Thursday, July 25, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ነጩን ጤፍ ከቀዩ ለመለየት ባጀን

ዕዝራ ኃይለ ማርያም  

ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን የወረረው ከ1928 – 1933 ዓ.ም. ነበር፡፡ ዕድሜውን ለማራዘም የሕዝቡን አንድነት ለማፈራረስ በጎሳ ማለያዩት ዋና ሥራው አድርጎ ነበር፡፡

የኦሮሞ ተወላጆችን ‹‹አማራን ከክልላችሁ አስወጡ›› በማለት ገፋፋቸው፡፡ የጠላት ሥልት ያልገባቸው አንዳንድ ዜጎች አማራዎችን ‹‹መሬታችንን ልቀቁ›› በማለት እስከ መጋደል ደረሱ፡፡ በጄኔራል ጃገማ ኬሎ የትውልድ አካባቢ የሚገኙ ባላባቶች፣ የጃገማ አጎት የሆኑትን ፊታውራሪ አባ ዶዮን በማሳመን አማራን ከአካባቢያቸው ለማስወጣት አሰቡ፡፡ ቀጠሮ ጠይቀው ቤታቸው ስብሰባ ይደረጋል፡፡

      ፊታውራሪ አባ ዶዮ የሰዎቹ አመጣጥ ለምን እንደሆነ ስላወቁ አንድ ኩንታል ሰርገኛ ጤፍ በራፍ ላይ እንዲቀመጥ አደረጉ፡፡ ስብሰባው ሳይጀመር የምሳ ሰዓት ደረሰና ምሳ ለመብላት ቤት ሲገቡ እንግዶቹ ከጤፉ እያፈሱ ወደ ቤት እንዲገቡ ካደረጉ በኋላ ‹‹ነጩንና ቀዩን ለዩልኝ›› ይሉዋቸዋል፡፡ ‹‹ከጤፍ ውስጥ ነጭና ቀዩን እንዴት መለየት ይቻላል? አይቻልም!›› ብለው እጃቸውን አራግፈው ምሳ መጋበዝ ጀመሩ፡፡

      የፊታውራሪ አባ ዶዮ ባለቤት እንግዶቹን ጋብዘው ወጡ፡፡ ከምሳ በኋላ ፊታውራሪ ‹‹የመጣችሁበት ጉዳይ ገብቶኛል፣ አማራን ከክልላችን እናስወጣ፣ አለዚያም እንግደላቸው፣ ለማለት ነው?›› ሲሏዋቸው ‹‹አዎን፣ ጌታችን ሆይ›› ይሏቸዋል፡፡ ፊታውራሪ አባ ዶዮም፣ ጃገማን ‹‹ልጆቼን ጥራልኝ›› ብለው ያዟዋቸዋል፡፡ ጃገማም የአጎታቸውን ልጆች ጠርተው፣ ልጆቹ ወደ ቤት ሲገቡ ‹‹በሉ ልጆቼን አቅርቤላችኋለውና ግደሏዋቸው! ከእዚሁ እንጀምር›› ብለው ይጠይቃሉ፡፡ እንግዶቹም ይደነግጡና ‹‹ልጆችዎን እንዴት እንገድላቸዋለን?›› ይሏዋቸዋል፡፡

      ፊታውራሪ አባ ዶዮም ‹‹አሁን ምሳ ጋብዛችሁ የወጣችው ባለቤቴ አማራ ነች፣ ቅድም ነጩንና ቀዩን ጤፍ ለዩልኝ ስላችሁ የማይቻል መሆኑን ነግራችሁኛል፡፡ በተለይ የሸዋ አማራና ኦሮሞ ከብዙ ዓመታት ጀምሮ የተጋባና የተቀላቀለ ነው፡፡ አሁን በጠላት ግፊት እንዴት ሊለያዩ ይችላሉ? ከእናንተ መካከል ከአማራ ጋር የተጋባ የለምን?›› አሏቸው፡፡ እንግዶቹም ‹‹እኔም ተጋብቻለሁ፣ እሱም ተጋብቷል›› በማለት እርስ በርስ በመተያየት ተግባቡ፡፡ ከዚያን ቀን ጀምሮ ግድያው ቆመ፡፡ የፋሺስት ጣሊያን የመከፋፈል ሴራ ከሽፎ አማራና ኦሮሞ አንድነቱ ሳይፈርስ ጠላት አገራችንን ለቆ ለመውጣት ተገደደ፡፡

      ከላይ የተገለጸው በጣሊያን ወረራ ወቅት በሌተና ጄኔራል ጃገማ ኬሎ ቤተሰብ የተፈጸመ እውነተኛ ታሪክ ነው፡፡ ጣሊያን ኢትዮጵያን ከለቀቀች ከሃምሳ ዓመታት በኋላ ዘረኝነት ‹‹የብሔር ብሔረሰቦች›› መብት በሚል የወርቅ ሽፋን በመንግሥት አቀንቃኝነት ብቅ አለ፡፡

      ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታትም ‹‹አንተ ትብስ፣ አንቺ ትብሽ›› ተባብሎ በሰላምና በፍቅር የኖረውን ሕዝብ ለማበጣበጥ ያልተደረገ ነገርና ያልተሸረበ ሴራ የለም፡፡ ሰላም ደፍርሶ ሕዝብ በደም ጎርፍ ሲጥለቀለቅና በጎጥ አውሎ ንፋስ ሲንገላታ፣ ጊዜንና አጋጣሚን ጠብቀው ከዕልቂት ገበያ ለማትረፍ ኅሊናቸውን በትርፍራፊ የሚያስገዙ የፖለቲካ ደላሎች አልጠፉም፡፡

      በዚህም አንፃር በጎጥ ተከፋፍለን እንደ ሩዋንዳ እንድንጨራረስ ያልተደረገ ነገር አልነበረም፡፡ በአማራ ተወላጆች ሕይወትና ንብረት ላይ በበደኖ፣ በአርባ ጉጉ፣ በጅማ፣ በኢሉአባቦራ፣ በወለጋ፣ በሐረርጌ፣ በአርሲ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጉራ ፈርዳና በሌሎችም አካባቢዎች እየደረሰ ያለው ዘርፈ ብዙ ጉዳት በጣም ከፍተኛ ነው፡፡

      አፈሩን ገለባ ያድርግላቸውና አቶ አበበ ምትኬ በሐረርጌ የበደኖ ከተማ ኗሪ ነበሩ፡፡ በ1984 ዓ.ም. በበደኖ ዕልቂት ሙሉ ቤተሰባቸውን ከነ ሕይወታቸው እንቁፍቱ ገደል ውስጥ ተጥለዋል። ሟቾቹን ወደ ገደሉ ሲወስዷቸው ባለቤታቸው ስለ ደከሙ እዚያው በአንካሴ ወግተው ገደሏዋቸው፡፡ ስድስት ልጆችንና ሚስትን በአንድ ቀን ማጣት የሚያስከትለውን ሐዘንና ሰቆቃ አስቡት፡፡

      በደኖ አካባቢ የኖሩ ሰዎች እንደሚናገሩት፣ አካባቢው በጣም ከመሽተቱ የተነሳ ኬሚካል በመርጨት ለአንድ ሳምንት አስክሬን ሲለቀም ቆይቷል፡፡ አቶ አበበም በሐዘን፣ በብቸኝነትና፣ በጭንቀት፣ ሲብሰከሰኩ ቆይተው ከዓመታት በኋላ አርፈዋል፡፡

      ይህ አሰቃቂ ጭፍጨፋ ሲካሄድ ፊታውራሪ አባ ዶዮዎች ቢኖሩም በቁጥር በማነሳቸውና በደካሞችና ልዩ ተልዕኮ ባላቸው ቡድኖችና ግለሰቦች በመዋጣቸው መርዙ ሳይስፋፋ እንዲቆም አልተደረገም፡፡

      ጎጠኝነት አገራችንን እንደሚበታትን በታያቸው ኢትዮጵያውያን ያልተባለና ያልፈሰሰ ቋንቋ አልነበረም፡፡ አልተማርንበትም፡፡ በአማራ ላይ የተጀመረው ግድያና ማፈናቀል አድማሱን በማስፋት በሱማሌና በኦሮሞ፣ በወላይታና በሲዳማ፣ በጉጂ ኦሮሞ፣ በአኝዋና በኑዌር፣ በሌሎች ብሔረሰቦች መካከል መገዳደሉና መፈናቀሉ ቀጥሎ የእግር ኳስ ውድድር ማካሄድ እስከ ማይቻልበት ደረጃ ደርሷል፡፡

      በማንነቱ የተነሳ የአሰቃቂ ግፍ ሰለባ የሆነው ታዳጊ ወጣት አበጥር ወርቁ መሰለብና የአካሉ መጨፍጨፍ ጎጠኝነት የሰውን አዕምሮ ምን ያህል በጥላቻ እንደሚሞላ አመልካች ነው፡፡ እግዚአብሔር ለታሪክ ትረፍ ብሎት በሕክምና ላይ ይገኛል፡፡ አሐዱ ሬዲዮ ባደረገለት ቃለ ምልልስ ተምሬ ዲያቆን በመሆን የጎዱኝን  ሰዎች ማስተማር እፈልጋለሁ በማለት ተናግሯል፡፡

      የአበጥር የይቅርታ ልብና መንፈስ በኢትዮጵያውያን ልብና መንፈስ መፍሰስ ይገባዋል፡፡  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና አቶ ደመቀ መኮንን ሆስፒታል ድረስ ሄደው ጠይቀውታል፡፡ መንግሥት የሕክምናውን ወጪ እንደሚሸፍን ገልጿል፡፡ ቸርና ማለፊያ ዜና ነው፡፡

      ይህ የዶ/ር ዓብይ የ‹‹መደመርፍቅር›› መርሕ ለዲያብሎስ አምባሳደሮች ርኩስ መንፈስን የሚያስለቅቅ ፀበል ሲሆን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ ሐሴት ነው፡፡ ሃሌ ሉያ!

የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅትም ባደረገው ግምገማ፣ በማፈናቀሉ ተግባር ላይ የተሠማሩ አመራሮችን ከሥልጣናቸው እንዲነሱ ማድረጉን ሰምተናል፡፡

      ‹‹በደምና በታሪክ የተሳሰረ ሕዝብ ከመሬቱ አይፈናቀልም፣ ሁሉም አገሩ ነው›› በማለት ከክልሉ የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆችን ወደ ቀዬያቸው እንደሚመልስ አስታውቋል፡፡ ይህን ጽሑፍ በማዘጋጅበት ወቅት የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ  ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)፣ በባህርዳር ከተማ የተፈናቀሉ አማራዎች ወደ ቀዬአቸው ስለሚመለሱበት ጉዳይ በመወያየት ላይ ናቸው፡፡

      አልፎ አልፎ እንደሚታየው ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ቤተ ፖለቲካውን፣ ቤተ መንግሥቱንና ቤተ ሃይማኖቱን የያዙት ‹‹እኔ ከሌለሁ ነገሩ ሁሉ የውኃ ጉሽ ይሆናል›› እያሉ የሚፎክሩ፣ የበኩር ልጅነት የሚሰማቸው ባለአዱኛ ግብረ በላ የፖለቲካ ኃይሎች ናቸው፡፡ በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያ የሚወረውሩት መርግ የሚያካክል ያልተሞረደ ዘለፋና ስድብ፣ እሽኮለሌና አሉባልታ አሳፋሪ ነው፡፡ እነዚሁ ኃይሎች ኅብረተሰባችንን የሚያገናኘው ማኅበራዊ ክር እንዲበጣጠስ፣ አፋቅሮ የያዘን የሞራል ዋጋ እንዲፈራርስና ፈሪሃ እግዚአብሔር እንዲጠፋ በትጋት ሠርተዋል፣ እየሠሩም ነው፡፡

      እንደ ፊታውራሪ አባ ዶዮ ዓይነት ልሂቃን በመኖራቸው እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ዳግም ሩዋንዳ እንዳትሆን ታድጓታል፡፡  

      ‹‹የእኔና የእኔ ብቻ›› የሚለውና አድማሰ ጠበቡ ዘረኝነት ከስስት ጋር ተጋብቶ ጥላቻን ወልዷል፡፡ ሁሉ ነገር የተጎለጎለ ልቃቂት በመሰለበት፣ የአገር ክብርና እውነት በተቸረቸረበት፣ ሕዝብ በብሔረሰብ ግጭት በታመሰበት፣ ብሔራዊ ብኩርና በተፈተነበትና መንፈስን የሚያቆሽሹ ወጥመዶች በተጠመዱበት ብሔራዊ ኩራታችን በተጎሳቆለበት፣ በሥልጣን መባለግና ዝርፊያ በበዛበት፣ ሕያዋን በሙታን ቀንተን እንባችን ሞልቶ በሚፈስበት ወቅት የደረሱልን ዶ/ር ዓብይ አህመድ ናቸው፡፡ የዶክተሩን የለውጥና የአንድነት ጉዞ ለማደናቀፍ በትጋት የሚሠሩ ፀረ ለውጥ ኃይላት እንዳሉ እንገነዘባለን፡፡

      ባሳለፍነው ሳምንት በሀዋሳ፣ በወልቂጤና በወላይታ ሶዶ ከተሞች በተፈጠረው ግጭትና ሁከት የሰው ሕይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፡፡ ይህን አስመልክቶ ዶ/ር ዓብይ በሰጡት መግለጫ ‹‹ሊያባሉንና ሊያጫርሱን ለተዘጋጁት የቀን ጅቦች ዕድል ልንሰጣቸው አይገባም›› ብለዋል፡፡ ‹‹በቃ›› ልንላቸው ይገባል፡፡ የደማው አካላችን ብቻ ሳይሆን ህሊናችንም ነው፡፡ የሰቆቃ ጠባሳው ዛሬም በህሊናችን አለ፡፡

      በአገራችን በየትም ቦታና ጊዜ የማንኛውም ብሔረሰብ ሕዝብ የሌላውን ሕዝብ አይጎዳም፡፡ ከሠላሳ ዓመታት በፊት የቀረበው የፀጋዬ ገብረመድኅን ድንቅ ቴአትር የሆነው ‹‹ኦቴሎ›› ዛሬም ፊቴ ድቅን ይላል፡፡ እኩይ ገጸ ባሕርይ የሆነው ኢያጎ ‹‹ቅን፣ የዋህና ገራገር መስሎ እንኳን ሰውን ሰይጣን አስቷል አሉ›› የሚለው ንግግሩ የሴራና መሰሪ ፖለቲከኞች ትክክለኛ ሥዕል ይመስለኛል፡፡ ይህ ታሪካዊ ጊዜ ሊያመልጠን አይገባም፡፡

      ዶ/ር ዓብይን ለመደገፍ ጊዜው አሁን ነው፡፡ አገራችንን የሚያድነው የዶ/ር ዓብይ የ‹‹መደመርና ፍቅር›› መርሕ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህን መርሕ ለመደገፍም ኢትዮጵያዊ መሆን ብቻ በቂ ነው፡፡

      ዛሬም ፊታውራሪ አባ ዶዮን የመሰሉ ትሁት ፖለቲከኞች ያስፈልጉናል፡፡ የለውጥ ኃይሉን ለማደናቀፍ ለሚያሴሩ መሰሪዎችና በሴራቸው ተጠልፈው ለወደቁ ወገኖቻችን ከሰርገኛ ጤፍ ውስጥ ነጭና ቀዩን እንዲለዩ በፍቅር እንጋብዛቸው፡፡ አገሬ ሆይ! እስከ መቼ ነጩን ጤፍ ከቀዩ ለመለየት እንባጃለን? የፊታውራሪ አባ ዶዮ አፅም እሾህ ሆኖ አይወጋንምን? እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

            ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles