃዋሚ (ተፎካካሪ) ኃይሎች  በአገር ውስጥም በውጭም ያሉ በኢትዮ ኤርትራ የሰላም ድርድር ጉዳይ ላይ ውይይት ቢያደርጉና የጋራ አቋም ቢይዙ ለመንግሥትና ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በጽሑፍ ቢያቀርቡ መልካም ይመስለኛል:: ለምሳሌ የተባበሩት መንግሥታት፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የአሜሪካና የእንግሊዝ መንግሥት፣ አፍሪካ ኅብረት፣ በኢትየጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ለታሰበው ድርድር ድጋፍ አድርገዋል:: ትልቅ የአገርን ጥቅምና ፍላጎትን የሚወስን ክስተት (ውሳኔ) ከተላለፈ በኋላ ውይይት ከማድረግ በቅድሚያ አገራዊ ግዴታንና ኃላፊነትን መወጣት ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ::

2.7. አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድና ሌሎችም ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣኖች በእዚህ ከፍተኛ አገራዊ ጉዳይ ላይከእዚህ በፊት እንደሚደረገው የመጨረሻውን ውሳኔ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሰበር ዜና ከማሳወቅ ይልቅ ታዋቂ ምሁራንን፣ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት፣ ዓለም አቀፍ ሕግ፣ ታሪክ፣ የአፍሪካ ቀንድ ላይ ጥናትና ምርምር ያካሄዱ ግለሰቦችን በመጋበዝ ሰፊ ውይይት እንዲደረግና ኢትዮጵያ በድርድሩ ላይ መያዝ ያለባትን አቋምና የመፍትሔ ሐሳብ ቢያቀርቡ መልካም ነው ብዬ አምናለሁ::

2.8. ይህ የሰላም ድርድር ውጤቱ መልካም ሊሆን የሚችለው የአልጀርሱ ስምምነትን እንደ መነሻና መድረሻ አድርጎ ሳይሆን ቅንነት በተሞላበት መንገድ የሁለቱ አገሮች የጋራ ዘላቂ ጥቅምና ፍላጎትን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ሲሆን ብቻ ነው:: ሰጥቶ መቀበልን ወይም ሁለቱም ወገን አሸናፊ የሚሆኑበት ሁኔታ (Win win situation) ዓላማ ያደረገ መሆን አለበት::

2.9. የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም የማያስጠብቅ ሌላ አዲስ ስምምነት ከኤርትራ መንግሥት ጋር ፈርሞ ሌላ ታሪካዊ ስህተት ውስጥ ከመግባት ይልቅ ይኼንን አገራዊ ጉዳይ ክፍት አድርጎት ለሚቀጥለው ትውልድ ቢያቆየው ይሻላል:: ይሄ ጉዳይ የአገር ሕልውና ጉዳይ ጋር አብሮ ስለሚያያዝ ክፍት መሆን አለበት:: ጊዜ ይፈታዋል::

2.10. በኢትዮጵያ ያሉ የግል ጋዜጦችም ሆነ ሚዲያዎች ይኼንን ታላቅ አገራዊ ጉዳይ ለሕዝቡ ግልጽ በሆነ መንገድ ታሪካዊና ሕጋዊ ሰነዶችን መሠረት በማድረግ ትንታኔዎችን በማቅረብ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጉዳዩ ለይ ውይይት አድርገው የጋራ መግለጫ እንዲያወጡና ለመንግሥት እንዲያቀርቡ ቢደረግ መልካም ነው::  

2.11. ኢትዮጵያ ኢፍትሐዊ በሆነ ሴራ ያጣችውን የባህር በር ማስመለስ የእዚህ ትውልድ ታሪካዊ ኃላፊነት ነው:: ኢትዮጵያ በክብር ለዘለዓለም ትኑር! እትዮጵያን ፈጣሪ ይባርክ!

      ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው[email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles