የኢትዮጵያ አየር መንገድ ራዕይ 2025 የተባለውን የ15 ዓመት የዕድገት መርሐ ግብር ቀርጾ ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረ እ.ኤ.አ. 2010 ጀምሮ ባሉት ስምንት ዓመታት ውስጥ በሦስት እጥፍ አድጓል፡፡ ከስምንት ዓመታት በፊት ከአፍሪካ አራተኛ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኬንያ፣ የደቡብ አፍሪካና የግብፅ አየር መንገዶችን ቀድሞ ከአፍሪካ በአውሮፕላን ቁጥር፣ በመንገደኞች ብዛትና በትርፋማነት ቀዳሚ አየር መንገድ እንደሆነ የዓለም አቀፍ አየር ትራንስፖርት ማኅበር መስክሮለታል፡፡ ይህ ውጤታማ ተቋም በከፊል ለግል ይዞታ ክፍት እንደሚደረግ በቅርቡ ይፋ ተደርጓል፡፡ በዚህና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ቃለየሱስ በቀለ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፉት ስምንት ዓመታት የ15 ዓመታት የዕድገት መርሐ ግብር ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት አየር መንገዱ ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ ላይ እንደሆነም ይታወቃል፡፡ ዋና ዋና ያሳካቸው የ2025 ግቦች ምንድናቸው?
አቶ ተወልደ፡- ራዕይ 2025ን ስናቅድ በጣም የተለጠጠ ዕቅድ ነው በማለት አስተያየቶች ይሰጡ ነበር፡፡ በተለይም በአቪዬሽን መስክ አተኩረው የሚሠሩ ታዋቂ የአቪዬሽን ሚዲያዎች ደጋግመው ይጠይቁን ነበር፡፡ ዓለም አቀፍ የኢቪዬሽን ኢንዱስትሪ በአራትና በአምስት በመቶ ነው የሚያድገው፡፡ አሁን ጥሩ በሚባልበት ወቅት ስድስት በመቶ እያደገ ነው ያለው፡፡ እኛ በ2025 በአማካይ ከ25 እስከ 30 በመቶ ዕድገት ነበር ያሰብነው፡፡ ይህ ለዓለም አቀፍ አቪዬሽን ኢንዱስትሪ እንግዳ ነው፡፡ ለዚህ ነው ይህ የተለጠጠ ዕቅድ ነው፣ ሊደረስበት የማይችል ነው፣ አንዳንዶቹም የቀን ቅዠት ነው ሲሉ የነበረው፡፡ እኛ ግን እርግጠኞች ሆነን ነው የጀመርነው፡፡ ነገር ግን እጅግ በጣም ጥሩ በሚባል ሁኔታ እያጠናቀቅን ነው ያለው፡፡ በ2025 ዕቅድ ስምንት ዓመት ተጉዘናል፣ ገና ሰባት ዓመታት ይቀሩናል፡፡ የስምንት ዓመታት ጉዟችንን ያየን እንደሆነ በየዓመቱ ካስቀመጥናቸው ግቦች ሁሉንም አልፈናቸዋል፡፡ በቅርቡ ወደ ጄኔቫ ስዊዘርላንድ በረራ ጀምረናል፡፡ በአሜሪካ አራተኛ መዳረሻ ወደ ቺካጎ ከፍተናል፡፡ እንዲሁም 100ኛ አውሮፕላችንን ተረክበናል፡፡ ወቅቱ ለአፍሪካ አየር መንገዶች ከባድ ጊዜ ነው፡፡ ብዙ የአፍሪካ አየር መንገዶች ኪሳራ ውስጥ ናቸው፡፡ በድምሩ የአፍሪካ አየር መንገዶች 500 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ አስመዝግበዋል፡፡ በአንድ ወቅት በዓመት አንድ ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ አስመዝግበዋል፡፡ በዚህ ምክንያት የበረራ መስመሮችን እያጠፉ አውሮፕላኖቻቸውን እያከራዩ፣ በአጠቃላይ የአፍሪካ አየር መንገዶች እየቀነሱ ነው ያሉት፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻውን ሊያድግ የቻለበት ምክንያት ምንድነው? የሚል ጥያቄ በየሄድንበት የአቪዬሽን ጉባዔ ላይ ይቀርብልናል፡፡
ሪፖርተር፡- የዕድገቱን መጠን በአኃዝ ቢገልጹልን?
አቶ ተወልደ፡- በ2025 የአውሮፕላኖቻችን ብዛት 120 ይደርሳል ብለን ነው የተነሳው፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት መቶኛ አውሮፕላናችንን ተቀብለናል፡፡ አንድ መቶ አውሮፕላኖችን በአፍሪካ ደረጃ በምንመለከትበት ጊዜ በጣም ብዙ ናቸው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የሚከተለው የግብፅ አየር መንገድ 70 አውሮፕላኖች ነው ያሉት፡፡ ሦስተኛ ደረጃ ያለው የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ 60 አካባቢ አውሮፕላኖች አሉት፡፡ በአራተኛ ደረጃ የሚገኘው የኬንያ ኤርዌይስ 40 አካባቢ ነው ያሉት፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአንድ መቶ አውሮፕላኖች ባለቤት መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከተፎካካሪዎቹ ጋር ያለው ልዩነት ሰፊ ነው፡፡ በዚህ ሳምንት የቦይንግ ኩባንያ አዲስ ምርት የሆነውን ቢ737 ማክስ አውሮፕላን ተረክበናል፡፡ በሚቀጥለው በጀት ዓመት 20 አውሮፕላኖችን እንረከባለን፡፡ ስለዚህ እ.ኤ.አ. በ2019 የ2025 ዕቅድን እናሳካለን ማለት ነው፡፡
በመንገደኛ ቁጥር የተመለከትን እንደሆነ 18 ሚሊዮን እንደርሳለን ብለን ነው የተነሳነው፡፡ በዚህ ዓመት 11 ሚሊዮን እንደርሳለን፡፡ የመዳረሻ ብዛት ግን አስገራሚ ነው፡፡ በ2025 ዓለም አቀፍ የመዳረሻ ብዛት 90 እንደርሳለን ብለን ነበር ያቀድነው፡፡ አሁን ግን 112 ደርሰናል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2010 ስንነሳ ገቢያችን 1.3 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ዛሬ ሦስት ቢሊዮን ዶላር አልፏል፡፡ በአጠቃላይ አየር መንገዱ የራዕይ 2025 የዕድገት መርሐ ግብር መተግበር ከጀመርንበት እ.ኤ.አ. 2010 በሦስት እጥፍ አድጓል፡፡ በስምንት ዓመታት በሦስት እጥፍ ማደግ ማለት በኢንዱስትሪው ላሉ ሰዎች አስገራሚ ነው፡፡ ይህ የሆነው አየር መንገዱ ትርፋማ ሆኖ በራሱ ተበድሮ ብድሩን እየከፈለ የመጣ በመሆኑ መንገድ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2010 በፊት አውሮፕላን ለመግዛት የብድር ጥያቄ በምናቀርብበት ወቅት ጥቂት ባንኮች ነበር የሚቀርቡት፡፡ ብድር የምንበደረው አጫርተን ነው፡፡ አሁን የብድር ጥያቄ ስናቀርብ ከ20 በላይ ታዋቂ ዓለም አቀፍ ባንኮች ይወዳደራሉ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ገናና ስም አለው፡፡ ጠንካራ የሒሳብ መዝገብ አለው፡፡ የብድር ታሪኩ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ትልቁ ኢኮኖሚ ባትሆንም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀዳሚ አየር መንገድ ሆኗል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2010 ግን አራተኛ ነበር፡፡ በሌላው ዓለም ያለን ስምና አድናቆት ከፍተኛ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ፣ በአጠቃላይ የጥቁር ሕዝቦች ኩራት ሆኗል፡፡ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ልንኮራበት ይገባል፡፡
ሪፖርተር፡- አየር መንገዱ መቶኛ አውሮፕላኑን በቅርቡ ተረክቧል፡፡ አንድ መቶ አውሮፕላኖች ለአየር መንገዱ ምን ማለት ናቸው?
አቶ ተወልደ፡- አንድ መቶ አውሮፕላኖች ለአየር መንገዱና ለአገሪቱ ምን ማለት ናቸው ብለን በምናይበት ጊዜ፣ የአውሮፕላኖቹ ብዛት ብቻ ሳይሆን እጅግ ዘመናዊ አውሮፕላኖች መኖራቸውን መመልከት አለብን፡፡ እንደ ቦይንግ 787 ድሪምላይነር፣ ኤርባስ ኤ350 እና ቦይንግ 737 ማክስ እጅግ ዘመናዊና አዲስ አውሮፕላኖች ናቸው፡፡ ያሉን አውሮፕላኖች አማካይ ዕድሜ በጣም ትንሽ ነው፡፡ የኢንዱስትሪው አማካይ የአውሮፕላን ዕድሜ 12 ዓመት ነው፡፡ የእኛ አጠቃላይ አማካይ የአውሮፕላን ዕድሜ አምስት ዓመት ነው፡፡ ልዩነቱን መመልከት ይቻላል፡፡ ሌላው በኩራት መናገር የምንችለው በራዕይ 2025 ይህ አየር መንገድ የተዋጣለትና የተሳካላት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ተወዳዳሪ አየር መንገድ እንዲሆን፣ የ21ኛው ክፍለ ዘመን በቴክኖሎጂ የመጠቁ አውሮፕላኖች ይኖሩታል ብለን አስቀምጠን ነበር፡፡ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የተፈበረኩ አውሮፕላኖች ሁለት ናቸው፡፡ አንዱ ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን ነው፡፡ በሌላ በኩል ተፎካካሪው ኤርባስ ኤ350 ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሁለቱም የ21ኛ ክፍለ ዘመን ምርጥ የሆኑት ሁለት አውሮፕላኖች ባለቤት ነው፡፡ አየር መንገዱ መሠረቱን የጣለው በቢ787 እና በኤ350 አውሮፕላኖች ላይ ነው፡፡ እነዚህ አውሮፕላኖች ለመንገደኞች የሚሰጡት ምቾት፣ ነዳጅ ቁጠባቸውና ዘመናዊነታቸው የተመሰከረላቸው ናቸው፡፡ በአካባቢ ላይ ያላቸው ተፅዕኖ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ የካርቦን ልቀታቸው ዝቅተኛ በመሆኑ ለአካባቢ ተስማሚ ናቸው፡፡
ይህ ማለት ምን ማለት ነው? ኢትዮጵያ አገራችን በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን በምታደርገው ጉዞ በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በቱሪዝም ልትገናኛቸው ከምትፈልጋቸው አገሮች ጋር ሙሉ በሙሉ ቀጥታ በረራዎች ረዥም ይሁን አጭር በየቀኑ መደበኛ በረራ በመስጠት አገናኝተናታል፡፡ ዛሬ ከኮሪያ፣ ጃፓን፣ ቻይና፣ ህንድ፣ ፊሊፒንስ፣ ታይላንድ፣ ሲንጋፖርና ማሌዥያ በቀጥታ ለንግድ፣ ቱሪዝምና ለኢንቨስትመንት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ይችላል፡፡ ኢትዮጵያውያንም ወደ እነዚህ አገሮች ሳይጉላሉ ምቾታቸው ተጠብቆ መጓዝ ይችላሉ፡፡ በየቀኑ በሚሰጥ ቀጥታ ምቾት ያለው በረራ ቱሪስቶችና ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ እናጓጉዛለን፡፡ አውሮፓን ስንመለከት 13 መዳረሻዎች አሉን፡፡ እነዚህ 13 የአውሮፓ ከተሞች ከኢትዮጵያ ጋር ትልቅ የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ትስስር ያላቸው ናቸው፡፡ ማንኛውም አውሮፓዊ ለንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ሲፈልግ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በቀላሉ ምቾቱ ተጠብቆ መምጣት ይችላል፡፡ ኢትዮጵያውያንም በተመሳሳይ ወደ አውሮፓ በቀጥታ መጓዝ ይችላሉ፡፡ ወደ አሜሪካ ዋሽንግተን፣ ኒውዮርክ፣ ሎሳንጀለስና ቺካጎ ከምሥራቅ ዳርቻ እስከ ምዕራብ ዳርቻ በየቀኑ እንበራለን፡፡ ቶሮንቶ ካዳናም እንበራለን፡፡ ዛሬ ማንኛውም ቱሪስት ወይም ለንግድ የሚመጣ ሰው ቁርሱን ዋሽንግተን በልቶ የሚቀጥለውን ቁርስ አዲስ አበባ መመገብ ይችላል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በከፈታቸው ቀጥታ በረራዎች ምክንያት የመሸጋገሪያ ቆይታ ሳያደርግ በቀጥታ የ13 ሰዓታት ከአሜሪካ አዲስ አበባ በረራ በመዘርጋቱ ነው፡፡ ብራዚልና አርጀንቲና በቀጥታ መስመር ከአፍሪካ ጋር አገናኝተናቸዋል፡፡
አሁን ኢትዮጵያ እየተከተለችው ባለው የግሎባላይዜሽን፣ ገበያን የመክፈት እንቅስቃሴ የአየር ትራንስፖርት ትስስር ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ አዲስ አበባ በመሆኗ ከኒውዮርክና ከጄኔቫ ቀጥሎ ከፍተኛ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ ያላት በመሆኑ፣ የአፍሪካ ኅብረት የሚያካሂዳቸው ጉባዔዎችንና ሌሎች የንግድና የኢንቨስትመንት ጉባዔዎችን በከፈትናቸው ቀጥታ ዕለታዊ በረራዎች ማቀላጠፍ ችለናል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት በምንሰጣቸው አገልግሎት ደስተኛ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የምታካሂደው የኤክስፖርት ኢኮኖሚ በተለይ የሆርቲካልቸር ኤስፖርት ካለ ኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚታሰብ አይደለም፡፡ አበባ አነስተኛ ኢኮኖሚ ምርት (Low Economic Commodity) በመሆኑ፣ ብቻውን በአየር ትራንስፖርት ተጓጉዞ ወጪውን ለመሸፈን አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብሔራዊ አየር መንገድ እንደመሆኑ መጠን አቻችሎና ከሌላውም ገቢ ደጉሞ የአበባው ኢንዱስትሪ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ዛሬ በአበባ ኤክስፖርት ከኬንያ ቀጥለን ሁለተኛ ሁነናል፡፡ በዚህ አካሄድ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት በአገራችን የተከሰተው ሁኔታ ትንሽ ወደ ኋላ ጎተተው እንጂ ኬንያን እንበልጣለን፡፡ ለሥጋ ኤክስፖርት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትልቅ እገዛ ያደርጋል፡፡ ሌላው አየር መንገዱ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርገው የውጭ ምንዛሪ በማስገባት ነው፡፡ እዚህ ላይ ሊታይ የሚገባው አየር መንገዱ የሚጫወተው ሚና ሁለት መሆኑ ነው፡፡ አንደኛ በዓመት እስከ 200 ሚሊዮን ዶላር እናመጣለን፡፡ ነገር ግን በአጠቃላይ ከአገልግሎትና ኤክስፖርት እስከ ሦስት ቢሊዮን ዶላር እናመጣለን፡፡ የውጭ ምንዛሪ በሚታይበት ጊዜ ሌሎች አየር መንገዶች ቢያጓጉዙት ኖሮ ሊወጣ ይችል የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ማዳን አለበት፡፡ ለምሳሌ አንድ መንገደኛ በኤምሬትስ ወደ ለንደን ከተጓዘ በኢትዮጵያ ብር ይክፈል እንጂ በወሩ መጨረሻ ላይ የኤምሬትስ አየር መንገድ ከብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ ይወስዳል፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚጓዝበት ጊዜ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያ ስለሆነ የኢትዮጵያ ብርን እዚሁ ነው የሚጠቀምበት፡፡ ከኢትዮጵያ ሊወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሪን ያድናል፡፡ ይህ በዓመት ሦስት መቶ ሚሊዮን ዶላር ይደርሳል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብሔራዊ ዓርማችንን በዓለም ይዞ የኢትዮጵያን ህዳሴ ማብሰሩ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ ዕድገታችን ላይ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡ እነዚህ አዳዲስና ዘመናዊ አውሮፕላኖች እነዚህን ሁሉ አገራዊ ግዴታዎች ለመወጣት ያስችሉናል፡፡ አውሮፕላኖች ቀድመን ማዘዝ ስላለብን 70 ያህል አውሮፕላኖች በትዕዛዝ መዝገባችን ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ሳምንት የተረከብነው ቢ737 ማክስ አውሮፕላን 15 በመቶ የነዳጅ ፍጆታ ይቀንሳል፡፡ የአየር ብክለትና የድምፅ ብክለት በ15 በመቶ ይቀንሳል፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ በርካታ አውሮፕላኖች መግዛቱን የሚተቹ አሉ፡፡ አየር መንገዱ በርካታ አውሮፕላኖች ለመግዛት የወሰደው ብድር ከፍተኛ በመሆኑ መክፈል ከማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል የሚሉም አሉ፡፡ ኩባንያው ዕዳውን መክፈል ተስኖታል?
አቶ ተወልደ፡- ይህ ትችት ሥጋት ነው፡፡ ይህን አስተያየት የሚሰጡ ግለሰቦች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ማንኛውንም ቢዝነስ ስታካሂድ ያለውን ሥጋት ማወቅ፣ መተንተንና እዚያ ደረጃ እንደርሳለን ወይ ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ያለውን ሥጋት እናየዋለን፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዕደገቱ ምክንያት ዕዳውን መክፈል ተስኖታል ወይ? ብለን በምንጠይቅበት ጊዜ ቀደም ብዬ እንደ ገለጽኩት ዛሬ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ታዋቂ ዓለም አቀፍ ባንኮች ተሠልፈው ነው የሚመጡት፡፡ ይህን የሚያደርጉት ዝም ብለው ለፅድቅ ሳይሆን የመክፈል አቅማችንን ገምግመው፣ የሒሳብ መዝገባችንን አገላብጠው ዓይተው ነው፡፡ ዛሬ የብድር ጨረታ ስናወጣ ከምንፈልገው ቁጥር በላይ ባንኮች ለመጫረት ይመጣሉ፡፡ ሲቲ ባንክ፣ ቼዝ፣ ኤችኤስቢሲ፣ ጄፒ ሞርጋንና አይኤንጂ የሚባሉ ትላልቅ ባንኮች መጥተው ተወዳድረው አሸንፈው እያበደሩን ነው ያሉት፡፡ ባለፈው ወር ቻይና ኤግዚም ባንክ ሄጄ ሊቀመንበሩን አግኝቻቸው ነበር፡፡ ማንኛውንም አውሮፕላን መግዛት ስታስቡ፣ ወይም የመሠረተ ልማት ግንባታ ስታስቡ፣ እንደ አውሮፕላን ጥገና ሐንጋር ወይም ካርጎ ተርሚናል ለመገንባት ስታቅዱ እባካችሁ መጀመርያ ለእኛ ቅድሚያ ስጡን ብለውኛል፡፡ ይህን ያሉት የብድር ክፍያ ታሪካችንንና ትርፋማነታችንን ተመልክተው ቢያበድሩን ልንከፍላቸው እንደምንችል ስላመኑ ነው፡፡ ከቻይና የምንወስደውን ብድር በዩዋን ነው የምንከፍላቸው፡፡ ቻይና ውስጥ በዩዋን ብዙ ነው የምንሸጠው፡፡ ስለዚህ የምንከፍላቸው በራሳቸው ገንዘብ ነው፡፡ እንደሚባለው ዕዳችን እዚያ ደረጃ አይደርስም፡፡ ብድራችንን በሚገባ ‹ማኔጅ› እያደረግን ነው፡፡ በአየር መንገድ ውስጥ 34 ዓመቴ ነው፡፡ የፋይናንስ ኃላፊያችን ከ20 ዓመት በላይ ልምድ አለው፡፡ ባለን ልምድ ተጠቅመን ብድራችን ምን ያህል ነው? ምን ያህል መክፈል እንችላለን? ብለን ተማክረን አቅደን ነው የምንበደረው፡፡
ሪፖርተር፡- የአየር መንገዱ የብድር መጠን ምን ያህል ደርሷል?
አቶ ተወልደ፡- በአሁኑ ወቅት 1.8 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ አለብን፡፡ ነገር ግን እንዳልኩህ በቂ የመክፈል አቅም አለን፡፡ ዕዳችንን መክፈል የሚያስችለን የገበያ ስትራቴጂ ያለን በመሆኑ ዕዳችንን በአግባቡ መክፈል ያስችለናል፡፡ ይህ ራዕይ 2025 የዕድገት መርሐ ግብር መተግበር ከጀመርንባቸው ባለፉት ስምንት ዓመታት አስመስክረናል፡፡ ሥጋት በአንዳንድ ወገኖች ሊኖር ይችላል፣ ተገቢም ነው፡፡ ጥያቄውን ማንሳቱ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን እኛ በጥናትና በጥንቃቄ አቅማችንን እያገናዘብን የምንበደር በመሆኑ ብድራችን ከአቅማችን በላይ አልሆነም፡፡ ስንበደር ምንም ዓይነት የመንግሥት ዋስትና (Sovereign Guarantee) አንወስድም፡፡ በራሳችን የሒሳብ መዝገብ ነው የምንበደረው፡፡
ሪፖርተር፡- መንግሥት የብድር ዋስትና አይሰጣችሁም?
አቶ ተወልደ፡- የመንግሥት ዋስትና ሳንጠይቅ በራሳችን ዋስትና ነው የምንበደረው፡፡ ብድሩንም እየሠራን በራሳችን ነው የምንከፍለው፡፡ መንግሥትን ዕዳ ውስጥ አንከትም፡፡ በአፈጻጸማችን አበዳሪዎቻችን ደስተኞች ናቸው፡፡ ጥሩ የሆነ የሒሳብ መዝገብ ከሌለህ እኮ የሚያበድርህ ባንክ አታገኝም፡፡
ሪፖርተር፡- ከአውሮፕላኖች ግዥ ጋር ተያይዞ ሰሞኑን የተነሳ ጉዳይ አለ፡፡ የሮልስ ሮይስ ትሬንት 1000 ሞተር የተገጠመላቸው አውሮፕላኖች ሞተር ላይ በተገኘ የቴክኒክ እክል እንዲቆሙ ተደርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድም የሮልስ ሮይስ ሞተር የተገጠመላቸው አራት አውሮፕላኖች እንዲቆሙ መደረጉን ሰምተናል፡፡ ከመቼ ጀምሮ ነው የቆሙት? አየር መንገዱ ላይ ምን ተፅዕኖ አሳድሯል?
አቶ ተወልደ፡- ይህ ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተለያዩ የሐሰት ዜናዎች ሲሠራጩ ስለምመለከት ነው፡፡ ሁለት ነገሮችን አንስቼ በግልጽ ማስረዳት እፈልጋለሁ፡፡ አንደኛ መጀመርያ ከተመረቱ ቢ787 አውሮፕላኖች በክብደት ትንሽ ከፍ ይላሉ፡፡ መጀመርያ የተሠሩት 12 ድሪምላይነሮች መጀመርያ ስለተሠሩ ቦይንግ የሰጠው ክብደት (በሽያጭ ቅስቀሳ ወቅት) ከፍ ያለ ነበር፡፡ በኋላ ከ13ኛ ጀምሮ ንድፉን አስተካክሎ ቀጥሏል፡፡ የመጀመርያዎቹ 12 ግን ከፍ ያለ ክብደት አላቸው፡፡ ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ከፍተኛ ድርድር አድርገን ከ12 ስድስቱን በጥሩ ዋጋ ገዛናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- በምን ያህል ዋጋ ነው የገዛችኋቸው?
አቶ ተወልደ፡- በቦይንግና በኢትዮጵያ አየር መንገድ መካከል መረጃን ያለመግለጽ ውል አለ፡፡ ቢሆንም ሕዝብ እውነታውን ማወቅ ስላለበት እያንዳንዳቸውን በ80 ሚሊዮን ዶላር እንደገዘናቸው እንድታውቁ እፈልጋለሁ፡፡ የድሪምላይነር ዋጋ 120 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ሌሎቹን የገዛነው በመደበኛ ዋጋ 120 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ይህ ሚስጥር ነው፡፡ ይህን ካደረግን በኋላ አውሮፓ 10 ሰዓት የምንበርባቸው ቦታ ክብደታቸው አሳሳቢ እንዳልሆነ አረጋገጥን፡፡ ምን ያህል ጭነት መሸከም እንደሚችሉ አረጋገጥን፡፡ ከዚያ ቀጥሎ የአውሮፕላን ኢንጂነሮቻችን አጠኗቸው፣ መረመሯቸው፡፡ የቴክኒክ አማካሪ ቀጥረን አስጠንተናል፡፡ አውሮፕላን አከራዮችን እነዚህን አውሮፕላኖች ብንገዛቸው እናንተ ገዝታችሁ ልታከራዩን ትችላላችሁ ወይ? ብለን ጠየቅን፡፡ አውሮፕላኖቹ ምንም ችግር እንደሌለባቸው አረጋገጡልን፡፡ የእኛም መሐንዲሶች አውሮፕላኖቹ ችግር እንደሌላቸው አረጋግጠውልናል፡፡ ቦይንግ አውሮፕላኖችን ብንገዛ ለ18 ዓመት ዋስትና እንደሚሰጡን ገለጹልን፡፡ ቦይንግ አውሮፕላኖች እንከን ቢገጥማቸውና ችግር ቢፈጠርብን ኩባንያው የሚደርስብንን ኪሳራ እንደሚሸፍን አረጋግጦልናል፡፡ በአየር መንገድ ኢንዱስትሪ ውስጥ ሸጦ መልሶ መከራየት የሚባል ነገር አለ፡፡ በጣም የተለመደ አሠራር ነው፡፡ አውሮፕላን ትገዛና ጥሬ ገንዘብ መክፈል ካስቸገረህ ወይም በወቅቱ ሌላ ቅደሚያ የምትሰጣቸው ጉዳዮች ካሉ መልሰህ ትሸጥናት ትከራያቸዋለህ፡፡ ይህ ማለት ገንዘብ አታወጣም፡፡ በየወሩ ኪራይ ትከፍላለህ እንጂ ለአውሮፕላኖቹ ብድር አትወስድም፡፡ እነዚህን አውሮፕላኖች እያንዳንዳቸውን አትርፈን 90 ሚሊዮን ዶላር ሸጠናቸዋል፡፡ በእያንዳንዱ አውሮፕላን አሥር ሚሊዮን ዶላር በድምሩ 60 ሚሊዮን ዶላር አትርፈናል፡፡ 60 ሚሊዮን ዶላር በጥሬ ገንዘብ ትርፍ ወደ ባንክ ሒሳባችን ገብቷል፡፡ መልሰን ተደራድረን በጥሩ ዋጋ ተከራይተናቸዋል፡፡ በዚህ ተጠቃሚ ሆነናል፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያ እንደሚሠራጨው የፈጠራ ዜና ሳይሆን አትራፊ ሆነናል፡፡ ይህ በሒሳብ መዝገባችን በግልጽ የሰፈረ በመሆኑም በማንኛውም ጊዜ መርምሮ ማግኘት የሚቻል ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንግሥት የልማት ድርጅት እንደመሆኑ መጠን በማንኛውም ሰዓት በመመርመር ማወቅ የሚቻል እውነታ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የሮልስ ሮይስ ሞተር ያላቸው እክል ስለገጠማቸው አራት አውሮፕላኖች ጉዳይ ቢያስረዱን?
አቶ ተወልደ፡- የቦይንግ ቢ787 ድሪምላይነር አውሮፕላን ሁለት የሞተር አማራጮች አሉት፡፡ ጄኔራል ኤሌክትሪክ (ጂኢ) እና ሮልስ ሮይስ ለድሪምላይነር አውሮፕላን የሚሆን ሞተር ነው ያመረቱት፡፡ የገበያ ድርሻቸው ሃምሳ ሃምሳ ነው፡፡ የድሪምላይነር አውሮፕላኖች በቴክኖሎጂ የመጠቁ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙላቸው በመሆናቸው ሁለቱም የሞተር ዓይነቶች ችግር አጋጥሟቸዋል፡፡ ቴክኖሎጂው እስኪዳብር ድረስ አንዳንድ ችግሮች ይፈጠራሉ፡፡ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ አዲስ አውሮፕላን ሲፈበረክ ቴክኖሎጂው እየዳበረ፣ እንከኖች እየተፈጠሩና እየተስተካከለ ነው የሚሄደው፡፡ አዲስ አውሮፕላን ገና እንደተወለደ ሕፃን ነው፡፡ የጂኢና የሮልስ ሮይስ ሁለቱም ሞተሮች ችግር ያጋጠማቸው ቢሆንም፣ ጂኢ ተለዋጭ ሞተሮችን በመጠባበቂያነት አዘጋጅቶ ስለነበር ፈተናውን በቀላሉ ተወጥቶታል፡፡ ቦይንግ ቢ777 ዛሬ በጣም ተወዳጅ አውሮፕላን ነው፡፡ ታሪክን ወደ ኋላ ሄደህ ብታይ የመጀመርያዎቹ ከአምስት እስከ ስድስት ዓመት ቴክኖሎጂው እስኪዳብር አንዳንድ የቴክኒክ እክሎች ገጥመውታል፡፡ ይህ በማንኛውም አዲስና ዘመናዊ አውሮፕላን ላይ የሚፈጠር ችግር ነው፡፡ የአቪዬሽን ባለሙያዎች ሕፃናት ጥርስ ሲያበቅሉ ከሚፈጠርባቸው የጤና መታወክ ጋር ያመሳስሉታል፡፡ ቢ787 አዲስ አውሮፕላን እንደመሆኑ መጠን ይህን የዕድገት ደረጃ እያለፈ ነው፡፡ ወደ ሮልስ ሮይስ ሞተር የመጣን እንደሆነ የአውሮፕላኑ ሞተር ውስጥ ብሌድ የምንላቸው ዕቃዎች አሉ፡፡ በእነዚህ ብሌዶች ላይ ስንጥቅ ተገኘ፡፡ እነዚህ ብሌዶች ይለወጣሉ፡፡ ሞተሩ ይወርድና ስንጥቅ የተገኘባቸው ብሌዶች ይለወጣሉ፡፡ በንድፍ ሥራ ችግር የተፈጠረ ነው፡፡ አሁን ያጋጠመው የሴፍቲ ችግር ሳይሆን ሞተሮቹ እየወረዱ ሮልስ ሮይስ ኩባንያ የጥገና ማዕከል ሄደው ተጠግነው እስኪመጡ ጊዜ እየፈጀ ነው፡፡ ሮልስ ሮይስ እንደ ጂኢ በቂ ቅድመ ዝግጅት አላደረገም፡፡ በቂ ተለዋጭ ሞተሮች አላዘጋጀም፡፡ የጥገና ማዕከሉ ወስዶ ጠግኖ እስኪመልስ እስከ አንድ ወር ይፈጃል፡፡
ሪፖርተር፡- ጥገናው እንግሊዝ ነው የሚካሄደው?
አቶ ተወልደ፡- የእንግሊዝ ኩባንያ እንደመሆኑ እንግሊዝ ውስጥ የጥገና ማዕከል አለው፡፡ ሁለተኛው የጥገና ማዕከል ሲንጋፖር ይገኛል፡፡ ሮልስ ሮይስ ሁለት የጥገና ጣቢያዎች ብቻ ናቸው ያሉት፡፡ ይህ አንዱ ችግር ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ሞተሮቹ ወርደው ተጠግነው እስኪመጡ ጊዜ እየወሰደ ነው፡፡ ተለዋጭ ሞተር ባለማዘጋጀታቸው ይህ የቴክኒክ ችግር የገጠማቸው ድሪምላይነር አውሮፕላኖች ለመቆም ተገደዋል፡፡ ዛሬ በመላው ዓለም 47 ድሪምላይነር አውሮፕላኖች ቆመዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አራት አውሮፕላኖችም ከሚያዝያ ወር ጀምሮ በየተራ ሞተራቸው ሄዶ ተሠርቶ እየመጣ ነው፡፡ ይህን ቃለ መጠየቅ ስናደርግ አንድ አውሮፕላን ብቻ ነው መሬት ላይ ያለን፡፡ የሦስቱ አውሮፕላኖች ስድስት ሞተሮች እንግሊዝ አገር የሚገኘው የሮልስ ሮይስ የጥገና ማዕከል ከተጠገኑ በኋላ አውሮፕላኖቹ ወደ ሥራ ተመልሰዋል፡፡ የቀረው የአንዱ አውሮፕላን ሁለት ሞተሮች ለጥገና ተልከው እየጠበቅን ነው፡፡ እነዚህም ሁለት ሞተሮች ተሠርተው ሲመጡ የቀረው አንድ አውሮፕላን ተመልሶ ይበራል፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ ችግር ነው፡፡ ችግር የገጠማቸው 47 አውሮፕላች በአብዛኛው የጃፓን ኦልኒፖን ኤርዌይስ፣ የመካከለኛው ምሥራቅ ኳታር ኤርዌይስ አለ፣ አውሮፓ፣ ደቡብ አሜሪካና ህንድ አሉ፡፡ እኛ ጥሩ የሠራነው ምንድነው? ተለዋጭ ሞተር ካላመጣችሁ ካሳ ትከፍላላችሁ ብለን ውል ስላስገባናቸው አሁን ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ ካሳ እያስከፈልናቸው ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በበረራ ሥራችሁ ላይ ያደረሰው ተፅዕኖ ምን ያህል ነው?
አቶ ተወልደ፡- በበረራ ሥራችን ላይ የጎላ ተፅዕኖ አላሳደረም፡፡ ኤ350 እና ቢ787-900 አውሮፕላኖች እየገቡልን ስለሆነ ይህን ያህል ተፅዕኖ አልፈጠረብንም፡፡
ሪፖርተር፡- ከሮልስ ሮይስ ምን ያህል ካሳ እየተከፈላችሁ ነው?
አቶ ተወልደ፡- በወር እስከ ሁለት ሚሊዮን ዶላር እናገኛለን፡፡ ጥሩ ያደረግነው ነገር ከሮልስ ሮይስ ጋር ውል ስንፈጽም ተለዋጭ ሞተር ካላመጣችሁ የማካካሻ ክፍያ ትከፍላላችሁ የሚል ውል ስላስፈረምናቸው፣ ዛሬ ችግሩ ሲፈጠር አልተጎዳንም፡፡ እንዲያውም ገቢ እያገኘን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርቡ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ ዋና ዋና የሚባሉ የንግድ ተቋማትን ወደ ግል ይዞታ በከፊል እንደሚዘዋወሩ ተገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እስካሁን ስኬታማ በመሆኑ ለምን በከፊል መሸጥ አስፈለገ? የሚል ጥያቄ በኅብረተሰቡ ዘንድ አጭሯል፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ተመሳሳይ ጥያቄ ተነስቷል፡፡ በአፍሪካ ቀዳሚ አትራፊ የሆነ ድርጅት ለምን መሸጥ አስፈለገ? የፕራይቬታይዜሽኑ ሒደትስ እንዴት ነው የሚሆነው? ዛሬ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስምንት የትርፍ ማዕከላት ያሉት በመሆኑ የትኛዎቹ ናቸው ለሽያጭ ክፍት የሚሆኑት?
አቶ ተወልደ፡- በዚህ ላይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ትክክለኛና ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬታማ ድርጅት ነው፡፡ ይህ በዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማኅበርና በሌሎችም የኢንዱስትሪው አካላት እየተመሰከረ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ እንደ አገር ከደረሰችበት ደረጃ ልማታዊ አገር እየመራን መጥተን፣ ጥሩ ውጤት አግኝተን በበለጠ ወደ ግሎባላይዜሽን ልንገባ ነው፡፡ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል መሆን ስላለብን፣ ከዓለም ኢኮኖሚ ጋር ያለን ትስስር እየተጠናከረ ስለሚሄድ የገበያ በር መከፈት ይኖርበታል፡፡ ከዓለም ተነጥለን በራችንን ዘግተን መቀጠል አንችልም፡፡ ዛሬ በሞኖፖሊ የሚገኙ ዘርፎች ለፉክክር ክፍት ሆነው ይቀጥላሉ፡፡ ፉክክር ውጤታማነትን ያመጣል፡፡ በመንግሥትና በግል ይዞታ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ጥሩ የሚሆነው ተወዳዳሪዎች ሲኖሩ ነው፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነትንና ውጤታማነትን ለማምጣት ታስቦ ነው እየተሠራ ያለው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ስንመጣ አየር መንገዱ ከመጀመርያ ጀምሮ ለዓለም አቀፍ ውድድር የተጋለጠ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ከምናጓጉዘው መንገደኛ 70 በመቶ ትራንዚት ነው፡፡ የትራንዚት መንገደኛ የምናገኘው ከፍተኛ ፉክክር ውስጥ ገብተን ነው፡፡ አንድ ናይጄሪያዊ ከሌጎስ ተነስቶ ቤጂንግ መሄድ ቢፈልግ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአዲስ አበባ በኩል ሊወስደው ይችላል፡፡ ኳታር ኤርዌይስ በዶሃ በኩል ሊወስደው ይችላል፡፡ ኤምሬትስ በዱባይ በኩል ሊወስደው ይችላል፡፡ ኢትሃድ በአቡዳቢ በኩል ሊወስደው ይችላል፡፡ የቱርክ አየር መንገድ በኢስታንቡል በኩል ሊወስደው ይችላል፡፡ የግብፅ አየር መንገድ በካይሮ በኩል ሊወስደው ይችላል፡፡ የኬንያ አየር መንገድ በናይሮቢ በኩል ሊወስደው ይችላል፡፡ ቢያንስ ከአሥር ያላነሱ አማራጮች አሉት፡፡ ከዚህ ሁሉ ውድድር አሸንፎ መንገደኛውን መውሰድ ከፍተኛ ጠንካራ ፉክክር ይጠብቀዋል፡፡
ስለዚህ አየር መንገዱ በየዕለቱ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ አሸናፊ ሆኖ ነው የቆየው፡፡ ሰፊ የሆነ ዓለም አቀፍ ገበያ ፉክክር ልምድ አለው፡፡ ነገር ግን በቀጣይ ትልቅ ሽግግር ይጠብቀዋል፡፡ እስካሁን ድረስ በአብዛኛው አየር መንገድ ሆኖ የቆየው፡፡ አሁን ግን የአቪዬሽን ቡድን ሆኗል፡፡ በአቪዬሽን ቡድኑ ውስጥ ስምንት የትርፍ ማዕከላት አሉ፡፡ በኢትዮጵያ የንግድ ሕግ ሆልዲንግ ኩባንያ በሚፈቅድበት ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቡድን ሆልዲንግ ኩባንያ ሆኖ የትርፍ ማዕከላቱ እህት ኩባንያ ሆነው ይቀጥላሉ፡፡ እነዚህ እህት ኩባንያዎች በዋና እናት ኩባንያ ሥር ሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግማሽ ወይም ከዚያ በላይ ድርሻ ኖሮት፣ የግሉ ዘርፍ ገብቶባቸው የተቀረው ድርሻቸው በግል ሊያዝ ይችላል፡፡ ለግሉ ዘርፍ ክፍት የምናደርጋቸው ዘርፎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ሆቴል እንውሰድ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆቴል ሥራ ውስጥ ገብቷል፡፡ እንደሚታወቀው ሆቴል ከአቪዬሽን ዘርፍ ወጣ ያለ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቱሪዝም ዘርፍ ውስጥ የመሪነት ሚና መጫወት ፈልጓል፡፡ ከእኛ የበለጠ ይህን ዘርፍ ሊያንቀሳቅሰው የሚችል ዘርፍ ላይኖር ይችላል፡፡ ምክንያቱም 112 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች እየበረርን ብዙ ቱሪስቶች ማምጣት ስንችል፣ የኢትዮጵያ ቱሪዝም እንደዚህ ወደ ኋላ ቀርቶ መቀጠል የለበትም የሚል እምነት አለን፡፡ አሁን እንደምታዩት የምንገነባውን ሆቴል አስተዳደር ለቻይና ኩባንያ ነው የሰጠነው፡፡ በሆቴላችን ላይ ማንኛውም ፍላጎት ያለው የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብት ሊሳተፍ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ሎጂስቲክስ ውስጥ እየገባን ነው፡፡ የካርጎ ሥራችንን ወደ ሎጂስቲክስ ዘርፍ እያስፋፋን ነው፡፡ ከዲኤችኤል ኩባንያ ጋር በጋራ እየሠራን ነው፡፡ እኛ 51 በመቶ ዲኤችኤል 49 በመቶ ባለቤትነት ድርሻ ኖሮን የምንሠራበት ሁኔታ እያመቻቸን ነው፡፡ በአዲሱ የንግድ ሥራ አቅጣጫ እክሲዮን ሸጥን ማለት ነው፡፡
ሦስተኛው ወደ የኤሮስፔስ ማኑፋክቸሪንግ እየገባን ነው፡፡ ኤሮስፔስ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ውስጥ በጣም ትልቅ ዘርፍ ነው፡፡ በቀላሉ በዚህ ጥሩ ተሞክሮ ያላትን ሞሮኮ ማየት ይቻላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሞሮኮ ከ10,000 በላይ ዜጎች የሚያሰማራ የኤሮስፔስ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ አላት፡፡ እኛም ያንን ካለን የተማረ ወጣት ብዛት ስናየው እንደ አገር ኢንዱስትሪውን ብናጎለብተው ይጠቅመናል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአውሮፕላን ጥገና ሥራ ላይ ያለውን የረዥም ዓመት ልምድ ተጠቅሞ ይህን ዘርፍ ሊያሳድግ ይችላል፡፡ ይህን በሚያደርግበት ጊዜ ከግዙፍ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ኤርባስ፣ ቦይንግ፣ ቦምባርዲየር፣ ዩታስና ሳፍራን ካሉ ኩባንያዎች ጋር እየተደራደርን እንገኛለን፡፡ ለቦይንግ፣ ኤርባስና ቦምባርዲየር የአውሮፕላን ዕቃዎች አምርተን ለማቅረብ ነው ያሰብነው፡፡ ሳፍራን የተባለው የፈረንሣይ ኩባንያ የተለያዩ የአውሮፕላን ዕቃዎች የሚያመርት ነው፡፡ ዩታስ የቢ787 አውሮፕላን 60 በመቶ አካል የሚያቀርብ የአሜሪካ ድርጅት ነው፡፡ ከአምስቱ ድርጅቶች ጋር ውይይት ጀምረናል፡፡ እኛ በምናቋቁመው ኤሮስፔስ ድርጅት እነዚህ ኩባንያዎች በባለድርሻነት ጭምር ሊገቡ ይችላሉ፡፡ እንደሚታወቀው በአራት የአፍሪካ አየር መንገዶች ላይ የባለቤትነት ድርሻ ይዘናል፡፡ አስካይ 40 በመቶ፣ ማላዊ 49 በመቶ፣ ዛምቢያ 45 በመቶና ሞዛምቢክ መቶ በመቶ ድርሻ የሚኖረን አየር መንገድ ለመመሥረት ዝግጅት ላይ ነን፡፡ ጊኒ አየር መንገድ 49 በመቶ፣ ቻድ 49 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ይኖረናል፡፡ ሌሎችም ላይ እንቀጥላለን፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትክክለኛው ፓን አፍሪካን አየር መንገድ ነው፡፡ በሌሎች አፍሪካ አየር መንገዶች አክሲዮን እየገባ በመሆኑ አንዳንድ አገሮች በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ እንግዛ በሚሉበት ጊዜ በተለይ አክሲዮን ከገዛንባቸው አገሮች ጋር ግንኙነታችንን ያጠናክረዋል፡፡ አነስተኛ አክሲዮን ስለሚሆን ችግር አይኖረውም፡፡ እነዚህን ዓላማዎች ለማሳካት ሲባል እንጂ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያውያን ኩራትና ውጤታማ የሆነ ድርጅት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የፕራይቬታይዜሽኑ ሐሳብ መንግሥት አገሪቱ የገጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግር ለማቃለል ብሎ ያመጣው እንደሆነ ይነገራል፡፡ በሌላ በኩል የአየር መንገዱ ዕዳ ስለበዛ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?
አቶ ተወልደ፡- ይህ መላምት ነው፡፡ ግርታ ሲፈጠር ሰው ሁሉ የየራሱ ትንታኔ ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተሸጦ ሳይሆን የውጭ ምንዛሪ የሚያመጣው እየሠራ ነው፡፡ በየዓመቱ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እያመጣ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ብክነትን እያዳነ ነው፡፡ በዚህ አገር ተጠቃሚ ናት፡፡ የአየር መንገድን ዕዳ በራሳችን የምንወጣው ነው፡፡ በአግባቡ እየተከፈለ ነው፡፡ የሚያሳስብ አይደለም፡፡ መንግሥትም ያን ያህል የሚያሳስበው አይደለም፡፡ ምክንያቱም ብድሩን ያለመንግሥት ዋስትና በራሳችን የሒሳብ መዝገብ ያመጣነው በመሆኑና ትርፋማ ሆኖ እየሠራ ያለ ድርጅት ስለሆነ መንግሥትን ሊያሳስበው አይገባም፡፡
ሪፖርተር፡- ወደ ግል ይዞታ ሊዞር የሚችለው እስከ ስንት ፐርሰንት ነው?
አቶ ተወልደ፡- ቀደም ብዬ ለመግለጽ እንደሞከርኩት የኢቪዬሽን ቡድኑ በአጠቃላይ ሳይሆን ለእያንዳንዱ የትርፍ ማዕከል (ወደፊት በኩባንያ ደረጃ የሚቋቋሙ) እንደ ሁኔታው በጥናት የሚወሰን ይሆናል፡፡ አሁን ዝርዝር ጥናቱ ገና ያልተሠራ በመሆኑ ለግሉ ዘርፍ ክፍት የሚሆነው የድርሻ መጠን ዛሬ አናውቀውም፡፡ ለወደፊቱ በጥናት የሚታወቅ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅትም ከእኛ ጋር ነው፡፡ የውጭ ኤርፖርቶች ማስተዳደር ልንጀምር ነው፡፡ በኤርፖርት ዘርፍም የባለቤትነት ድርሻ እንገዛለን፣ ከእኛም ፍላጎት ያላቸው ሊገዙ ይችላሉ፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ሲዋሀዱ የተቃወሙ ሰዎች ነበሩ፡፡ አየር መንገዱ የሞኖፖሊ መብት ይኖረዋል፣ ኤርፖርቶችን ማስተዳደር የለበትም የሚሉ ተቃውሞች ተሰምተዋል፡፡ አየር መንገዱ ከኤርፖርቶች ድርጅት ጋር አብሮ መሥራት ከጀመረ በኋላ ምን ውጤት ተገኝቷል? መቀላቀሉስ ለምን አስፈለገ?
አቶ ተወልደ፡- መነሻው የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት በነበሩበት ችግሮች ወደ ኋላ እየቀረ ስለነበረ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ዕድገት ሙሉ በሙሉ መደገፍ የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ በመሠረተ ልማት አቅርቦትና በአገልግሎት አብሮ መሄድ እየተሳነው መጥቶ ነበር፡፡ ብዙ አማራጮች ቀርበው መጨረሻ ላይ በመንግሥት ብናዋህዳቸው ይሻላል ተብሎ ተወስኖ ነው የገባንበት፡፡ መነሻው ይኼ ነው፡፡ ሁለቱም የመንግሥት ድርጅት ናቸው፡፡ በአንድ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሥር የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ ብዙ ሰዎች ይህ የመጀመርያው ነው ብለው ያስባሉ፡፡ ይህ ግን ስህተት ነው፡፡ ብዙ አየር መንገዶች በተለያየ ሁኔታ የኤርፖርቶች ባለቤት ይሆናሉ፡፡ የአትላንታ ኤርፖርትን ዴልታ አየር መንገድ ተርሚናሎቹን ለ20 ዓመታት በኪራይ ይዟል፡፡ ጄኤፍኬ ኤርፖርት በኪራይ በአየር መንገዶች ነው የሚሠራው፡፡ ኳታርን የወሰድን እንደሆነ ኳታር ኤርዌይስና ኳታር ዶሃ ሃማድ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት በአንድ ቡድን ውስጥ ነው ያሉት፡፡ በአንድ ሊቀመንበር በሚስተር አክባር የሚመራ ነው፡፡ ኤርፖርትና አየር መንገድ በአንድ የአቪዬሽን ቡድን ሥር መተዳደር ኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረ እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ በዚህ ዘርፍ ዓለም አቀፍ ልምድ ስላለን፣ ያንን በማካፈል አብረን ተባብረን የኤርፖርት አገልግሎትና መሠረተ ልማት ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሳደግ ነው ዓለማ ይዘን የተነሳው እንጂ ሌላ ሚስጥር የለውም፡፡ ከተዋሀደ አሥረኛ ወር ይዟል፡፡ በአሥር ወራት ምን ተሠርቷል ካልን አንደኛ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የደረሰበት የኢንፎሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ላይ ደርሷል፡፡ ማንኛውም የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ሠራተኛ የደመወዝ አከፋፈሉ፣ የፋይናንሱና የግዥ አሠራሩ በአጠቃላይ ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ዘመናዊ አሠራር ለማምጣት ችለናል፡፡ ኤርፖርቱን የማዘመን ሥራ ውጤታማ በሆነ መንገድ ተሠርቷል፡፡ የአዲስ አበባ ኤርፖርትን በምናይበት ጊዜ በየሳምንቱ የተጓዥ መንደገኞች ግብረ መልስ እናገኛለን፡፡ እስከ 70 በመቶ መንገደኞቻችን በአዲስ አበባ ኤርፖርት እርካታ እንዳላቸው እየገለጹልን ነው ያሉት፡፡ በአዲስ አበባ ኤርፖርት የገመድ አልባ ኢንተርኔት አገልግሎት አልነበረም፡፡ አሁን የገመድ አልባ ኢንተርኔት አገልግሎት በነፃ እንሰጣለን፡፡ ከመፀዳጃ ቤት ጀምሮ ያሉ ጥቃቅን አገልግሎቶች ተሻሽለዋል፡፡ በመስተንግዶ ብዙ ለውጦች አምጥተናል፡፡ ከመንገደኞች ጥሩ መሻሻል እንዳለ እየተገለጸልን ነው፡፡
ሌላው በዋነኛነት ተጠቃሽ የሆነው የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የመንገደኞች ማስተናገጃ ሕንፃ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት ሥራው ተጓቶ ነበር፡፡ አሁን የማስፋፊያ ሥራው እንዲቀላጠፍ አድርገን በያዝነው የአውሮፓውያን ዓመት መጨረሻ ይጠናቀቃል ብለን እንጠብቃለን፡፡ የምሥራቁ ክፍል በቀጣዩ ሳምንት እንረከባለን፡፡ ይህ እንደሚታወቀው ሦስት ዓመት ሙሉ ሲጓተት የቆየ ፕሮጀክት ነው፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2015 እስከ 2018 ነበር ውሉ፡፡ በጥር 2018 ማስረከብ ነበረበት፡፡ መሠራት የነበረበት ሳይሠራ ስለቆየ ሊፈጸም አልቻለም፡፡ ሁለቱ ድርጅቶች ከተዋሀዱ በኋላ በፕሮጀክቱ ውስጥ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት፣ ከውጭ ምንዛሪ ጋር፣ ከግዥ ሥርዓት ጋር የተያያዙ ችግሮች በሙሉ በማቀላጠፍ በአስቸኳይ እንዲጠናቀቅ ሌት ተቀን እየሠራን ነው፡፡ አሁን ያለው ተርሚናል ንድፍ ሲሠራ በዓመት አምስት ሚሊዮን መንገደኛ እንዲያስተናግድ ተደርጎ ነው፡፡ አሁን ግን አሥር ሚሊዮን መንገደኛ እያስተናገደ በመሆኑ ከፍተኛ መጨናነቅ ይታያል፡፡ በመጪው ሳምንት የምሥራቁን ክፍል እንከፍታለን፡፡ ከስድስት ወራት በኋላ ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ ይውላል፡፡ እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 2019 ይመረቃል፡፡ በክልል ኤርፖርቶች ላይ ይታዩ የነበሩ ጉድለቶችን እያሻሻልን ነው ያለነው፡፡ ድሬዳዋ ኤርፖርት ከርከሮዎች ከአውሮፕላን ጋር በመጋጨታቸው አንድ አውሮፕላን አጥተናል፡፡ እንዲህ ዓይነት የአራዊት አደጋ በክልል ኤርፖርቶች እንዳያጋጥመን የተጠናከረ አጥር ማጠርና ሌሎች የደኅንነት ሥራዎች እያከናወንን እንገኛለን፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርቡ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ ለኩባንያው የዳይሬክተሮች ቦርድ አቅርበዋል የሚል ዘገባ ተሠራጭቷል፡፡ ሥራዎን ለመልቀቅ አስበዋል?
አቶ ተወልደ፡- ቅድም እንዳልኩት የማኅበራዊ ሚዲያ የሐሰት ዜና ማምረቻ ሆኗል፡፡ እንደምታዩኝ ሥራዬን እየሠራሁ ነው፡፡ አሁንም ያገኛችሁኝ ቢሮዬ ውስጥ ነው፡፡ ሥራዬን በትክክል እየሠራሁ ነው፡፡ እንዲያውም ከበፊቱ የበለጠ የሥራ ጫና እየበዛብን ነው፡፡ ድሮም ይበዛብናል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ከአየር መንግዱ ፈጣን ዕድገት ጋር ተያይዞ ሥራ የበለጠ በዝቶብናል፡፡ ይህ ግን እኔና የሥራ ባልደረቦቼ የተረከብነው ብሔራዊ ግዴታ ስላለብን ለክፍያ ብለን የምንሠራው ሳይሆን፣ በፍቅር ብሔራዊ አየር መንገዳችንን ተባብረን ጠንክረን በማገልገል ላይ ነን፡፡ የጠየቅከኝን ጥያቄ ለመመለስ ሥራዬን የመልቀቅ ሐሳብ የለኝም፣ እቀጥላለሁ፡፡ የተወራው ሁሉ ውሸት ነው፡፡