Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እንመራረቅ እንጂ!

ሰላም! ሰላም! እንደምን ከርማችኋል የተወደዳችሁ የዚህ ዘመን ዕንቁዎች! ቤት ሠፈር ቀዬው ሰላም እንደሆነ ሳላበስራችሁ አላልፍም፡፡ ሰሞኑን ባሻዬ፣ ‹‹እንግዲህ ለአገር የሚበጅ፣ ለትውልድ የሚጠቅም ሲከናወን እኛም ዕገዛ ማድረግ አለብን፤›› ያሉትን አድንቄያለሁ፡፡ ‹‹ይኼ ልጅ ብቻውን በምን አቅሙ? እኛ ደግፈነው ካልቆምን እንዴት ይሆናል?›› በማለት የአገር ዘብ ነኝ የሚል አስተያየት ይዘው ብቅ ብለዋል፡፡ እሳቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ነገር እንቅልፍ እንደነሳቸው ነው ያለው፡፡

ሰሞኑን ሥራ እየበዛ ነው፡፡ የመሬትና የመኪና ዋጋ ሲንር ብቻ ሳይሆን፣ የምንም ነገር ዋጋ ጨመረ ሲባል ሰዎች እጃቸውን ወደ ደላላ ይጠቁማሉ፡፡ እርግጥ ነው ሕገወጥ ደላሎች አይጠፉም፡፡ ዳሩ ግን ጥሬውን ከበሰለው፣ የተበላሸውን ደግሞ ከደህናው መለየት የአባት ነው፡፡ ከራሱ ጥቅም በላይ ማሰብ የተሳነው ደላላ መቼም አይጠፋም፡፡ የሰፊውን ሕዝብ ተጠቃሚነት የማይፈልግ ስንት ራስ ወዳድ ደላላ አለ መሰላችሁ? ኧረ ተውኝ አናንተ፡፡ ስንቱን ጣጣ ችለን እኮ ነው የኖርነው?

ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹መንግሥት ዶላር የሚያበቅል ዛፍ ካልተከለ በቀር የዶላር እጥረቱን ሊያረግበው አይችልም፤›› በማለት ላነሳው ሐሳብ ባሻዬ ደግሞ፣ ‹‹እንግዲህ ዕድሜ ይስጥህና ታየዋለህ፤›› ብለው የመለሱለት አይረሳኝም፡፡ እሱም እንደ አባቱ አይደል? ‹‹አብረን የምናየው ይሆናል፤›› አላቸው፡፡ ማን ነበር ‹ጠብ ሲል ስደፍን . . . › እያለ አሳሩን ሲያይ ሰነበተ የተባለው?

ባሻዬም የዋዛ አይደሉም፡፡ ‹‹የቴሌና፣ የአየር መንገድ አክሲዮን ከነዳጅ ጋር ተዳምሮ ሲሸጥ ያን ጊዜ ለጎረቤት ሳይቀር የምናበድረው ዶላር ይኖራል፡፡ ታዲያ ዶላር የሚያፈራ ዛፍ ተከልን ማለት አይደል?›› ብለው መለሱለት፡፡ የመልስ ምት ማለት ይህም አይደል? ‹ከሳሽ የተከሳሽን መልስ ቢያውቅ ኖሮ ፍርድ ቤት አይሄድም ነበር› ማለት አሁን ነው፡፡  

ውዷ ማንጠግቦሽ፣ ‹‹ዕድሜ ለኢቲቪ! የማረሚያ ቤቱ ጉዳይ ፍርድ አገኘ፤›› እያለች ሰሞኑን የኢቲቪን ሚና እያሞካሸች ነው፡፡ በዚህ ብቻም አላበቃች፡፡ ‹‹አሁን ነው መታሰር . . . ›› ብትለኝ የድንጋጤ ሳቅ አመለጠኝ፡፡ እንሳቅ እንጂ ምን ይባላል ታዲያ? ባሻዬ ደግሞ፣ ‹‹ኢትዮጵያ የመቶ ሚሊዮን ፖለቲከኞች አገር ሆናለች፡፡ ሁሉም በየጓሮው፣ በየቡና መጠጫው እየቦተለከ ነው፤›› እያሉ ቀለዱ፡፡ ልጃቸው ተቀብሎ፣ ‹‹ሁሉም ጸሐፊ! ሁሉም ዓምደኛ! ሁሉም የአገር ጉዳይ ተንታኝ ሆኗል፤›› በማለት አጀባቸው፡፡ ‹‹ተመሥገን ነው ቢያንስ በመጻፍ በአገሩ ጉዳይ ላይ ተሳታፊ ይሁን እንጂ፤›› በማለትም ቀጠለ፡፡ ልክ ነው፡፡ ‹የሚጽፉ እጆች የተባረኩ ናቸው› አይደል የሚባለው?

‹‹ኢትዮጵያዊ መቼ አገሩን ጠልቶ ያውቅና ነው? በተለያዩ ዘመናት የነበሩ ኢትዮጵያውያን አገር ወዳድና ለአገር ሟች እንደነበሩ ማንም የሚያውቀው ነው፡፡ እነሆ ዘንድሮም ያ ታሪክ ተደገመ፤›› እያሉ ባሻዬ በኩራት ሲናገሩ፣ እኔም ትንሿን የራሴን ሐሳብ እያውጠነጠንኩ በደስታ ተጥለቀለቅኩ፡፡ ደላላ ኩራት ባይኖረው ደስታ ይጎለዋል እንዴ?

የባሻዬ ልጅ ሁልጊዜም የማይሆን ሐሳብ የሚሰነዝር የእኔ ቢጤ ሲያጋጥመው፣ ‹‹ሸኙት! ሸኙት!›› ይላል፡፡ እንግዲህ እሱ ሸኙት ብሎ ከተናገረ አንዳች መሰሪ ነገር ሲያደርግ አስተውሎታል ማለት ነው፡፡ በዚህ ዘመን ደግሞ ጭንቅላታቸውን ለሰይጣን ያኮናተሩ ሴረኞች በየቦታው እንደ እንጉዳይ ስለፈሉ፣ ደግ ደጉን ብቻ ስናስብ ጠልፈው እንዳይጥሉን፡፡ በፍየል ዘመን በግ መሆን ጅልነት ነዋ! አይደለም እንዴ?

ባሻዬ ዘንድሮ አልተቻሉም፡፡ ‹‹በሚስጥር አገርን የሚያፈርስ ድርጊት ውስጥ የተሳተፉን ሁሉ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ይሸኙልን፤›› ሲሉ ለሰላማዊ ሠልፍ የተዘጋጀ የሚመስል መፈክር ተናገሩ፡፡ የቤታችን ፖለቲካ ተንታኝ የሆነችው የእኔዋ ማንጠግቦሽም፣ ‹‹እንዲያው መሪያችን ምሕረትንና ይቅርታን በጥብጠው ስለጋቱን ነው እንጂ፣ መሰሪዎቹን ሰብስቦ አንድ አንድ ባልዲ ውኃ ነበር ማጠጣት፤›› ብላ የተናገረችውን ነገር ሰምቼ ደነገጥኩ፡፡ አንድ ባልዲ ውኃ እንኳንስ ተጠጥቶ ለሸክም እንዴት እንደሚከብድ የሚያውቅ ያውቀዋል፡፡

አንድ ወዳጄ የጠቅላያችንን ጎዞ በመቃወም ጥቂት የማይባሉ ሰላማዊ ሠልፍ ሊወጡ እንደሚችሉ ነገረኝ፡፡ እኔም በግርምት ውስጥ ሆኜ፣ ‹‹እንዴ ለምንድነው የሚቃወሙት? መቼም በዚህ ዘመን ጠቅላያችንን የሚቃወሙት ጥቅማቸው የተነካባቸው ናቸው እየተባለ ነው . . . ›› ብዬ የሰማሁትን ብቻ ብነግረው ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? ‹‹በፖለቲካ ምክንያት ‹አሳይለም› የጠየቁ ሁሉ ጠቅላያችን ያወረደው ሰላምና መረጋጋት የእግር እሳት ሆኖባቸዋል፡፡ ስለዚህ ጥፋልን . . . ›› እያሉ ሰላማዊ ሠልፍ ሳይወጡ አይቀርም እያለ ሲቀልድ ሕልም እየመሰለኝ ነበር፡፡ ለካ አልተኛሁም፡፡  

‹‹አንድ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆነ በአሜሪካ የሚኖር ጠበቃ ‹አሳይለም› እንዲያገኝ ጉዳዩን እየተከታተለለት ያለ ኢትዮጵያዊ የፌስቡክ ‹ፕሮፋይሉን› የጠቅላዩን ፎቶ አድርጎ ተመልክቶ፣ ብለህ ብለህ የጠቅላዩን ፎቶ ለጥፈህ ጠበቅኸኝ?›› ብሎ ተበሳጨበት ብሎ የነገረኝም ይኼው ጓደኛዬ ነው፡፡ ምስኪኑ ምንም እንኳን ‹አሳይለሙ›ን ቢፈልገውም በሌላ ወገን ደግሞ የዓብይ ፍቅር ጠፍሮ ይዞት ነው፡፡ ‹ምን ታረጊዋለሽ?› የሚለው ዘፈን አለማርጀቱን የምናውቀው እኮ እንዲህ ዓይነቱን ጉድ ስንሰማ ጭምር ነው፡፡

ይኼው ጓደኛዬ፣ ‹‹ከዚህ በኋላ አሜሪካ አገር ሄደው ‹አሳይለም› ማግኘት ከፈለጉ ብቸኛው መንገድ የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂ ነኝ ማለት ብቻ ነው . . . ›› በማለትም አስፈግጎኛል፡፡ ‹‹ከዚህ በኋላ የመንግሥት ባላንጣዎች ሁሉ ጦራቸውን አስቀምጠው ወደ አገር ቤት እየተመለሱ፣ ከመንግሥት ጋር ተጣላሁ ቢባል ትራምፕ ክትክት ብሎ ነው የሚስቀው፤›› እያለም ሲቀልድ ነበር፡፡ ዘንድሮማ ሁሉም ቀልደኛ ሆኗል፡፡ ቀልድ በጎመዘዘበት ዘመን በግድ እንሳቀው እንጂ፡፡

የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ብዙ ሚሊዮን ዶላር አፋፍሰው እንደሚመጡ አትጠራጠር፤›› በማለት አባቱ ቅድም የተናገሩትን ለመደገፍ ሞከረ፡፡ ይኼን ጊዜ ባሻዬ ፊታቸው በደስታ በርቶ፣ ‹‹ባሻዬ ምን አለ በለኝ፡፡ እንኳንስ ውጭ አገር ሄደው ቅስቀሳ አድርገው ቀርቶ፣ ገና ደመወዝ በዶላር ሲከፈል በዓይናችን እንመለከታለን፤›› እያሉ ሕልማቸውን ተናገሩ፡፡

ይኼን ጊዜ ልጃቸው፣ ‹‹ነዳጅ ሸጠን ዶላር፣ ቴሌን ሸጠን ዶላር፣ አየር መንገድን ሸጠን ዶላር፣ ቤተ መንግሥቱን ወደ ሙዚየም ለውጠን ዶላር፣ ከሳዑዲ ዓረቢያ ዶላር፣ ከአሜሪካ ዶላር . . . ሰብስበን . . . ሰብስበን ግድባችንን እንገነባለን፡፡ የጦር ኃይላችንን እናጠናክራለን፡፡ የደመወዝ ጭማሪ እናደርጋለን፡፡ ዳግም ኢትዮጵያን ታላቅ እናደርጋታለን፡፡ ያለን አንድ አማራጭ ይህ ብቻ ነው፡፡ ዶላሬን የት ልጣለው የምትል ታላቂቱን ኢትዮጵያ መገንባት . . . ›› እያለ በአንዴ በሀብት ሲያንበሸብሸን ማንጠግቦሽ በደስታ ጮቤ መርገጥ ጀመረች፡፡

ይኼን ጊዜ ባሻዬ ተቀበሉትና፣ ‹‹እኛ ኢትዮጵያዊያን በዶላር ሸጠን በዶላር የምንገዛበት ዘመን አክትሞ፣ የዶላሩን ፏፏቴ እዚህ እንደምናደርገው አትጠራጠር፤›› ብለው ፈገግ አሉ፡፡ ልጃቸው ደግሞ፣ ‹‹መቼም ጥቁር ገበያ የሚባለው የዶላር ቤርሙዳ አለቀለት እያልከኝ ነው?›› በማለት ጥያቄ አቀረበላቸው፡፡ ሆኖም ይኼ ለእኔም ግልጽ አልነበረም፡፡ የወሬ ጥማቴን ዓይቶ እንዲህ ሲል አብራራልኝ፡፡

‹‹ጠቅላዩ በቅርቡ አሜሪካ የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ዶላሮቻቸውን በባንክ እንዲልኩ አግባብተዋቸው ነው የሚመጡት፡፡ ለመቶ ዶላር ያላቸውን ዋጋ ባለፈው በአርቲስቶች ስብሰባ ላይ ተመልክተናል፡፡ ስለሆነም መቶ ዶላርም ብትሆን በሕጋዊ መንገድ የምትላክበትን የጋራ መግባባት ቀይሰው እንደሚመጡ ምንም ጥርጥር የለኝም፤›› ሲለኝ ሐሳቡ ገባኝ፡፡ ቀጥሎም፣ ‹‹ይህንን ስል ባለሥልጣናቱና ባለሀብቶቹ የደበቁትን ይዘነጋሉ ለማለት እንዳልሆነ ልብ ይባልልኝ፤›› ሲል የጠቅላዩ ዋና አማካሪ መሰለኝ፡፡ 

እንግዲህ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ለጠቅላያችን መልካሙን ሁሉ እየተመኘሁ ጉዞ ላለባችሁ፣ በተለይ በተለያዩ አገሮች ‹አሳይለም› ጠይቃችሁ ጉዳያችሁ ለፈረሰባችሁ ሁሉ፣ እንግዲህ ያለው አማራጭ ወደ አገር ቤት መመለስ ነው፡፡ ለሚሄደው መልካም ጉዞ፡፡ ለምትመጡት እንኳን ደህና መጣችሁ እላለሁ፡፡ ዘመኑ የመደመር ነው ከተባለ የእምዬ ኢትዮጵያን ጉዳይ አንድ ላይ እንደመርበት፡፡ ‹መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ› እየተባባልን ከምንለያይና ከምንረጋገም፣ ተደምረን ብንመራረቅ ምን ይለናል እላችኋለሁ፡፡ እስቲ እንመራረቅ! መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት