Thursday, May 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ለነጋዴው ጥያቄዎች የተግባር ምላሾች

ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ በርካታ ፖለቲካዊና አኮኖሚያዊ ማሻሻያዎች የተደረጉባቸውና ወደፊትም የሚደረጉባቸው ጉዳዮች የትኞቹ እንደሚሆኑ ሲገለጽ ሰምተናል፡፡

መንግሥት የሚለው እንዳለ ሆኖ፣ ከኅብረተሰቡም መንግሥት ሊያሻሽላቸው ይገባል የተባሉ ጉዳዮች ከአቅጣጫው እየተሰነዘሩ ነው፡፡ አድማጭ ከተገኘ እንዲህ ሊሆን ይገባል፣ እንዲህ ሊደረግልን እንፈልጋለን የሚሉ ሌላም በርካታ ጥያቄዎች መቅረባቸው አይቀርም፡፡

ሌላውን ትተን እንደ ምሳሌ የፋይናንስ ዘርፉን የተመለከቱ ጉዳዮችን እንጥቀስ፡፡ አገራዊ ኢኮኖሚውን ለማጎልበት የሚያስችለውን የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ለመቀየር መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ ጀምሮ የመንግሥት የፋይናንስ ተቋማትን ጊዜው በሚጠይቀው የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ ድጋሚ ያዋቅራቸው፣ የፋይናንስ ፖሊሲውን ይኑረው፣ ካለውም ይለውጥ፣ ያሻሽል የሚሉ ሐሳቦች ከተለያዩ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እየሰነዘረ ነው፡፡

የዘርፉ ተዋናዮችም ለአገር የሚጠቅም ሥራ ለመሥራት መደረግ አለበት ያሉትን ሐሳብ ሲያቀርቡ ሰምተናል፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን፣ በወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎችም የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንዲሻሻል ከተፈለገ የመንግሥት አሠራር መስተካከል አለበት ብለዋል፡፡ የንግዱ ኅብረተሰብም በጋራና በተናጠል የብድር አሰጣጥ ሥርዓቱ መስመር ይያዝልን የሚሉትን ጨምሮ ሌሎችም ሊስተካከሉ ይገባቸዋል ያላቸውን ጉዳዮች በማንሳት ጥያቄዎቹን ሲያቀርብ ተደምጧል፡፡

የተሻለ አገልግሎት ለማቅረብ ካሰበ መንግሥት ከንግድ ሥራ ይውጣ፣ የግል ዘርፉ ይነግድበት የሚል ሙግትም ቀርቧል፡፡ በተለይም ፍትሐዊ የውድድር ሜዳ ይኑር የሚለው ጥያቄ ከንግዱ ኅብረተሰቡ ብቻም ሳይሆን፣ ከምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች በኩልም እየቀረበ ይገኛል፡፡ የጉምሩክ አሠራር በአግባቡ ካልተስተካከለ በቀር ለውጥ አይታሰብም የሚል ሐሳብም ተነስቷል፡፡ ጥሩ ግብር እንዲሰበሰብ ከተፈለገ የገቢዎችና የጉምሩክ አሠራሮች ይስተካከሉ የሚሉ ሙግቶችም ተስተናግደዋል፡፡

የመሬት አቅርቦት ጉዳይ ምሬትን ሲያስነሳ በመቆየቱ፣ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርን በግንባር ያገኙ የንግዱ ኅብረተሰብ አባላት፣ ጠጣር ቃላትን በመጠቀም ጭምር የመሬት አሰጣጥ ሥርዓቱ መስመር እስካልያዘ ድረስ ሠርተን አገር መጥቀም አንችልም በማለት መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

በጥቂት ወራት ውስጥ እንዲህ ያሉ ከየአቅጣጫው የተወረወሩት ጥያቄዎች በአግባቡ ምላሽ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ አንዶንዶቹን ለማስተካከል እንደ ሙከራ  አቅጣጫዎች ተሰጥቶባቸው እየተመከረባቸው ነው፡፡ ሌሎችንም አዎንታዊ ምላሽ እንዲያገኙ የሚደረግ መሆኑንም ያደመጥንባቸው መድረኮች አሉ፡፡ ለውጥ ሊደረግባቸው በሚገባው ልክ ይህን አይሁን ማወቅ ባይቻልም የማሻሻያ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ የተሠሩ ያሉ ሥራዎችም ስለመኖራቸው ይነገራል፡፡

ከእነዚህ ጥያቄዎች ባሻገር ግን በተለይ ከንግዱ ኅብረተሰብ የቀረቡ አቤቱታቸው አግባብ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እነሱስ የሚጠበቅባቸውን እየተወጡ ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፡፡

ለሥራችን እንቅፋት ሆነብን ብለው እንዲስተካከልላቸው ያቀረቡት ጥያቄ ቢመለስ ምን ያህል ተገልጋዮቻቸውን ለመጥቀም ተሰናድተዋል? ጥቂት የማይባሉት በእስካሁኑ አገልግሎታቸው በንፅህና ያለመሥራታቸው ይታወቃልና ይደረግልን እንዳሉት ሁሉ ከእነሱም እንዲሟላ የሚጠበቀው ግዴታ መፈጸም አለበት፡፡ 

መንግሥት ይኼንን ያደርግልኝ ከሚለው ጥያቄ ጎን ለጎን እኛ አገልግሎታቸውን ለሚሹና ለሸማቾቻቸው ምን እያሰቡ እንደሆነ እንኳን አንድም ጊዜ አለመስማታችን ነው፡፡

ዛሬ በግብይት ውስጥ የሚታየው ሥርዓት አልበኝነት ያላግባብ ዋጋ መቆለልና ሸማችን ምርር እያደረጉ ያሉ ነጋዴዎች መንግሥት ይኼንን ያድርግልን ከሚሉ ጠያቂዎች መካከል ይገኙበታል፡፡ የፋይናንስ ፖሊሲ ይስተካከል የሚሉ የባንክ ባለሙያዎች አሁንም ለውጭ ምንዛሪ ጠያቂዎች ዶላር ፈርቅ እየሰጡ ነው የሚለው ወሬ ከተሰማባቸው መንግሥት የቱንም ያህል ፖሊሲውን ቢያሻሽል እነርሱን ለማበርታት የሚወሰደው ውሳኔ ተገልጋዩን ካልጠቀመ ትርጉም የለውም፡፡

የውጭ ምንዛሪ እጥረት ገጠመኝ እያለ የሚያማርር ነጋዴ ወረፋም ጠብቆ ያገኘው ዶላር ተጠቅሞ የሚያስወጣውን ዕቃ እዚህ ለሸማቹ ሲያቀብል ምን ያህል የትርፍ ድርሻ ይዞ እንደሆነ ከተጠና በንግዱ ኅብረተሰብም ለውጥ ሊያደርግባቸው የሚገባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡

የዋጋ ግሽበት አላሠራ አለን የሚሉና የዋጋ ማካካሻ የሚጠይቁ ኮንትራክተሮች ጥያቄያቸው የቱንም ያህል ትክክል ቢሆን ጥራት የሌለው ግንባታ እየገነቡ መንግሥት ይኼንን ያድርግልን ሲሉ እኛስ ምን እየሠራን ነው ብለው ራሳቸውን ጠይቀው ካልታረሙ ማስተካከያ ይደረግልን ማለት ሊከብድ ይችላል፡፡ እንዲህ ያለ አሠራር መዘርጋት አለበት መንግሥት ሊደግፈን ይገባል ከተባለ ድጋፉ የአንድ ወገን ጥቅምን ብቻ በማየት የሚወሰን አይደለም፡፡

ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረ የንግድ ኅብረተሰቡ ሸማቹንና ተገልጋዩን ሊያገለግል የሚችል አሠራር መፍጠር አለባቸው ማለት ነው፡፡ ለዚህ ኢንቨስትመንት ተብሎ ብድር የተለቀቀለት ደፋር ነጋዴ ብድሩን ባገኘ ማግሥት ዱባይ ላይ ከተሽከርካሪ ብዙ ሠራተኛ ይቀጥርበታል የተባለ ፕሮጀክት ተቀጬ እንደማለት ነው፡፡ ስለዚህ በምንጠይቀው ልክ እኛም የሚሠራውን ሥራ በአግባቡ መከወኑን የሚያረጋግጥ መመዘኛ ሊኖረው ይገባል፡፡ እንዲህ ባለው ነገር የምንተቻቸው ጥቂት የማይባሉ ነጋዴዎች በሚሠሩት ስህተት ደግሞ በአግባቡ ለመሥራት የሚፈልገውንም የሚጐዱ መሆኑ ደግሞ የበለጠ ያማልና ፖሊሲዎች ይለወጡ ሲባል ለተሻለ አገልግሎት ብሎም ታች ያለውን ተገልጋይና ሸማች ለመጥቀም ጭምር ነውና የንግድ ኅብረተሰቡ አመለካከት ይቀየር የግብይት ሥርዓታችንም መስተካከል ይኖርበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ የንግድ ኅብረተሰቡን የሚወክሉ እንደ ንግድ ምክር ቤት ያሉ በተለያዩ ዘርፎች አባላትን ይዘው የሚንቀሳቀሱ ማኅበራት ይኼንን ጉዳይ እንደ አንድ የሥራ ድርሻቸው መመልከት አለባቸው፡፡ እነሱም የንግድ ኅብረተሰቡ እንዲህ ይደረግለት ሲሉ ገበያን የሚያተረማምሱ ያላግባብ ገበያውን የሚያጋግሉትን አካሎቻቸውን መግራት ያስፈልጋል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት